Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እርቅና መደመሩ በጥላቻና በመነጠል አይበረዝ

0 827

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እርቅና መደመሩ በጥላቻና በመነጠል አይበረዝ

ኢብሳ ነመራ

ኢትዮጵያ ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችን እንዲሁም አሰቃቂና ጸያፍ ጥቃቶችን አስተናግዳለች። በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በጅግጅጋና በሌሎች የክልሉ ከተሞች ከተወላጆቹ ጋር ተቀላቀለው የሚኖሩ ሰላማዊ ኢትዮጵያውያን ላይ የህይወትና የአካል ጉዳት ያደረሰ ድንገተኛ ጥቃት ተፈጽሟል። በዚህ ጥቃት እስካሁን ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰላማዊ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል። የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም አሉ።  በርካቶች ለዓመታት ለፍተው ያፈሩት ንብረታቸው በድንገት ወድሞባቸዋል። ከኑሯቸው ተፈናቅለው ህይወታቸውን ለማትረፍ ከለላ ይሆናል ያሉት ስፍራ የተጠለሉ፣ ክልሉን ለቀው የሸሹም በርካቶች ናቸው።

ይህን ግጭት ድንገት የጫረው ትክክለኛ ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን በይፋ አልተገለጸም። ይሁን እንጂ ግጭቱ ዒላማ ያደረጋቸው ዜጎችና ግጭቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስፋፍቶ በተለያዩ ከተሞች ተመሳሳይ ጥቃት መፈጸሙ፣ እንዲሁም የሃገር ድንበር ቆርጦ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደሚኖሩበት ጅቡቲ መሻገሩ የተደራጀና መሪ ያለው መሆኑን ይጠቁማል። የጥቃቱ ሰለባዎች በሰጡት ምስክርነት፣ ከጥቃት ፈጻሚዎቹ ጋር የታጠቀ የክልሉ የጸጥታ ሃይል እንደነበረ ጠቁመዋል። ይህ ሁኔታ በክልሉ የመንግስት መዋቅር ውስጥ በተፈጠረ ቀውስ፣ ስልጣናቸውን ያጡ ወይም እናጣለን ብለው የሰጉ ግለሰቦች ያሉበት ቡድን እጅ ሊኖርበት እንደሚችል እንድንጠረጥር ያደርጋል። ለማንኛውም በዚህ ጉዳደይ ላይ የክልሉም ይሁን የፌደራል መንግስት ዝርዝር መረጃ እነዲሰጡ ይጠበቃል።

በዚህ ግጭት ከዚህ ቀደም በአካባቢ ያልተለመዱ ሁኔታዎችን ታዝበናል። የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን የግጭት ስፍራ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። በተለይ በ1969 ዓ/ም በሲአድ ባሬ የሚመራው የሱማሊያ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው ወረራ ታሪክ የማይረሳው ነው። በዚህ እሰከ ድሬ ደዋ ዘልቆ በነበረ ወረራ፣ በአሁኑ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የሚኖሩ በርካታ ዜጎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። ያኔ የነበረውን ሁኔታ ያስታወሱ የሃገር ሽማግሌዎች በሰጡት ምስክርነት፣ በዚያን ወቅት እንኳን የእምነት ተቋማት እንዳልተቃጠሉ፣ የሃይማኖት አባቶች ላይ ግድያ አለመፈጸሙን ተናግረዋል። ከዚያ ወዲህም በአካባቢው ግጥቶችና ጦርነቶች ነበሩ። ያኔም ቢሆን ሰዎች በማንነታቸውና በእምነታቸው ተነጥለው ጥቃት አልተፈጸመባቸውም፤ አብያተ ክርስቲያን አልተቃጠሉም። ሰሞኑን በክልሉ በተነሳው ግጭት ግን ባዕድ ወራሪ ሃይል ያልፈጸመው በተክርስቲያን የማቃጠል፣ ቀሳውስትን የመግደልና የመደብደብ ጥቃት ተፈጽሟል። ይህን በሃገራችን ያልነበረ የመጨካከን ምግባር አሁን በተለይ ምን አመጣው? የሚለው  እንቆቅልሽ ነው።

እንቆቅልሽ የሆነው  ይህ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ያጋጠመው ሁኔታ ብቻ አይደለም። በሌሎችም የሃገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁ ነባር የማህበረሰቡን የሰብአዊነትና የመቻቻል ስነምግባር የጣሱ ድርጊቶች ተፈጽመዋል። እነዚህን ድርጊቶች ማስታወስ በራሱ የሚዘገንን ቢሆንም፣ የችግሩ አሳሳቢነት መታወቅ ስላለበት ደፍሮ ማስታወሱ ተገቢ ይመስለኛል፤ ሁሉንም ሳይሆን የችግሩን አሳሳቢነት ለማሳየት ያህል የተወሰኑትን።

ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ላይ የኦሮሞ የፖለቲካ አክቲቪስት የሆነውን ጃዋር መሃመድ ለመቀበል በተካሄደ የአደባባይ ትዕይንት ላይ አንድ ግለሰብ ቦምብ ይዟል በሚል ሰበብ (ፖሊስ ይህ ውንጀላ ሃሰተኛ መሆኑን አረጋግጧል) አደባባይ ላይ፣ ሰዎች ከበው እየተመለከቱ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሏል። ይህ አሰቃቂ ግድያ በህዝቡ ዘንድ ድንጋጤ ፈጥሯል። ሰው መሞቱ አይደለም ድንጋጤ የፈጠረው፤ ይህን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተለማምደነዋል። ድንጋጤ የፈጠረው የአገዳደሉ ሁኔታ አሰቃቂ መሆኑ ነው።

በዚህ አሰቃቂ አኳኋን እንስሳ እንዲሞት የማይፈቀድው የኢትዮጵያውያን ስነምግባር፤ ግድያው በተፈጸመበት አካባቢ ያሉ የአርሲ ጎሳ ኦሮሞዎች ስነምግባር በምን አኳኋን ጉልበት አጥቶ ረክሶ ይህ አሰቃቂ ድርጊት ተፈጸመ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። ልብ በሉ፣ ይህ ድርጊት የተፈጸመው አሁን በሃገሪቱ የተጀመረው ለውጥ አማጭና አራማጅ ነን በሚሉ ወጣቶች መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። በዚህ ድርጊት የረከሰው የህዝቡ ስነምግባር ብቻ አይደለም። ህግም ተጥሷል። የመንግስት ዕውቅና በተሰጠው፣ በጸጥታ ሃይሎች ጥበቃ በሚደረግለት በዚህ የአደባባይ ትእይንት ላይ ይህ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጸም ህግ ማስከበር ሳይቻል የቀረው ለምንድነው? ድርጊቱን የፈጸሙ ግለሰቦች ህግን እንዴት አልፈሩም? ህግ አስከባሪ የጸጥታ ሃይልስ እንዴት የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አቃተው? እንቆቅልሽ ነው።

ሌላ ህግና ነባር ስነምግባር የተጣሰበት አሰቃቂ ሁኔታ እናስታውስ። ከቀናት በፊት በአማራ ክልል በጣና በለስ ፕሮጀክት ሶስት ግለሰቦች በማንነታቸው ብቻ በድንጋይ ተወግረው ተገድለዋል። በድብቅ ሳይሆን በገሃድ፣ በጠራራ ጸሃይ። ፍጹም ሩህሩህ የሆነውን ፈጣሪ በማመን በሚታወቀውና ይህን እምነቱን አንገቱ ላይ ባሰረው ማተብ ባጸና የአማራ ማህበረሰብ ውስጥ፣ አንገቱ ላይ ማተብ ያሰረ ሰው፣ ሌላ ማተብ ያሰረ ወገኑን ያለምንም ሃጢያት በድንጋይ ወግሮ የሚገድልበት ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ይህን በገሃድ የተፈጸመ ድርጊት ህግ እንዴት ማስቆም ሳይችል ቀረ? እንቆቅልሽ ነው።

እንግዲህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድ ሰሞን አውርተን እንደዋዛ የምናልፋቸው በርካታ አሰቃቂና ጸያፍ የስነምግባር እንዲሁም የህግ ጥሰቶች ተፈጽመዋል። ከላይ የተጠቀሱትን ለማሳያነት ካነሳን በቂ ነው። እዚህ ላይ ዋናው ጉዳይ  በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ጭምር ሰላማዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲር ያደረገ፣ መከባበርና መቻቻል ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገ ስነምግባር ድንገት በቀላሉ በምን አኳሀን በቀላሉ ሊረክስ ቻለ የሚለው ነው። ወይንስ ቀድሞውኑም እርስ በርሱ የሚዋደድ፣ የሚከባበርና የሚቻቻል ህዝብ ወዘተ ስንል የነበረው የውሸት ነበር? መንግስት ሳይፈርስ፣ ህግ እያለ፣ ህግ አስከባሪ ተቋማትና የጸጥታ ሃይል በስራ ላይ እያለ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥስ ለምን አልተቻለም? ይህ የበርካታ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ነው።

