Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወጣት ማዕከላቱ ያልተሻገሯቸው ዐቢይ ችግሮች

0 669

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወጣት ማዕከላቱ ያልተሻገሯቸው ዐቢይ ችግሮች

መሠረት ጌቱ

በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ቁጥር ያለው ወጣት ይገኛል፡፡ ይህ ኃይል ጤናው ተጠብቆ “ለሀገራዊ ልማት የበኩሉን አስተዋፅኦ በአግባቡ  እንዲያበረክት ደግሞ በመከላከሉ ዙሪያ ጠንካራ ስራዎች ከሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ ነው፡፡ በሀገሪቱ በኤች. አይ.ቪ መከላከል ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች የሚያመላክቱት ይህ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ ተጠቂ መሆኑን ነው፡፡ በወጣቱ ዙሪያ ኤች. አይ.ቪን በመከላከል ረገድ ከሚሰራባቸው ተቋማት አንዱ በየክፍለ ከተሞች የሚገኙ ወጣት ማዕከላት ናቸው፡፡ በዚህ ዙሪያ በአዲስ አበባ ከተማ የልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ወጣት ማዕከል ተገኝተን ወጣቶችን እና የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረን ያዘጋጀነውን ፅሁፍ በሚከተለው መልክ አቅርበናል፡፡

በወጣት ማዕከላት በዋነኝነት እንዲሰጡ የሚጠበቁት አገልግሎቶች የቤተ መጽሀፍት፣ የአይ ሲቲ እና የተለያዩ ስፖርታዊ መዝኛጫዎች እንደሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በተጨማሪም ወጣቱ ጤናውን ጠብቆ አምራች እንዲሆን የሚያስችሉ የተለያዩ የጤና አገልግሎቶች እንዲሰጡ ይፈለጋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የኤች አይቪ አገልግሎት አንዱ ነው፡፡ በማዕከሉ የተለያየ አገልግሎት ፈልገው ከመጡ ወጣቶች ጋር ወዳደረግነው ውይይት እናልፋለን፡፡

ወጣት ሪኩማ አለማየሁ ዕድሜው 20 ዓመት ሲሆን በኤች.አይ ቪ ዙሪያ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ እንደሌለው ይናገራል፡፡ ሪኩማ ስለ በሽታው ምንነት፣ እንዴት እንደሚተላለፍ እና ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ከማዕከሉም ሆነ ከሌላ አካል ምንም መረጃ እንዳላገኘ አጫውቶናል፡፡

ወጣት ማዕከላት በዋናነት ዓላማ አድርገው የሚቋቋሙት የወጣቶችን ስብዕና መገንባትን  ነው፡፡ ይህም ወጣቱን በአዕምሮና በአካል ብቁ ማድረግን ያካትታል፡፡ የወጣቱ ጤና እንዲጠበቅ ግንዛቤ በመፍጠር አስቀድሞ የመከላከሉን ስራ ከጤና ጣቢያዎች እና ከወረዳ ጤና ፅህፈት ቤቶች ጋር በመቀናጀትና የሰለጠነ ባለሙያ በመመደብ ማከናወን ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር ወጣት ማዕከላት በባለሙያ ረገድ ያለባቸው ክፍተት ከዚህ በፊት በሰራነው ዘገባ ለመረዳት የቻልን ሲሆን የባለሙያ ፍልሰትና በለቀቁ ባለሙያዎች ምትክ ቶሎ ያለመቅጠር ክፍተት በስፋት ተስተውሏል፡፡ ይህም የታቀደው ስራ በአግባቡ እንዳይሰራ ከማድረጉም በላይ አገልግሎቱ ለረጅም ጊዜ እንዳይሰጥ ያደርጋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወጣቶች ማግኘት ያለባቸውን መረጃ ስለማያገኙ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡

ሌላው ያነጋገርነው ወጣት ፍቅሬ ሎምቢሶ ይባላል፡፡ በማዕከሉ በኤች. አይ.ቪ ዙሪያ የሚሰሩ ስራዎች የሚፈለገውን ያህል ውጤት አላመጡም፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ አይሰጥም፡፡ ብዙ ወጣት ወደ ማዕከላቱ እንደሚመጣ ታውቆ የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ቢሰሩ መልካም ነው፡፡ ወጣቶች በአሁኑ ጊዜ በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸው ለኤች. አይ ቪ እየተጋለጡ ይገኛሉ ሲል አስተያየቱን ሰጥቶናል፡፡

የኤች. አይ.ቪ ስርጭት ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ላይ ጎልቶ እንደሚታይ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለቫይረሱ ተጋላጭ ተብለው አብዛኛውን ቁጥር ይዘው የሚገኙት ደግሞ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 30 የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡ በከተማችን እንደምናስተውለው በየመንደሩ እንደ አሸን በዝተው የሚታዩት እና በርካታ ወጣቶችን ለመጤ ባህልና ለተለያዩ አደንዛዥ ዕፆች የሚያጋልጡ በርካታ የንግድ እና መኖሪያ ቤቶች ወጣቱን ለከፋ የጤና ችግር እያጋለጡት ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ የጤና ችግሮች መካከል  ኤች.አይ.ቪ አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ወደዚህ ዓይነቱ ተግባር እንዳይገቡ መስራት ከሚጠበቅባቸው ማዕከላት አንዱ ወጣት ማዕከላት ናቸው፡፡ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዙም ይታመናል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ማዕከላት በሚፈለገው ልክ ባለመስራታቸው ከፍተኛ ክፍተት ሊፈጠር ችሏል፡፡

አሁንም ምልከታችንን ቀጥለናል፡፡ ወጣት ፋሲል ሌላው አስተያየት ሰጪ ነው፡፡ ወጣት ማዕከላት ለወጣቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ቢኖራቸውም በተለይ ወጣቱ ጤናውን ጠብቆ  አምራች እንዲሆን በማገዝ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው፡፡ በማዕከሉ በዓመት አንዴ የዓለም ኤች.አይ.ቪ ቀንን በማስመልከት ከሚሰጥ መድረክ በስተቀር ለወጣቱ የግንዛቤ፣ የምርመራ እና ሌሎች አገልግሎቶች በሚፈለገው ልክ አያገኝም፡፡ በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው በአግባቡ በጀት በመመደብ እንዲሁም የባለሙያ ቅጥር እና የምርመራ አገልግሎቶችን በቅንጅት ተደራሽ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡

በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ወጣት ማዕከል የኤች.አይ.ቪ አስተባባሪ ወይዘሮ መርሻ ተስፋዬ በበኩላቸው  በማዕከሉ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን በተመለከተ ከአቅራቢያቸው ካለ ጤና ጣቢያ ጋር እንደሚሰሩ ገልፀው፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ ኮንዶም ለወጣቶች የማሰራጨት ስራ ተሰርቷል፡፡ የምርመራ አገልግሎት ለመስጠትም የመመርመሪያ ኪቶች የአገልግሎት ጊዜያቸው በማለፉ ሌላ ግዢ እስኪፈፀም እየጠበቅን ነው፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫን በተመለከተ የበጀት እጥረት ስላለ ማካሄድ አልተቻለም ብለዋል፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው ለመረዳት እንደሚቻለው  በማዕከሉ ለወጣቶች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ቅንጅታዊ አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት በተሟላ መልኩ ለመስጠት አልተቻለም፡፡

በወጣቶች ዙሪያ ለሚሰሩ ማህበራት እየተደረገ  ያሉ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ሊፈተሹ የሚገባቸው መሆኑን ካደረግነው ቅኝት መረዳት ችለናል፡፡

አቶ ተመስገን ጌጡ  የወጣት ማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በማዕከሉ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ነገሩን፡፡ የወጣቶችን ጤና በመጠበቅ ረገድ በኤች.አይ.ቪ ዙሪያ የሚሰሩ ስራዎች የተቀዛቀዙ ናቸው፡፡ ወጣት ማህበራት በማዕከሉ ለሚሰሩ ሰራተኞች ክፍያ ከመፈፀም ውጭ በኤች.አይ.ቪ ዙሪያ ተከታታይነት ያለው ስራ መስራት የሚያስችል በጀት አልመደቡም፡፡ በመሆኑም ከክልል እና ከወጣት ማህበራት ለተወጣጡ 50 ወጣቶች የአቻ ለአቻ ትምህርት ከመስጠት ውጪ ተከታታይነት ያለው ስራ አልተሰራም፡፡ በመሆኑም በጀት ጠይቆ ከመስራት አንፃር ክፍተቶች አሉ ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ወጣት ማዕከላት ጤናማ ዜጋን ከመፍጠር አንፃር የሚወጡት ሚና ከየትኛውም ተቋም የተሻለ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ወጣት ማዕከላቱ ምቹ የሆኑ እና ግብዓት የተሟላላቸው እንዲሁም በባለሙያ የተጠናከሩ ሲሆኑ ነው፡፡ ካገኘነው መረጃ በመነሳት በኤች.አይ.ቪ ዙሪያ የሚሰሩ ስራዎች ብዙ የሚቀራቸው መሆኑን ተረድተናል፡፡ በመሆኑም በመረጃ እጥረት ምክንያት ለቫይረሱ የሚጋለጡ ዜጎችን ለመታደግ ከላይ የተጠቀሱ ግብዓቶች ተሟልተውና ተግባራቱ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል እንላለን፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy