Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የምርጫ ባህልን…

0 279

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የምርጫ ባህልን…

                                 ዳዊት ምትኩ

በመጪው 2012 ዓ.ም የሚካሄደው አገራዊ ምርጫን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በርቡ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህም መንግስት የምርጫ ጊዜውን የማራዘም ሃሳብ የሌለው መሆኑንና ምርጫው ያለ ምርጫ ኮረጆ በዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ በታገዘ መንገድ በታቀደለት ጊዜ እንዲከናወን ፍላጎት እንዳለው ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

እንዲሁም መንግስት ሁሉም የሚያምንበትና ፍትሐዊ የሆነ ምርጫ ለማካሄድ ብሎም ተዓማኒ የሆነ የምርጫ ተቋም እንዲኖር ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ገልፀዋል። ይህም እዚህ አገር ውስጥ ሲካሄዱ ከነበሩት ቀደምት ምርጫዎች የተለየ፣ ጥርጣሬንም በእጅጉ የሚቀርፍና የነበረንን የምርጫ ባህል ከመሰረቱ የሚቀይር ተግባር ነው ማለት ይቻላል። ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግስት ምን ያህል ለለውጥ ቁርጠኛ እንደሆነና ይህም የዴሞክራሲያዊነቱ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የሚያስገነዝብ ይመስለኛል።

ታዲያ እንዲህ ዓይነት ለለውጥ ዝግጁና ዴሞክራሲያዊ የሆነ መንግስት ሲፈጠር ህዝቡም በምርጫው ተሳታፊ በመሆን ዴሞክራሲያዊ መብቱን መጠቀም ይኖርበታል። እንደሚታወቀው ሁሉ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዋነኛ መገለጫው ምርጫ ነው፡፡

የምርጫ ጠቀሜታም ሕዝቦች ሊመሯቸውና ሊያስተዳድራቸው የሚችሉ፣ በተጨባጭ በምረጡኝ የምርጫ ዘመቻ ወቅት ፖርቲዎች ያከናወኑትን ወይም የሚያከናውኑትን  ተግባር በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የእገሌ ፖርቲ በቀጣይ ለውጥ ያመጣልናል ብለው ያመኑበት፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያላንዳች ተጽዕኖ ካርዳቸውን በመስጠት ተመራጩን ፓርቲ ለስልጣን ማብቃት ነው፡፡ ይህም በህገ መንግስቱ በግልፅ እንደተደነገገውም ስልጣን በሕዝብ ድምፅ እንጂ በሌላ መንገድ የሚገኝ እንዳልሆነ ያስረዳናል፡፡

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲጎለብት ባለፋት ጊዜያት የተከናወኑ አገራዊና ክልላዊ ብሎም የአካባቢና የአዲስ አበባ የምክር ቤቶች የሟሟያ ምርጫዎች ጅምሮች ቢሆኑም በእኔ እምነት ግን የውዝግብ መንስኤዎች ሆነው ነው ያለፉት፡፡ በእነዚህ የምርጫ ሂደቶች የሕዝቡ ተሳትፎና ዴሞክራሲውን ወደፊት ለማራመድ የነበረው ሚና አኩሪ ነበር ሊባሉ የሚችሉ አይደለም፡፡

እንዲያውም በእኔ እምነት ለሐሜታና ለጥርጣሬ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ከምርጫ ድምጽ አሰጣጡ ጀምሮ የነበረው የኮረጆ አፈታት ሁኔታ ሁሉ የአንዳንድ ወገኖች መቀለጃ እንደነበር እናስታውሳለን።

የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር በማስፋት በኩልም የተካሄዱት ምርጫዎች ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ብዬ አፌን ሞልቼ መናገር ይከብደኛል፡፡ ምክንያቱም ጉድለቶቹ ሰፊ ስለነበሩ ነው።

የፖለቲካ ፖርቲዎችም ቢሆኑ በቁጥር ይሁን በአስተሳሰብ ደረጃ የዴሞክራሲን ምንነት በውል ተረድተው በምርጫ በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ የነበራቸው ድርሻ ጉልህ አልነበረም፡፡

አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ይከፋፍለናል ሲሉ ይደመጡ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በዚህም ሳቢያ በአገር ውስጥ የነበሩ ተቃዋሚዎች በተለያዩ ወቅቶች ራሳቸውን ከምርጫ ሲያገሉ ነበር፡፡

ዛሬ ግን ይህ ሁሉ ተለውጦ ተዓማኒና ፍትሐዊ ምርጫ እንደሚካሄድ እንዲሁም የኮሮጆ ድምጽ አሰጣጥን በኤሌክትሮኒክስ አሰራር የመለወጥ ብሎም ተዓማኒ የምርጫ ቦርድ ለመፍጠር እንደሚሰራ መንገስት ገልጿል፡፡ ይህ ትልቅ አመኔታን የሚያሳድርና ለአገራችን እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት የሚጥል ነው፡፡

እርግጥ ለውጡ ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ አገራችን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ ባባህልና በቋንቋ የተለያዩ ሕዝቦች አብረው የሚኖሩባት ቢሆኑም፣ እነዚህን ልዩነቶች በማክበር አንድነትንና ኢትዮጰያዊነትን ለማምጣት እየሰራ ነው፡፡

በአንድነት ስንንቀሳቀስ ችግሮቻችንን ሁሉ መፍታት እንችላለን የሚል አቋም በመያዝም አገራዊ መግባባትን ለማምጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ስራዎች ተናውነዋል፡፡

ምንም እንኳን ባለፋት ዓመታት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን ለመፍጠር በህገ መንግሰቱ ላይ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ቢሰፍሩም በተገቢው መንገድ ሲተገበሩ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ እንዲያውም ከህገ መንገስቱ ውጭ በርካታ ተግባሮች ሲፈፀሙ አስተውለናል፡፡

ይህም ከአንድነታችን ይልቅ ልዩነታችን እንዲገነግን ያደረገ ተግባር ነው፡፡ በዚህም ከፍቅርና ከይቅርታ እንደሁም ከህጋዊ አሰራሮች ይልቅ መነቋቆርና መነካከስ እንዲሁም ኢ ህገ መንግስታዊ አሰራሮች ተፈጻሚ ሲሆኑ ነበር፡፡

እነዚህ ሁኔታዎች በአገሪቱ የምርጫ ስነ-ምህዳር መስፋት ላይ ጠባሳ አሳርፈዋል፡፡ ምህዳሩ እንዳይሰፋ ያደረጉ ተግባሮችም ናቸው፡፡ ዛሬ ግን መንግስት ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በእኩል ሜዳ ላይ እንዲወዳደሩና ምርጫውን ተዓማኒ ማድረግ የሚችል ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ አቋቁሞ ለመስራት ቁርጠኛ አቋም ይዟል፡፡  

እርግጥ በአገሪቱ የሚቋቋመው ምርጫ ቦርድ በየደረጃው በሚከናወኑ ምርጫዎች ስኬታማ ሆነው እንዲጠናቀቁ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጥቃቅን ጉድለቶችን ከወዲሁ የማስተካከል ሃላፊነት የተጣለበት ነው፡፡ ስለሆነም በምርጫ የሚሳተፋት ገዥው ፓርቲም ይሁን ተፎካካሪ ፖርቲዎች ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ድርሻቸውን መወጣት ይገባቸዋል፡፡

በምርጫ የሚሳተፋ ሁሉም ፖርቲዎች ሕዝቡ በምርጫው ተሳታፊ እንዲሆን ቅስቀሳቸውን በሰላማዊ መንገድ ማካሄድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአገሪቱን ህጎች በማክበርና የምርጫ ስነ-ምህዳሩን ለማስፋት የበኩላቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡

ይህን ሲያደርጉም መንግስት የያዘውን ቁርጠኛ የለውጥ መንገድ በመደገፍ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ያጠናክራሉ፡፡ የመንግስት አቋም ከዚህ በፊት የነበረውን የተሳሳተ የምርጫ ባህል የሚያርምና እውነተኛ ዴሞክራሲን የሚፈጥር በመሆኑ ይህን በመደገፍ ረገድ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy