የተሻለ ኑሮ እንዳማረው እንዳይቀር
ኢብሳ ነመራ
የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የኢትዮጵያ አካል ሆኖ ዘመን መሻገሩ ይታወቃል። በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ህዝብ እንደተቀሩት ኢትዮጵያውያን የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ የሃገሪቱን ነጻነትና ሉዓላዊነት ሲያስከብር ቆይቷል። ሱማሊያን በቅኝ ግዛታቸው ስር አድርገው የነበሩ አውሮፓውያን የኢትዮጵያ ሱማሌን ህዝብ ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ ቢወተውቱትና ቢያባብሉት እንኳን ለዚህ ማባበልና ምልጃ አልበገር ብሎ በኢትዮጵያዊነቱ ጸንቶ የኖረ ህዝብ መሆኑን ታሪክ ያስረዳናል።
ይህ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ጽኑ እምነት ያለው ህዝብ ግን እነደተቀሩት የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ማንነቱ በህግ እውቅና ተነፍጎት ቆይቷል። በዚህ ጊዜ ብሄራዊ መብቶቹንና ነጻነቶቹን ለማረጋገጥ ታግሏል። በተለይ አንድ ሺህ ኪሎ ሜት ያህል ድንበር ከሚጋራው፣ ባህልና ሃይማኖት ከሚወራረሰው የኦሮሞ ህዝብ ጋር ጊዜውና ሁኔታዎች በሚፈቅዱት መልክ ግንባር ፈጥሮ ሲታገል ቆይቷል። ይህ ከተቀሩት የኢትዮጵያ ብሄሮች ጋር የተደረገ ትግል ፍሬ አፍርቶ የኢትዮጵያ ሱማሌ ህዝብ የራሱን ክልል አዋቅሮ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት አካል ሆኖ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን ተጎናጽፏል፤ በኢፌዴሪ ህገመንግስት። ክልሉ እንደተዋቀረ የነበረውን ሱማሌ የሚል ስያሜ ወደ የኢትዮጵያ ሱማሌ የቀየረው የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።
የኢትዮጵያ ሱማሌ ህዝብ በኢፌዴሪ ህገመንግስት ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ ቢረጋገጠለትም፣ የተለያዩ ታጣቂ ሃይሎች በክልሉ ውስጥ ሲያካሂዱት በነበረው እንቅስቃሴ ሰላም ርቆት ቆይቷል። በተለይ ለዓመታት መንግስት አልባ ሆና የቆየችው ሱማሊያ አዋሳኝ መሆኑ ሰላምና መረጋገቱተን የማረጋገጡን ስራ አስቸጋሪና ውስብስብ አድርጎት መቆየቱም ይታወቃል። ይሁን እንጂ በተለይ ባለፈው አንድ አስርት ዓመታት ገደማ ጉልህ እፎይታ መታየቱ አይካድም። በዚህ የእፎይታ ጊዜ የክልሉ ህዝብ ልማት፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ያስቻለ እድል ፈጥሯል።
ይሁን እንጂ የክልሉ ህዝብ እነዚህን የመልካም አስተዳደር፣ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት መከበር በረከቶች በሚፈልገው ልክ አላጣጣመም። የመልካም አስተዳደርና የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ የዴሞክራሲ ምህዳር መጥበብ፣ የህዝብና የመንግስት ሃብት ምዝበራ ወዘተ ፈተናዎች ገጥመውታል። እርግጥ እነዚህ ችግሮች የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ብቻ ሳይሆን የተቀሩት የኢትዮጵያ ክልሎችም የሚጋሩት ችግር ነው።
እነዚህ ችግሮች ስር እየሰደዱ ሄደው ባለፉ ሶስት ዓመታት በአብዛኛው የሃገሪቱ አካባቢዎች ታላቅ ህዝባዊ ንቅናቄ መካሄዱ ይታወቃል። ይህ የብዙዎችን መስዋዕትነት የጠየቀ ህዝባዊ ንቅናቄ ፍሬ አፍርቶ በፌደራል መንግስትና በተለይ ኢህአዴግ በሚያስተዳድራቸው ክልሎች የለውጥ አመራር ወደስልጣን እንዲመጣ አድርጓል። ከኢህአዴግ ውጭ በሆኑ ክልሎችም የለውጡን እንቅስቃሴ የሚመጥን እርምጃዎች የመውሰድ ዝንባሌዎች ታይተዋል።
በህዝባዊ ንቅናቄ ወደስልጣን የመጣው የለውጥ አመራር የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፉ፣ ሃገራዊ መግባባት የሚፈጥሩና የሰብአዊ መብት አያያዝን የሚያሻሽሉ በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል። በበዙ ሺህ የሚቆጠሩ ፍርደኛና በክስ ሂደት ላይ የነበሩ እስረኞች በይቅርታና በምህረት እንዲለቀቁ ተደርጓል። በውጭ ሃገራት ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ የፖለቲካ ሃይሎች፣ በትጥቅ ትግል ላይ ለነበሩ ጭምር ወደሃገር ቤት ገበተው ሰላማዊ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል። በዚህ ጥሪ መሰረት ወደሃገር ቤት መግባት እንዲችሉ በሃገሪቱ የጸረ ሽብርተኝነት ህግ መሰረት በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩት የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ግንቦት 7 የተሰኙ ድርጅቶች የሽብርተኝነት ፍረጃው እንዲነሳላቸው ተደርጓል። በዚህ የሰላም ጥሪ መሰረት በርካቶቹ ወደሃገር ቤት ተመልሰዋል። የተቀሩትም በቅርቡ እንደሚመለሱ በይፋ አሳውቀዋል።
በፌደራልና በክልል መንግስታት የተወሰዱ እነዚህ የፖለቲካ ምህዳርን የማስፋት፣ የሰብአዊ መብት አያያዝን የማሻሻል፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የማቃለል፣ ምዝበራን የመከላከል እርምጃዎች በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልልም እንዲከናወን የክልሉ ህዝብ ፍላጎቱን አሳይቷል። በተለይ የክልሉ ልሂቃን፣ የጎሳ መሪዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ኡጋዞች፣ ወጣቶች ፍላጎታቸውን፣ በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎችና የተገኙ ፍሬዎች ለእነርሱም እንዲደርሱ ጠበቅ ያለ ጥያቄ አቅርበዋል።
ይሁን እንጂ ይህን የክልሉን ህዝብ ፍላጎት የሚመጥን እርምጃዎች በክልሉ መንግስት አልተወሰዱም። በመሆኑም የክልሉ ልሂቃን፣ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ ኡጋዞች የክልሉ የሰብአዊ መብት አያያዝና የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ የሃብት ምዝበራ ወዘተ ችግሮች እንዲቃለሉ በአዲስ አበባና በድሬ ደዋ ባደረጓቸው ስብሰባዎች ድምጻቸውን አሰምተዋል። እነዚህ የክልሉ ተወላጆች አሁን ባለንበት ህዝብ ችግሩን ያለምንም ፍርሃት በድፍረት በሚናገርበት የለውጥ ሂደት ወቅት፣ በክልሉ ውስጥ ጅግጅጋና ሌሎች የክልሉ ከተሞች ተሰብስበው ድምጻቸውን ማሰማት አልቻሉም። የመብት ጥያቄዎች የቀረቡባቸው ስብሰባዎች አዲስ አበባና ድሬ ደዋ የተካሄዱት በዚህ ምክንያት ነው።
ያዛሬ ወር ገደማ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ልሂቃን፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች በአዲስ አበባ ስብሰባ ማካሄዳቸው ይታወሳል። በወቅቱ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተወሰኑ የክልሉ ተወላጆች፣ በፌደራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የክልሉ ተወካዮች የሆኑ ግለሰቦች ጭምር ስብሰባውን ረብሸው እንደነበረ ይታወሳል። የታሸገ ውሃ በመወረወር የተከበሩ የሃገር ሽማግሌዎች ጭምር የተደበደቡበት ሁኔታ እንደነበረ እናስታውሳለን። ይህ የሆነው በክልሉ የመልካም አስተዳደርና የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ የዴሞክራሲ ምህዳርን የሚያሰፋና ምዝበራን የሚያቃልል እርምጃ እንዳይወሰድ፣ ለውጥ እንዳይመጣ በሚፈልጉ ጥቂት አመራሮች ትእዛዝ እንደነበረ ታውቋል። ይህ ሁኔታውን የተመለከቱትን በሙሉ ያሳዘነ ድርጊት ነበር። በማንኛውም የሃገር ውስጥ ሚዲያ ሽፋን ሳይሰጠው መታለፉም አስተዛዛቢ ነው።
ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ሃሙስ ሃምሌ 26፣ 2010 ዓ/ም የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ተወላጆች – ልሂቃን፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች ለተመሳሳይ ዓላማ በድሬደዋ ከተማ ተሰብስበው ነበር። በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የጸጥታ ሃይል አባላት ከተማዋን ከክልሉ በሚያዋስነው አቅጣጫ ወደከተማዋ በመዝለቅ ስብሰባውን ለመበተን ተንቀሳቅሰው እንደነበረ በቦታው የነበሩ የአይን እማኞች መስክረዋል። የክለሉ ሃይል ወደ ደሬ ደዋ ከተማ መዝለቅ ያልቻለው በክልሉና በድሬደዋ ከተማ ድንበር አካባቢ ሰፈረው በነበሩ የፌደራል የጸጥታ ሃይሎች ክልከላ ነበር። ይህን ተከትሎ ቅዳሜ ሃምሌ 28፣ 2010 ዓ/ም በጅግጅጋ ከተማና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በድሬ ደዋ ከተማ ማንነትንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ የሃይል ጥቃቶች፤ ድብደባ፣ ግድያ፣ አስገድዶ መደፈርና ዘረፋ ተፈጽሟል። በዚህ ጥቃት በክልሉ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በፈለጉበት ቦታ የመኖር፣ የመስራትና ሃብት የማፍራት፣ የሃብታቸው ባለቤት የመሆን መብታቸው ተጥሷል።
ከክልሉ ተወላጆች የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የዚህ ሁከትና ጥቃት ጠንሳሾችና አስፈጻሚዎች ጥቂት የክልሉ አመራሮች ናቸው። እነዚህ ጥቂት የክልሉ አመራሮች፣ ህዝቡ ያነሳቸውን የሰብአዊ መብት መከበር፣ የመልካም አስተዳደር መሰፈን፣ የምዝበራ መቆም ጥያቄዎች ለማፈንና ከተጠያቂነት ለማምለጥ ያሰቡ መሆናቸውን ነው ተወላጆቹ የሚናገሩት። እነዚህ ጥቂት አመራሮች በክልሉ የሚወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች ስልጣናችንን ያሳጡናል ብለው እነደሚሰጉ ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።
የሁከቱና የጥቃቱ ፈጻሚዎቹ ደግሞ በእነዚህ ጥቂት አመራሮች የተወናበዱ፣ ምናልባትም በጥቅም የተደለሉ የጸጥታ ሃይል አባላትና ወጣቶች ናቸው። አሁን በክልሉ መንግስት ጥያቄ የፌደራል መንግስት የጸጥታ ሃይል – መከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ ገብቶ ሰላምና መረጋጋት የማስፈን ተግባር በማከናወን ላይ የገኛሉ። በኡሁኑ ወቅት ቢያንስ ጥቃትን ማስቆም ተችሏል። ከኑሯቸው ለተፈናቀሉና በቤተከርስቲያኖች ለተጠለሉ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የማቀረብ ስራም ተጀምሯል። የሰላም እጦት ስጋቱ ግን አሁንም አልገፈፈም።
የክልሉ የጎሳ መሪዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ኡጋዞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች ወዘተ የክልሉ ሰላምና ልማት፣ የሰብአዊ መብት መከበር፣ የመልካም አስተዳደር መሰፈን፣ ተገቢ የህዝብና የመንግስት ሃብት አያያዝና አጠቃቀም ቀዳሚ ተጠቃሚ ህዝቡ መሆኑን ማስታወስ አለባቸው። የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልላዊ መንግስት – የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ፍርድ ቤቶችና ስራ አስፈጻሚ አካላት የራሳቸው ፍላጎትና ግብ የሌላቸው የህዝቡን ፍላጎትና ጥቅም ለማስጠበቅ በውክልና ወንበር የያዙ መሆናቸውን ማስታወስም ይኖርባቸዋል። የክልሉ ህዝብ ህጎችና ፖሊሲዎች በአግባቡ አልተፈጸሙም ብሎ ሲያስብ የመጠየቅ መብት አለው። የክልሉ መንግስት ህጎችና ፖሊሲዎችን በአግባቡ በመተግበር የልማት ፍላጎታችንን ማሟላት አልቻለም፣ ሰብአዊና ፖለቲካዊ ምብታችንን አላረጋገጠም ብሎ ሲያምን ደግሞ ከስልጣን ወንበሩ ላይ የማንሳት ህገመንግስታዊ መብት ያለው መሆኑም ለአፍታም መዘንጋት የለበትም።
በመሆኑም የክክሉ ህዝብ በተለይ ተሰሚነት ያላቸው የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ . . . . የክልሉ መንግስት ህዝቡ ለሚያነሳው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ የማድረግ፣ ህዝቡም ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርብ የማድረግ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው። የክልሉን ችግር በክልሉ ውስጥ በሚኖሩ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች፣ ሌሎች ክልሎችና የፌደራል መንግስት ላይ ማላከክ ተገቢ አለመሆኑን መገንዘብና ማስገንዘብም አለባቸው። በክልሉ ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂው የክልሉ መንግስት ብቻ ነው።
የግል ፍላጎታቸው ላይ በማተኮር የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ የተደራጀውን የጸጥታ ሃይል የፍላጎታቸው ማስጠበቂያ መሳሪያ ያደረጉ፣ ህዝቡን በተለይ ወጣቶችን በማደናገር አብረዋቸው የሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ፣ ከሱማሌ ህዝብ ባህል ውጭ ጥቃት እንዲፈጸም በማድረግ ላይ የሚገኙ አመራሮችን መገሰጽና መምከር ከሃገር ሽማግሌዎችና ከጎሳ መሪዎች ይጠበቃል።
በአጠቃለይ፣ ለበርካታ ዓመታት በጦርነትና በግጭት ውስጥ ያለፈው የኢትዮጵያ ሱማሌ ህዝብ የሰላምን ጥቅም ከማንም በላይ ያውቀዋል። የሰላም ፋታ ሲገኝ ልማት ምን ያህል እንደሚፋጠንም ባለፉ ጥቂት አመታት ተመልክቷል። በመሆኑም በክልሉ ተጠያቂነትና የህግ የበላይነትን በማስፈን ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን ማስታወስ ይኖርበታል። አሁን የተፈጠረው የሰላም እጦት ችግር በጊዜ ካልተፈታ፣ በአካባቢው ለሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖች መግቢያ ቀዳዳ በመክፈት፣ ልማትና የተሻለ ህይወት የሚያምረው የኢትዮጵያ ሱማሌ ህዝብ እንዳማረው እንዲቀር ለሚያደርግ መከራ መጋለጡ አይቀሬ መሆኑን ማስታስም ብልህነት ነው።