ያም ሆነ ይህ፣ አሁን ሃገሪቱ እመርታዊ የሆነ የለውጥ ሂደት ላይ ተገኛለች። ይህን ለውጥ የወለደው ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ መስፋት አቅቶት ተጨንቆ የነበረው የሃገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር፣ የዘትር እየሆነ የመጣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የመልካም አስተዳደር መጓደልና መዝብራ ነው። የለውጡ ጅምር ተስፋ ሰጪ ነው። በአስራ ሺህ የሚቆጠሩ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ወንጀል የተከሰሱና የተፈረደባቸው ዜጎች ነጻ መለቀቃቸው፤ በውጭ ሃገር የነበሩ የትጥቅ ትግልን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ሲታገሉ የነበሩ ተቃዋሚ ሃይሎች ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ለማደረግ መንግስት ያቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደሃገር ቤት መግባታቸው የለውጡን ተስፋ ሰጪነት ያሳያል። በውጭ ሃገራት የሚኖሩ በሃገራቸው ፖለቲካዊ ሁኔታ የተከፉና ያኮረፉ በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የለውጥ አመራሩን ተቀብለው በስርአቱ ላይ እምነት ማሳደራቸውም በሃገሪቱ ያለውን መጻኢ ተስፋ ያሳያል።

ይሁን እንጂ ከላይ ቀደም ሲል የተጠቀሱት አይነት የእርስ በርስ ግጭትና አሰቃቂ ግድያዎች፣ አንዱ ሲያበቃ ሌላው እየተቀበለ ስጋት የፈጠረበት ሁኔታ መኖሩ የለውጡን ያህል ገሃድ እውነት ነው። በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚያጋጥሙት ለስነምግባርና ለህግ አሻፈረኝ ያሉ አውዳሚ ሁከቶች፣ ግጭቶችና አሰቃቂ ግድያዎች ተስፋ ሰጪውን ለውጥ እንዳይበርዙት መጠንቀቅ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን። በተለይ በየአካባቢው የሚያጋጥሙት ግድያዎች የሚፈጸሙት የለውጡ አማጭና አራማጅ በሆኑ ቄሮ፣ ፋኖ ወዘተ በሚባለው ቡድን ውስጥ በሚቆጠሩ ወጣቶች መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ወዴት እየሄድን ነው? የሚል ጥያቄ ቀስቅሷል። እርግጥ ነው ይህ ድርጊት ሁሉንም ወጣቶች (ቄሮዎች፣  ፋኖዎች . . .) አይወክልም። ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ የቄሮና የፋኖ ስም መነሳቱ ግን አልቀረም።

የለውጡ ሃይል የሆነው ወጣት (ቄሮ፣ ፋኖ . . .) የህግ የበላይነትና የህዝቡ ስነምግባር እየተጣሰ በሚቀሰቀሱ ሁከቶች፣ ግጭቶችና ግድያዎች በመስዋዕትነት ያመጣው ለውጥ መና ሆኖ ሊቀር እንደሚችል፤ ሃገሪቱም ወደመቀመቅ እንዳትወርድ ማወቅ አለበት። ወጣቱ እውነተኛ የለውጥ አማጭና ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጠው ስነምግባርና የህግ የበላየነትን አክብሮ ሰላም በማስፈን ለውጡ ገናና ሆኖ እንዲወጣ ሲሰራ ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ የለውጡ አማጭና ባለቤት የሆነው ወጣት፣ የለውጡ አምካኝ እንዳይሆን ያሰጋል።

እንግዲህ በአንድ ወገን ስለ እርቅና መደመር እየተሰበከ፣ በሌላ ወገን ጥላቻ ሲሰበክና በተግባር ሲገለጽ አያየን ነው። በአንድ ወገን እርቅ ሲከናወን በሌላ በኩል ጠላትነት እየተስፋፋ ነው። በዚህ ሁኔታ መጠላላት እየሰፋ፣ ሰዎች በዘፈቀደ እየተገደሉ፣ እየተሳደዱ የተያዘው የእርቅና መደመር እንቅስቃሴ በጥላቻና በመነጠል እየተበረዘ ነው። እርቅና መደመሩ፣ በጥላቻና መነጠል ተበርዞ የሚደበዝዝ ከሆነ ተሰፋ የተደረገው ለውጥ መና እንደሚቀር ማስተዋል ብልህነት ነው። እናም ወጣቶች የለውጡ አማጭና ባለቤት ብቻ ሳይሆን ጠባቂና አጎልባችም ሁኑ፣ በእውነተኛ ሁሉን አቀፍ እርቅና መደመር።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy