የመደመር ምላሾች
ዋሪ አባፊጣ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ ሶስት ከተሞች (በዋሽንግተን ዲሲ፣ በሎስ አንጀለስና በሚኒሶታ) የመደመር ጉዞን ሲያካሂዱ የፈፀሟቸው የጎንዩሽ ውይይቶችም ስኬታማ ሀገራዊ ፋይዳ የነበራቸው ናቸው። ውይይቶቹን ያካሄዱት ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅት ሊቀመንበር ከዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ እንዲሁም ከአይ ኤም ኤፍና ከዓለም የገንዘብ ተቋም ፕሬዚዳንቶች ጋር ነው።
ውይይቶቹ ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ የኢትዮጵያዊያን መደመር በውጤትነት ያስገኛኘውን ምላሾች ናቸው ማለት ይቻላል። ይህም ለሀገራችን ወቅታዊና ዘላቂ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅምን የሚያስገኝ ነው። እናም ውይይቶቹን ከፋይዳቸው አኳያ በየፈርጃቸው ለመመልከት እንሞክራለን።
ዶክተር አብይ በውጭ ከሚገኘው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅት ሊቀመንበር ከዶክተር ብርሃኑ ነጋ ጋር ያደረጉት ውይይት፤ ድርጅቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገር ቤት ለመምጣት እንዲወስን ያስቻለ ነው። እንደሚታወቀው ድርጅቱ ባለፉት ጊዜያት በሀገራችን ሽብርተኝነት ተፈርጆ ነበር። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ባካሄዱት የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ጉዞ፤ ድርጅቱን ጨምሮ ኦነግና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ከሽብርተኝነት ዝርዝር ስማቸው እንዲሰረዝ ተደርጓል።
የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና ሌሎች ተያያዥ ክስ የነበረባቸው ወገኖች ክሳቸው ተቋርጦ በይቅርታ ከእስር እንዲፈቱም ሆኗል። የምህረት አዋጅ በፓርላማ ወጥቶ በሽብርተኝነትና በኩብለላ ወንጀሎች የተፈረጁ ወገኖች ምህረት እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህም በሀገር ቤት ውስጥ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የጥላቻና የቁርሾ ፖለቲካን እንዲያከትም ለማድረግ ወሳኝ ርምጃ እንደነበር አይካድም።
ታዲያ ይህ በአዲሱ አመራር የተወሰደው ርምጃ አርበኞች ግንቦት ሰባትም ይሁን ሌሎች በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ ቡድኖች በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ነፃ ሆነው ሃሳባቸውን እንዲያራምዱ የሚያደርግ ነው። በሌላ አገላለፅ፤ ላለፉት ወራቶች ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የተወሰዱት ርምጃዎች የሀገራችንን ፖለቲካዊ ምህዳር በማስፋት የትኛውም ዓይነት ሃሳብ እዚህ ሀገር ውስጥ በነፃነት እንዲንሸራሸር በመፍቀድ በመጪው 2012 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ሁሉም ፓርቲዎች እንዲወዳደሩ የሚያስችል ነው። ለዚህም ነው—ጠቅላይ ሚኒስትር ዶከተር አብይ በአሜሪካ ከኢትዮጵያንና ከትውልደ ኢትዮጵያን ጋር ውይይት ባካሄዱበት ወቅት፤ “…እኛ የሚያስፈልገን የሽግግር ሃሳብ ነው። እኔ እራሴ ሽግግር ነኝ፤ እኔ አሸጋግራችኋለሁ። ቀጣዩ ምርጫ ሁለት ዓመት ብቻ ነው የቀረው። ስለዚህ ተዘጋጁ፤ ጊዜ የላችሁም። ከእኛ የተሻለ ሃሳብ አምጡና ተፎካከሩ” በማለት የተናገሩት።
አዎ! ፓርቲዎች ለህዝቡ በሚያቀርቧቸው ሀገርን የመምራት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የህዝቡን ቀልብና ልብ መግዛት ከቻሉ የጋራ ቤታቸው የሆነችውን ሀገራቸውን መምራት ይችላሉ። በእኔ እምነት ይህን ለሁሉም እኩል የሚሆን የፖለቲካ ምህዳር በመፍጠርና በማመቻቸት እንዲሁም ለስራ በተሰማሩባቸው ቦታዎች ሁሉ በውጭ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት መጥተው በሰላማዊ መንገድ ለኢትዮጵያ እንዲሰሩ ከፍተኛውን የህዝብ ግንኙነት ስራ በማከናወን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከበሬታና አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል።
አርበኞች ግንቦት ሰባትም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገር ቤት ገብቶ የሰላማዊ ምህዳሩ አካል ሆኖ መደመሩ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። ድርጅቱ ከዶክተር አብይ ጋር ባካሄደው ውይይት በኋላ በሰጠው መግለጫ፤ ከሌሎች የፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ወይንም በተናጠል ለመንቀሳቀስ ያለውን አቋም በሂደት የሚወስን ቢሆንም፤ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተዋህዶ አንድ ጠንካራ ፓርቲን ለመፍጠር ከተለያዩ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር ውይይት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ያለው ለውጥ የመሸነፍና የማሸነፍ ሳይሆን፤ ወደ ዘመናዊ የዴሞክራሲ ስርዓት የመሸጋገሪያ አጋጣሚ መሆኑንም አስረድቷል።
ርግጥ ለሀገራችን የሚያስፈልጋት መናቆር ሳይሆን ዘመናዊ የዴሞክራሲ ግንባታ ነው። ዴሞክራሲያችን ሲዘምን፣ አሳታፊነትንና ተጠያቂነትን ሲያጎለብት የሀገራችን ሰላም በዘላቂነት ይረጋገጣል። ሰላማችን እውን ሲሆንም ልማታችንን በማፋጠን በድህነት ውስጥ የሚገኘውን ህዝብ ጉሮሮውን ማራስ ይቻላል። ያኔም በአንድነት ጥላ ስር ሆነንና ኢትዮጵያ የጋራችን ሆና በፍቅር በልፅገን መኖራችን አጠያያቂ አይሆንም። ያም ሆኖ በዶክተር አብይ አግባቢነት የተፈፀመው የድርጅቱ በአንድ ወር ውስጥ ወደ ሀገሩ የመመለስ ውሳኔ ለኢትዮጵያችን ዴሞክራሲ መጎልበት ተደማሪ አቅም ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካው የመደመር ጉዞ ወቅት ሌላው የጎንዮሽ ውይይት ያደረጉት ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ጋር ነው። ሚስተር ፔንስ በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ መንግስታቸው በአድናቆት እንደሚመለከተውና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ይህም አሜሪካ ከሀገራችን ጋር በሀገራዊና በቀጣናዊ እንዲሁም በፀጥታ ጉዳዩች አብራ ለመስራት ያላትን ፍላጎት የሚያሳይ ይመስለኛል።
ከወራት በፊት ‘የኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስበኛል’ ስትል የነበረችው አሜሪካ፤ ዛሬ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በመመልከት አብራን ለመስራት ፍላጎት ማሳየቷ የመደመራችን ምላሽ ያስገኘው ውጤት መሆኑ ግልፅ ነው። ስንደመርና በአንድነት ጥላ ስር ስንሰባሰብ የሃያላኑን ሀገራት ቀልብና ፍላጎት መግዛት እንደምንችል የምክትል ፕሬዚዳንት ፔንስ ንግግር አስረጅ ይመስለኛል። እናም ለውጡ እንዳይደናቀፍና በተጀመረው ግለት እንዲቀጥል ሁለም ሀገር ወዳድ ዜጋ ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል።
መደመራችን ምላሽ ያገኘው ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋሞች ጭምር ነው— ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) እና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ፕሬዚዳንቶች። የአይ ኤም ኤፍ ፕሬዚዳንት ክርስቲን ላጋርድ፤ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ሁሉንም ያማከለ እና ዘላቂ እንዲሆንና ድህነትን ለመቀነስ እንዲያስችል ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን በውይይቱ ወቅት አስታውቀዋል። ዶክተር አብይ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላምና እርቅ ማውረድ በመቻላቸውም ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል። የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ጂም ዮንግ ኪምም ድርጅታቸው የኢትዮጵያን ማሻሻያ እንደሚደግፍ አስረድተዋል። ዶክተር አብይ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ይፋ ያደረጓቸውን የፖሊሲ አቅጣጫዎች በቅርበት ሲከታተሉ እንደነበር የተናገሩት ሚስተር ኪም፤ ይህንንም ዓለም ባንክ እንደሚያደንቀው አብራርተዋል።
ታዲያ የሁለቱ የፋይናንስ ተቋማት አዲሲቷን ኢትዮጵያ አስመልክተው አንድ ዓይነት ቋንቋ መናገራቸውና ለውጡን ለመደገፍ መሻታቸው መደመራችን ያስገኘው ምላሽ ነው። ልክ እንደ ሌሎቹ የልማት አጋሮቻችን ሁሉ፤ ሁለቱ ተቋማትም በሀገራችን የመጣው ለውጥ የህዝቡን የአኗኗር ሁኔታ መለወጥ የሚያስችል መሆኑን ተገንዝበዋል። ድጋፍ እንደሚያደርጉልን የገለፁትም እዚህ ሀገር ውስጥ በሀዝቡ የነቃ ተሳትፎ የተገኘው ለውጥ ቢታገዝ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ስለሚያውቁ ነው።
በአዲስ አመራር እየተመራች በለውጥ ሂደት ላይ ያለችው አዲሲቷ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ከትናንቱ ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ እንደምትሻል ከተቋማቱ የሚሰወር ጉዳይ አይደለም። የኢትዮጵያዊያን በአንድነት ጥላ ስር ሆኖ መሻሻል ለሀገራቸው፣ ለቀጣናውና ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳው ትልቅ ነው።
በተለይ ዶክተር አብይ ከሀገራቸው አልፈው ቀጣናውን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር እያከናወኑ ያሉት የመደመር ተግባር ምስራቅ አፍሪካን ከእርስ በርስ ግጭት አላቅቆ ወደ ልማት ጎዳና የሚያመራት መሆኑ ግልፅ ነው። እናም ይህን ኢትዮጵያዊ አመራር መደገፍ ማለት ቀጣናውን ብሎም አፍሪካን መደገፍ መሆኑ ከተቋማቱ የተሰወረ አይደለም። እናም ኢትዮጵያንና አዲሶቹን መሪዎቿን መደገፍ አፍሪካን ማጠናከር ነው። የመደመር ምላሾቹ እስከዚህ ድረስ ርቀው የሚሄዱ ናቸው።