Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ድሎቹ…

0 295

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ድሎቹ…

                                                      ይሁን ታፈረ

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በቅርቡ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዶ የተከናወኑ አበይት ጉዳዩችን ለህዝቡ አሳውቋል። በዚህም የጥልቅ ተሃድሶውን አፈፃፀምና ያስገኘውን ውጤት በተለመደው ድርጅታዊ ባህል፣ ዴሞክራሲያዊነትን በተላበሰ እና በሰከነ አግባብ በጥልቀት መፈተሹን ገልጿል።

ጥልቅ ተሃድሶውን ተከትሎ በደርጅቱ የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች የአመራር ፈጠራ ታክሎባቸው የለውጡ ቱርፋት የሆኑ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን፣ ከአሁን በፊት ውሳኔዎች እየተወሰኑ እና አቅጣጫዎች እየተቀመጡ በአፈፃፀም ድክመት ይታይባቸው የነበሩ ጉዳዮች በፍጥነት መፈፀም መጀመራቸውን፣ በዚህ አጭር ጊዜ ሊመዘገቡ ይችላሉ ተብለው የማይታሰቡ ድሎች መመዝገባቸውን እንዲሁም ድሎቹ የመላ የኢትዮጵያውያንን ድጋፍ ያስገኙና ተስፋውን ያለመለሙ ስለመሆናቸውም አንስቷል።

እርግጥም ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የአገራችንን ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዩች አስመልክቶ ያነሳቸውንም ነጥቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፈፀሙ ናቸው የሚባሉ አይደሉም። እጅግ የገዘፉ ናቸው።

ድርጅቱ በፖለቲካው መስክ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ታራሚዎችን  ከእስር  ከመፍታት ጀምሮ፣ የትጥቅ ትግል ያካሂዱ የነበሩ የተለያዩ ድርጅቶች የትጥቅ ትግላቸውን በማቆም በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ በውይይትና በድርድር መተማመን በመፍጠር ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ አድርጓል። ይህም አገራዊ መግባባትን የፈጠረ ነው።

ህዝቡ ያለ ምንም መሸማቀቅ ሃሳቡን በተለያየ መንገድ በነፃነት ማራመድ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩ፣ የመንግስትን ሚዲያን ጨምሮ በሌሎች ሚዲያዎችም የተለያዩ ሃሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት ሁኔታ መጀመሩ፣ ተዘግተው የነበሩ ድረ-ገፆች መከፈታቸው የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት አይነተኛ ሚና መጫወት ተችሏል።

ለዜጎች ዋጋና ክብር በመስጠት ከአገር ውስጥ ባሻገር በጎረቤት አገራትና በመካከለኛው
ምስራቅ ዜጎቻችን ከእስር እንዲፈቱና የነፃነት አየር እንዲተነፍሱ መደረጉ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብበዋል በሚል በተደጋጋሚ ከህዝብ ቅሬታ የሚቀርብባቸውን ህጎች ህዝብንና የመስኩን ባለሙያዎች ባሳተፈ መልኩ ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ መፐጠናከር ያለባቸው ስኬቶች ናቸው።

ከዚሁ ጎን ለጎን በሰብአዊ መብት አያያዝ አስከፊ ችግር የነበረባቸው የማረሚያ ቤቶችና ሌሎች የፀጥታና ህግ አስከባሪ ተቋማት ሪፎርም ለማድረግ አመራሮቹን ከመለወጥ ጀምሮ እየተሰራ ያለው ሥራ እንዲሁም ህዝብ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያነሳባቸው ተቋማት ኃላፊዎችን በማንሳት የተጀመረው የአመራር ሪፎርም የተቀመጠውን አቅጣጫ በመከተል የተፈፀሙ እና ውጤትም ያመጡ ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱት እርምጃዎች የህዝቡን ድጋፍ ያገኙ፣ እንደ አገር የመቀጠል ስጋት ውስጥ ገብተን ከነበረበት ተጨባጭ አደጋ በመውጣት አንፃራዊ ሰላም እንዲመጣ ያስቻሉ መሆናቸው ግልጽ ነው። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በነፃነት በአገራቸው ጉዳይ እንዲሳተፉ ማድረግ መቻሉም በድልነት የሚታይ ተግባር ነው።

ከአገር ውስጥ ስራ ባሻገር በድርጅቱ መሪነት በውጭ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች የተከናወኑ ስራዎች ሌላዎቹ የድል ተጠቃሾች ናቸው። የዲፕሎማሲው ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአገራችንን ተቀባይነትና ተደማጭነት ከፍ ማድረግ ችሏል።

በዋነኛነትም የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት በህዝብ ለህዝብ እና በጋራ ጥቅሞች ላይ ተመስርቶና ህዝባዊነትን ተላብሶ በፍጥነት እንዲሻሻል ለማድረግ የተወሰደው እርምጃ ተጠቃሽ ነው።

ከአገራችን ጋር ጎረቤት ከሆኑት አገራት ጋር ያለው ግንኙነት በዘላቂ የጋራ ጥቅሞች ላይ ተመስርቶ እንዲጠናከር የተደረገው ጥረትና ያስገኘው ውጤት እንዲሁም ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር የተደረጉ ግንኙነቶች የድሎቹ አካል ናቸው።

በተለይ በአገራችን እየመጣ ያለውን ለውጥ ተከትሎ ከአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እየተገኘ ያለው ድጋፍ በአለም አቀፍ ደረጃም ኢትዮጵያ ያላትን ተሰሚነት ያሳደገና በአጭር ጊዜ ውስጥ ይገኛል ተብሎ የማይታሰብ ድል ነው።

ድርጅቱ በአገራችን ውስጥ ማህበራዊ ሁኔታዎች እንዲስተካከሉም አድርጓል። በዚህም ለበርካታ አመታት በሁለት ሲኖዶሶች ተከፍላ የቆየችው የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የእስልምና እምነት ተከታዮችን መከፋፈል በማስቀረት ወደ አንድነት ለማምጣት ችሏል። ይህም አገራዊ አንድነትን መፍጠር የቻለ ተግባር ነው። ይህ ሁኔታም ለብሔራዊ መግባባት በር የሚከፈት ነው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ይታዩ የነበሩ የኢኮኖሚ ችግርን ለመፍታት በተደረገው ጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ድል መጎናጸፍ ተችሏል። በተለይ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለል የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰድ በመጀመራቸው ችግሩን ለማስታገስ ያስቻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ያም ሆኖ ችግሩን በመሰረታዊነት ለመፍታት የግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ምርትና ምርታማነት የማሳደግ ስራ ላይ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ርብርብ መስራት ያስፈልጋል። ድርጅቱም በዚህ ረገድ ዘላቂ አቅጣጫ በማስቀመጥ እየሰራ ነው።

ድርጅቱ የዋጋ ንረትን፣ ህገ ወጥ ንግድን፣ የተጓተቱ ሜጋ  ፕሮጀክቶች ማሳለጥንና ሌሎች አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት የመፍትሄ አማራጮች በመጠቀም ርብርብ ያደርጋል። ይህን ለመፈፀምም ህዝቡ ከጎኑ በመቆም ለውጡን በማስቀጠል ሂደት መረባረብ እንደሚኖርበት አስረድቷል።

እርግጥ ድርጅቱ ባለፉት አራት ወራቶች የፈፀማቸው ተግባራት ከፍተኛ ናቸው። በተለይ ለእነዚህ ድሎች መገኘት ዶክተር አብይና ድርጅታቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ምክንያቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ድሎችን ማስመዝገብ ከተቻለ፣ ወደፊት ምን ዓይነት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተስፋውን ከወዲሁ መገንዘብ ስለሚቻል ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy