Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አገልግሎቱ

0 296

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አገልግሎቱ…

ገናናው በቀለ

በአገራችን ውስጥ የበጎ ፈቃድ አገልግለት ስራ ጅምር ቢሆንም፣ ተግባሩ ወደፊት ሊጠናከር የሚገባውና ማህበራዊ ፋይዳውም ከፍተኛ ነው። የወጣቶች የክረምት ወራት የበጐ ፈቃድ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ 13 ነጥብ ስድስት ሚሊዩን የሚሆኑ ወጣቶች በአገልግሎቱ ላይ እየተሳተፉ ነው። ከእነዚህ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ዋጠቶች በድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ላይ አንድ ሺህ ተመራቂ ወጣቶች ተግባራቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ።

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከየአካባቢዎቻቸው ወጥተው በድንበር ተሻጋሪነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑትን እነዚህን ወጣቶች በጽህፈት ቤታቸው በማነጋገር ገለጻ አድርገውላቸው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለጻቸው በጎ ፍቃደኛ በመሆን ህብረተሰቡን ልታገለግሉ ስትንቀሳቀሱ ለማስተማር እና ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ለማወቅም፣ ለመማርም፣ ለመቀበልም መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። ለዚህም በምክንያትነት ህብረተሰቡ ውስጥ በርካታ እውቀቶችን እና ልምዶችን እንደሚያገኙ ጠቅሰዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተሳታፊ ወጣቶች በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ ተግባርን ብቻ ሳይሆን መሳቅን፣ ማቀፍን እና አብሮ መብላትን እንደ መርህ ይዘው እንዲንቀሳቀሱ እንዲሁም የሚሄዱበትን አካባቢ ባህል እና ወግ ሊያከብሩ እንደሚገባም አስረድተዋል።

በወጣቶቹ ዛሬ የተጀመረው በጎ ነገር እንደቀላል እንደማይታይና በቀጣይም ይህ መልካም ነገር ባህል ሆኖ እንዲቀጥል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ገልፀዋል። በዚህ በጎ ተግባር የሚሰማሩ ወጣቶችን ለማበረታታትና ድርጊቱን አጠናክሮ እንዲቀጠል ይደረጋል ብለዋል።

ማህበረሰቡ ውስጥ የካበተ እውቀት አለ። ይህ እውቀት በዘመናት የህይወት ተሞክሮ የተገኘ ነው። ወጣቶች የሚሰማሩባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚገኘውን እውቀት መቅሰም ይኖርባቸዋል። ራሳቸው እውቀት ሰጪዎች ብቻ ሳይሆኑ ተቀባዩችም እንደሆኑ ማወቅ አለባቸው።

ማህበረሰቡ ተማሪ ብቻ ሳይሆን ካለው የካበተ የህይወት ተሞክሮ አስተማሪም ጭምር ነው። በመሆኑም አገልግሎት ለወጣቶች መማሪያም ጭምር ነው። በትምህርት ቤት የማያገኙትን ዕውቀት በነፃ ከማህበረሰቡ ያገኛሉ። ይህ ሁኔታም ወደ ፊት ወደ ስራ ዓለም ሲሰማሩ ለሚያጋጥማቸው ህይወት ጥሩ ትምህር ይሆናቸዋል።

የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መካሄድ አገራዊ ስሜትንና የህዝብ ለህዝብ ማህበራዊ ትስስርን የሚያጎለብት ነው። የበጐ ፈቃድ አገልግሎት ዜጐች በተለይም ወጣቶች ያለ ማንም አስገዳጅነት ለሚኖሩበት ማህበረሰብ ልማትና ለአካባቢ ደህንነት የራሳቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትም ነው።

ወጣቶቹ ለድንበር ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በመነሳሳታቸው ራሳቸውን፣ ህዝባቸውንና አገራቸውን ይጠቅማሉ። አገልግሎቱ ወጣቶች ስራን ሳይንቁ መስራት የሚያስገኘውን ጠቀሜታ እንዲያውቁና የስራን ክቡርነትም እንዲገነዘቡ የሚያደርጋቸው ነው።

በተጨማሪም ወጣቶች አገር መውደድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በተግባር ያዩታል። ህዝቡ ለእነርሱ ያለውን ከበሬታና ከእነርሱ እየተማረ ሊያስተምራቸው ጭምር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሲመለከቱ የህዝብ ፍቅር እስከየት ድረስ እንደሆነም እንዲገነዘቡ የሚያደርጋቸው ነው።

ወጣቶቹ ለአገልግሎቱ በሰማሩባቸው አካባቢዎችም ከሚያከናውኗቸው ተግባራት ውስጥ የሰላም አሰፈላጊነት ላይ በማተኮር ህብረተሰቡን ማስተማር ይኖርባቸዋል። ከግጭት ምንም እንደማይገኝና የሰላም ጠቀሜታ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያለውን ፋይዳ ከህይወት ልምዳቸው እየተነሱ ማስተማር የወጣቶቹ አንዱ ተልዕኮ መሆን አለበት።

የትኛውም አገር ሰላም በህዝብ እጅ ያለ ነው። ስለ ሰላም በሚደረጉ ማናቸውም ክንዋኔዎች ውስጥ የህዝቡ ተሳትፎ ፋና ወጊ መሆኑን ማስረዳት ይገባል። የአገራችንንና የህዝቦቿን ሰላምና መረጋጋት የማይሹ ለውጥ ቀልባሽ ሃይሎች የት ድረስ እንደ ዘለቀ ከህዝቡ የተሰወረ እውነታ አይደለም። ህዝብ ሁሌም ከማንኛውም ተግባር በፊት ግራና ቀኝ የሚያይ፣ ህጋዊ አካሄዶችን በማጤንና አሉታዊና አዎንታዊ ጎኑን በመገንዘብ ሚዛናዊ ውሳኔ የመስጠት ባህል ያለው በመሆኑ ለሰላሙ የሚበጀውን መንገር ይገባል።

ስለሆነም የህዝቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው አገራችን በምታካሂደው የለውጥ መንገድ መሆኑን ስለሚያውቅ ሁሌም ሰላም ወዳድ ኃይሎች ጋር የሚቆም ነው። የሰላምን ጠቀሜታ ስለሚገነዘብም ከምንግዜውም በላይ ሁሌም በየአካባቢው ለሰላሙ ዘብ እንደቆመ ነው። ይህን እውነታ በማንሳት ዛሬም እምነቱን በማጠናከር ለውጡን የሚጻረሩ አካላትን መታገል እንደሚኖርበት ማስረዳት ይገባል።

በየቀየው ላለው የሰላም ሁኔታ ህዝቡ መሰረት መሆኑን ማስተማርም ይገባል። በዚያ አካባቢ ለሚከሰት ማናቸው ለውጥን የመቃወም ድርጊት መልሶ የሚጎዳው እርሱን መሆኑንና በዚህም ለሰላሙ ይበልጥ መትጋት እንዳለበት ማስተማር አስፈላጊ ነው። ሰላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑና ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን መከተል እንዳለበትም ማስረዳት ያስፈልጋል።

ሰላም ከሌለ ምንም ዓይነት የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት እንደማይቻልም ማስረዳት ተገቢ ነው። ምናልባትም በማወቅ ይሁን ባለማወቅ በተሳሳተ አቅጣጫ የሚጓዝ ዜጋ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ተሳታፊ ይሆናል። ይህም የጥፋት አውድን እንደሚፈጥር መንገር ተገቢ ነው። ጥፋቱ የህዝቡን ክቡርና የማይተካ ህይወት ከመንጠቅ ባሻገር ሃብቶቹንና መጠቀሚያዎቹን ያወድማል። ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲያጤኑት ግን ቁጭትን እንደሚፈጥር መግለፅም ይገባል።

ለውጡን የማይደግፉ ሃይሎች ያላቸውን የቅጥፈትና የአሉባልታ አቅማቸውን ሁሉ አሟጠው በመጠቀም የህዝቡን የዘመናት የመቻቻል እሴቶችን ለመስለብ ይሞክራሉ። እነርሱ በዚህም ይሁን በዚያ የራሳቸውን የከሰረ ፖለቲካዊ ጥቅም እስካሳካላቸው ድረስ ምንም ዓይነት ጉዳይ ለመፈፀም ከፈለጉ ሙዝ ልጦ እንደመብላት ቀላል መሆኑን ማስተማር ያስፈልጋል። እንዲያውም ጉዳዩን ለማፋፋም ራሳቸው በለኮሶት ሁከት የተፈጠረውን ሞትና የንብረት ውድመት በየማህበራዊ ሚዲያው በማስተጋባት ሌላ ችግር ለመፍጠር ይሯሯጣሉ።

በእነዚህ ፍላጎታቸው ሳቢያ ምንም አገርን ለማተረማመስ ይሰራሉ። ህዝቡ ይህን በማወቅ ለሰላሙ ሁሌም ዘብ መቆም እንዳለበት ማስተማር ያስፈልጋል። ድንበር ተሻጋሪ በጎ አገልግሎት የሚሰጡት ወጣቶች ይህን ማድረገ ከቻሉ ለሀገራቸውና ለወገናቸው ታለቅ ስራን መከወን ይችላሉ። ለወገንና ለአገር መስራት የሚያስገኘውን እርካታንም ይጎናጸፋሉ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy