Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ

0 852

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ

ወንድይራድ ኃብተየስ

አሁን ወቅቱ ክረምት ነው – ነሐሴ ወር። በነዚህ የክረምት ወራት ውስጥ ሁሉም የጋራ የቤት ሥራ ይዟል – የችግኝ ተከላ ዘመቻ። ይህም ተግባር ኢትዮጵያ የምትከተለውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ የሚያግዝ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሥራ ለኢትዮጵያ የሚያበረክተው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። እየተካሄደ ያለው የችግኝ ተከላ ከአረንጓዴው ልማት ጋር ያለው ትስስር ከፍተኛ ነው። በተለይም በተደጋጋሚ በሚከሰተው የተፈጥሮ አየር መዛባት ሣቢያ በድርቅ አደጋ ለምትጎዳው አገራችን በአረንጓዴ ልማቱ ዘርፍ የሚኖራት ተጠቃሚነት የላቀ መሆኑ አያጠያይቅም።

በግልጽ እንደሚታወቀው ማንኛውም አገር ሁኔታዎቹን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለማጣጣም መከናወን ያለባቸውን ችግሮች መዘርዘርና መፍትሄ ማፈላለግ ይገባዋል። እናም ወደአገራችን ስንመለስ የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እነዚህን ችግሮች ለይቶ በማውጣት በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።  

እዚህ ላይ ለዚህ ተግባርም ተስማሚ የሆነ፣ የሥራ ዕድልን የሚፈጥር፣ ምርትንና ምርታማነትን የሚያሳድግ የአካባቢ መራቆት ሂደትን የሚከላከል፣ ለአካባቢው ልማት የሚውል ዕቃና አገልግሎት የማቅረብ እንዲሁም ቀጣይ አቅምን የሚያጎለብት፣ በጎ ተሞክሮን እና ቴክኖሎጂን ማሰስ ያስፈልጋል፡፡

የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በተለያዩ አካላት ሲተገበሩ ከነበሩ የአካባቢ እንክብካቤ ተግባራት በመነሳት መልካም ተሞክሮዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማስፋፋት ሙከራ ሲያካሄድ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በመነሳትም የአካባቢ አንክብካቤን መሠረት ያደረገ የእፅዋትና የፍራፍሬ ልማት ቴክኖሎጂን ወደ አገሪቱ በማስገባት ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል፡፡

ቴክኖሎጂው ተራራማና ደጋማ በሆኑ አካባቢዎች በዓመታዊ ሰብሎች አመራረት ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የእፅዋትና የፍራፍሬ ልማት እንዲሁም የአፈርና ውኃ ዕቀባ ተግባራትን በማቀናጀት የሚያራምድ ነው፡፡

ይህም የኅብረተሰቡን ገቢ በማሻሻል በተለይም ወጣቶችን እንደ ደን ቆረጣ ካሉ አካባቢን ከሚጎዱ የገቢ ማስገኛ መስኮች በማላቀቅ ህገ አማራጭ ወደ ሆኑ የገቢ ማስገኛ መስኮች እንዲዞሩ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም በእርሻ ላይ የተመሰረተው ምጣኔ ሀብት ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ያግዛል፡፡ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ የሰብል፣ የዛፍ፣ የፍራፍሬና አትክልት ዝርያዎች፣ የእንስሳት ዕርባታና ድለባ፣ የንብ ማነብ ሥራን አቀናጅቶ በማልማት የገቢ ምንጭን ማሳደግ ያስችላል።  

ክንዋኔው በምጣኔ ሀብቱ ላይ ከሚኖረው አዎንታዊ ተፅዕኖ ባሻገር፤ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጫና በመቀነስ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ ፊዚካላዊና ሥነ – ህይወታዊ የአካባቢ ሥራዎችን በመተግበርም የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የአፈር ለምነትን ለመጨመር እገዛ ያደርጋል።  

በሌላ በኩልም ቴክኖሎጂው የዕፅዋት እና እንስሳት ዓይነቶች እንዲበራከቱ አድርጓል፡፡ አካባቢውም በተለያዩ ዕፅዋቶች ሲሸፈን የአካባቢው ውበት ስለሚያምር ለኅብረተሰቡ ደግሞ የመዝናኛ ቦታን ስለሚያበረክት ንፁህ ከባቢን ለመፍጠር የሚደረገውን ርብርብ የሚያግዝ ይሆናል፡፡

የአካባቢ ጥበቃን መሠረት አድርገው እየተሰራባቸው ካሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል የተጎዱ መሬቶችን ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነጻ በማድረግ እንዲያገግሙ የሚረዳ ቴክኖሎጂ አንዱ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው በዕፅዋት ሽፋን መሳሳትና በአፈር ለምነት መቀነስ ሣቢያ የተጎዱና ምርታማነታቸው የተቋረጡ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ ከማድረግ አንፃር የበኩሉን አስተዋጽኦ ይኖረዋል።  

ቴክኖሎጂው የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግሙ ለማድረግ በየአካባቢው መልክዓ ምድር ሊተገበር ይችላል። ለአካባቢው አየር ፀባይ ተስማሚ የዕፅዋት ዝርያ በመምረጥ ተስማሚ የእርከን ዓይነቶችን መለየት እና የገቢ ምንጭ ሊያስገኙ የሚችሉ ሥራዎች ተቀናጅተው የሚከናወኑበት ሁኔታ በማጤን ኅብረተሰቡ የሚጠቀምበትን መንገድ ለማሳየት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እንዲከናወኑ አስችሏል፡፡

ዜጎችም የተጎዱ ቦታዎች መልሰው እንዲያገግሙ የማድረግና የማልማት እንዲሁም እውቀትና ክህሎት እንዲያዳብር አጋዥ ነው። ከዚህም ጋር የመሬት ጥበቃ ችግርን በማሳበብ ኅብረተሰቡ ከአካባቢው እንዳይሰደድ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የጓሮ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን አልምቶ ራስንና ቤተሰብን ለመመገብ ብሎም ጤናው እንዲሻሻል በማድረግ ረገድ መንግሥት አስቀድሞ በሽታን ለመከላከል ለያዘው ዕቅድ የራሱን ድርሻ ይጫወታል፡፡

በዚህም ምክንያት በየአካባቢው ጠፍተው የነበሩ የእፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች በመመለስ ላይ ናቸው። ቴክኖሎጂው ለአካባቢ ጥበቃ ከሚያደርገው ጉልህ ድርሻ ባሻገር ከግብዓት አቅራቢዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው አድርጓል፡፡ ምጣኔ ሀብቱም አስተማማኝ በመሆኑ ለቴክኖሎጂ ዘላቂነት ወሣኝ ሚና ይጫወታል።  

የተጎዱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን መትከል ዋነኛው አማራጭ ነው፡፡ ለዚህም በርካታ የችግኝ ማፍያ ጣቢዎችን በብዛት መጠቀም ይገባል፡፡ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶችም ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የዛፍ፣ የፍራፍሬና የአትክልት ችግኞችን ለገበያ በማቅረብ የሥራ መስክ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ግለሰቦች የሰብል ፍርፍሬና፣ አትክልት የዛፍ ችግኞችን አቀናጅቶ በማምረት የገቢ ምንጭን ማሳደግም ይችላል፡፡

ለአካባቢ ጥበቃ አጋዥ ናቸው ተብሎ እየተሰራባቸው ካሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል የቀርከሃ ልማትና ዕደ ጥበብ ቴክኖሎጂ ዋነኛው ተጠቃሽ ነው፡፡ የቆላም ሆነ የደጋ የቀርከሃ ምርት ለማገዶና ለግንባታ ሥራዎች፣ ለቤት ውስጥ ቁሳቁሶች እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ግልጋሎትነት መዋል መቻሉ የቀርከሃ ዕደ ጥበብ ውጤቶችን ከማምረትና ለገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ ሌላው የገቢ ምንጭ ነው፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የቀርከሃ ተክል ብዛት ያላቸው እርስ በርሳቸው የሚጠላለፉ ረዣዥም ሥሮች አሉት። ይህም አፈርን አቅፎ መያዝ ይችላል። በአየር ውስጥ ያለውን ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመምጠጥ የምድርን ሙቀት በመቀነስ ረገድም አስተዋጽኦ አለው። ከዚህ በተጨማሪም የተጎሳቀለ መሬት መልሶ እንዲያገግም ያግዛል። በዚህም የተነሳ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶት እየሰራበት ይገኛል፡፡

ከዚህም ጋር የአካባቢ ጥበቃን የተሻለ ለማድረግ የተፈጥሮ ሥነ – ምህዳርን ለመጠበቅ ከሚደረገው ርብርብ ባሻገር ለዕለት ተዕለት ኑሮ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች መመልከት ጠቃሚ ይሆናል። ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ከፀሃይ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ ቴክኖሎጂዎችን በአማራጭነት እየተጠቀመች ነው፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ የፀሃይ ኃይልን በመሰብሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ ቴክኖሎጂ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ታዳሽ በመሆኑ በዘላቂነት መጠቀም ይቻላል፡፡ በየትኛውም መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና በቂ ፀሐይ ጨረር በሚገኝባቸው አካባቢዎች ሁሉ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ቴክኖሎጂ ስለሆነ ለኢትዮጵያም ተመራጭ ሆኗል፡፡ ቴክኖሎጂው በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ከዚህ ጋር አያይዞ ማንሳት ተገቢ ይሆናል።

በዚህ የክረምት ጊዜያት እየተካሄደ ያለው የደን ተከላ የዘመቻ ፕሮግራም በደን ሃብት ሽፋን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለመቀነስ የሚደግፍ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ቁም ነገር የችግኝ ተከላውን ማከናወን ብቻ ሳይሆን በክትትል እንዲፀድቅ ማድረግ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy