Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢኮኖሚው የበለጠ ያድጋል

0 300

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢኮኖሚው የበለጠ ያድጋል

ይልቃል ፍርዱ  

በኢትዮጵያ ሰፊ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተከናውነዋል። በመሰራትም ላይ ይገኛሉ፡፡  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተሰርተው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ወደስራ እንዲገቡ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ ችግር አጋጥሞ ነበር፡፡ ያልተፈታ ችግር ሆኖ የዘለቀ ቢሆንም ዛሬ ላይ መልክ እየያዘ ይገኛል፡፡ ከቀውስ ለመውጣትና የጎለበተ ሀገራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገው ሰፊ ጥረት ቀጥሏል። በአገር ደረጃ ተከስቶ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመፍታት በተወሰዱት ጠንካራ ርምጃዎች ከውጭ ለጋሽ መንግሥታትና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አገራችን ድጋፍ እያገኘች በመሆኑ ችግሩ እየተፈታ ይገኛል፡፡

መንግሥት አስቀድሞ በእጃቸው የውጭ ምንዛሪ ገንዘብ ያከማቹ ግለሰቦች መጠኑ የቱንም ያህል ቢሆን ያለምንም ችግር በብሔራዊ ባንክ  እንዲመነዝሩ በሰጠው ማስጠንቀቂያ መሰረት በቀን ብቻ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ብሔራዊ ባንክ እየገባ ይገኛል፡፡

በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ (የውጭ ምንዛሪና የሀገር ውስጥ ብር) በግል ቤታቸውና ካዝናቸው አስቀምጠው የውጭ ምንዛሪውንም አንቀው የነበሩ ግለሰቦች በብሔራዊ  ባንክ ስራ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድረው ሀገራችን በውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር እንድትመታ አድርገው ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ችግሩ እየተፈታ ይገኛል፡፡ ይህ ሁኔታ በሀገራዊ የኢኮኖሚና የልማት ስራዎቻች ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሮ ቆይቶአል፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ስራቸው እንዲጓተትና በፍጥነት እንዳይራመዱ ተፈላጊ ግብአቶች እንዳይቀርቡ ስራዎችም በታቀደው የግዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ ከፍተኛ ጫና አሳድሮ ቆይቶአል፡፡ በሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገታችንም ሆነ በሕብረተሰቡ የእለት ተእለት ሕይወት ላይ ይሄን የመሰለው በሀገር ላይ የሚፈጸም ደባና ሴራ ብዙ ችግሮችን አስከትሏል፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት መድሀኒቶችን እንደልብ ከገበያ ለማግኘት የማይቻልበትም ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገንዘብን በይበልጥም ዶላርን በቤታቸው ያከማቹ ወገኖች ወደ ባንክ እንዲያስገቡ ይህን ማድረግ ካልቻሉ መንግስት በሚወስደው  እርምጃ ገንዘባቸው ዋጋ ሊያጣ እንደሚችል መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት ጥሪውን የተቀበሉት ወገኖቻችን ገንዘባቸውን ወደ ባንክ በመውሰድ እያስገቡ ሲሆን አሻፈረኝ ያሉት ደግሞ በየቦታው በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለማስወጣት ሲሞክሩ እየተያዙ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አሁንም ገና ብዙ ሊያዝ እንደሚችል ይገመታል፡፡ ይህ ሀገር ገዳይ የሆነ የኢኮኖሚ ሸፍጥ ማመን በማይቻል መልኩ በብሔራዊ ባንክ የነበረውን መጠባበቂያ ጭምር አሳጥቶ ነበር፡፡ በሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትና ልማት ስራዎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሮ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ሰአት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በመንግስት በኩል እየተፈታ ሲሆን በጥቁር ገበያ ያለውም ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ በማሽቆልቆል ላይ ይገኛል፡፡የበለጠም ዋጋው እንደሚወርድ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሀገር ውስጥ ገብተው ከተሰማሩትም በላይ በርካታ የውጭ ኢንቨስተሮች በተለያዩ ዘርፎች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው ለመስራት ፍላጎታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ መንግስት ከኤርትራ ጋር ያደረገው ስምምነት የወደብ ችግሮቻችንን ከመፍታትም አልፎ  ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገታችን ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡ ሀገራዊ ኢኮኖሚያችን ገብቶበት ከነበረው የኢኮኖሚ ድቀትና ኪሳራ ለመውጣት በርካታ ስራዎች የሚጠብቁን ቢሆንም ዛሬ ላይ እያገገመና የበለጠ ውጤታማ ስራ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በከተሞች መስፋፋትና ማደግ፤ በኢንዱስትሪው ዘርፍ፤ በትምህርት፤ በጤናው በትራንስፖርት ዘርፍ፤ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ መንገዶችን በመላው ሀገሪቱ በማስፋፋት፤የኃይልማመንጫ ግድቦችን በመስራት፤ኤየር ፖርቶችን በማስፋፋት፤ ለዜጎች የሚሆኑ መጠነ ሰፊ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለመገንባት፤ በሆቴልና ቱሪዝም መስክ፤ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስፋፋት፤ ግብርናውን ከነበረበት ኋላቀር አሰራርና አስተራረስ በማውጣት ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ ትምህርት በመስጠት ሰፊ ለውጦችን በሀገር ደረጃ ለማስመዝገብ ተችሎአል፡፡ ኢኮኖሚያችን ተፈጥሮ በነበረው ሀገራዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ ዝግመት ውስጥ ገብቶ የነበረ ቢሆንም ከዚህ በመውጣት የተሻለ ጉዞ ጀምሯል፡፡ ከግብርናው የሚገኘው ምርት ቀድሞ ከነበረው በእጥፍና ከዚያም በላይ እንዲያድግ የተደረገበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

የሀገር ኢኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው እያንዳንዱ ዜጋ በየተሰለፈበት መስክ ተግቶ መስራት ሲችል ነው፡፡ መንግስት ወደ ሀገራችን  የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲገባ በዲፕሎማሲው መስኮች ሰፊ ጥረቶችን አድርጎአል፤ ስኬቶችንም አስመዝግቧል፡፡ በዚህም መሰረት ከአረቡ አለም እስከ ምእራባውያን ድረስ ድጋፋቸውን እየገለጹ  ይገኛሉ፡፡ የኢኮኖሚ እድገት የበለጠ ሊያድግና ሊሰፋ የሚችለው በተቀመጠው እቅድ መሰረት ሕዝብና መንግስት በጋራ ሆነው በመረባረብ ያለእረፍት ቀን ከሌሊት መስራት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡,ካለፉት አመታት ሰፊ ተሞክሮዎቻችን ማረጋገጥ እንደቻልነው ብርቱና ጠንካራ ስራ ብቻ ሀገርን መለወጥ እንደሚችል ነው፡፡ በዚህ መልኩ መስራት ከቀጠልን በእርግጠኝነት ዛሬም ከትላንቱ የበለጠ የኢኮኖሚ ድል እናስመዘግባለን፤ ሀገራዊ ኢኮኖሚያችንም የበለጠ  ያድጋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy