Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ይቅርታ— እስከ ሚኒሶታ

0 980

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ይቅርታ— እስከ ሚኒሶታ

                                                   እምአዕላፍ ህሩይ

(ክፍል ሁለት)

በክፍል አንድ ፅሑፌ ላይ ቃል በገባሁት መሰረት የ“ግንቡን” እና “ድልድዩን” ትርክት አልቋጨሁም። የትረካው ቀጣይ ክፍልና ቀሪ መቋጫው እንዲህ የሚነበብ ነው።….የአንድ ወንዝ ልጆች ሲፋቀሩ የሚጠላ ሰው የለም። ፍቅር፤ ዘር፣ ቀለም፣ ፆታ፣ ሀገር ሳይለይ የሰው ልጆችን ሁሉ የሚያግባባ ዓለማቀፋዊ መግባቢያ ይመስለኛል።

እንኳንስ የአንድ ቀዬና አድባር ልጆች ቀርቶ የማይተዋወቁ ሰዎችም ቢሆኑ በፍቅር ደምቀው ሲታዩ የማይደሰት ሰው የለም—የጥላቻ፣ የቂም በቀልና የተንኮል ጎሬ ካልሆነ በስተቀር። ምናልባትም ትናንት በተለያዩ እንካ ሰላንቲያ ውስጥ ሆነው መለያየትን በየአደባባዩ ሲያሳዩ ወይም ውግዘትን ሲያሰሙ የነበሩት የሀገሬ ልጆች፤ ዛሬ በይቅርታ ደምቀው፣ በፍቅር አሸብርቀውና በመደመር ታድመው ለአንዲት ሀገራቸው ለመነጋገር በአንድ አዳራሽ ውስጥ ሲወያዩ መመልከት በማንም ልብ ውስጥ ሐሴትንና ፍሰሐን ማጫሩ አይቀሬ ነው።

እናም ይህ ሁኔታ የሎስ አንጀለስ ከንቲባን ልባቸውን የነካቸው ይመስለኛል። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ እኔ የተሰማኝ እንዲህ ነው። ከንቲባው ዕለቱን “የኢትዮጵያዊያን ቀን” ብሎ በመሰየም በመደመሩ ላይ ዘመን ተሻጋሪ ማህተም አሳርፈወበታል ብዬ አስባለሁ። ይህም “ከጨፌ አራራው” ይቅርታን፣ ፍቅርንና አንድነትን ከማፅናት እሳቤ ልህቀት ጋር አብሮ የሚሄድ ነው።

ሌላኛው የዕለቱ በኢትዮጵያዊያን ቀንነት መሰየም፤ የመንደሩ መሃንዲስ ዶክተር አብይ በየመድረኩ “አንድ ስንሆን እንከበራለን” እያሉ ከሚናገሩት እሳቤ ጋር አብሮ የሚሄድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ርግጥ የተበታተነን፣ የተለያየንና በየጊዜው በሰበብ አስባቡ የሚናቆርን ህዝብ የሚያከብረው አካል አይኖርም። በአንፃሩም በአንድነት የሚጓዝን፣ በሀገሩ ጉዳይ በአንድነት የሚሰራን፣ ሌት ተቀን ለሀገሩ የሚሰራን የማይወደውና የማያከብረው ወገን የለም። ሎስ አንጀለሶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ያሳዩን ይህን አክብሮት ነው። ዕውቅና መስጠትም ጭምር ነው። አክብሮትን በአክብሮት መመለስ ይገባልና እኔም እንደ ዜጋ ለተሰጠን ክብር ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌያለሁ።

ከ“ኢትዮጵያዊያን ቀን” ስያሜው ወደ መደመር ጉዞው ስለመስ፤ በሎስ አንጀለሱ መድረክ ላይ የመለያየት “ግንቡ” ሲፈርስ ተመልክቻለሁ። በጠንካራ ኮንክሪት፣ ፌሮና የአርማታ ሙሌት የተገነባው የይቅርታና የፍቅር “ድልድይ”ም በአንድነት ስሜት ግሞ እየተቀጣጠለ ሲገነባ አይቻለሁ—በዳያስፖራው፣ በዶክተር አብይና በፈላስፋው አቦ ለማ መገርሳ አማካኝነት። በዚያ ልዩነትን የማፍረስና ይቅርታን፣ ፍቅርንና አንድነትን የመገንባት መድረክ ላይ፤ ኢትዮጵያዊያን ላለፉት ጊዜያት ብዙ ዋጋ እንደከፈሉና ኢትዮጵያን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ሁሉን አቀፍ ርብርብ አስፈላጊ መሆኑ ተወስቷል። ይህ አስተሳሰብ ‘የትናንት ውጣ ውረዶቻችንን በይቅርታና ለይቅርታ ትተን ዛሬ በአዲስ መንፈስ ሀገራችንን ለመገንባት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንነሳ’ የሚል አንድምታ ያለው ይመስለኛል።

ርግጥ አስተሳሰቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት “በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በድህነት የሚኖር ወገናቸውን በተለይ፤ በመሰረተ ልማት፣ በትምህርትና ማህበራዊ ተቋማትን በማስፋፋት ረገድ ሊያግዙ ይገባል” በሚል ትክክለኛ ምልከታ በመድረኩ ላይ ተገልጿል። አዎ! እንዳልኩት ዳያስፖራው ኢትዮጵያ ሀገሩ ናት። ዜጎቿም ወንድምና እህቶቹ ናቸው። በዚህች ሀገር ላይ የሚካሄድ ጥሩም ይሁን መጥፎ ነገር ስሙ አብሮ መነሳቱ አይቀርም። ሀገሪቱ ስታድግ ዳያስቦራው በያለበት አካባቢ አንገቱን ቀና አድርጎ ይሄዳል። በድህነት ስትጠራም ተቃራኒውን ማሳየቱ ግልፅ ነው። ምክንያቱም ዶክተር አብይ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት፤ እንዳሉት ኢትዮጵያዊ በሄደበት ሀገር ሁሉ ኢትዮጵያን ይዟት ስለሚዞር ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህን፣ ሰላምንና አንድነትንና ሀገራዊ ዕድገትን ማምጣት የሚያስችል ለውጥ እውን እየሆነ ነው። ድህነት በተጨባጭ ሊማረክበት የሚችልበት አውድ ተፈጥሯል። እናም ለውጡ ድጋፍ ይፈልጋል። ዳያስፖራው በገንዘቡና በእውቀቱ የድጋፉ ተባባሪ መሆን ይገባዋል። አንድነትን ለማምጣት የሚደረገው ጥረት አካል መሆን ድህነትን ለመቅረፍ አንድ ርምጃ ወደፊት የሚያስኬድ ይመስለኛል። እናም ኢትዮጵያን በየሄደበት ሁሉ ይዟት የሚዞረው ዳያፖራው ወገኔ መደመሩን በዚህ መንገድ በማረጋገጥ የወገኑን ችግር ሊካፈል የሚገባው ይመስለኛል።  

በሎስ አንጀለሱ መድረክ ስለ ወጣቶችና ስለ እርሻም ምክክር ተደርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የወጣቱን ስነ ልቦና የመገንባትና ህግ የሚያከበር እንዲሁም ሀገሩን የሚወድ ዜጋ የመፍጠር ዓላማ ይዞ መንግስት እንደሚሰራ አስታውቀዋል። ርግጥ ወጣቱ በሀገሩ ሰርቶ ማደግ እንደሚችል በተገቢውና በተጨባጭ መንገድ ማሳየት ከተቻለ ወደ ውጭ የሚያይበትን ምልከታ ማረቅ ይቻላል። በሀገሩ ላይ ሰርቶ መለወጥ ከቻለም ወደ ውጭ የሚያይበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። በሀገራችን የመጣው ለውጥ ባለቤት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ቢሆንም፣ ወጣቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። ዛሬም ለውጡን ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር በመሆን እየጠበቀ ያለው እርሱ ነው።

ለውጡ ከሀገሪቱ ዕድገት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ለመጥቀም ከወዲሁ እየሰራ ነው። በሶስትና አራት ወራቶች ውስጥ ብቻ ምን ያህል መስራት እንደተቻለ ወጣቱ የሚገነዘበው ጉዳይ ነው። እናም መጪው ጊዜ ከአዲሱ አመራር ጋር በአንድነት መንፈስ ተጠቃሚነቱን ይበልጥ የሚያጠናክርበት ጊዜ በመሆኑ ተስፋውን ከሀገሩ ጋር ማቆራኘት ይኖርበታል፤ ወጣቱ።   

እርሻን በተመለከተም የሎስ አንጀለሱ መድረክ ውይይት አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሀገራችን በረሃማ አካባቢዎች እምብዛም እንዳልተሰራባቸው ገልጸዋል። በ2011 ዓ.ም በጀት ከፍተኛ በጀት የተበጀተው ለዚሁ ዘርፍ በመሆኑ መንግስት ለመስኖ እርሻ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። የእርሻ ስራ የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው። እርሻው የሚከናወነው ከ85 በመቶ በላይ የህዝብ ቁጥር ባለው አርሶ አደር ውስጥ በመሆኑም የእርሻው መዘመንና ማደግ ይህን ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ከመመገብ ባለፈ የከተማውንም ነዋሪ ቀለብ የሚሸፍን እንዲሁም ለውጭ ገበያ የሚውል በመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት መስጠት ትክክለኛ አቅጣጫ ነው።

ርግጥ ዘርፉ እጅግ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የያዘና በርካታ የህብረተሰብ ክፍልን መቅጠር የሚችል ነው። አዋጭ መሆኑም አያጠያይቅም። ዳያስፖራው በዚህ ዘርፍ ላይ ቢሰማራ ራሱንና ሀገሩን መጥቀሙ አያጠያይቅም። የግብርና ስራ ያልተነካና ድንግል ዘርፍ ነው።

በዘርፉ ገንዘብ አሊያም እውቀት ያላቸው ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በስራው ላይ ኢንቨስት አድርገው ሲሰማሩ በአንድ ድንጋይ ሶስት ወፎችን ይመታሉ ብዬ አስባለሁ። አንደኛው፤ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ይጠቅማሉ። ሁለተኛው፤ ግብርናውን በሚያካሂዱበት አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮችንና ወጣቶችን በመቅጠር ተደማሪ እሴቶችን የሚፈጥሩ ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ፤ ሀገራችን የተያያዘችውን ልማት በማጎልበት በኢኮኖሚው ላይ ጉልህ ለውጥ እንዲመጣ ሊያደርጉ ይችላሉ። እናም ዶክተር አብይ በተለይ በረሃማው አካባቢ አልተሰራም ማለታቸው ዳያስፖራው ወደ ሀገሩ ቢያለማ ለራሱም ይሁን ለሚወዳት ሀገሩ ሊያስገኝ የሚችለውን ጠቀሜታ ማመላከታቸው ይመስለኛል። ለዚህም ነው—የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ፈላስፋው ኦቦ ለማ መገርሳም በሎስ አንጀለሱ መድረክ ላይ፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በእውቀትና በሃብታቸው በሀገራቸው ግንባታ መሳተፍ እንዳለባቸው ያሳሰቡት። እናም እኔ በበኩሌ ዳያስፖራው በመደመር ይህን ጥሪ ተቀብሎ የሀገሩ ዋልታና ማገር እንደሚሆን ቅንጣት ያህል ጥርጥር የለኝም። ያም ሆኖ በዲሲና በሎስ አንጀለስ የጥላቻ “ግንቡ” ተደርምሷል፤ የቅርታና የፍቅር “ድልድይ” ብረት በማይበሳው ሙሌት ተገንብቷል።…ፍርስራሹ ግን?…

ፍርስራሹ የተጠረገባት ከተማ

እዚህ ላይ ‘የምን ፍርስራሽ?’ ብሎ መጠየቅ አይቻልም። ምክንያቱም የልዩነት “ግንቡ” በዲሲና በሎስ አንጀለስ ፈርሶ ሲደረማመስ፤ ፍርስራሽ መፈጠሩ የግድ መሆኑን የዚህ ፅሑፍ ታዳሚ ስለሚገነዘብ ነው። እናም በዚህች 60 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን እንደሚኖሩባት በሚገመተውና አንዳንዶችም “ትንሿ ኦሮሚያ” (The Little Oromia) እያሉ የሚጠሯት ሚኒሶታ ከተማ፤ በሁለቱ ከተማዎች የፈረሰው የልዩነት “ግንብ” የፈጠረው ፍርስራሽ ካብ ሳይሰራና የሰው ሀገር ሳያበላሽ እንዲጠራረግ ተደርጓል—“በጨፌ አራራዎቹ” የእኛ ሰዎች።

የጥላቻ፣ የቂም በቀልና የተንኮል ፍርስራሹ ከመጠረጉ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተጋርዶ ስለነበረው “ግንብ” ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም፤ የተገነባው “ግንብ” ብዙ ቋንቋ በመናገራችን፣ ከተለያየ ዘር በመምጣታችን አሊያም የተለያየ ሃይማኖት በመከተላችን አይደለም ብለዋል፤ እነዚህ ሁሉ ልዩነታችን ውበታችን መሆናቸውን በማስረዳት።

እናም “ግንቡ” የተሰራው ከጥላቻ፣ ከመናናቅ፣ ከራስ ወዳድነትና ከቂም በቀል ግብዓቶች ነው። በዘመናችን እነዚህን ግብዓቶች የተከለከለ ነው ማለት አለብን ብለዋል። ርግጥም ባለፉት ጊዜያት ግንቡ እንዲጸና ያደረጉትን ግብዓቶች “ውግዝ ከመአርዩስ” ብለን ልናወግዛቸው የግድ ይለናል። አዎ! የመለያየትና የመቃቃር አጀንዳ ግብዓተ መሬቱ መፈጸም ይኖርበታል፤ በእኛ ዘመን።

ያም ሆኖ በአሜሪካ የመደመር ጉዞ በዲሲና ሎስ አንጀለስ “ግንቡ” ፈርሶ፣ ፍርስራሹን የመጥረግ ተግባር ደግሞ ሚኒሶታ ላይ ተፈፃሚ ሆኗል። ዶክተር አብይም በተምሳሌትነት አክቲቪስት ጃዋር መሐመድን በማቀፍ አረጋግጠዋል። እኔም፤ ለሀገሬ ልጆች በሙሉ፤ “ለጨፌ አራራ” አንበሶች በተለይ፤ መለያየትንና ጥላቻን አስወግደው እንዲሁም ክፋትና ተንኮልን አክስመው፣ ፍቅርንና ይቅርታን አብስረውና መደመርን አክለው ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱት ሁሉ፤ እነርሱም ሰላሙን ያበዛላቸው ዘንድ በመመኘት ይህችን አጭር ምልከታዬን አጠናቅቃለሁ። አማን ያሰንብተን።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy