Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዲያስፖራው እና አሻራው

0 344

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዲያስፖራው እና አሻራው

                                                         ደስታ ኃይሉ

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመንግስት የተዘጋጀውን ትረስት ፈንድን ለማገዝ ከፍተኛ ተነሳሽነት አሳይተዋል። በዚህ ረገድ በቀን አንድ ዶላር ሳይሆን 10 ዶላር ለመስጠት ቃል የገቡም እየታዩ ነው። ይህ ሁኔታ ዲያስፖራው በተጀመረው የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የመደመር ጉዞ በአገሩ ልማት ላይ አሻራውን ለማሳረፍ ያለውን ፍላጎት የሚያመላክት ነው።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በኢንቨስትመንት በመሰማራት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የአገራቸውን የቱሪዝም መስህቦች እና ምርቶች ለዓለም በማስተዋወቅ…ወዘተ መስኮች ሊሳተፉ ይችላሉ። እነዚህን ተግባሮች ዲያስፖራው በሚፈለገው መጠንና ዓይነት መፈጸም ከቻለ፣ ኢኮኖሚያዊ እመርታን ለሚወዳት አገሩ በማስመዝገብ ታሪካዊ አሻራውን ሊያሳርፍ መቻሉ አያራጥርም።

ዲያስፖራው እዚህ ሀገር ውስጥ ሊያሰራ የሚችል የለውጥ አመራር መኖሩን ማወቅ ይኖርበታል። ይህ አመራር ከመቼውም ጊዜ በላይ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማመቻቸት ሁሉንም ወገን ሊጠቅም የሚችል መንገድ ቀይሷል።

መንግሥት የግሉና የመንግሥት የዘርፎች ተዋንያን በፍትሃዊ የገበያ ውድድር የተመሩ ልማታዊ ኢንቨስትመንት የማስፋፋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ገበያው የማይመልሳቸውን የልማት ጥያቄዎች በተጠናና በተመረጠ ሁኔታ መንግሥት በራሱ በቀጥታ የሚሳተፍባቸው አቅጣጫዎች በመከተል ላይ ይገኛል። መንግሥት የገበያ ጉድለቶችንና ተያያዥ የሙስና ምንጮችን ለመዝጋት በመሰረተ ልማት እና በሰው ሃብት ልማት ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የመሰረተ ልማትና የሰው ሃብት ልማት ኢንቨስትመንት የማስፋፋት ሥራ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ እንደ ልማታዊ መንግሥት ማከናወን ያለበት ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ታምኖበታል የሚካሄድ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። መንግስት በዚህ መልኩ የገበያ ጉድለቱን በማጥበብ የኪራይ ምንጮችን ለማድረቅ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርናና የመሳሳሉት ድጋፎች በማድረግ ልማታዊ ባለሃብቶች እንዲበረታቱ እያደረገ ይገኛል።

ይህ ሁኔታም እንደ መሬት፣ ብድርና የመሳሰሉትን ድጋፎችን የግሉ ባለሃብት በቅድሚያ እንዲያገኝ፣ ቀልጣፋና ግልጽ፣ ተገማችና ውጤታማ እንዲሆኑ ብሎም ለልማታዊ ኢንቨስትመንቶች ይበልጥ አዋጪ የሚሆኑበትና የሚስፋፉበት ሁኔታ በየጊዜው እየጎለበተ እንዲሄዱ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ርግጥ ለሀገራችን ፈጣን ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ኢንቨስትመንቶች ገበያው ላያስተናግዳቸው እንደሚችል ይታመናል። ስለሆነም ፈጣን ዕድገቱን ሳይቆራረጥ ለማስቀጠል የዚህ ዓይነት የኢንቨስትመንት መስኮች በጥንቃቄ እየተጠኑና እየተመረጡ በቀጥታ በመንግሥት በራሱ ብቻ ወይም ከግሉ ዘርፍ በጋራ እንዲካሄዱ እያደረገ ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ከዕድገት ደረጃችን ጋር ተያይዞ ከሚኖረው የገበያ ጉድለት እና ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ጋር ተያይዞ ሊከሰትና ፈጣን ዕድገቱን ሊያስተጓጉል የሚችለው አደጋ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። አደጋውን ለማስቀረት አስቀድሞ የተለየና መፍትሔም የተቀመጠለት ጉዳይ ሆኗል።

የመሬትና የባንክ አስተዳደር ሥርዓቶቹ እንደታቀደው ልማትን በሚያፋጥንና የህዝብ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የተሟላ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት ሁኔታ መከናወን እንዳለባቸው መንግሥት በፅኑ ያምናል። ማመን ብቻም ሳይሆን፣ የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱም ፍትሃዊ ውድድርን የሚያሰፍንና ህጋዊ ያልሆነ ጥቅምን የሚዘጋ ለማድረግ የሚያስችል ስራ ማከናወኑንም ቀጥሏል። የመንግሥት ተሳትፎ የባለ ሃብቱን ልማታዊ እንቅስቃሴ የሚያሳድግ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም መካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂና የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል። ከእነዚህም መካከል የአቅም ግንባታ፣ የገበያ ትስስርን መፍጠር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ክትትልና ድጋፍ መስጠትን ያጠቃልላል። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል። መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በወጭ ንግዱ ለማጠናከር ባከናወነው ተግባር ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተመልክተናል። ለአብነት ያህል የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ለውጦች ታይተውባቸዋል።

የመንግሥት ደጋፊ ተቋማት አቅም ለማሳደግ የፋብሪካዎች የቴክኖሎጂና የማኔጅመንት አቅም ካደገ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ከባለሃብቱ ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውና ለመፍትሔውም በጋራ መሰለፋቸው የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው እሙን ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ልማትን በማስፋፋት የተፋጠነ ልማትን ለማረጋገጥ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ ይገኛል። ባደረጋቸው ማሻሻዎችም የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ተጨባጭ በሆነ ሁኔታ እየለወጠ ነው። በአሁኑ ሰዓት የጥቁር ገበያና የባንክ የዶላር ገበያ ተቀራራቢ ሆኗል።

ከዚህ በተጨማሪም አገራችን እየተከተለችው ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ነፃ የመሬት አቅርቦት መዘጋጀቱ፣ የአበባ ማምረቻ ስፍራዎች በመንገድ እና በኤሌክትሪክ እንዲተሳሰሩ መደረጋቸው፣ የታክስ እፎይታ ጊዜ መኖሩ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ አገራችን እየገቡ ነው። ኢትዮጰያ የምትከተለው ምቹ የኢንቨስትመንት መንገድና አንፃራዊ ሰላም በርካታ ባለሃብቶች በአሁኑ ሰዓት ወደ አገራችን እየመጡ ነው።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መንግስት አገሪቱንና ህዝቦቿን ከድህነት ከኋላቀርነት ለማላቀቅ የተከተለ አዲስ አቅጣጫ ተስፋ ሰጪ ዕድገት ማስመዝገብ የሚችል በመሆኑ የውጪው ዓለምና ባለሃብቶቻቸው ሳይቀሩ ምስክርነት እየሰጡ ይገኛሉ።

እንዲሁም ከአገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ ጋር ለመተሳሰር ፍላጎታቸውን እያሳዩ ነው። አገራችን ውስጥ ኢንቨስት አድርገው ራሳቸውንና አገራችንን ብሎም ህዝባችንን ለመጥቀም እየሰሩ ይገኛሉ። ወደፊትም ገብተው ለመስራት ከፍተኛ ምኞት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችም በርካታ ናቸው።

ዲያስፖራው ግን ኢትዮጵያ አገሩ ናት። እዚህ አገር ውስጥ የሚያፈሰው ገንዘብ ከራሱ ባለፈ ለአገሩና ለወገኑ ነው። ስለሆነም በሁሉም የኢንቨስትመንት መስኮች በመሳተፍ የሚወዳትን አገሩን መደገፍ ይኖርበታል። በዚህም ለአገሩ እድገት ከቀን ማኪያቶው ላይ እየቀነሰ ከመስጠት ባሻገር ተደማሪ እሴት በሚያስገኙ የስራ መስኮች ላይ እየተሳተፈ የአገሩ መከታ መሆኑን ማስመስከር ይኖርበታል እላለሁ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy