ልዩ ትኩረት…
ገናናው በቀለ
በአሁኑ ሰዓት የክረምት መኸር ግብርና ሥራ እየተከናወነ ነው። በዚህ ስራ ሰብልን ከአውዳሚ ተባዮችና ሌሎች ችግሮች ለመከላከል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህም በመኸሩ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀውን የምርት መጠን በተሻለ ሁኔታ እንድናገኝ የሚያደርገን ነው።
እንደሚታወቀው የግብርና ስራ አገራዊ ኢኮኖሚን የሚያጠናክር ቀዳሚ ዘርፍ ነው። በተለይ በመኸር ሰብል የሚገኘው ከፍተኛ ምርት በአገራችን እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ነው። ስለሆነም በአሁን ሰዓት የሚመለከታቸው አካላትና አርሶ አደሮች ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት የወጡ መረጃዎች እንደሚያስረዱት፤ ከ2010/11 በአገር አቀፍ ደረጃ ከመኸር ምርት ለማግኘት የታሰበውን 370 ሚሊየን ኩንታል ነው። በአሁኑ ሰዓት የኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች ለ2010/11 የመኸር ምርት ቀደም ብለው ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የመኸር ምርት ከሚያመርቱት ክልሎች ውስጥ አንዱ የኦሮሚያ ክልል ነው። ክልሉ በመኸር ስድስት ሚሊየን ሄክታር መሬትን በሰብል በመሸፈን 203 ሚሊየን ኩንታል ለመሰብሰብ አቅዷል። እንዲሁም አራት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ለማዋል አቅዷል። ለአብዛኛው የመኸር አብቃይ አርሶ አደርም ማዳበሪያ አሰራጭቷል።
ሌላኛው የመኸር ምርት አምራች የሆነው የአማራ ክልል በመኸር ምርት አራት ነጥብ አራት ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን 110 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እቅድ ይዞ እየሰራ ነው። ይህን ለማሳካትም ከሶስት ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ማህበራት ማሰራጨቱን አስታውቋል። እጅግ የሚበዛውን የመኸር ምርት አብቃይ አርሶ አደር መድረስ እንደተቻለም ክልሉ አመልክቷል።
በአንዳንድ የክለሉ አካባቢዎች ከታየው የዝናብ መዘግየት ውጭ ያለው በአሁኑ ወቅት የሚታየው የዝናብ ስርጭት ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን ክልሉ አስታውቋል። ይህ ሁኔታም በክልሉ ከ157 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ በቆሎ እና ማሽላ የመሳሰሉ ሰብሎችን መሸፈን እንዳስቻለ ታውቋል።
ሌላኛው በመኸር ምርት እየሰራ ያለው የደቡብ ክልል ነው። ክልሉ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ሄክታር መሬትን በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን ከ38 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅዷል። ከዋና ዋና አዝዕርት ሰብሎች በተጨማሪ በሆልቲካልቸር ሰብሎች ከ55 ሚሊየን ኩንታል በላይ ለመሰብሰብም ዕቅድ ይዞ ስራውን እያሳለጠ ይገኛል።
የእነዚህና የሌሎች አካባቢዎች ድምር ውጤት በአገር አቀፍ ደረጃ በ2010/11 የመኸር እርሻ 370 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እንዲታወድ አድርጎታል። ይህን አገራዊ ምርት ለማገኘት መንግስት በአሁኑ ሰዓት 13 ነጥብ አምስት ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች አቅርቧል፤ ወደፊትም ያቀርባል። በመንግስት የቀረበውና የሚቀርበው ማዳበሪያ ከአምናው በአምስት ነጥብ አምስት ሚሊዩን ኩንታል ብልጫ ያለው መሆኑ ተመልክቷል።ይህም የበልግ ምርትንና ምርታማነትን ሊያሳድገው የሚችል ነው።
በአብዛኛዎቹ የመኸር አብቃይ አከባቢዎች የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት በመኖሩ በአሁኑ ወቅት ጥሩ የምርት ሁኔታ በእርሻ ማሳ ላይ መኖሩም ተገልጿል። አርሶ አደሩም በእሸትና በቡቃያ ደርጃ ያሉ ምርቶችን በአግባቡ የመጠበቅ፣ በየጊዜው ማሳውን የመፈተሽ ሰብሉ በአረም እንዳይጠቃ ክትትል ማድረጉም ተመልክቷል።
ተባዮችን በባህላዊ መንገድ መከላከል ከአቅም በላይ በሚሆንበት ወቅትም ፀረ- ተባይ ኬሚካሎችን በመርጨትና መከላከል ያስፈልጋል። በአጨዳና በምርት ስበሰባ ወቅትም ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። ምርቱ በታሳቢነት ከሚታወቀው የምርት ብክነት ባሻገር ሙሉ ለሙሉ ከተሰበሰበ የዋጋ ንረትን ሊከላከል ይችላል።
እርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የግብርናው ስራ በጥንቃቄ ከተያዘ ዘላቂ ለውጥ አምጭነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ግብርናው በአግባቡ ከተያዘ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ችግርንም ይቀርፋል። በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገራችን የሚታየውን የዋጋ ንረት መከላከል መቻሉ አጠያያቂ አይደለም።
በመሆኑም በግብርናው ስራ ላይ የሚደረጉ ጥረቶች የሁሉም አካል መሆን አለባቸው። ለመንግስት ወይም ለአርሶ አደሩ ብቻ የሚተው አይደለም። ሁሉም በኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀስ ይገባል። ይህ ሲሆንም ምርቱ የሚጠበቀውን ያሀል ይሆንና የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ጉልህ ሚና ይጫወታል። ግበርና የኢኮኖሚ ምሶሶ በመሆኑም የሁሉን ሃላፊነት የሚጠይቅ ስራ እየሆነ ነው።
በአሁኑ ሰዓት ምጣኔ ሃብታችን በፍጥነት እያደገ መሆኑ ይታወቃል። አሁን ባለንበት ሁኔታ በኤክስፖርትና በኢምፖርት መካከል ክፍተት መኖሩ ግልፅ ነው። ጉድለቱ እየሰፋ መጥቶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ማድረግ ግን ያስፈልጋል።
ባለፉት ዓመታት የታየው ደካማ የኤክስፖርት አፈፃፀም አስተማማኝ የውጪ ምንዛሬ ግኝት በማረጋገጥ ለፈጣን ዕድገታችን አስፈላጊ የሆኑ መሣሪያዎችና ዕቃዎች ከውጪ በማስገባት ዕድገታችን ለማስቀጠል አና ከውጪ ብድርና ዕርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ ትልቅ ማነቆ ሆኗል።
በግብርናም ምርታማነቱ መሻሻል ያሳየ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ባለመድረሱ ለኤክስፖርት የምናቀርባቸው የግብርና ውጤቶች በመጠን፣ በጥራትና በዓይነት ውሱን ናቸው ማለት ይቻላል። ታዲያ እነዚህን ሁኔታዎች መቀየር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ልዩ ትኩረት በማድረግ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀውን የመኸር ምርት ከወዲሁ በጥንቃቄ ማምረት ያስፈልጋል።
በክረምቱ መሰራት የሚገባቸው የግብርና ተግባሮች መከናወን ይኖርባቸዋል። ተባዩችና መጤ አረሞች ሰብሉን እንዳያበላሹት መጠንቀቅ ይገባል። ምንም እንኳን የግብርና ስራው የሁሉንም ወገኖች ድጋፍና ንቁ ክትትል የሚጠይቅ ቢሆንም፣ በተለይ ለአርሶ አደሩ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማቅረብና የግብዓቶቹን አጠቃቀም በመከታተል የመኸር ምርቱን ምርታማነት ማጎልበት ያስፈልጋል።
በየደረጃው የሚካሄዱ የሰብል ቁጥጥሮች ልዩ ትኩረት የሚሹ በመሆናቸው የቅርብ ክትትል ሊቸራቸው ይገባል። የመኸር ምርትን ምርታማነት ለማሳደግ መነሻው አሁን የምንገኝበት የክረምት ወቅት ስለሆነ በልዩ ትኩረት መንቀሳቀስ ወሳኝ ነው።