ጥቅመኛ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች…
ወንድይራድ ሃብተየስ
ሁሌም ለውጥ በጥቂቶች ይጀመርና ብዙሃኑን ማስከተል የሚችል ከሆነ በአጭር ጊዜ የታሰበውን ግብ መምታት ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የአገራችን ለውጥ ስኬታማ የሚሆነው በ“መደመር” ስሌት የምንጓዝ ከሆነ መሆኑን አበክረው ይናገራሉ። እንደእኔ እንደኔ “መደመር” አዎንታዊነትን የሚያመላክት ቃል ነው። እኔ እንደተረዳሁት “መደመር” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል እያንዳንዱ ዜጋ በቅንነትና ታማኝነት የሚንቀሳቀስ ከሆነ ለአገራቸው ዕድገትና ሰላም አስተዋጽዖ ማበርከት ይችላል የሚል መልዕክት ያለው ነው። አሁን ላይ በአገራችን ያለውን ለውጥ በተለያየ ምክንያት የማይደግፉ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ይሁንና ይህ አይነት አካሄድ እንደእኔ ጤናማ እንደሆነ ይሰማኛል። የሃሳብ ልዩነት ጥፋት የሚሆነው ልዩነትን በሃይል ለማራመድ ሲሞከር ነው።
ባለፉት 27 ዓመታት መንግስት፣ ፓርቲና ህዝብ ተቀላቅለው ተመልክተናል። ይህን አይነት አካሄድም ይመስለኛል ዛሬ ላይ ለመደመር ፖለቲካ እንቅፋት እየፈጠረ የሚገኘው። ኢህአዴግ ባለፉት ሁለት ዓስርት ዓመታት ከገዥ ፓርቲነትና መንግስትነት አልፎ እንደአገር እንዲቆጠር አድርጎ በመስራቱ በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት አገራችን ስትታመስ፤ በርካታ ዜጎች በማያውቁት ነገር ዕዳ ከፋይ ሆነው ተመልክተናል። ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገራችን በተከሰተው ሁከት ሳቢያ በርካታ ዜጎች አገራችን ልትፈርስ ነው የሚል ስጋት አድሮባቸው እንደነበር ይታወሳል። ዛሬ ላይ ሁሉም ነገሮች ተስተካክለዋል ባይባልም ተስፋ ሰጪ ነገሮችን ግን መመልከት ችለናል።
አንዳንድ ጉምቱ የሚባሉ የፓርቲ አመራሮች ሆን ብለው ይሆን ሳያውቁት ለውጡን ለማደናቀፍ የሚያደርጉት ነገር አግባብነት የጎደለው እንደሆነ ይሰማኛል። ለአብነት ያክል ፓርቲና ህዝብ አንድ እንደሆኑ አድርገው በሚዲያ ሲናገሩ አድምጠናል። ይህን አይነት አካሄድ ሊስተካከል የሚገባው ጉዳይ ይመስለኛል። በእኔ ዕይታ ህወሃትና የትግራይ ህዝብ፣ ብአዴንና የአማራ ህዝብ፣ ኦህዴድና የኦሮሞ ህዝብ፣ ደህዴንና የደቡብ ህዝቦች፣ ወዘተ አንድ ሊሆኑ ከቶ አይችሉም። መንግስትና አገር፤ ፓርቲና ህዝብ ለየቅል ናቸው።
በእርግጥ በትግል ወቅት የትግራይ ህዝብ ከህወሃት ጎን ተሰልፎ ከሌላው ህዝብ የበለጠ መስዋዕትነት መክፈሉ የሚካድ አይደለም። ይሁንና የትግራይ ህዝብና ህወሃት አንድ ናቸው ማለት ግን አይደለም። ፓርቲንና ህዝብን ከቶ አንድ ሊያደርግ የሚችል ነገር እስካሁን በዓለማችን አልተመለከትንም። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በአንድ መድረክ ላይ “ህወሃትና የትግራይ ህዝብ አንድ አይደሉም፤ ህብረተሰቡ ለያይቶ ሊመለከት ይገባል” ሲሉ የተናገሩትን ቃል አንዳንድ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ከአውድ ውጪ የተጠቀሙበት ይመስለኛል። እንደእኔ አረዳድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሃትንና የትግራይ ህዝብን የገለጹበት መንገድ ተገቢና ትክክለኛ ነው ባይ ነኝ።
እንደእኔ እንደእኔ ፓርቲና ህዝብ አንድ ሊሆኑ ከማይችሉበት የመጀመሪያው አሳማኝ ምክንያት መካከል ፓርቲ ይሳሳታል፣ ፓርቲ ይመጣል በተመሳሳይም ይሄዳል፤ ታዲያ ፓርቲው በሚፈጽማቸው ስህተትና ጥፋት ወደ ህዝብ እንዳይተላለፍና በህዝቦች መካከል ቅሬታ እንዳያስከትል ፓርቲና ህዝብ አንድ ናቸው ማለት ተገቢነት የጎደለው አካሄድ ነው። ለዚህም ይመስለኛል ፓርቲና ህዝብ ለይተን እንይ እየተባለ በከፍተኛ ሃላፊዎች ጭምር እየተገለጸ ያለው። ኢህአዴግ የአራት ፓርቲዎች ግንባር ነው። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት እነዚህ እህት ድርጅቶች ይብዛም ይነስም በአገራችን ለተመዘገቡት ልማት ብቻ ሳይሆን ድክመትም የየራሳቸው አስተዋጽዖ እንደነበራቸው አምነን ልንቀበል ይገባል። አሁን ላይ በአገራችን ለሚስተዋሉ ችግሮች ወይም ድክመቶች ሁሉ ለህወሃት ጠቅልሎ መስጠት ተገቢ አይደለም። እንደእኔ ብአዴንም፣ ኦህዴድም ሆነ ደህዴን ለአገራችን ችግሮች የነበራቸው አስተዋጽዖ ከህወሃት የሚተናነስ አይደለም።
ታዲያ አንዳንድ የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች የትግራይ ህዝብን ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ “ህወሃትና የትግራይ ህዝብ አንድ ናቸው” በማለት ህብረተሰቡን የማይገባ ነገር ውስጥ ለመክተት ሙከራ ሲያደርጉ ተመልክተናል። ይህን ስህተት በቅርቡ ህውሃት ያወጣውን መግለጫ ውስጥም ተመልክቼው አግራሞትን ጭሮብኛል። በእኔ አረዳድ ህወሃት የህዝብን ድጋፍ በአግባብ መንገድ ተጉዞ ማግኘት ይኖርበታል እንጂ በእንዲህ ያለ ስሜት ኮርኳሪ በሆነ መንገድ መሆን የለበትም። ነገ በአገራችን ምርጫ ሲካሄድ ህወሃት ከአረና ጋር ተወዳድሮ ላያሸንፍ የሚችልባቸው ሁኔታዎች ቢፈጠር ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይደለም። በበርካታ ምክንያቶች ፓርቲዎች ይመሰረታሉ፤ እንዲሁም ይፈርሳሉ፤ መንግስታት ይመጣሉ በተመሳሳይ ይሄዳሉ፤ ህዝብ ግን ሁሌም ይኖራል። በዚህ ዕውነታ ላይ ስንመሰረት ህዝብና ፓርቲ እንዲሁም ህዝብና መንግስት አንድ ሊሆኑ እንደማይችሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
እነዚህ ሃይሎች ይህን አይነት አካሄድን የተጠቀሙት ሁኔታው ሳይገባቸው ቀርቶ ነው ብዬ አላምንም። አንድም የትግራይን ህዝብ ከለላ አድርገው ወደ ስልጣን ለመመለስ ወይም ከሌላው የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች የከፋ በደል በመፈጸማቸው ሳቢያ በትግራይ ህዝብ ከለላ ከህግ የበላይነት ለማምለጥ ሲሉ ይመስለኛል። ህወሃት በትግራይ ክልል ተመሰረተ እንጂ ሁሉንም ትግራይዋን ይወክላል ማለት አይደለም፤ በተመሳሳይ ብአዴንም፣ ኦህዴድም እንደዛው ናቸው። ከላይ ባነሳኋቸው ምክንያቶች ሳቢያ ህዝብና ድርጅት አንድ ሊሆኑ አይችሉም። እውነት እንነጋገር ከተባለ ህወሃት ላጠፋው ጥፋት አንድ ተራ ትግራውያን ዕዳ ከፋይ መሆን የለበትም። ቀኑን ሙሉ በርካታ ዕቃ ተሸክሞ በየሰፈሩ “ለዋጭ” ሲል የሚውል ተራ ደሃ የትግራይ ተወላጅ በህወሃት የተሳሳተ ስሌት ዋጋ የሚከፍልበት ምክንያት ሊኖር አይገባም።
ትግራዊያን ለዘመናት ከየትኛውም ህዝብ ጋር አብሮ የኖረ፤ ከየትኛውም ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ጋር ተጋብቶ ተዋልዷል፤ በሃይማኖትም ሆነ በባህል ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ፤ አብሮ መኖርን የሚያውቅ፤ እጅግ ታታሪ ህዝብ ነው። ህወሃት በተሳሳተ መንገድ ድጋፍ የሚፈልግ ከሆነ ይህን ህዝብ ለጥቃት እንዲጋለጥ ያደርገዋል ባይ ነኝ። እኔ ህወሃት እንደሌሎቹ የኢህአዴግ ፓርቲዎች ያጠፋው ጥፋት ካለ ሊጠየቅ ይችላል እንጂ ደሃ ትግራውያን ዕደ ከፋይ መሆን የለባቸውም። በእርግጥ ይህ የእኔ ዕይታ ነው። ትግራዊያን ምርጫቸው የእነርሱና የእነርሱ ብቻ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የትግራይን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ግለሰቦች በተለያየ ሚዲያዎች ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ የተናገሩትን ነገር በማጣመም ሌላ ትርግም ለመስጠት ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። እስኪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን ቃል በቃል እንመልከተው፤ “የትግራይን ሕዝብና ሕወሐትን ነጣጥላችሁ እዩ፤ ሕወሐት ባጠፋው የትግራይ ሕዝብ ሊሰደብ ንብረቱ ሊወድም ሕይወቱን ሊያጣ አይገባውም እውነተኛ የትግራይን ሕዝብ ኑሮ ማየት ከፈለጋችሁ ገጠር ሔዳችሁ እዩ” ማለቱ ነው። እዚህ ዐረፍተ ነገር ውስጥ እስኪ የትኛው ሃረግ ወይም ቃል ነው ስህተት? ወይም ደግሞ ሌላ ትርጉም ሊያሰጥ የሚችለው አገላለጽ?
ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከወጡ ጀምሮ አየሰሩ ካሉት ዋነኛ ስራዎች መካከል ቂም በቀልን ማጥፋትና ይቅርታ፣ ምህረትን ፍቅርን፣ አንድነትንና መደመርን መስበክ ነው። ይህ ተግባር የትግራይ ህዝብን በየትኛው መስፈርት ይሆን የሚጎዳው? በፍትሃዊነት የትግራይ ህዝብ ለምን ይጎዳል? ፍቅር፣ ይቅርታን እርቅን መስበክ ክፋቱ እምኑ ላይ ነው? በኢትዮጵያ አንድነትና የመደመር ታሪክ ጉልህ ሚና ያለውና የኢትዮጵያ ሞተር ሲሉ ዶ/ር አብይ በመቀሌው መድረክ የገለጹት የትግራይ ሕዝብ ከወንድሞቹ አማራዎች፣ ኦሮሞዎች፣ ሶማሌዎች፣ አፋሮች፣ ሲዳማዎች፣ ወዘተ ቢደመር ከማንም በላይ የሚጠቅመው ለእርሱ ነው። በዚህ ዘመን መደመር ምን ያህል አቅም እንደሚፈጥር አውሮፓዊያኖችን መመልካት ይቻላል።