Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አገልግሎት ሰጭዎቹ

0 419

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አገልግሎት ሰጭዎቹ

                                                        ዋሪ አባፊጣ

ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭ ወጣቶች በተሰማሩባቸው የህበረተሰብ ክፍሎች ውስጥ በርካታ ስራዎች እያከናወኑ ነው። ተግባሮቻቸው በህዝቡ ውስጥ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር አስተሳሰብ ምን እንደሆኑም እያሳዩ ነው። ርግጥ ወጣቶቹ በዚህ ስራ ከሚያበረክቱት አገልግሎት በላይ፤ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚኖረውን አገራዊ ፋይዳ በአያሌው ተገንዝበዋል።

እንዲህ ዓይነት ስራዎች ህዝቦችን በማቀራረብ የሀገሪቱን የወደፊት ተስፋ ብሩህ የሚያደርጉ መሆናቸውንም ማወቅ የቻሉ ይመስለኛል። ታዲያ ይህን በጎ ተግባር ሲፈፅሙ ሌሎች የዕድሜ አቻዎቻቸውም ለተመሳሳይ ዓላማ እንዲነሳሱ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭዎች ባሻገር፤ ከ13 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። እነዚህ አገልግሎት ሰጭ ወጣቶች በጥቂት የጉልበት ስራዎች ላይ ብቻ የተሰማሩ አይደሉም።

ይልቁንም ጽንፈኝነትን በመታገል፣ ህግን በማስከበርና ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ ሊያበረክቱ የሚችሉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በዚህ ክንዋኔያቸው አገልግሎት ሰጭዎቹ ሀገርንና ህዝብን በሚጠቅሙ ሁለንተናዊ ተግባሮች በመሳተፍ በአንድነትና በፍቅር መደመራቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ።

በዘጠኙም ክልሎች የተሰማሩት አገልግሎት ሰጭዎቹ ለህብረተሰቡ ከሰጡት አገልግሎት ይልቅ፤ የተማሩት የትየለሌ እንደሚበልጥ እየገለፁ ነው። ይህን አውነታ ከራሳቸው አንደበት በመረዳት መገንዘብ ይቻላል።

ወጣቶቹ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ስለሚኖሩ ህዝቦች ከሚሰሙ መረጃዎች በተቃራኒ በአንድነትና ፍቅር አብሮ ተቻችሎ የሚኖር ህዝብ መሆኑ በተግባር ማረጋገጣቸውን ይናገራሉ። የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ ተሳታፊዎቹ በ13 ዘርፎች እያከናው ያሉ ተግባራት በአካባቢዎቹ የሚገኙ ነዋሪዎችን ከማነቃቃት ባለፈ ለቀጣይ ህይወታቸው ስንቅ የሚሆኑ ልምዶችን ቀምረዋል።

በአሁኑ ወቅት በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡትና ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች ከምርቃታቸው ማግስት አንስቶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በመወያየት ከትውልድ ቄያቸው ውጭ ባሉ ክልሎች የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን እያከናወኑ ነው።

ከእነዚህ ውስጥ 260ዎቹ በኦሮሚያ ክልል በመሰማራት፤ በየቀኑ በአካባቢ ፅዳት፣ በደም ልገሳ፣ የትምህርት ልምድን በማካፈል እንዲሁም በሌሎች ስራዎች በ13 ዘርፎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ወጣቶቹ በየአካባቢው የተሰማሩት ተሰባጥረው ወደ ስለሆነ ከስራ ዕረፍታቸው በኋላ ምሽት ላይ በማረፊያቸው በሚያደርጉት ውይይትና የባህል ትውውቅ ይበልጥ ኢትዮጵያዊነታቸውን ያጎለበተላቸው ነው። አንድነትና ፍቅር የማይፈታው ችግር እንደሌለም እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል።

እነዚህ ወጣቶች በየተሰማሩባቸው ቦታዎች የተመለከቷቸው ተጨባጭ ሁኔታዎች ቀደም ሲል ካላቸው እውቀት ጋር ሲነፃፀር የተለየ ነው። ይህም በየቀየው ያለውን እውነታና በወሬ ደረጃ የሚናፈሰውን ተግባር የተለየ እንዲሆን አድርጎታል። ወደፊትም ለየትኛውም ዓይነት የተሳሳተ መረጃ እንዳይጋለጡ የሚያደርጋቸው ነው።

አገልግሎት ሰጭዎቹ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ አካባቢዎች ርቀት ቢገድባቸውም ቅሉ፤ በአንድነት እና ፍቅር አብረው ተቻችለው የሚኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን በአገልግሎታቸው ወቅት  በተግባር ማረጋገጥ መቻላቸውን ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲገልፁ አድምጠናል። ርግጥ የትኛውመ ወገን ወደ አንድ የሀገሪቱ ክፍል ቢሄድ እንዲህ ዓይነቱን የፍቅር፣ የአንድነትና ተቻችሎ የመኖር ኢትዮጵያዊ እሴትን መመልከቱ አይቀርም። ምክንያቱም የሀገራችን ህዝቦች የዘመናት ህይወት በእንዲህ ዓይነት ጠንካራ የፍቅር ድር የተሳሰረ በመሆኑ ነው። እናም ወጣቶቹ በተሰማሩባቸው ቦታዎች ሁሉ የአስተማሪነትንና የአነሳሽነትን ተግባር በቻ ሳይሆን የተማሪነትንና የተነሳሽነትን ባህልም ሊሰንቁ መቻላቸው የሚያጠያይቅ አይሆንም።

አገልግሎት ሰጭዎቹ ከተሰማሩበት ህዝብ የሚገኙትን ጥቅም እየቀመሩና ማንነቱን እያከበሩ፤ በሚያከናውኗቸው እንደ ችግኝ ተከላ፣ የአካባቢ ፅዳትና ሌሎች የበጎ ፍቃድ ተግባራት የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች በማነቃቃት ረገድ ጉልህ ሚና ሊያበረክቱ ይችላሉ። በአንድ ክልል ውስጥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች ለክሉ ማህበረሰብ ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች በበለጠ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በሚያደርጓቸው መስተጋብራዊ ግንኙነቶችና ውይይቶች በርካታ ጉዳዮችን በማንሳት ትክክለኛ ግንዛቤ እንደሚያገኙ ግልፅ ነው።

በየትኛውም አካባቢ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ወገናችን ለበጎ ተግባር በጋራ የሚቆም ነው። አገልግሎት ሰጭዎቹ በሚያከናውናቸው ተግባራት ህዝቡ ከጎናቸው እንደሚቆም ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ለዚህም ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተሰማሩ ወጣቶች ሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች ከጎናቸው እንደሆነና በባህላዊ ዜማዎች ታጅበው የተሻለ ስራ መስራት እንደቻሉ መናገራቸውን መጥቀስ ይቻላል። በሌሎች አካባቢዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶችም የተናገሩትም ተመሳሳይ ነገር ነው። ይህም የኢትዮጵያ ህዝብ እያስተማረ የሚማር፣ እየተማረ የሚያሰተምር ስራ ወዳድ መሆኑን ሁነኛ ማሳያ ይመስለኛል።

በየትኛውም አካባቢ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ለወጣቶቹ እየለገሳቸው ያለው ፍቅር ኢትዮጵያዊነት በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል አንድ ዓይነት መገለጫ ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ከማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል የመጣ ወገንን ተቀብሎ በማቆየት ወደር የሌለው ፍቅር ባለቤት ነው—ኢትዮጵያዊ። ይህም ወጣቶቹን በኢትዮጵያዊነታቸው እንዲኮሩ የሚያደርጋቸው መሆኑ አያጠያይቅም። ርግጥም ወጣቶቹ ኢትዮጵያዊነትን ከቃል ባሻገር በተግባር የሚማሩበት መድረክ ነው—ድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት።

ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈቃቅዶ በመኖር ረገድ ምንም ዓይነት ልዩነት የለም። ከደቡብ ጫፍ እስከሰሜን ዳርቻ እንዲሁም ከምስራቅ እስከ ፀሐይ መጥለቂያው ምዕራብ ድረስ ኢትዮጵያዊ እሴት አንድ ዓይነት ነው። ዜጎች ከየትኛውም አካባቢ ቢመጡ፤ ሚዛን የሚደፉት እሳቤዎች፤ የመከባበር፣ የመቻቻል፣ የአንድነትና አብሮ ተፈቃቅቀሮ የመኖር እሴቶች ናቸው። ከዚህ ውጭ ኢትዮጵያዊነት የሚገልፅ ነገር ፈልጎ ማግኘት አይቻልም።

በመሆኑም ወጣቶቹ በየተሰማሩባቸው አካባቢዎች እነዚህን እሴቶች ይበልጥ በማጎለበት ለህብረተሰቡ ተጨማሪ አቅም መሆን ይጠበቅባቸዋል። በየትኛውም የሀገሪቱ ጫፍ ላይ የሚገኘውና በታሪክ ዑደት ውስጥ ያለፈው የሀገራችን ህዝብ ያሉት አኩሪ እሴቶችን ከአንድነት፣ ከመደመርና ከፍቅር እሳቤዎች ጋር በአዲስ መልክ እንዲንሰላሰሉ ማድረግ የአገልግሎት ሰጪ ወጣቶቹ ድርሻ ይመስለኛል።

ከዚህ በተጨማሪ ተምረው ማስተማር የሚችሉት እነዚህ ወጣቶች ከህዝቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለቸው እንደመሆኑ መጠን፤ የፅንፈኝነት አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ ሚያስከትለውን አደጋ የማሳወቅ፣ የህግ የበላይነትን በማስከበር አካባቢያዊ ሰላምን ማስጠበቅ እንደ ሀገር ጠንክረን እንድንወጣ የሚያደርጉን ተግባሮች መሆናቸውን ማስረዳት ያለባቸው ይመስለኛል።

በየትኛውም መልኩ ሊገለፅ የሚችል የአንድ ወገን ፅንፈኝነት ጉዳትን እንጂ ሀገራዊ አንድነትን ሊያመጣ እንደማይችል እንዲሁም ህግን ባለማክበር ሰላምን ማረጋገጥም ይሁን ፍላጎቶችን ማስፈፀም እንደማይቻል ለህብረተሰቡ ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል። እነዚህን ተግባሮች ሲከውኑም ፍቅርን፣ መቻቻልንና አገራዊ አንድነትን ይበልጥ ያጠናክራሉ።     

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy