Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሥልጣን ጥማት ያሰከራቸውና ያከሰራቸው ኃይላት

የሥልጣን ጥማት ያሰከራቸውና ያከሰራቸው ኃይላት

0 522

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሥልጣን ጥማት ያሰከራቸውና ያከሰራቸው ኃይላት

ደመላሽ አንጋጋው

በኢትዮ ሶማሌም ይሁን በሌሎች አንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ባለፉት ሳምንታት የታዩ ግጭቶች  በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ በማድረስ ለሀገር ዕድገት አሉታዊ ሚና የነበራቸው ነበሩ፡፡ የተሻለች ሀገር ለመፍጠር ቅድሚያ ለሰላማችን እና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ በጋራ ዘብ ልንቆም ይገባል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለተሻለ ዕድገት እና ብልጽግና ሁሉን አቀፍ በሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች፡፡ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ለውጥ ባለቤትም፣ ጠባቂም ሕዝቡ ነው፡፡

በየትኛውም አካባቢ የታዩት እና ወደፊትም ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶች አንዳችም የብሔር ሆነ የኃይማኖት ግጭት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ይልቁንስ በአመራር ብልሹነት የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ ከሰሞኑን በሶማሌ ተከስቶ የነበረውም ግጭት የሕዝብ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢሶዴፓ/ በውስጡ ችግር ምክንያት የተፈጠረ ነው፡፡ ይህ ውስጣዊ ችግር ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ባለመፈታቱ ምክንያት ወደ ግጭት ያመራበት ሁኔታ ነበር የነበረው፡፡ ይህ በክልሉ ውስጥ ተስተውሎ የነበረው ችግር ቀደም ሲል በኢትዮ ሶማሌ በኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ተከስቶ ለነበረው ችግር በአዲስ መልክ ግጭቱ እንዲያገረሽና እንዲባባስ የራሱን ሚና ተጫዉቶ አልፏል፡፡

በተከሰተው ችግር ምክንያት የተነሳ ቀላል የማይባል ንብረትና የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ግጭቶች ምክንያት በብሔር ማንነትና የሃይማኖት ግጭት አልነበረም፡፡  የሰላም እና የልማት ፀር የነበሩ ሰዎች ግጭቱን የሃይማኖት እና የብሔር ይዘት ለማስመሰል ያደረጉት ሙከራና ጥረት ውጤቱ ኪሳራና እፍረት ብቻ ነበር፡፡ በተወሰነ ቦታ ብቻ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ሀገራዊ ይዘት ለማላበስ ብሎም የብሔር እና የሀይማኖት ተኮር ብጥብጥ ለማስመሰል ቢፍጨረጨሩም ሃሳባቸው ህልም ሆኖ ቀርቷል፡፡

ግጭቱ የሀይማኖትና የብሔር ይዘት እንዳልነበረው እንደ ዋና ማሳያ ሊሆን የሚችለው በኢትዮ ሶማሌ ክልል የወደሙትን አብያተ ክርስቲያናት “እኛው መልሰን እንገነባለን” እያሉ ያሉት በክልሉ ተቀባይነትና ተደማጭነት ያላቸው የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ዑጋዞች እንዲሁም ነዋሪው ሕዝብ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ደጉና ገራገሩ የሶማሌ ሕዝብ ጥቃት የደረሰባቸውን ዜጎች በመሸሸግ፣ በመታደግ የሚያኮራ ተግባር ፈጽሟል፡፡

በኢትዮ ሶማሌ ክልል የተለያዩ ብሔሮች እና የሀይማኖት ተከታዮች ለዘመናት በመከባበር “አንተ ትብስ አንች ትብሽ” ተባብለው የኖሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡  አማራዉ፣ ሶማሊያው፣ኦሮሞውና ትግራዩ ሌሎችም ብሔር ብሔረሰቦች ለዘመናት ተዋልደው እና ተከባብረው የኖሩ ህዝቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በእምነት ተቋማት ላይ የእሳት ቃጠሎ ደርሷል፡፡ ብዙ የቤተክርስቲያንም ቅርሶች በቃጠሎው ወድመዋል፡፡ ይህንንም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች የተወሰኑ እና ትንሽ የስልጣንና የፖለቲካ ጥማት ያሰከራቸውና ያከሰራቸው ኃይሎች ናቸው፡፡

በእርግጥም አልተሳካለቸውም፡፡ በእምነት ተቋም ላይ ደርሶ የነበረውን ችግር በመቅረፍ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ የአካባቢው ተወላጆች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ከመንግሥት ጎን እንሰለፋለን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አክለውም ክስተቱን በማውገዝ፣ ይህ ተግባር የሶማሌን እና የሙስሊሙን ማኅበረሰብ እንደማይወክል እና መደገም የሌለበት ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ለጥቂት ቀናትም ቢሆን ያጣነውን ሰላም ወደ ቦታው ለመመለስ ዘር፣ ሀይማኖት ሳይለያየን እንሠራለን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ወጣቱም የጥቅመኞች መሣሪያ ከመሆን መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡

በግጭቶች ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች መንግሥት በየብስና በአየር ላይ የምግብ፣ የመጠጥ እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለተጎጅዎች በአፋጣኝ እያከፋፈለ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብም ለተጎዱት መጠለያ በመስጠት እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡

 

በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በተፈጠረው ችግር የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት ሳይቀር የጥቃቱ ሰለባ ሁነዋል፡፡ ንብረታቸው ወድሟል፣ እንደሌላው ብሔር በነጻነት ተዘዋዉሮ የመሥራት መብታቸውን ተነፍገዋል፡፡ እንዲሁም ለረሀብ እና ለእንግልትም ተዳርገዋል፡፡ አንዳንድ የአካባቢው ተወላጆች እንደሚሉት ችግሩ በአመራር ክፍተት ምክንያት የተፈጠረ እና ለዚህ ተግባር ሲባል የተወሰኑ የጎሳ አባሎች እንደተመረጡ እና ለግጭቱም መነሳት ምክንያት የሆኑት ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን ሴራውን እናዳሴሩት ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ተወላጂ የሆኑት ምሁራን እንደሚሉት በክልሉ ምንም ዓይነት የሀይማኖትም ሆነ የብሔር ግጭት የለም፡፡ ነገር ግን ስልጣን ላይ ያለው የክልሉ መንግሥት አያሌ የመብት ጥሰቶችን ሲፈፅም ኑሯል፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ብቻ ህዝብን ከህዝብ በማበጣበጥ ቀላል በማይባል ንብረትና የሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ እንዲሁም ምሁራኑ እንደሚሉት ይህ ሁሉ ሲሆን የፌደራል መንግሥት ዝም ብሎ ከመመልከት የይልቅ ተገቢዉን ርምጃ መውሰድ ነበረበት ባይ ናቸው፡፡ በአፋጣኝ የሰብዓዊና የዲሞክራሲ መብት ጥሰቶችን ለማስቆም እርምጃ አለመውሰዱ እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል፡፡

 

በክልሎች በጣም የከፋ ሰብአዊ የመብት ጥሰት ሲፈጠር እና በራስ ዐቅም ችግሩን ማስቆም ካልተቻለ የክልል ምክር ቤት ወስኖ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ መግባት ይችላል፡፡ እንዲሁም የክልል አስተዳደሮች የፌዴራል ሥርአቱን አደጋ ላይ የሚጥል አሠራርን ማስቆም ካልቻለ ፌዴራል መንግሥት ጣልቃ የመግባት መብት ስላለው በክልሎች በመግባት ለችግሩ መፍትሄ መስጠት ይችላል፡፡ የፌዴራል መንግሥትም ሕገ- መንግሥታዊ ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ እና ከክልሉ በተደረገለት የእርዳታ ጥሪ መሠረት ወደ ክልሉ በመግባት ተፈጥሮ ለነበረው ችግር አፋጣጥ ምላሽ መስጠት ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል  ልዩ ኃይል በአሁኑ ጊዜ ከአገር መከላከያ ሠራዊት እና ከፌዴራል ፖሊስ ጎን ተሰልፎ በጋራ እየሠራ ይገኛል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ተከስቶ የነበረው ችግር ከክልሉ ቁጥጥር ውጭ በመሆኑ ምክንያት በክልሉ ጥያቄ መሠረት የፌዴራል መከላከያ ሠራዊት ጣልቃ በመግባት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲሰፍን ለማድረግ ተችሏል፡፡ በየአካባቢው ያለውን ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ ለማድረግ በየአካባቢው ሕዝባዊ ውይይቶች በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የክልሉ ሕዝብ ለሰላም እና ለአብሮነታችን ትልቅ ሚና መኖሩን በመገንዘብ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ርጋታ በተሞላበት ሁኔታ ለመፍትሄ መታተር ይኖርበታል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy