Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጃዋር ሆይ!…

0 416

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጃዋር ሆይ!…

                                                    እምአዕላፍ ህሩይ

በሀገራችን በተፈጠረው የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ሳቢያ የተለያዩ የሚዲያ ባለሙያዎችና አክቲቪስቶች ወደ ሀገራቸው ገብተው ለመስራት ፍላጎት እያሳዩ ነው። አንዳንዶቹም ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል። ከእነዚህ ውስጥ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ (OMN) ስራ አስኪያጅና አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ አንዱ ነው። አቶ ጃዋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተገናኝቷል። ውይይቶችንም አካሂዷል።

በዚህ መሰረትም ይህ ፅሑፍ እስከተሰናዳበት ጊዜ ድረስ፤ በአምቦ ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርጓል። በባዶ እግሩ በመሄድም በዚያ አካባቢ ለውጡን ለማምጣት ሲታገሉ መስዋዕት ለሆኑ ወገኖች ያለውን ተምሳሌታዊ አክብሮት አሳይቷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድንም ጎብኝቷል። ወደ ባህር ዳር አቅንቶም ከክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይቷል። ከአክቲቪስቶች ጋር በመገናኘትም ስለሚያስበውና መሆን አለባቸው ብሎ ስለሚያምናቸው ጉዳዩችም ሃሳቡን አጋርቷል። ሃሳቦቹ ፍቅርን፣ ይቅርታንና አብሮነትንና ተቻችሎ መኖርን የሚያውጁ ናቸው። ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚያደረጁም ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።

እናም እኔ በበኩሌ አቶ ጃዋር የሚያራምዳቸውን ሃሳቦች ወድጃቸዋለሁ። እንዲያውም አስደማሚዎች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ከጥቂት ዓመታት በፊት አቶ ጀዋርን አሁን እየሰማሁ ባለሁት ድምፀ ቃና እና ምልከታ ፈፅሞ አስቤው አላውቅም ነበር። ምናልባትም ያኔ ሲነገር የነበረው ነገር አሉታዊ ጎኑ ብቻ ያመዝን ስለነበር ይሆናል።

አሁን ግን፤ ሃሳቡን፣ ፍላጎቱን፣ ምኞቱንና ለሀገሩ ያለውን ቀናዒ እሳቤ ስመለከት፤ አክቲቪስት ጃዋር ማን እንደሆነና ምን እንደሚያስብ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ማንኛውም ሰው የሚመዘነው በሚናገራቸው ነገሮች እንደመሆኑ መጠን፤ እርሱንም ከተናገራቸውና ሊያደርጋቸው ከሻታቸው ፍላጎቶቹ በመነሳት ምን ያህል ለአንድነት የሚቆረቆር እንደሆነ ለመገንዘብ የሚከብድ አይመስለኝም። እናም ሃሳቦቹ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ስለሆኑ ‘ጃዋር ሆይ!…ቀጥልበት!’ የሚያሰኙ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። አዎ! ‘ጃዋር ሆይ! የምታስባቸው ነገሮች በጎዎችና ለሀገር የሚጠቅሙ በመሆናቸው ተጠናክረው ይቀጥሉ’ ማለት የሚገባ ይመስለኛል።    

አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር በቤተ መንግስት ተጋነኝቶ ተወያይቷል። በውይይቱም መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች በጣም አስፈላጊና የሚያበረታቱ መሆናቸውን ተናግሯል። የተጀመረው የለውጥ ጉዞም በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መጠናከር እንዳለበት ያምናል። ለለውጡ መገኘት ከፍተኛ ትግል መደረጉን የሚናገረው አቶ ጃዋር፤ “የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከየሀገሩ በማስገባት በምርጫ ህጉና አካሄዱ ላይ ስምምነት ካልተደረሰ እንደገና ወደ ግጭት መግባታችን አይቀርም” የሚል አቋም አለው። ይህን ለመግታት ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች አብረው ቁጭ ብለው በፍጥነት የምርጫ ህጉን ሊያስማማ በሚችል መልኩ ማሻሻልና ከላይ እስከ ታች ታማኝነት ያለው የምርጫ ቦርድን መገንባት ትልቅ ስራቸው ሊሆን እንደሚገባም ያስረዳል።

እርሱም በበኩሉ ቢሆን፤ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና ለውጡ እንዲጠናከር የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቋል። ይህ ሃሳቡ “ይበል!” የሚያሰኝ ነው። ምክንያቱም ማንኛውም ሀገራችንን ወደ ሰላም ጎዳና የሚወስዳት ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ዓላማው ሰላምንና መረጋጋትን እስካመጣ ድረስ ሁሉም የሀገራችን ህዝብ ስለሚቀበለው ነው። ሰላምን ሊያመጣ የሚችል አንድ ጠጠር መወርወር የቻለ ኢትዮጵያዊ ወገን ሊመሰገን ይገባል። ለዚህም ነው—‘ጃዋር ሆይ!…ሃሳብህ ቅቡል ነውና አጠናክረህ ቀጥለው’ የምለው።  

አቶ ጃዋር፤ በፕሬስና በፀረ ሽብር ህጎች እንዲሁም በበጎ አድራጎትና ማህበራት ህጎች የሚሰሙትን እሮሮዎችን ማስወገድ እንደሚገባም ያምናል። ለዚህም ህጎቹን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ባሳተፈ መልኩ መቀየር እንደሚገባ ያስረዳል። ይህም የሚወጡትን ህጎች ስራ ላይ ለመተርጎም የሚያስችል ነው። ርግጥ ማንኛውም በሀገሪቱ የሚወጣ ህግ መንግስትና የጉዳዩ ባለቤቶች በመመካከር ካረቀቁት ህጉ በምክክር የወጣ ስለሚሆን ለተግባራዊነቱ ሁሉም ይተጋል። ተጠያቂነትና የህግ የበላይነት ይረጋገጣል። እናም በዚህ ረገድ አቶ ጃዋር ያነሳቸው ሃሳቦች የህግ ልዕልናን ለማረጋገጥ የሚበጁ በመሆናቸው የሚመለከታቸው አካላት ግምት ውስጥ ያስገቧቸዋል ብዬ አስባለሁ።  

እርሱ በስራ አስኪያጅነት የሚመራው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ (OMN) የኦሮሞ ትግል ልሳን ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር ያስታወሰው አክቲቪስት ጃዋር፤ ከአሁን በኋላ የሚዲያ ተቋሙ ሙያውን መሰረት አድርጎ በአገር ውስጥና በቀጣናው ተምሳሌታዊ ሚዲያ ሆኖ ይሰራል ብሏል። በተለያዩ ቋንቋዎች ለሁሉም የሀገራችን ክፍል ተደራሽና ሙያዊ የሆነ የሚዲያ አገልግሎት ለመስጠት ዕቅድ መያዙንም አስታውቋል።

በእኔ እምነት፤ መንግስት በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሚዲያ ተቋማትና ወደ ሀገራቸው ገብተው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ መጎልበት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ባቀረበው ጥሪ መሰረት፤ “ኦ ኤም ኤን” አዲስ አበባ ላይ በቀዳሚነት ቅርንጫፍ መክፈቱ ተገቢና ትክክለኛ ርምጃ ነው። ምክንያቱም ሚዲያ እንደ አንድ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሳሪያ በተለይ ሀገራችን በምትገኝበት በአሁኑ የለውጥ ሂደት ላይ ገንቢ ሚና ሊጫወት ስለሚችል ነው።

እናም በአቶ ጀዋር የሚመራው “ኦ ኤም ኤን” በተለያዩ የሀገራችን ቋንቋዎች እንደ ሚዲያ ሀገራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት መወሰኑ ሊመሰገን ይገባል ባይ ነኝ። ሌሎች በውጭ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማትም የ“ኦ ኤም ኤን”ን አርአያነት ተከትለው ተመሳሳይ ርምጃ በመውሰድ ለሀገራቸው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ የበኩላቸውን ጠጠር እንደሚወረውሩ ተስፋ አደርጋለሁ። ስለሆነም በዚህ ረገድም የአቶ ጀዋር ሃሳብ ቅቡል ስለሆነ፤ ‘ጃዋር ሆይ!…አጠናክረህ ቀጥልበት’ እላለሁ።

አቶ ጃዋርና ቡድኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድንም ሲጎበኝ በድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ገለፃ ተደርጎለታል። ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካውያን ኩራት መሆኑን፣ የበረራ መዳረሻዎቹን፣ የአውሮፕላን ብዛትና በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች ድርሻ መግዛቱን አስረድተዋል። ለስኬቱ ምስጢርም፤ የቁጥጥር ስርዓቱ፣ የገንዘብ አያያዙና የባለሙያዎች ታታሪነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልፀዋል። አክቲቪስት ጀዋርም፤ አየር መንገዱ በቀጣይ ስኬታማ እንዲሆን የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት አስታውቋል። በእውነተ ‘በርታ!’ የሚያሰኝ እምነትና ፍላጎት ነው።

በእኔ እምነት፤ አቶ ጃዋር የሚዲያ ስራ አስኪያጅና ብዙ ተከታዮች ያሉት አክቲቪስት እንደመሆኑ መጠን፤ አየር መንገዳችን ያለውን አቅምና አሰራር በማስተዋወቅ አሁን የሚገኝበትን ስኬት ይበልጥ በማጎልበት ድርሻ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። እናም በዚህ ረገድ የሚያደርገው ድጋፍ ጠንካራ እንደሚሆን ተስፋ አድርጋለሁ። ጥረቱም በዜጎች ሊበረታታና ‘ጃዋር ሆይ!…ቀጥልበት!’ ሊባል የሚገባ ይመስለኛል።

የአቶ ጃዋር ቡድን ሌላኛው ጉብኝት በአማራ ክልል ነበር—በባህር ዳር ከተማ። በዚያም ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና ከኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንዲሁም ከከተማው ወጣቶችና ከተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎች ጋር ተገናኝቷል። ውይይትም አድርጓል። አቶ ገዱ ጃዋርን “ከፍተኛ የፖለቲካ ግለት በነበረበት ወቅት አጋርነቱን ያሳየ” ሲሉ ገልፀውታል። ጃዋርም በበኩሉ፤ ወደ አማራ ክልል ያቀናው ሀገሪቱ እንዳትፈርስ ላደረጉት አስተዋፅኦ ለማመስገን እንደሆነ ተናግሯል— የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ለአገሪቱ ምሰሶ በመሆናቸው የላቀ ትብብራቸው ኢትዮጵያን እንደሚያሳድግ ጭምር በመግለፅ።

በእኔ እምነት ይህ የአቶ ጃዋር ንግግር፤ ለለውጥ ተባብሮ በመስራትና አብሮ በመደመር ሀገርን ከብተና መታደግ እንደሚቻል የሚያሳይ ሁነኛ ማረጋገጫ ነው። ርግጥ ስለ ሀገር ከውስጥ በመነጨ የቅንነት ስሜት የሚሰነዘሩ ሃሳቦች ልበ ግቡ ናቸው። ኢትዮጵያዊነት መዓዛና ጣዕም ያላቸውም ናቸው።

ሃሳቦቹ በኦሮሞም በአማራም ይሁን በሌላው የሀገሬ ህዝብ ዘንድ ወደ ውስጥ ሰርገው በመግባት አብሮነትን የሚያስታውሱና ለቀጣይ የጋራ ስራ ያነሳሳሉ። ነገን ከወዲሁ እንድንተልም ያደርጋሉ። እናም ተገቢውን አክብሮት ልንቸራቸው ይገባል፤ ያስፈልጋልም። ‘ጃዋር ሆይ!…በርታ!’ በማለት የሃሳብ ደርዞቹ ወደ ሌሎች የሀገራችን ክፍሎችም እንዲንሸራሸሩ ድጋፍ ማድረግ የሚኖርብን ይመስለኛል።

ርግጥ በአንዳንድ ማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ፤ አቶ ጀዋር ወደ ትግራይ ክልል በማቅናት ከክልሉ መንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚነጋገርና ለእውነተኛ እርቅ መስራት እንደሚፈልግ ገልጿል። የአሸንዳ (ሻደይ) በዓልን ለመታደም እንደሚፈልግም ሰምቻለሁ። ጊዜው የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የእርቅና የመደመር በመሆኑ ቅዱስ ሃሳብ ነው። የበደል ዘመን አክትሟልና የተጣላም ካለ ይታረቅ። ዛሬ ይቅር ባይነት በሀገራችን እየነገሰ ነው። ሊጠናከር ይገባል። ሆኖም አሁንም ቂም በቀልና ቁርሾ ዳግም እንዳይመለስ በሩን ጥርቅም አድርጎ መዝጋት ያስፈልጋል። እነዚህን ወቅታዊ ጉዳዩች ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል የእኔ ትውልድ የቤት ስራ ነው። እናም የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በማጠናከር ኢትዮጵያዊነትን ማጎልበት ጊዜው የሚጠይቀው ወቅታዊ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብና ለተግባራዊነቱም መትጋት የኢትዮጰያዊነት መገለጫ ሊሆን ይገባል እላለሁ።

ያም ሆኖ እንዳልኩት የአቶ ጀዋር ሃሳብ የተቀደሰ ነው። ይቅርታና እርቅ እንዲሁም የተሳሳቱ ጉዳዩችን በማረም በኢትዮጵያዊነት የአንድነት ጥላ ስር በመደመር መተኪያ ለሌላት ለአንዲት ሀገራችን በጋራ ዘብ እንድንቆም ያደርገናልም ብዬ አስባለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአንድ ወቅት “አንድ ስንሆን ሁሉም ያስከብረናል” እንዳሉት፤ አንድነታችን ውስጥ ነፋስ እንዳይገባ ልንጠነቀቅ ይገባል። እናም አቶ ጃዋር እስካሁን ድረስ ያነሳቸው ሃሳቦች ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩና ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎለብቱ እንዲሁም ሚዛን የሚደፉ በመሆናቸው ‘ጃዋር ሆይ!…አጠናክረህ ቀጥላቸው’ ሊባሉ የሚገባቸው ናቸው። ጃዋር

 

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy