Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለኢኮኖሚው ስኬት

0 290

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለኢኮኖሚው ስኬት

                                                      ሶሪ ገመዳ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የውጭ ምንዛሬን ጉዳይ አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ጉዳዩን ከተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ እድገት ቃኝተውታል። በዚህም ኢኮኖሚው በሌሎች ዘርፎች ላይ በርካታ ለውጦችን ቢያመጣም፣ በውጭ ምንዛሬ በኩል ግን እጥረት ማጋጠሙን አስታውቀዋል።

ለእጥረቱም በምክንያትነት የውጭ ምንዛሬ ኮንትሮባንድ መኖሩ፣ የውጭ ምንዛሬ ግብዓቶች ከመንግስት ይልቅ ወደ ግለሰቦች እጅ መግባታቸው የዘርፉ ዋነኛ ችግር መሆኑ ተገልጿል። ስለሆነም ችግሩን ለመቅረፍ በቅንጅት እየተናበቡ መስራት እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ብሎም ከቱሪዝም የሚገኘውን ምንዛሬ ብሎም ከውጭ ወደ አገር ቤት የሚላከውን ገንዘብ በህግ አግባብ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ያስፈልጋል። ይህም የአገራችንን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሊፈታው የሚችልና ኢኮኖሚው ይበልጥ እንዲያንሰራራ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።

ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አንዱ የውጭ ምንዛሬ ችግርን መቅረፊያ መንገድ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተመሰረተው በግብርና ላይ ነው። ስለሆነም የአርሶ አደሩ የአመራረት ዘይቤን በመለወጥ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል። እናም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ማምረት ያስፈለጋል። ይህም አጠቃላይ የሀገሪቱን ምጣኔ ሃብት ዕድገት ከፍ እንዲል ያደርገዋል።

ባለፉት ዓመታት መንግሥት ግብርናውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተገንዝቦ ሲሰራ ቆይቷል። በያዝነው ሁለተኛው የልማት ዕቅድ ላይም በመጀመሪያው የዕቅድ ዓመት ላይ የተገኘውን አመርቂ ውጤት ይበልጥ አጎልብቶ ለመቀጠል እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ። በሁለተኛው የልማት ዕቅድ አጋማሽ ላይ የታዩ ለውጦችንና ክፍተቶችን በመገምገም ወደፊት የተሻለ ምርታማነትን ለመፍጠር እየተሰራ ነው።

በአገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ይህ ግብርናው ውጭ ከፍተኛ እምቅ ሃብት መሆኑ አይካድም። ይህን ሃብት በመጠቀም ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ይገባል።

በተለይ ለውጭ ገበያ የሚውሉ የሰብል ምርቶችን ለማሳደግ አዳዲስና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ለማስተዋወቅ ያስፈልጋል። እንዲሁም የአርሶ አደሩን ጉልበት የሚያግዙ የሚደግፉና ጉልበቱን ውጤታማ የሚያደርጉ መጠነኛና አነስተኛ የሜካናይዜሽን ስራዎች እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በስፋት በማምረት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን መቅረፍ ይቻላል።

ከቱሪዝም የሚገኝ ገቢን በህግ አግባብ መጠቀም ሌላኛው የውጭ ምንዛሬን ማጠናከሪያ መንገድ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ የሰዎች ፈጣንና ገደብ የሌለበት ህጋዊ ዝውውር እስካለ ድረስ ቱሪዝም ማደጉና መጎልበቱ አይቀርም።

ስምምነቱ ለየሀገራቱ አየር መንገድ ከሚያስገኘው ፋይዳ ባሻገር፤ ሀገሮች ለተጓዦች ባህላቸውን፣ ወጋቸውንና እሴቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። እናም አጋጣሚውን በተሻለ መንገድ መጠቀም የሚገባ ይመስለኛል። በተለይ በሀገራችን ውስጥ እያደገ የመጣውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በዚህ አጋጣሚ ይበልጥ ማሳደግ ይቻላል።

የቱሪዝም ዘርፍ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ያላቸውን የምርትና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በማስፋፋት፣ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ዘላቂ ልማትን በማስገኘት እና ድህነትን በማስወገድ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል።

ቱሪዝም ከሌሎች ዋና ዋና የኢኮኖሚና ማህበራዊ ሴክተሮች ፋይዳዎች ባልተናነሰ ሁኔታ በመልማት ላይ ለሚገኙትም አገሮች ዋና ጠላት የሆነውን ድህነት በማጥፋትና ልማትን በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው።

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት የቱሪዝም ኢንዱስትሪያችን የህዝቦች መገኛ የሆነችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ባህልን፣ ቅርስንና የተፈጥሮ መስህቦችን ቀጣይነት ባለው መልኩ በመጠበቅና በማልማት እንዲሁም የአገራችንን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማጎልበት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ብሎም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጎልበት ተገቢውን አስተዋፅኦ እንዲያበርክት እየተደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ባህላዊ እሴቶች፣ ተፈጥሯዊ መስህቦቻችንንና ቅርሶቻችንን በመመዝገብና በመጠበቅ እንዲሁም እንዲታወቁና እንዲለሙ በማድረግ ለህዝቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲውሉ መደረጉ ይታወቃል።

የሀገሪቱ ባህላዊ እሴቶች ጎልብተው በህዝቦች መካከል መተማመንና መከባበርን እንዲጠናከርና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲያግዙ የማድረግ ግብን ያነገበው ይህ ዘርፍ፤  ባህላዊና ተፈጥሯዊ መስህቦቻችንና ቅርሶቻችንን እንዲለሙ ብሎም ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል። ከዚህ ዘርፍ የሚገኘውን ገንዘብ ሳያባክኑ መጠቀምም ያስፈልጋል።

በተለይ በኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ በህጋዊ መንገድ በመጠቀም የውጭ ምንዛሬን እጥረት መፍታት ይቻላል። በዚህ ረገድ ዜጎችም የደርሻቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል። በመዲናችን የዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጉባኤዎች ሲካሄዱ በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘው ገንዘብ የምንዛሬ እጥረቱን የሚቀርፍ በመሆኑ ህጋዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል።

በተለያዩ መንገዶች ወደ አገር ቤት የሚገባው የውጭ ምንዛሬ በህጋዊ መንገድ እንዲመነዘር በማድረግና የውጭ ምንዛሬን ኮንትሮባንድ ስራዎች በመከላከል ኢኮኖሚውን ማንሰራራት ይቻላል። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ የሁለተኛው የልማት ዕቅድ ሶስተኛ ዓመት እየጀመረች ነው። ዕቅዱ የኢኮኖሚ ለውጥ የሚያመጣ ነው።

ዕቅዱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬንም ይጠይቃል። በሁሉም መስኮች ይህንን የምንዛሬ ችግር መቅረፍ አለብን። ምክንያቱም ዕቅዱን ለማሳካት ምንዛሬው ስለሚያስፈልገን ነው።

ስለሆነም ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ፣ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪውና ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ከሚገባው ገንዘብ የሚገኘውን ገቢ ህጋዊ በሆነ መንገድ እየተናበቡ በመጠቀም እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ኮንትሮባንድን በቁርጠኝነት በመከላከል ችግሩን በመቅረፍ ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ማድረግ ያስፈልጋል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy