Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እንተዋወቅ

0 482

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እንተዋወቅ

ዓለምአየሁ አ

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የገንዘብ ወይም ሌላ የተለየ ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን ሌሎችን ለመጥቀም ዓላማ ብቻ የሚከናወን ከሰብአዊነት የሚመነጭ ተግባር ነው። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዓላማ ሌሎችን መጥቀም ላይ ያተኮረ ቢሆንም፤ እውቀትን፣ የስራ ልምድን በማጎለበት አገልግሎት ሰጪውን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚጠቅምበት ሁኔታ አለ። በዓለም አቀፍ ደረጃ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከአራት መቶ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። ይፋዊ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት የተጀመረው በ16ኛው ክፍለ ዘመን ገደማ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ የፍቃደኝነት አገልግሎት በአመዛኙ በወታደራዊ አገልግሎት የተገደበ ነበር። ከዚህ ውጭ በተለይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከቀይ መስቀል ማህበር ጋር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ሰዎች ነበሩ።  

በተለይ በአሜሪካ በወጣት ወንዶች ክርስቲያነች ማህበር (ወወክማ) እና መሰል ማህበራት የተደራጁ ወጣቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚያቀናጁ ተቋማትም ተደራጅተዋል። የብሄራዊና ማህበረሰባዊ አገልግሎት ኮርፖሬሽን (Corporation for National and Community Service) በአሜሪካ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ከሚያስተባብሩ ተቋማት አንዱ ነው። በዚህ ተቋም መረጃ መሰረት እ ኤ አ በ2012 ዓ/ም ብቻ 64 ነጥብ 4 አሜሪካውያን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ተሰማርተዋል። ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች አሃዝ ለአካለ መጠን የደረሱ አሜሪካውያንን 26 ነጥብ 5 በመቶ ይሸፍናል። እነዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪዎች የ7 ነጥብ 9 ቢሊየን ሰአታት አገልግሎት ሰጥተዋል። ይህ በገንዘብ ሲተመን 175 ቢሊየን ዶላር እንደሚሆን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።  

በኢትዮጵያ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚል ይፋዊ ስያሜ ተሰጥቶት በመደበኛነት ባይከናወንም የዳበረ የበጎ ፍቃድ አገልሎት ባህል አለ። ደቦ ወይም ጂጊ አንዱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚካሄድበት ስርአት ነው። አንድ ሰው ቤት ሲገነባ የአካባቢው ሰው በቁሳቁስ ልገሳ፣ በሞያ ያግዘዋል። ድግስ ሲኖር ጎልማሳ ወንድና ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ህጻናት ጭምር እነደአቅማቸውና ሞያቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ። የታመመን ወደወጌሻ/ህክምና መወሰድ፣ ቀብር ወዘተ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚከናወን ነው። ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመደበኛ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መነሻ የሚሆን በቂ ጥንስስ መኖሩን ያረጋግጣል።

ወደመደበኛ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስንመለስ በተለይ ባለፉ አራት አስርት ዓመታት ጎልተው የታዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህሪ ያላቸው ዘመቻዎችን እናገኛለን። በ1967 ዓ/ም ከ10ኛ ክፍል በላይ የሆኑ 60 ሺህ ተማሪዎች የተሳተፉበት የእድገት በህብረት የዕውቀትና የስራ ዘመቻ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ታሪክ ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዝ የመስለኛል። ይህ ዘመቻ በተወሰነ ደረጃ የአሰገዳጀነት ባህሪ ቢኖረውም፣ አብዮቱን ያመጣውና ገና ለህዝቡ መብትና ጥቅም የመፋለም ወኔው ያልበረደው አብዛኛው ወጣት ዘመቻውን ፈቅዶት ነበር። ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው ይህ ዘመቻ በመሰረተ ትምህርት፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በተለይ የገበሬ ማህበራትን በማደራጀትና የመሬት ለአራሹን አዋጅ በማስፈጸም ረገድ ትልቅ ድርሻ ነበረው። ይህ ዘመቻ የኢትዮጵያ ብሄሮች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ – አንዱ የሌላውን ወግና ባህል፣ ቋንቋ እንያውቁ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱ አይካድም።

በመቀጠል ከ1971 ዓ/ም ጀምሮ ለ12 ዓመታት ያህል በገጠርና በከተማ በሃያ ሁለት ዙሮች ወጣቶች የተሳተፉበት የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ተካሂዷል። ይህም ዘመቻ የአስገዳጅነት ባህሪ ቢኖረውም በዘመቻው ላይ የሚሳተፉት ወጣቶች እንደ እዳ አይወስዱትም ነበር። ይህ በመላ ሃገሪቱ ዜጎች መሰረታዊ እውቀት በተለይ ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ የማደረግ ዓላማ ይዞ የተካሄደ ዘመቻ ውጤታማ ነበር። ይህን የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ አሁን ሊካሄድ ለታቀደው ወሰን ተሻጋሪ የበጎ አገግሎት ዘመቻ እንደ መነሻ ሊሆን ይችላል።

በ1977 ዓ/ም አስከፊ ቸነፈር ያስከተለ ድርቅ ተከስቶ በነበረበት ወቅት፣ ተጽእኖውን ለመቋቋም በትግራይና አማራ አካባቢ የቸነፈሩ ተጠቂ የሆኑ ዜጎች በቤኒሻንጉል፣ በጋንቤላና በምእራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች እንዲሰፍሩ ተደርጎ ነበር። በዚህ ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ለሰፋሪዎቹ የመኖሪያ ጎጆ በመስራት አገልግሎት ሰጥተዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታትም በተለይ በክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። አዲስ አበባና ድሬደዋን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ሲካሄድ በቆየው በዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በየዓመቱ ከ10 ሚሊየን በላይ በተለያየ የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ወጣት ተማሪዎች ተሳትፈዋል። ይህ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ በጽዳት፣ የትራፊክ ደንብ በማስከበር፣ የደካሞችን መኖሪያ ቤት በመጠገን፣ በደም ልገሳ ወዘተ ላይ ያተኮረ ነበር። ዘንድሮም በሃገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄድ የወጣቶች የክረምት ወራት ለበጐ ፈቃድ አገልግሎት 13 ነጥብ 6 ሚሊየን ወጣቶች ተሰማርተዋል።

ሰሞኑን ደግሞ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ አንድ ሺህ ያህል ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች ወደሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ዘምተዋል። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፕሮግራሙን በጋራ አስተባብረውታል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘማቾቹ የዘንድሮ የዩኒቨርሲቲዎች ተመራቂዎች ናቸው።  ከነሃሴ 1 እስከ ነሃሴ 15፣ 2010 ዓ/ም የሚቆየው ይህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወሰን ተሻጋሪ የተሰኘው የአንድ ክልል ወጣቶች ወደሌሎች ክልሎች በመዝመት የሚከናወን በመሆኑ ነው። ይህ ከዚህ ቀደም ሲካሄድ ከነበረው ሃገር አቀፍ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ልዩ ያደርገዋል።

ይህ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚያበረክተው ኢኮኖሚያና ማህበራዊ ፋይዳ በተጨማሪ ወጣቶች ከሚኖሩበት ወደ ሌላ ክልል በመሄድ የሚያከናውኑት መሆኑ የአንዱ ብሄር ተወላጆች ሌሎችን እንዲያውቁና ወጣቶቹም እርስ በርስ እንዲተዋወቁ በማድረግ የጋራ እሴትን መገንባት ያስችላል።  ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ ወጣቶች መሃከል የሚመሰረት ትውውቅና የጋራ እሴት ደግሞ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ከፍ በማድረግ ሃገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር መሰረት መጣል ያስችላል። በተለይ ባለፉ ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት በልዩነታችን ላይ አተኩረን በመስራታችን እየሳሳ የመጣውን ሃገራዊና የአንድነት ስሜት በማጠናከር ረገድ የማይናቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ይሁን እንጂ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያስገኝ፣ ተቋማዊ መሆን እንደሚያስፈልገው ማስታወስ ተገቢ ነው። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሃገር አቀፍ ፖሊሲ፣ የስነምግባር ደንብ፣ ፖሊሲ አስፈጻሚ፣ አፈጻጸሙን የሚገመግም . . . ራሱን የቻለ ተቋም ያስፈልገዋል።

በአጠቃላይ፣ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ያበረክታል። ከዚህ በተጨማሪ ወጣቶች ከስራ ዓለም ጋር እንዲተዋወቁ፣ በሰለጠኑበት ሞያ ብቃታቸውን እንዲያዳብሩ፣ የማህበረሰቡን ችግሮችና ጥያቄዎች እንዲረዱ ያደርጋል። በተለይ አሁን ባለው የሃገራችን ሁኔታ የተለያየ ብሄር፣ ብሄረሰብ ተወላጅ ወጣቶች እንዲተዋወቁ፣ ብዝሃ ኢትዮጵያን እንዲገነዘቡና የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲያጎለብቱ ማድረግ ያስችላል። በመሆኑም የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሊስፋፋና ባህል ሊሆን ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy