Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመደመር ፍልስፍና

0 1,559

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

የመደመር ፍልስፍና

አሜን ተፈሪ

የነበረው ነገር እንደነበረ መቀጠል ከማይችልበት ነጥብ የሚደረሰው፤ የነበረውን ነገር እንደነበረ ለማስቀጠል የሚደረገው የተለያየ ሙከራ ረጅም ጊዜ ከወሰደ እና ነባሩን ነገር ከዚያ በላይ ማስቀጠል ከማይቻልበት ደረጃ ሲደረስ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ነባሩን አቅቦ ለማቆየት ወይም ሚዛን ለመጠበቅ የሚወሰደው እርምጃ ምንም ዓይነት ሥራ አለመሥራት ነው፡፡ ከአጭር ጊዜ አኳያ ሥራ ባለመሥራት ወይም የትኩረት አቅጣጫ በመቀየር ፋታ ማግኘት የሚቻል ቢሆንም፤ ከመካከለኛ እና ከረጅም ጊዜ አኳያ ግን ይበልጥ ተጋላጭ የሚያደርግ ነው፡፡ አሁን አንድ ነገር ይበልጥ ግልጽ ሆኗል፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም፡፡ ከዚህ በኋላ ማድረግ የሚቻለው ወደፊት መሄድ ብቻ ነው፡፡ ግን ብዙ ልፋት እና ማስተዋልን የሚጠይቅ ሥራ በመሆኑ ወደፊት መሄድ እንዲህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡

ከነብዙ እንከኑ፤ በእኔ ግምት አሁን የምናየው ሰላም፤ በአንድ ቃል የመጣ ሰላም ነው፡፡ በግራ በቀኝ የሚናጠቁት ችግሮች ቢኖሩም፤ የሰላማችን ምንጭ ‹‹መደመር›› ነው፡፡ ‹‹መደመር›› ኢትዮጵያን ከመከራ የጠበቀች ቃል ነች፡፡ መደመር አሰባሳቢ ቃል በመሆን አገልግላለች፡፡ ‹‹መንግስቱ ኃ/ማርያምን ከሐራሬ፤ አቦይ ስብሐትን ከመቀሌ፤ ጃዋር መሐመድን ከሚኒሶታ፤ ኢሳያስ አፈወርቂን ከኤርትራ ወዘተን›› በአንድ ለማሰባሰብ የምትመኝ ቃል ነች፡፡ ‹‹መደመር›› ለኢትዮጵያ የተስፋ መዝሙር ሆናለች፡፡ ‹‹መደመር›› ባለፉት 50 ዓመታት የተበላሸውን ነገር ለማረም የሚያስችል እና አዲስ ምዕራፍ በመክፈት ለገዢው ፓርቲም ሆነ ለተቃዋሚዎች መሰባሰቢያ ታዛ ሆናለች፡፡ ከዚህች ቃል ከዚህ በላይ የምንጠብቅ ከሆነ፤ ከዚህ በላይ ማሰብ ይኖርብናል፡፡

‹‹መደመር›› የታሪክ እልባት ሆናለች፡፡ የ27 ዓመታት የአመለካከት ሰልፍን ቀኝ ኋላ ዙር ያለች ኣዋጅም ሆናለች፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ምድር የመደብ እንጂ የብሔር ጭቆና አልነበረም›› የሚል የጥላቻ ግንብ ማፍሻ መዶሻም ሆናለች፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ምድር የመደብ ጭቆና እንጂ የብሔር ጭቆና አልነበረም›› በሚል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቦ ለማ መገርሳ የተናገሩትን ቃል፤ አንድም ሰው ቁም ነገር ብሎ ሲያነሳው አልሰማሁም፡፡ ነገር ግን ከመደመር ፍልስፍና የወጣች እና ባለፉት ዓመታት የነበረውን የፖለቲካ ሐቲት የምታፈርስ አዋጅ ነች፡፡ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለማጠናከር የምታግዝ አዋጅም ነች፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ በለውጥ ጉዞ ላይ ነች፡፡ ግን ይህን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ፡፡ ህዝብን ለብሶት የዳረጉት፤ በግል ፍላጎት እና በሥልጣን ታውረው ስርዓቱን ለቀውስ ያጋለጡት ወገኖች፤ አሁን ከገባንበት አጣብቂኝ ውስጥ ከተውናል፡፡ ህዝብ አንድ ቀን እንዲህ እንደሚነሳ ስለማያውቁ አይደለም፡፡ ይልቅስ ሁልጊዜም ችግሩን ሊያቆሙት የሚችሉ ስለሚመስላቸው ነበር፡፡ አሁን ጠ/ሚ ዐቢይ እንዳሉት ‹‹አንድ ነገር ሲኖር እና ሲሞት መለየት የሚሳናቸው ሰዎች ሆነዋል፡፡››

እነዚህ ሰዎች ህዝቡ በቃኝ ብሎ ለመለወጥ እና ለውጥ ለመስራት ሲሞክር እንቅፋት ይሆናሉ፡፡ በቁጣ፣ እውነትን በመካድ፣ በመደናገጥ ወዘተ ለውጡን ማደናቀፍ ይዘዋል፡፡ በእርግጥ እነዚህ ወገኖች ውሎ አድሮ ለውጡን መቀበላቸው አይቀርም፡፡ ሆኖም አሁን ለውጡን ከመቀበል ደረጃ አልደረሱም፡፡ አሁን በቁጣ፣ እውነትን በመካድ፣ በመደናገጥ ስሜት ውስጥ ሆነው የቀቢፀ ተስፋ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ  ናቸው፡፡ በሁከት እና በጸያፍ ድርጊት ህዝቡን ከትኩረቱ ሊያናጥቡት እየሞከሩ ናቸው፡፡ ይህ ድርጊታቸውም ህዝቡ ለውጡ ሊቀለበስብን ይችላል ከሚል ስጋት ውስጥ እንዲገባ እያደረገው ነው፡፡ ስለዚህ ህዝቡ እነሱን አደብ ለማስገዛት በሚደረግ እንቅስቃሴ ከመደመር፣ ከሰላም፣ ከፍቅር እና ከይቅርታ ከመንገድ እንዳይወጣ መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ወጣ ባለ ምክንያትም ስርዓተ አልበኝነት የሚታይባቸው በርካታ አጋጣሚዎችም አሉ፡፡

የሆነ ሆኖ የለውጥ ኃይሉ አንድ ነገር ማመን አለበት፡፡ አሁን የለውጥ ሂደቱ ሊሰናከል የሚችለው፤ አደናቃፊዎች የሚባሉት ወገኖች በሚሰሩት ሥራ ወይም በሚሸርቡት ሴራ አይደለም፡፡ ይልቅስ ራሱ የለውጥ ኃይሉ በሚፈጽመው ስህተት ነው፡፡ ስለዚህ የለውጥ ኃይሉ በጥንቃቄ መራመድ ይኖርበታል፡፡ ችግር ይፈጥሩብናል ብለን የምናስባቸውን ሰዎች እኩይ ተግባር ለመከላከል የምናደርገው ጥረት፤ ከመሠረታዊ መርሆአችን እንዳያወጣን በጥንቃቄ መራመድ ያስፈልገናል፡፡ አሁን የለውጡ ጉዞ የሚወሰነው በአብዛኛው በለውጡ አራማጅ እና ደጋፊዎች እርምጃ እንጂ በአደናቃፊዎች ተንኮል አለመሆኑን ማመን ይገባናል፡፡

ባለፈው ጊዜ ኢንጂነር ስመኘው በድንገት ሞተው ተገኙ ሲባል ተበሳጨን፡፡ ተበሳጭተን አደባባይ ወጣን፡፡ ተበሳጭተን በአንዳንድ ዜጎች ላይ የቁጣ እርምጃዎች ወሰድን፡፡ ንብረት አወደምን፡፡ አሁን አንድ ነገር ልብ ማለት አለብን፡፡ የመደመር መንገድ ትዕግስት እና ማስተዋል የሚጠይቅ መንገድ መሆኑን መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ከሚሽነሩም፤ ‹‹ትዕግስት ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡ ትክክል ናቸው፡፡ ይህ በህዝቡ በኩል ያለ አደጋ ነው፡፡

በሌላ በኩል፤ አመራሩም ሊገነዘበው የሚገባ ነገር አለ፡፡ ህዝብ በመጨነቅ ስሜት ውስጥ ሆኖ ለብዙ ጊዜ መቆየት አይችልም፡፡ ስለዚህ ጭንቀት እና ሥጋቱ በቶሎ የሚወገድበትን መላ መፈለግ አለበት፡፡ እንዲሁም ሁሉም ዜጎች ከለውጡ የሚጠብቁትን ነገር ማቀራረብ ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ፤ ህገ መንግስቱን እንቀይር፣ የሽግግር መንግስት እንመስርት እና ፌዴራላዊ ስርዓቱን እንለውጥ ከሚለው ጀምሮ የተለያዩ ሐሳቦች ሲነሱ እናያለን፡፡ ይህ ፍላጎት በፍጥነት መቀራረብ አለበት፡፡

እንደሚታወቀው፤ በትናንሽ ንግዶች ስኬታማ የሚያደርግ የአመራር ዘይቤ በፖለቲካ አይሰራም፡፡ ስኬታማ ሰዎች ሙሉ ትኩረታቸውን በሚሰሩት ሥራ እንጂ ከህዝብ በሚያገኙት እይታ የሚያደርጉ አይደሉም፡፡ የስኬት ተነሳሽነት የሚመነጨው፤ ከምንሰራው ሥራ ትክክለኛነት እንጂ፤ የሚጣረስ ፍላጎት ካላቸው ዜጎች ሙገሳ አይደለም፡፡ ሆኖም አንድ ነገር ማስተዋል አለብን፡፡

የስኬት ተነሳሽነት፤ አንድ ሰው በግለሰባዊ ወይም በህዝባዊ ህይወት መስክ የላቀ ደረጃ የሚይዝ ሥራ ለመስራት ያለውን ፍላጎት የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ የስኬት ተነሳሽነት ያለው ሰው፤ የሚሰራውን ሥራ ምርጥ አድርጎ በመስራት እንጂ ከሰው የሚያገኘውን አድናቆት በመመለክት የሚተጋ አይደለም፡፡ ሆኖም የፖለቲካ ሥራ የሚሰራውን ሥራ ምርጥ አድርጎ በመስራት የሚወሰን አይደለም፡፡ እንዲህ ያለ ሰብእና ለኢኮኖሚያዊ እንጂ ለፖለቲካዊ ሥራዎች ብዙ ፋይዳ የለውም፡፡ ምክንያቱም ግለሰቦች ‹‹ምርጥ›› ተብሎ በሚገምተው ነገር ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ለአንዱ ሰው ‹‹ምርጥ›› የተባለ ተግባር ለሌላው ‹‹ምርጥ›› ላይሆን ይችላል፡፡ በፖለቲካ መስክ የሚኖሩ የተለያዩ ወገኖች የላቀ ነገር ተብሎ በሚቀርበው ነገር ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ የፖለቲካ መሪዎች አንድን ፖሊሲ ተፈጻሚ ለማድረግ፤ የራሳቸው ሥልጣን እና ህዝባዊ መሠረት ያላቸውን የተለያዩ ቡድኖች ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ሥራ የተለያዩ ቡድኖችን ማሳመንን እና የእነሱን ፍላጎት ከግምት ማስገባትን ይጠይቃል፡፡

በአንጻራዊ ሚዛን፤ አዲስ ፖሊሲ ማሰብ እና ለህዝብ ይፋ ማድረግ እጅግ ቀላል ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በመንግስታዊ አመራር የሚተገበር አዲስ ፖሊሲ የተለያዩ የጥቅም በድኖችን ፍላጎት በተለያየ መንገድ ይነካል፡፡ አዲሱ ፖሊሲ የተለያዩ የጥቅም በድኖች የሚያነሱትን ጥያቄ የመመለስ ዕዳ አለበ፡፡ አዲስ ፖሊሲ ትግበራ፤ በበጀት ጉዳይ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር ከስምምነት መድረስን፤ ወደ ሙሉ ትግበራ ለመሄድ የፓይለት ጥናት ማካሄድን የሚጠይቅ ከመሆኑ ባሻገር፤ አንዳንድ ጊዜ በፖሊሲው የመጣውን ለውጥ ለማጣጣም ወይም ለውጡን በተጨባጭ ለማየትም በርካታ ዓመታትን ሊጠይቅ ይችላል፡፡ በፖለቲካ ህይወት ውስጥ የተለመዱ የሆኑት እነዚህ የሥራ ሂደቶች፤ ከፍተኛ የስኬት ተነሳሽነት ያላቸውን ሰዎች ትዕግስት የሚፈታተኑ ይሆናሉ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ የፖለቲካ አመራሩ በስራ ገበታው በየዕለቱ እንዲፈተን እና ቀስ በቀስም የስኬት ተነሳሽነቱ እንዲፈተን ያደርገዋል፡፡

እንደሚታወቀው በለውጥ ሂደት ውስጥ የመሪው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ሾፌሩ የመኪናው ወሳኝ ክፍል ነው፡፡ ይህ ሐሳብ በአንድ አንጻር ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን የዚህ እውነት ሌላ ክንፍ የሆነ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ያለ መኪናው ሰውዬው ሾፌር አይሆንም፡፡ ይህም እውነት ነው፡፡  መኪናውም ሰዋዊ (human) እና ኢ-ሰዋዊ (nonhuman) በሆኑ ነገሮች የሚገነባ ነው፡፡ ስለሆነም፤ አመራሩ ሰዋዊ (human) እና ኢ-ሰዋዊ (nonhuman) አላባዎች አሉት፡፡ የሁለቱ አላባዎች ቅንጅት ለለውጡ ስኬት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡

በመሆኑም፤ የመደመር ሰዋዊ እና ኢ-ሰዋዊ አላባዎች በደንብ ሊተነተኑ እና ህዝብም ፍልስፍናውን በአግባቡ እንዲገነዘብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሰዋዊ አላባዎች ያለ ኢ-ሰዋዊ (nonhuman) አላባዎች አይቆሙም፡፡  ስለዚህ ዋናው ነገር የቱ ነው የሚለው ጥያቄ ከንቱ ነው፡፡ ምክንያቱም ዋናው ነገር የሁሉቱ አላባዎች ውህድ ነው፡፡

ሰዋዊ አላባዎችን ስንመለከት፤ መሪ እና ተመሪ አሉ፡፡ መሪ እና ተመሪ ሁለቱ ጥምር ቃላት ይመስላሉ፡፡ ግን አይደሉም፡፡ ትክክለኛው የአመራር ዘይቤ ሲተገበር፤ ሰዎች ከመመራት ስሜት ጋር በሩቁ እንኳን የሚዛመድ ስሜት አይኖራቸውም፡፡ ምርጥ አመራር የሚታየው፤ ሰዎች ተመሪነት ሳይሰማቸው ‹‹ተመሪ›› በሚሆኑበት ሁኔታ ነው፡፡ ወዳጆች እና አጋሮች ንቅናቄ ውስጥ እንዲገቡ ሲደረጉ፤ ተከታዮች ሳይሆኑ ተነሳሽነት ያላቸው ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡ ተነሳሽነት ያላቸው ተሳታፊዎች – ሠራተኞች እና ዜጎች – ብዙውን ጊዜ ከሚጠበቀው በላይ በሆነ መጠን እና ከኃላፊነት ክልላቸውም ተሻግረው በመሄድ ከለውጡ ፊት የተጋረጡ ተግዳሮቶችን ለማስወገድ በገዛ ራሳቸው ለሥራ ይነሳሳሉ፡፡ አጋሮችም ይሆናሉ፡፡

ሆኖም ብዙዎቹ ምርጥ ‹‹አመራሮች›› ወዳጅ እና ደጋፊዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚዎቻቸውን እና አጥር ላይ ቆመው የሚመለከቱትን ሰዎች ጭምር የሚያነቃንቁ ናቸው፡፡ በለውጥ ሂደት ውስጥ ወዳጆችን እና አጋሮችን ያለ ብዙ ድካም (በአንጻራዊ ሚዛን) ጉዞውን በቀላሉ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ይቻላል፡፡ አስቸጋሪው ሥራ በለውጥ ሂደቱ ብዙ ነገር የሚያጡትን እና በተቃውሞ ጎራ የሚገኙትን ሰዎች የለውጡ አካል እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡

አጥር ላይ ተቀማጮች እና ተቃዋሚዎች ንቅናቄ ውስጥ ሲገቡ፤ እንዲለወጡ ከሚያስገድዳቸው የለውጥ ሂደት ጋር ይጋፈጣሉ፡፡ ከለውጡ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ፈተናዎች ፊት ይቆማሉ፡፡ ያገኙት የነበረውን ጥቅም ከማጣት እና ለለውጡ ታማኝ ከመሆን ተቃራኒ ምርጫዎች ጋር ይፋጠጣሉ፡፡ እንዲሁም ከለውጡ ጋር ለመራመድ ብቃት ከማግኘት ጋር ተሳስረው የተቀሰቀሱ ችግሮችን መጋፈጥ ይጀምራሉ፡፡ በእርግጥም መዋጋታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በዚህም ለለውጡ አስፈላጊ ለሆነው የሐሳብ ብዝሐነት ምንጭ ይሆናሉ፡፡ በዚህም በተዘዋዋሪ መንገድ ለለውጡ ስኬት አስታጽኦ ያደርጋሉ፡፡

በአመራሩ የላቀ ሚና የሚደመሩት እና ንቅናቄ ውስጥ የሚገቡት ሁለቱ ኃይሎች (አጥር ላይ ተቀማጮች እና ተቃዋሚዎች)፤ የአሰራር እና የአኗኗር ዘይቤ ማመቻመችን ከሚጠይቁ አዲስ ውስብስብ አጀንዳዎች ጋር ግብግብ ይገጥማሉ፡፡ ተቃዋሚዎቹ  ‹‹አጋር›› ከመሆን ሳይደረሱ፤ ደጋፊዎቹም ‹‹በተከታይነት›› መንፈስ ሳይታሰሩ፤ የአሰራር እና የአኗኗር ዘይቤ ማመቻመችን ከሚጠይቁ አዲስ ውስብስብ አጀንዳዎች ጋር ግብግብ ይገጥማሉ፡፡ ቀስበቀስም ለውጡን የሚመራውን ግለሰብ ወይም ቡድን ማመን፣ ማድነቅ እና የለውጡን ፋይዳ መገንዘብ ይጀምራሉ፡፡ በዚህም ለመሪው ግለሰብ ወይም ቡድን ኢ-መደበኛ ስልጣን ይሰጡታል፡፡ ሆኖም የለውጡን ፋይዳ የመገንዘቡ ነገር ወይም የአመኔታው ስሜት ‹‹እኔ የአመራሩ ተከታይ ሆኛለሁ›› በሚል ስሜት የታጀበ ላይሆን ይችላል፡፡

አመራር የሚፈጠረው በችግሮች እና በተግዳሮቶች ውስጥ ነው፡፡ ዘውትራዊ ሥራዎችን ለማስተባበር የሚያስችል የተጽዕኖ እና የሥልጣን ችሎታ በሁሉም ሥፍራ ደረጃ ባለበት እና ሁሉም ሰው ‹‹በጥሩ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን›› የሚል ዜማ በሚያዜምበት ጊዜ የአመራርን ፋይዳ መገንዘብ አይቻልም፡፡ የአመራርን ፋይዳ መገንዘብ የሚቻለው፤ አንድ ነባር መዋቅር፣ የአሰራር ስልት እና ሂደት እንዳለ እንዲቀጥል በሚደረግበት ሁኔታ ውስጥ ሳይሆን፤ መቀየርን ግድ በሚል ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ አስተዳደራዊ ብቃት መያዝ ብቻ በቂ በሚሆንባቸው ሁኔታዎች ውስጥ የሚገጥሙን ችግሮች ቴክኒካዊ ናቸው፡፡ አመራር የሚፈተነው ነባር አሰራርን መለወጥን በሚጠይቅ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ አመራር የሚፈተነው፤ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመጋፈጥ፤ ከሚለወጠው ዓለም ጋር የተጣጣመ ብቃት በመያዝ፤ አንዳንድ የቅደም ተከተል፣ የዝንባሌ እና የባህርይ ለውጥ ማድረግን በሚጠይቁ አዳፕቲቭ ተግዳሮቶች (adaptive challenges) ውስጥ ነው፡፡  

ለወጥን የሚጠይቁ ተግዳሮችን ለመጋፈጥ ህዝቡን የማንቀሳቀስ ሥራ የአንድ አመራር ዋና ተግባር ነው፡፡ ከአጭር ጊዜ አኳያ፤ ከፊቱ የተደቀኑ ወቅታዊ ችግሮችን ለመጋፈጥ ህዝብን ሞቢላይዝ የማድረግ ሥራ ነው፡፡ ከመካከለኛ እና ከረጅም ጊዜ አኳያ፤ ተከታታይ ለውጥን የሚጠይቁ እውነታዎችን ወይም ግፊቶችን እያግተለተለ አዳፕቲቭ ተግዳሮቶችን (adaptive challenges) የሚያመጣውን ዓለም ለመጋፈጥ የሚያስችል አዲስ አስተሳሰብ እና ምግባር መፍጠር ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ፤ ከረጅም ጊዜ አንጻር፤ የአመራሩ ሚና የድርጅቱን ወይም የማህበረሰቡን ‹‹ለአዲስ ሁኔታ ብቁ ሆኖ የመገኘት አቅምን›› (አዳብቲቭ ካፓሲቲ) ማሳደግ ነው፡፡

ሁሉም ችግር፤ በመሻታችን እና በተጨባጩ ሁኔታ ያለ ክፍተት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ አሁን ባለው ብቃት ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉ ገዳዮች ‹‹ቴክኒካዊ ተግዳሮቶች›› ናቸው፡፡ በተቃራኒው አሁን ባለው ብቃት ምላሽ ሊያገኙ የማይችሉ ችግሮች ‹‹አዳብቲቭ ተግዳሮቶች›› ናቸው፡፡ ‹‹ቴክኒካዊ ተግዳሮቶች›› የሚደቅኑት አሁን ባለን ዕውቀት ሊዘጋ የሚችልን ክፍተት ነው፡፡  በተቃራኒው፤ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮት›› በመሻታችን እና በተጨባጩ ሁኔታ ያለው ክፍተት አሁን ባለው አሰራር እና ዕውቀት ሊሸፈን የማይችል ክፍተትን የሚፈጠር ነው፡፡ ስለዚህ ለችግራችን መፍትሔ የሚገኘው አሁን ከዘረጋነው ስርዓት እና ከምናደርገው ድርጊት ክልል ውጭ ይሆናል ማለት ነው፡፡

አንድ ሰው በኢንፌክሽን በሽታ ታሞ ወደ አንድ ሐኪም ቢሄድ፤ ዶክተሩ ቀድሞ የነበረውን ዕውቀት በመጠቀም በሽተኛውን ይመረምራል፡፡ መድኃኒትም ያዝለታል፡፡ ቀድሞ በነበረ ዕውቀት ችግሩ ይፈታል፡፡ በሌላ በኩል፤ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮት›› በተጨባጭ ባለው ሁኔታ እና በምንመኘው ነገር መካከል ያለው ክፍተት፤ አሁን ባለው ባህል በተቀረጸ ባህርይ፣ የአሰራር ዘዴ፣ እውቀት እና ክህሎት ችግሩ ሊሸፈን አይችልም፡፡ አንድ ሰው የልብ በሽታ ቢይዘው፤ የኑሮ ዜይቤውን ለመቀየር ይገደዳል፡፡ ማለትም አመጋገቡን መቀየር ይኖርበታል፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ሲጋራ አጫሽ ከሆነም ማጨሱን ማቆም እና ጤናማ ያልሆነ ወይም ሚዛን የሳተ የኑሮ ዘይቤን ማስወገድ ይኖርበታል፡፡ ለውጥ ለማምጣት ህመምተኛው ለራሱ ጤና ኃላፊነት መውሰድ ወይም አዲስ የኑሮ ዘይቤን መማር ይኖርበታል፡፡

ስለዚህ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮት›› አዳዲስ ነገሮችን መማርን የሚጠይቅ ነው፡፡ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮት›› የሚፈጠረው፤ ራሳቸው ሰዎቹ የችግሩ ምንጭ ሲሆኑ እና የተፈጠረውም አዲስ ሁኔታ የምንሰራበትን መሣሪያ (የአስተሳሰብ እና የአሰራር ዘይቤን) መቀየርን (retooling) የሚጠይቀን ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ በተጨባጭ ባለው ሁኔታ እና በምንመኘው ነገር መካከል ያለው ክፍተትም ሊሞላ የሚችለው፤ አዳዲስ ነገሮችን በመማር ብቻ ነው፡፡

አንድ አማካሪ ድርጅት ስለ አንድ ድርጅት ጥናት አድርጎ ምክረ ሐሳብ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ሆኖም የድርጅቱ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ምክረ ሐሳቡን ካልተገበሩት ወይም የአስተሳሰብ እና የአሰራር ዘይቤ ለውጥ እስካላመጡ ድረስ ችግሩ አይወገድም፡፡ እንዲሁም ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮት›› ኃላፊነትን ከስልጣን መዋቅሩ ወይም ከባለስልጣናት ትከሻ ወደ ባለድርሻ አካላት (በአንድ የሥራ ውጤት ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች) ማዛወርን ይጠይቃል፡፡

ችግሩ በአንድ ባለሙያ ክንውን መፍትሔ የሚያገኝ ሲሆን፤ ችግሩ ቴክኒካዊ መሆኑ ነው፡፡ በተቃራኒው፤ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮቶች›› ለየት ያለ ውይይት፣ ምክክር እና ለየት ባለ ሁኔታ ኃላፊነትን የመሸከም ውሳኔን ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮትን›› በምንጋፈጥበት ጊዜ፤ በርካታ ሰዎች የኃላፊነት ስሜት ሊሰማቸው እና ሸክሙን ሊጋሩት ይገባል፡፡ ለቴክኒካዊ ችግሮች፤ ባለሙያዎች መፍትሔ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ሆኖም ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮቶች›› ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከተው አንድ ባለሙያ ወይም መሪ መፍትሔ ሊያገኝ አይችልም፡፡ አሁን እኛን የገጠመን ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮት›› መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ መደመር ይህን ሁኔታ መገንዘብን ይጠይቃል፡፡ ከችግሩ ለመውጣት ሁሉም ዜጎች (ባለድርሻ አካላት) ኃላፊነት እንዳለባቸው ሲገነዘቡ መደመር እውን ይሆናል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮቶችን›› ቴክኒካዊ አድርጎ የማየት ከባድ ስህተት ሲፈጽሙ፤ ኃላፊነት ላይ ያለው ሰው ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲነግራቸው ይጠብቃሉ፡፡ ሆኖም በኃላፊነት ላይ ያለውም ሰው አስተያየት እንጂ እውነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ሊያደርግ የሚችለው መገመት ብቻ ነው፡፡ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ስህተት ሲፈጽሙ፤ ጥሩ መሪ ብናገኝ ኖሮ፤ ችግራችን መፍትሔ ሊያገኝ ይችል ነበር ብለው ያስባሉ፡፡ ባልሆነ ነገርም ይታመናሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የአመራሩ ዋና ተግባር፤ ኃላፊነቱ በባለ ድርሻዎቹ ትከሻ እንዲያርፍ ማድረግ ነው፡፡ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የምናካሂደው ለውጥ ጥቂቶች ተዋናይ የሚሆንበት እና ብዙዎች ተመልካች የሚሆኑበት አይደለም ማለታቸው ለዚህ ነው፡፡

እንዲሁም ‹‹አዳብቲቭ ተግዳሮት›› ከባለ ጉዳዮቹ የሚጠይቀው ሌላ ሥራ አለ፡፡ ይህ ሥራ ካለፈው ነገር የትኛው ውድ እና ሁነኛ ሐብት ወይም ቅርስ እንደሆነ፤ የትኛውስ ሊወገድ የሚገባው ነገር እንደ ሆነ የመለየት ሥራ ነው፡፡ ባህልን ለዘመኑ ተስማሚ እንዲሆን የማድረግ ሥራ፤ ከታሪካችን ውስጥ ምርጥ የሆነውን መውሰድ እና ሊጠቅም የማይችለውን ኣራግፎ መጓዝ ነው፡፡ ጥበብን በተመረኮዘ አኳኋን በአዲሱ ሁኔታ ውስጥ በድል ለመጓዝ የሚያስችለውን መንገድ ማወቅ ነው፡፡ ስለዚህ የለውጥ ሥራ ተራማጅ እና ወግ አጥባቂነት ባህርይ አለው፡፡

ስኬታማ ሥነ ህይወታዊ የለውጥ ጉዞ፤ ካለፈው ነገር ምርጡን መውሰድ እና ከእንግዲህ ወዲህ እርባና የማይኖረውን DNA ገድፎ የመጣል ጉዞ ነው፡፡ በተመሳሳይ፤ በለውጥ ወደፊት በምንራመድበት ጊዜ፤ ጥበብን በተመረኮዘ አኳኋን፤ ከታሪካችን ምርጡን ለይቶ አውቆ ትውልድ እንዲሻገር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡  

ሁኔታዎች በተለወጡ ጊዜ ከለውጡ ጋር የተጣጣመ አቋም ይዞ ለመገኘት ስንሞክር፤ በውስጣችን ለውጥን የመግፋት ዝንባሌ ይፈጠርብናል፡፡ ምክንያቱም፤ ከለውጡ ጋር የተጣጣመ  አቋም ይዞ የመገኘት ሥራ፤ ካለፈው የአሰራር እና የአኗኗር ልማዶቻችን ውስጥ የተወሰኑ ነገሮችን መተውን ወይም መጣልን የሚጠይቅ ነው፡፡ በውስጣችን ለውጥን የመግፋት ዝንባሌ የተወሰኑ ነገሮችን የመጣል የብቃት ማጣት ነው፡፡ ልማድን የመተው አቅም ማጣት ነው፡፡ ይዘናቸው የቆየናቸውን ትውፊቶች ላስተማሩን ሰዎች ያለንን ታማኝነት የመንፈግ ጉዳይ ነው፡፡

ስለዚህ፤ ‹‹አዳፕቲቭ ተግዳሮቶች›› ከባድ ሰጥቶ የመቀበል እና ሚዛን የመጠበቅ ፈተና ውስጥ እንድንቀረቀር የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ያመጣብናል፡፡ ሰዎች ለውጥን ለመቀበል የሚያደርጉት ማንገራገር ምንጩ፤ በቀጥታ ለውጥን ካለመቀበል ግፊት ጋር የሚያያዝ ብቻ ሳይሆን፤ የተወሰኑ ነገሮችን የመጣል ብቃት ከማጣት እና ከማቃት ጋር የሚያያዝም ነው፡፡ ሰዎች ጠቃሚ ሆኖ የታያቸውን ለውጥ በጣም ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ ነገሮችን የመጣል ብቃት ያጣሉ፡፡ አንድ አመራር አዲስ ለውጥን ከማከናወን ጋር ተያይዞ በተለያየ መልክ የሚነሱ (እውነተኛ እና በሥጋት የተፈጠሩ) ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል ብቃት መፍጠር መታገል ይኖርበታል፡፡ መደመር እውን የሚሆነው በዚህ መንገድ ነው፡፡

በአጠቃላይ፤ ከዚህ በላይ የተባለው ነገር የመደመር ፍልስፍና አንድ ዐ.ነገር እና የፍልስፍናው የመጀመሪያ ረቂቅ (ዜሮ ድራፍት) ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy