Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተቀነባበሩ ሴራዎች

0 378

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተቀነባበሩ ሴራዎች

                                                             ይሁን ታፈረ

በአገራችን የተወሰኑ አካባቢዎች የታዩት ግጭቶች ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት እና ብጥብጥ እየገባች ነው የሚል ስጋት በህዝቡ ዘንድ ለማሳደር እንደሆነ ግልጽ ነው። እንዲሁም ኢትዮጵያ ከተያያዘችው የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የመደመር ጉዞል ለማሰናከል የታለመ ነው። ይሁን እንጂ የህዝቡ ፍላጎት የሆነውንና ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ማሰባሰብ የቻለውን አገራዊ ለውጥ መቀልበስ አይቻልም። ይህን ለማድረግም ህዝቡ ለውጡን ለማስቀጠል ሰላምን እና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይኖርበታል።

በአሁኑ ወቅት ከ100 ሺህ በላይ የሃሰት ፌስ ቡክ አካውንቶች ተከፍተው ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ ይታያል። እነዚህ የፌስ ቡክ አካውንቶች በመደበኛነት ከሚነዙት የሃሰት መረጃ እና ቅስቀሳ በተጨማሪ ተዓማኒነትን እያተረፉ ያሉትን የአገር ውስጥ ሚዲያዎችን እና የአንዳንድ መንግሥታዊ ተቋሞችን አርማና ስያሜ በመጠቀም የሃሰት አካውንቶችን ፈጥረው አፍራሽ መረጃዎችን መልቀቅ ጀምረዋል። ህብረተሰቡም የገጾቹ ባለቤቶች እውነተኛዎቹ ሚዲያዎችና ተቋማት አለመሆናቸውን በመረዳት የሚጠበቅበትን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት።

በፌስ ቡክ የተጀመረው ይህ የአሉባልታ ዘመቻ ተዓማኒነት ባላቸው ሚዲያዎችና ተቋማት ኦፊሴላዊ ገጾች ላይ የሚለቀቁ አገራዊ መረጃዎች ላይ በኮሜንት መልክ በስፋት በመግባት አሉታዊነትና አፍራሽነት የሚስተዋልባቸው አስተያዬቶችን የብዙሃኑ ህዝብ በማስመሰልም እየቀረቡ ለማደናገር ጥረት እየተደረገ ነው። ስለሆነም ህብረተሰቡ ይህን እውነታ በመረዳት ከአሉባልታዎችና ከፈጠራ ወሬዎች ራሱን በመጠበቅ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። አሉባልታዎቹ የተቀነባበሩ ሴራዎች ስለሆኑ መጠንቀቅ ተገቢ ነው።

በተለይም የፌስ ቡክን በብዛት የጠቀማል ተብሎ የሚታሰበው ወጣት ከእነዚህ አደናጋሪዎች ራሱን መጠበቅ አለበት። 100 ሺህ የሃሰት አካውንቶች ምን ያህል መረጃ በመልቀቅ በለውጥ ሂደት ላይ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል ሊያደናግሩ እንደሚችሉ ማወቅ ይገባል። እነዚህ አካውንቶች ስርዓት አልበኝነትን የሚያበረታቱ፣ በሃሰተኛ ወሬዎች እውነተኛ መስለው የሚቀርቡ፣ የህዝቡን የለውጥ ስሜት ለማኮላሸት ሆን ተብለው፣ ታስበውና ታቅደው የሚሰራጩ መሆናቸውን በመገንዘብ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

እርግጥ ወጣቶች በባህሪያቸው ሁሉንም ነገር የማወቅ ፍላጎት አላቸው። ይህ ባህሪያቸውም ለውጡን ለማይቀበሉ ሃይሎች የፌስ ቡክ አሉባልታ ሊያጋልጣቸው ይችላል። አሉባልታዎቹ ወጣቶቹን ወዳልተፈለገ ጉዳይ ሊመሯቸው ይችላሉ። ይህ ደግሞ ስራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ ያደርጋቸዋል።

ስራቸውን በአግባቡ ካልከወኑ ደግሞ እንደ ዜጋ በአገር ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፋቸው አይቀርም። ይህ ደግሞ የራሳቸውን፣ የዜጎችንና የአገርን ሁለንተናዊ ጥቅም የሚጎዳ ነው። ለውጡን የማይቀበሉ ሃይሎች የተቀነባበሩ ሴራዎች እዚህ ድረስ የዘለቁ በመሆናቸው ወጣቶች ለእነዚህ ሃይሎች አሉባልታዎች በር መክፈት የለባቸውም። በጥንቃቄና በሃላፊነት መንፈስ መረጃዎቹን መፈተሽ አለባቸው።

ወጣቶች የእነዚህ ለውጥ አዋኪ ሃይሎች መንገድ የሰላም ሳይሆን የሁከት፣ የልማት ሳይሆን የድህነት፣ የነፃነት ሳይሆን የባርነት እንዲሁም የዴሞክራሲ ሳይሆን የፀረ ዴሞክራሲያዊነት መሆኑን ማወቅ አለባቸው። የሚለቀቁ መረጃዎችን እየመረመሩ መውሰድ በአሁኑ ወቅት አገራችን እያከናወነች ያለችውን የለውጥ ሂደት እንዳይስተጓጎል ድጋፍ ማድረግም ነው።

ዛሬ በሁሉም መስኮች የሚከሰቱ ችግሮችን ህገ መንግስቱን ምርኩዝ አድርጎ መፍታት እየተቻለ ሴረኞች መብቶቻችንን ነጥቀው ጥገኛቸው እንዲያደርጉንና እንድንጨራረስ በር እንዲከፍቱልን መፍቀድ የለብንም። ልንታገላቸው ይገባል።

ዴሞክራሲያዊ መብታችንን የመብቱ ባለቤት ከሆነው ህዝብ በስተቀር ጥቅማቸው የተነካባቸው ሴረኞች እንዲቀሙን በር መክፈት የለብንም። ምክንያቱም መብቱን ዜጎች ታግለው ያመጡት እንጂ ማንም የሰጣቸው ስላልሆነ ነው።

በተለይም ሴረኞች በአጎራባች ክልሎች ውስጥ መካከል ያለውን የወሰን መካከል ጉዳይ እንደ የግጭት መንስኤ አድርገው በመጠቀም በህገ መንግስቱ መሰረት የሚፈታውን የወሰን ችግር እያጦዙ ለሴራ ፖለቲካቸው እንዲጠቀሙበት እድል መስጠት አይኖርብንም።

እርግጥ ማህበረሰብ እስካለ ድረስ ግጭት መቼም ቢሆን ሊጠፋ አይችልም። እንኳንስ የህዝቦች ንቃተ ህሊና እየተገነባና ይበል የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ባለበት፣ መደመርና አንድነት እንዲሁም ፍቅርና ይቅርታ እየነገሰ በሚገኝበት ብሎም ኢትዮጵያዊነት በአንድ ጥላ ስር እያሰባሰበን ባለበት በአሁኑ ወቅት ቀርቶ እንዲህ የተካረረ ግጭት ኖሮ አያውቅም።

የችግሩ መንስኤ ምንም ይሁን ይህ እውነታ ምን የሚያሳየን ነገር ቢኖር፤ የከሰሩ ፖለቲከኞች ሴራቸውን ቀምረው ህዝቡን ለማጋጨት እየሰሩ መሆናቸውን ነው። ፌስ ቡክ ደግሞ “ምርጥ” የሴራ ማቀነባበሪያ ቦታቸው ሆኗል። ሆኖም ወጣቶች መረጃዎቹን በትክክል እስከተገነዘቡ ድረስ ለሴራቸው ሊጋለጡ አይችሉም።

በሴረኞች የሚከሰቱ ችግሮች የስርዓቱ አሊያም የህዝቦች የዘመናት የተንሰላሰሉ እሴቶችን የሚወክሉ አይደሉም። የአገራችን ህዝቦች ባለፉት ዓመታት ከመልካም አስተዳደር እጦት ውስጥ ነበሩ። ይህ ሁኔታ በጥቂት ወራቶች ውስጥ እየተቀየረ ነው። ችግር ሲፈጠር በአግባቡ መፍታት ያልቻሉ አመራሮች ራሳቸው በፈቃዳቸው የስራ ሃላፊነታቸውን እየለቀቁ ነው። ይህም የግል ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ጥቂት ግለሰቦች የሚያባብሷቸው ወይም የሚቀሰቅሷቸው ግጭቶች እንዳይኖሩ እያደረገ ነው።

ይህ ሀኔታም በመላ አገሪቱ ሰላሙ የተረጋጋ ማህበረሰብ እንዲኖር የሚያስች ከመሆኑም በላይ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና መንግሥት መላ አቅማቸውን አቀናጅተው በድህነትና በኋላ ቀርነት ላይ ይበልጥ እንዲዘምቱ የሚያደርጋቸው ነው። ሕዝቦች በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን አገራዊ መግባባት ተመርኩዘው ኢትዮጵያን ለመለወጥ እንደ አንድ ማህበረሰብ በልማት አጀንዳዎች ላይ እንዲረባበረቡም ያስችላቸዋል።

አገራችን ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን አግባብ ባለው መንገድ ለመፍታት አገራችን የምትከተለው ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ በአዲስ መልክ እየተሰራ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚከተሉት አዲስ መንገድ ለችግሩ እልባት የሚሰጥ ነው።

የአገራችን ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር የጋራ አገራቸው የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማልማት አዲስ መንገድ ተከፍቶላቸዋል። ይህ መንገድ የሴረኞች ስግብግብ ፍላጎት የገታ ነው። ፍትሐዊ ተጠቃሚነትንና እኩልነትን ወደ መሬት አውርዶ ህዝቡ ጋ የሚያደርስም ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው አዲስ አመራር ህዝቡ ጥላቻንና ቂም በቀልን አሽቀንጥሮ እንዲጥል እያደረገ ነው። አገር በቁርሾ ስለማይመራ እንዲሁም ህዝብም በጥላቻ ስሜት የሚወዳትን አገሩን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን ማረጋገጥ ስለማይችል በዶክተር አብይ የተቀየሰው የፍቅርና የመደመር ስሜት ሴረኞችን ማስደንገጡ የሚገርም አይደለም።

ይሁን እንጂ አሁን የተያያዝነው ለውጥ ለችግሮቻችን መፍትሔ እያበጀ ነው። በሂደትም ችግሮች መቀረፋቸው አይቀሩም። የተቀነባበሩ ሴራዎች ይህን አይነግሩንም። ጉዳዩን ገልብጠቅ በማጦዝ የተገኘውን ለውጥ ለማዛባት ይሞክራሉ። ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች ይህን እውነታ በሚገባ ማወቅ አለባቸው። ስለሆነም በፌስ ቡክ እየተቀነባበሩ የሚቀርቡ ሴራዎችን በማጋለጥና ራስም በመጠንቀቅ መታገል ያስፈልጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy