Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፍቅርን በተግባር

0 501

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፍቅርን በተግባር

ገናናው በቀለ

ግብር መክፈል ለራስ ነው። ግብር የከፈለ በግብር ከፋይነቱ ማግኘት የሚገባውን ማናቸውንም አገልግሎት ከመንግስት ሊጠይቅ ይችላል። ምክንያቱም የከፈለው ግብር የሚውለው ለዚህ ዓይነት ህዝባዊ ግልጋሎት የሚውል ስለሆነ ነው። በተለይ አሁን እንደ አገር ባለንበት የለውጥ ሂደት ውስጥ ግብር መክፈል የአገር ፍቅር ማሳያ ነው። በለውጥ ሂደቱ ውስጥ መደመርና ፍቅር ሲባል የአገርና የወገን ፍቅር በተግባር የሚገለጽበት አንዱ መንገድ በወቅቱ አገራዊ ግብርን በመክፈል ግዴታን መወጣት ነው።

አገሩንና ወገኑን የሚወድ የተደመረ ዜጋ ማድረግ ያለበት ይህንኑ ነው። አገሩን የሚያያፈቅር ማንኛውም ግለሰብ አገሩ ከእርሱ የምትጠብቀውን ግዴታ ያለ ጎትጓች  በወቅቱ መፈፀም ይኖርበታል። ግብርን መክፈል የአገርና የወገን ፍቅር እውነተኛ መገለጫ ነው። በመሆኑም ግብር ከፋዩች ሳይጠየቁ በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ይህን አገራዊ ፍቅራቸውን በተግባር ሊያሳዩ ይገባል።

ማናቸውንም ስራዎች ለህዝቡ የሚሰራ መንግስት እንዲኖር ዜጎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ግብራቸውን መክፈል ይኖርባቸዋል። ጉዳዩ የራስ ተጠቃሚነት በመሆኑም ግብርን በአገራዊ ፍቅር መክፈል የማንኛውም ዜጋ በውዴታ ላይ የተመሰረተ ግዴታ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት አቅዳለች። አገራችን በምታራምደው የፊሲካል ፖሊሲ መሰረት በ2012 ዓ.ም ፍፃሜውን የሚያገኘው የሁለተኛው የዕድገት እቅድ የወጪ በጀትን በሂደት በዋናነት በሀገር ውስጥ ገቢ በመሸፈንና የበጀት ጉድለት ዝቅተኛ እንዲሆን በማድረግ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ ሁኔታን ለማስፈን ያለመ ነው።

አሁን ባለንበት ሁኔታ የታክስ ገቢው እያደገ ከመጣው የመንግስት የወጪ ፍላጎት አንፃር ብዙ የሚቀረው መሆኑ አይታበይም። እንዲሁም የታክስ ገቢው ዕድገት እየሳየ ቢመጣም፣ ምጣኔ ሃብቱ ሊያመነጭ ከሚችለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሲተያይ የሚጠበቀውን ያህል መሻሻል ያሳየ ነው ለማለት አያስደፍርም።

ባለፉት ዓመታት የታክስ ገቢው ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ብዙም ለውጥ ማሳየት አልቻለም። እናም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የታክስ ገቢው ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 17 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል።

በተለይ ቀደም ባሉት ዓመታት ውስጥ በምንም ዓይነት የታክስ ስሌት ውስጥ ያልነበሩ ነጋዴዎችን ወደ ታክስ ስርዓቱ ማስገባት ይገባል። እንዲያውም ነጋዴው ራሱ ወደ ታክስ ስርዓቱ ውስጥ መግባት አለብኝ ብሎ በማመልከት ለአገሩ ያለውን ፍቅር ተደማሪ መሆኑን ማሳየት ይኖርበታል። መደመር አንዱ መገለጫው በእንዲህ ዓይነት መንፈስ ኢትዮጵያዊ ፍቅርን ማረጋገጥ ስለሆነ ነው።

በአሁኑ ሰዓት መንግስት የታክስ ስርዓቱን በጥብቅ ዲስፕሊን ተፈፃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው። በተጨማሪም የመንግስትን ፋይናንስ አጠቃቀም ውጤታማነትን ለማሳደግ፣ የተሟላ ግልፅነትና ተጠያቂነት ለማስፈን፣ ብክነትን ለማስወገድና የተያዘውን በጀት በቁጠባ ለመጠቀም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ስራው እየተከናወነ ነው። በዚህ ረገድ እያንዳንዱ የመንግስት አስፈፃሚ ተቋማት ፓርላማ ቀርበው ውል እንዲፈፅሙ የተደረገው ስራ ተጠቃሽ ይመስለኛል።

እርግጥ በመንግስት የሚከናወኑት ማናቸውም ስራዎች በዋነኛነት ህዝቡ በሚከፍለው ግብር ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ዜጎች ግብር ካልከፈሉ ምንም ዓይነት የልማት ስራዎችን ማከናወን አይቻልም። አይታሰብምም።

የተደመረ ዜጋ ግብሩን በወቅቱ በመክፈል ለአገሩ ያለውን ታማኝነትና ፈቅር ይገልጻል። ይህ ካልሆነ ዜጎች በአገራቸው መጠቀም አይችሉም። ስለሆነም ግብር መክፈል ለራስ ጠቀሜታ የሚውል መሆኑን በመገንዘብ ለአገራችን መደመራችንን በፍቅር ተግባራዊ ስራችን መግለጽ ይኖርብናል።

የመንግስት አገልግሎቶችን በጥራት ለማግኘትም ግብር ወሳኝ ሚና አለው። መንግስት ከዜጎቹ ተገቢውን ግብር ካገኘ ለህዝቡ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በዚያው ልክ ጥራታቸው፣ ፍትሐዊነታቸው፣ ዴሞክራሲያዊነታቸውና ሁሉን አቀፍነታቸው ከፍ ይላል።

ምናልባት በግብር አወሳሰኑ ላይ የተወሰነ ችግር ሊኖር ይችላል። ሆኖም በመነጋገር የማይፈታ ችግር የለም። የግብር ትመናው ቅሬታን ለማቅረብ የሚቻልበት አሰራር ያለው ነው። በመነጋገርና ቅሬታን በተገቢው መንገድ በማቅረብ መፍታት ይቻላል። የሚፈጠርን ችግር ለአገር ፍቅር ሲባልም በመቻቻል መንፈስ መፍታት ይገባል። ለአገሬ ተደምሬያለሁ የሚል ዜጋ ፍቅሩን አገሩን በመጥቀም መግለጽ ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችን በፈጣን እድገት ውስጥ ትገኛለች። መሰረተ ልማቶች፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችና ሌሎች የመንግስት ወጪዎች የሚሸፈኑት ከየትም በመጣ ገንዘብ ሳይሆን ህብረተሰቡ ከሚከፍለው ግብር ነው። መንግስት መልሶ ለህዝቡ ለሚሰጣቸው አገልግሎት የሚውሉ ናቸው።

በዓለም ላይ ግብር የማይከፈልበት ስራ የለም። ይህ እውነታ እንኳንስ በምድራዊ አሰራር ቀር በሃይማኖታዊም የሚታወቅ ነው። ምክንያቱም ከኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮቶች ውስጥ አንዱ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የኢየሱስን ለኢየሱስ” ተብሎ ስለተገለፀ ነው። በመሆኑም ግብር መክፈል ከምድራዊ አስተሳሰቡ በላይ ሃይማኖታዊ ተቀባይነትም ያለው ነው።

ይህን አስተሳሰብ በመያዝ ለአገር ያለንን ፍቅር በተግባር ማሳየት አለብን። አገራችንን የምንወድ ዜጎች የምትተዳደርበትን ግብር በጊዜው መክፈል ይጠበቅብናል። አንዳንድ ወገኖች ለአገራቸው ሲሉ መስዕዋት በሚሆኑበት ኢትዮጵያ ውስጥ ግብር መክፈል እጅግ የቀለለው ጉዳይ ነው። ለምንወዳት አገራችን እንኳንስ ገንዘባችንን ቀርቶ ህይወታችንም ልንሰጥ እንችላለንና። በመሆኑም ግብር መክፈል በአንድ በኩል ግዴታ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አገራችንንና ራሳችንን የምንጠቅምበት ፍቅር መገለጫ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

ይሁን እንጂ የሚሰበሰበውን ግብር በአግባቡ መጠቀም ይገባል። በተለይ ሙስናን መታገል ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሙስና ላይ ቀይ መስመር አስምረው ወደ ስራ ከገቡ ቆይቷል። በዚህም ውጤት ማምጣት እየተቻለ ነው።

ሙስናን ከምንጩ ለማድረቅ በመሬት አስተዳደር፣ በታክስ አስተዳደር፣ በመንግስት ግዥ አስተዳደር እንዲሁም በንግድ ውድድር ስርዓት የተጀመሩት የሪፎርም ስራዎችን የበለጠ ጥልቀት አግኝተው እየተከናወኑ ነው። ተቋማዊ ባህልም እንዲሆኑም እየተሰራ ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም የታክስ ስርዓቱን በማሻሻል ከታክስ የሚሰበሰበው ገቢ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የማድረግ ስራዎች በመተግበር ላይ ይገኛሉ።

እነዚህ እርጃዎች መንግስት ከህዝቡ የተሰበሰበው ግብር በትክክል ለታለመለት ዓላማ እንዲውሉ የሚያደርጉ ናቸው። ስለሆነም ይህን የመንግስት ዓላማ ዜጎች በውል ተረድተው ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል መደመራቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ግብር መክፈል አገራዊ ፍቅርን በተግባር የሚገልፁበት አንዱ ማረጋገጫ ስለሆነ ነው።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy