Artcles

ሕግና ሥርዓት ሲጠፋ ጭካኔ ይነግሳል

By Admin

August 15, 2018

ሕግና ሥርዓት ሲጠፋ ጭካኔ ይነግሳል

 

ስሜነህ

 

በሕግና በሥርዓት የማይተዳደር አገር የሥርዓተ አልበኞች መፈንጫ ይሆናል፡፡ በተለይ አገር የፖለቲካ ሽግግር ውስጥ ስትሆን ሕግና ሥርዓት ካልኖረ ለትርምስ በር ይከፈታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚሰሙት የግጭት፣ የሞትና የውድመት ዜናዎች እረፍት ይነሳሉ፡፡ ለዓመታት የተዘጉ እስር ቤቶች ተከፍተው እስረኞች ሲለቀቁ፣ በከባድ የጭቆና ቀንበር ውስጥ የቆዩ ሰዎች ዘና ሲሉ፣ በዝምታ ተሸብበው የነበሩ አንደበቶች መናገር ሲጀምሩ፣ ስለፍትሕና ነፃነት ሲጮኹ የነበሩ ተስፋ ሲሰንቁና አገርን ቀውስ ውስጥ የሚከቱ አጓጉል ድርጊቶች አደብ ሲገዙ ለውጥን ማስተናገድ አለመቻል ያስተዛዝባል፡፡

 

አገራችን ፍትህ፣ ነጻነትና ሰላም የሰፈኑባት፣ ዜጎችዋ በሰብዓዊነት የሚተሳሰቡት፣ በእህት/ወንድማማችነት የተሳሰሩባት እንድትሆን እንፈልጋለን፡፡ይህ ህልማችን እውን የሚሆነው ከእንቅልፋችን ነቅተን ስንሰራ ነው፡፡ መመኘታችን መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ምኞታችን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ መሥራት፣ መትጋት፣ መታገል ይጠበቅብናል፡፡ በመጀመሪያ ሥራችን ልናደርገው የሚገባንና ትግላችን ማተኮር ያለበት ራሳችን ላይ ነው፡፡ አመለካከቻችንን ከጥላቻ፣ ከቂም በቀል ስሜትና ከዘረኝነት ማጽዳት ይገባናል፡፡ በብሔር፣ በጾታ፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በኃይማኖት… ወዘተ ያሉንን ልዩነቶች እንደ በረከትነታቸው በፍቅር በማስተናገድ ከልዩነቶቹ የሚነሳ አለመግባባት ቢኖር እንኳ ከፍትህ እንጂ ከበደል ጋር ባለመተባበር ሞራላዊ እይታዎቻችንን ልናስተካክል ይገባል፡፡ ፍትህ ዋናው መርሃችን ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርና ክብር የሞራል መልህቃችን ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ሰርተን የማናገባድደው፣ ሁሌም ልፋት፣ ትግል የሚጠይቅ የእድሜ ዘመን ሁሉ የቤት ሥራ ነው፡፡

 

ሀገራችን በአሁሉ ወቅት ለደረሰችበት ምእራፍ በርካታ ትውልዶች መስዋእት ሆነዋል፡፡አዲሱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን እውን እንዲሆንም አእላፎች ተሰውተዋል፡፡ ታዳጊውን ዴሞክራሲያችንን ለማዳበር ግን ተጨማሪ የህይወትም ሆነ የአካል መስዋእትነት አያስፈልገንም፡፡ ባለፉት ዓመታት እንደመንግሥትም እንደ ዜጎችም ከዴሞክራሲ ባህላችን አለመዳበር ጋር ተያይዞ በታዩብን እጥረቶች በዜጎቻችን ህይወት እና በግልም በጋራም ንብረቶቻችን ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህንን ሁላችንም ማስቀረት እንችልና ይገባንም ነበር፡፡ በተለያየ ጊዜ፣ መስዋእትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎችና ፖለቲከኛች፤ በቅጡ ሳይቦርቁ ህይወታቸውን ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች፤ ለስነልቦናዊና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ እንዲሁም ሰላም ለማስከበርና ህገመንግሥታዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ሲንቀሳቀሱ ህይወታቸውን ላጡ የፀጥታ ኃይሎች አባላት ለከፈሉት መስዋእትነት ያለኝን አድናቆትና አክብሮት ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ለተፈጠሩ ችግሮች እልባት በማበጀት ህዝባችንን እንደምንክስም ጭምር በዚሁ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ፡፡

 

በአገር ውስጥም ሆነ በስደት ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ የትናንትናውን ምእራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምእራፍ እንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ይህ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ መጋቢት 24 2010 በበአለ ሲመታቸው ያስተላለፉት መጪው ጊዜ በኢትዮጵያችን የፍቅርና የይቅርታ ጊዜ ነው አዋጅ ወይም ሃገራዊ መልእክት ነው።

 

የተደመሩትም ሆነ ካልቀነስን የሚሉቱ ይህ መልእክት በአግባቡ የገባቸው አይመስልም። ኢትዮጵያ ያሉባት ችግሮች ተዘርዝረው አያልቁም፡፡ አንዱ ከሌላው የበለጠ በደል ደርሶብኛል ብሎ ችግሮችን አግዝፎ ቢያቀርብ፣ ሌላውም ከእሱ የበለጠ ሰቆቃ እንዳለው መረዳት የቻለ ሰው ያለም በማይመስል ደረጃ የህግ የበላይነት አደጋ ላይ እየወደቀ ነው፡፡ ወደ ኋላ እየተጎተቱ ወደ ፊት መራመድ እንደማይቻለው ሁሉ፣ ለውጥን እየተመኙ ከለውጥ በተቀራኒ መሽከርከርም ፋይዳ የለውም፡፡ ይህ ዘመን ብዙ ጥያቄዎች አሉት፡፡ እያንዳንዱ ሰው ራሱን በግሉ ቢጠይቅ ለአገር ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ጀምሮ እስከ የገዛ ራሱ አኗኗር ድረስ ለምን? እንዴት? የት? መቼ?…የመሳሰሉ ጥያቄዎች አሉበት፡፡ የዘመኑ ምጡቅ አስተሳሰብ የሚመራውም በዚህ መንገድ ነው፡፡ ከመንገድ ላይ እንደተቆረጠ መፋቂያ ያገኙትን መረጃ ሳይተነትኑ መጉረስ ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ መተቸትና መሞገት የሚቻለው በተጣራ መረጃ ላይ መመሥረት ሲቻል ነው፡፡ ዘመኑ ደግሞ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የበለፀገ ስለሆነ ያግዛል፡፡ አገር ለማደግ ከሚያስፈልጓት ሁነኛ መሣሪያዎች መካከል ደግሞ አንዱ መረጃ ነው፡፡ የተጣራ መረጃ ለአገር ፍቱን መድኃኒት ሲሆን፣ ያልተጣራው መርዝ ግን ሃገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት ነው፡፡  

 

ለውጡ ያልተዋጠላቸው ሌቦች በየትኛውም አካባቢ የሚፈጥሩትን ግጭት በአስተማማኝ ሁኔታ መቆጣጠር የሚቻለው ሕብረተሰቡ የሰላም ዘብ ሆኖ ከጸጥታ ሃይሉ ጎን ተሰልፎ ስልህግ የበላይነት ሲሰራ ብቻ መሆኑም የተዘነጋ ይመስላል። በአንዳንድ አካባቢዎች እየታየ ያለው ስርዓት አልበኝነትና የህግ ጥሰት ይህንኑ የሚያጠይቅ ነው።  አመራሮች ይነሱልን በሚል ቤቶቻቸውን፣ የመንግስት ተቋማትን ማውደምና መዝረፍ የለየለት ሥርዓተ አልበኝነት እና ማንንም የማይጠቅም፣ የህብረተሰቡንም ጥያቄ ሊመልስ የማይችል ነው። ማንኛውም ጥያቄ እና ችግር ሊፈታ የሚችለው በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ብቻ መሆኑን የዘነጋ መደመር ብሎ ነገር የማይታሰብ ነው። በየትኛውም የአገራችን ክፍል እያስተዋልን ያለው የስርዓት አልበኝነት ተግባር ለውጥ አደናቃፊ ነው። በተለይ  የለውጥ ኃይል የሆነው ወጣቱ በተሳሳተ እና በህገወጥ መንገድ በመሄድ የለውጡ አደናቃፊዎች ዓላማ አስፈጻሚ ሆኖ ብዙ ጉዳት እያደረሰ ነው።

 

የአገርን ሰላምና የሕዝብን ደኅንነት ችግር ውስጥ የሚከቱ ብሔር ተኮር ጥቃቶች ሲፈጸሙ እንዳላዩ ሆኖ ማለፍ አይቻልም፡፡ ሕግና ሥርዓት እየተናዱ በየቦታው ጉልበተኞችና እንዳሻቸው አዳሪዎች ሲፈነጩ ዝም ማለት፣ ራስን ለሌላ ዙር ቀውስ ማዘጋጀት እንደሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በረባ ባልረባው ምክንያት የሚፈጠር የግለሰብ ፀብ ሳይቀር የብሔር ገጽታ እየተላበሰ በየቀኑ የግድያ ዜና መስማት ያሳምማል፡፡ ለውጡን በይቅር ባይነትና በፍቅር መቀበላቸውን በአደባባይ የሚገልጹ ሰዎች ሳይቀሩ፣ ጥላቻና ቂማቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ እነሱን እንደ አርዓያ የሚከተሉ ወጣቶች ደግሞ አንድ ነገር ሲፈጠር ሕገወጥ ድርጊት ውስጥ ይሰማራሉ፡፡ ፀጥታ ማስከበር የሚገባቸው ተቋማትም ሆኑ አመራሮች ከሕገወጦች ጋር መፋጠጥ ስለማይፈልጉ አሳዛኝ ጉዳቶች እየደረሱ ነው፡፡  

 

የቂምና የቁርሾ ሕመም አገር እንደሚያጠፋ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ለማጥፋትና የበላይነት ለማግኘት የሚደረገው ሩጫ የፖለቲካው ደዌ ማሳያ ነው፡፡ አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት እርም በሆነበት ልማዳዊ አኗኗር ላይ፣ ብልሹው ፖለቲካ ተጨምሮበት አገርና ሕዝብ ብዙ መከራ አይተዋል፡፡ ለአገሩ ላቡን ጠብ አድርጎ የሠራ ትሁት ሰው በአደባባይ በጥይት መገደሉ በራሱ አሳፋሪ እና የሚያሳምም ቢሆንም አሳሳቢው እና ሃገርን አደጋ ላይ የሚጥለው መረጃና ማስረጃ ተጠናቅሮ በይፋ የገዳዩ ማንነት ሳይረጋገጥ የደም ፍላት ዕርምጃ በተገኘው ላይ ለመውሰድ ያዙኝ ልቀቁኝን ማየት ነው።  የሕግ የበላይነት ልዕልና ካላገኘ ጦሱ የሚተርፈው ለሕዝብ እንደሆነ ከዚህ በላይ አስረጅ የለም፡፡ ፍትሕ የሚሰፍነው የሕግ የበላይነት ሲረጋገጥ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት መኖሩ የሚበጀውም ሕገወጥነትን ለመከላከል ይሆናል ማለት ነው፡፡

 

የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ሕግና ሥርዓት ሲያስከብሩ የዜጎች ነፃነትና መብት ዋስትና ያገኛሉ፡፡ ማንም ሰው የመሰለውን ሐሳብ በነፃነት መግለጽ አለበት፡፡ የፈለገውን የመደገፍ ያልፈለገውን የመቃወም መብቱም እንዲሁ፡፡ በመላ አገሪቱ በፈለገው ሥፍራ የመኖር፣ የመዘዋወር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብት በሕግ የተረጋገጠለት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ በማንነቱም ሆነ በእምነቱ ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስበት የሚከላከልለት ሕግ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ዋስትና የሰጠውን ሕግ ተማምኖ በመላ አገሪቱ ተሠራጭቶ የሚኖር ኢትዮጵያዊ በሕገወጦች ምክንያት ከቀዬው ሲፈናቀል፣ ሲዘረፍ፣ ሲገደልና ሲሳደድ ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገድለው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉበትን የቅርብ ጊዜ ክስተት ብቻ ማውሳት ተገቢ ነው፡፡ መብራት ለምን ጠፋብን ተብሎ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው በማይመለከታቸው ጉዳይ ሲገደሉ ማየት ያሳፍራል። አንድ ችግር ባጋጠመ ቁጥር የገዛ ወገንን የጥቃት ሰለባ ማድረግ መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት ካልተከበረ ከፊታችን ከፍ ያለ አደጋ ይጠብቀናል፡፡

 

ሰላም ከሌለ ልማትና ዕድገት አይታሰቡም፡፡ ሰላም ከሌለ እንኳን ልማት አገርም አትኖርም፡፡ ይህ ሕዝብ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲቀባበል የዘለቀው አብሮ በሰላም በመኖር ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ማንነትና እምነት ሳይገድቡት ተጋብቶና ተዋልዶ ትስስር ፈጥሯል፡፡ ይህ የሚያኮራ የጋራ እሴቱ በዚህ ዘመን በሕገወጦች ሲደፈር በሕግ መባል አለበት፡፡ መንግሥት ሕዝብን የማገልገል ኃላፊነቱ የሚጀምረው ደኅንነቱን በመጠበቅ ነው፡፡ የፀጥታና የፍትሕ አካላትም ወንጀል ሲፈጸም ተከታትሎ በመያዝ ተገቢው ፍትሕ እንዲሰፍን የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ ሕገወጥነት በሕጋዊነት ላይ የበላይነት እያገኘ ሲሄድ ውጤቱ ውድመት ነው፡፡