Artcles

“…መልሰን እንገነባቸዋለን!”

By Admin

August 21, 2018

“…መልሰን እንገነባቸዋለን!”

                                                         ደስታ ኃይሉ

በኢትዮጵያ ሱማሌም ይሁን በሌሎች አንዳንድ የአገራችን ክፍሎች በቅርቡ የታዩ ግጭቶች እና ወደፊትም ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶች አንዳችም የብሄር ወይም የኃይማኖት መልክ የላቸውም። ይልቁንም ከስልጣን አተያይ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ የአመራር ብልሹነት የተፈጠሩ ናቸው።

እርግጥ በአገራችን ውስጥ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ደረጃ አንዳችም ችግር የለም። ኢትዮጵያዊያን በታሪካቸው እርስ በስር የተሳሰሩ፣ የተዋለዱና ለዘመናት ተቻችለው የኖሩ ህዝቦች በመሆናቸው እንዲህ ዓይነት ችግር አያውቃቸውም። በሃይማኖት ደረጃም ተቻችለውና ተሳስበው የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የወደሙትን አብያተ ክርስቲያናት የክልሉ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ዑጋዞች “እኛው መልሰን እንገነባቸዋለን!” በማለት እያከናወኑት ያሉት ተግባር ይህን ሃቅ የሚያረጋግጥ ነው።

ምንም እንኳን በቅርቡ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በተፈጠረው ችግር የክልሉ ተወላጆች ሃብትና ንብረት ጭምር ያወደመ ቢሆንም፣ የክልሉ ተወላጆች ለወደሙት አብያተ ክርስቲያኖች ቅድሚያ መስጠታቸው በህዝቡ ውስጥ የብሄርም ይሁን የሃይማኖት ችግር አለመኖሩን የሚያሳይ ነው።  

እደሚታወቀው ሁሉ የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ከመልካም አስተዳደር ችግርና ከሙስና ጋር በተያያዘ ህዝቡን በማወያየት ዕርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሱ ነው። በክልሎች በተካሄዱ ሰፋፊ የውይይት መድረኮች ከህዝቡ በተገኘው ግብዓት መሠረት ጥፋት በፈፀሙ አመራሮች ላይ ዕርምጃ እየወሰደ ነው፤ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

እርምጃውን በጥልቀትና በስፋት በማስቀጠል የሰብዓዊ መብቶችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት መሥራት የግድ ነው። የህልውና ጉዳይም ነው። ምክንያቱም ችግሩ በቅርቡ በተወሰኑ የሃገራችን አካባቢዎች ለሰላም እና መረገጋት መጥፋት መንስኤ ሆኖ ተስተውሏልና። ሰላም ደግሞ የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።

እርግጥ ከማናቸውም ችግሮች በስተጀርባ ግጭቶችን ተገን አድርገው የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳከት የሚጥሩ ኃይሎች መኖራቸው የግድ ነው። እነዚህ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለመቀልበስ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ ኃይሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሰላማችንን ለማድፍረስ፣ የዕድገት ግስጋሴያችንን ለማደናቀፍ ደፋ ቀና ማለታቸው በቅርቡ ተስተውሏል። ለስልጣን ባለቸው የተሳሳተ አተያይም ሀዝቦችን እርስ በእርስ ለማጋጨት ጥረት አድርገዋል። በኢትዮጵያ ሱማሌ የታየውም የኸው ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል።

በማንነት አሊያም በሃይማኖት ላይ የተመሰረተ ግጭት እንደ እኛ ያለና ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መርስቶ አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ለመገንት በሕገ መንግስቱ ላይ ሳይቀር ያሰፈረ ህዝብ ውስጥ ቦታ አይኖረውም። ብሔርን ለይቶ ማጋጨት ኢትዮጵያዊ ባህልና ጨዋነት አይደለም።

ስለሆነም አንድ በምጣኔ ሃብት የዳበረ ማህበረሰብ ለመገንባት በኢትዮጵያ ሶማሌ ውስጥ ያለው ዜጋ ኦሮሚያ አሊያም አማራ ወይም ትግራይ ክልል ሄዶ፣ በኦሮሚያ ክልል ያለውም በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በአማራ ወይም በትግራይ ክልል ሄዶ መስራት ይኖርበታል። ማንኛውም ዜጋ በየሄደበት በየትኛውም ክልል ተዘዋውሮ መስራት ህገ መንግስታዊ መብቱ ነው።

ህዝቦች በጋራ ሰላም የመሆን፣ በጋራ የመልማትና የማደግ፣ በጋራ ዴሞክራሲን ለማጎልበት እምነትና ፈቃዳቸውን በለውጥ ሂደቱ ላይ እያሳዩ ነው። በጥላቻና ላይ በተመሰረተ የጥቂት የስልጣን ጥመኞች ፍላጎት እውን ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም አስተሳሰቡ መቻቻል ባህሉ የሆነውን የአገራችንን ህዝብ ስለማይወክል ነው።

አሁን የምንገኝበት የለውጥ ወቅት አንድነትን ለሚያጠናክሩና መሰረቱን ለሚያሰፉ እንጂ ባለማወቅ ወይም ሆን ተብሎ በሚፈፀም አስተሳሰብ ሳቢያ የሚፈጠሩ ብሔር-ተኮር ግጭቶች ቦታ አይሰጥም።

የለውጡ ባለቤቶች የሆኑት ወጣቶች ኢትዮጰያዊነትን፣ አንድነትንና ፈቅርን እንዲሁም ነጻነትን ለማስፈን ነው። የራሳቸውን ነጻነት ለማምጣት የታገሉት የአገራችን ህዝቦች ስለ አንድነት እየዘመሩ የሌሎችን መሰረታዊ የእምነት ነጻነትን አይጋፉም።

ለውጡ በዝቦች መካከል ጠንካራ አንድነት የፈጠረ እንጂ በየትኛውም መስፈርት በህዝቦች መካካል መቃቃር እንዲፈጠር በር የሚከፍት አይደለም። ይህ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ህዝቡ የትኛውም ብሔረሰብ ከየትኛውም ብሔረሰብ ጋር ምንም ዓይነት ቅራኔ የሌለው መሆኑን ስለሚያውቅ በስልጣን ጥመኞች ምክንያት ሳቢያ የተፈጠሩ ስህተቶችን “ራሳችን መልሰን እንገነባቸዋለን!” እያለ ነው። ይህ እውነታ የኢትዮጵያ ሱማሌ ህዝብን ትክክለኛ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ነው።

እርግጥ የሃይማኖት እኩልነት በተከበረበት አገር ውስጥ አንድ ወገን የሌላውን ነጻነት ሊጋፋ አይችልም። የትኛውም የአገራችን ሀዝብ በሃይማኖት ሳቢያ አገር እንድትረበሽና ህዝብ እንዲከፋፈል እንዲሁም እንዲጋጭ አይፈልግም። ስለሆነም ሁሉም ሃይማኖቶች በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት ቁጭ ብሎ በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር፣ በመቀራረብና በፍቅር ተወያይተው መፍታት ይችላሉ።

ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት በኦርቶዶክስም ይሁን በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ያለው ክፍተት እንዲጠብ ተደርጓል። ለሁለት ተከፍለው የነበሩት ቤተ-እምነቶች አንድ ሆነዋል።

መንግስትና ሃይማኖት አገራችን ውስጥ የተለያዩ ቢሆኑም፤ የአንድን ሀገር ህዝብ በተለያየ መንገድ የሚያገለግሉት ሁለቱ አካላት ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም ማለት አይቻልም።

ሁለቱም አካላት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በየራሳቸው የነጻነት ማዕቀፍ ሲንቀሳቀሱ ይገናኛሉ። ለሰላምና ለአብሮነት ብሎም ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ከፍ ለማድረግ አብረው ይሰራሉ። ከዚህ አኳያ በፍቅርና በአንድነት የኖሩት የክርስትና እና የእስልምና እምነቶች ምንም ዓይነት የሚያጋጫቸው ነገር የለም። ተቻችለው በመኖር ዘመናትን ዘልቀዋል።

በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የእምነት ነጻነትና የሃይማኖት እኩልነት ተረጋግጠዋል። አገራችን በምትከተለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ እነዚህ መብቶች ህገ መንግስታዊ ከለላና ጥበቃ ያላቸው ናቸው።

ይህም ማንኛውም ዜጋ የመሰለውን እምነት በነጻነት ለመከተል  በሌሎች ሰዎች አምልኮ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ የሚከለክል ነው። ከዴሞክራሲ አስተሳሰብ አንጻር የራስን መብት  ማክበር የሚቻለው፣ ተመጣጣኝ በሆነ ሁኔታ የሌሎችን መብቶች ባለመጋፋት ስለሆነ ነው። በራስህ ላይ እንዲሆን የማትፈልገውን ነገር በሌሎች ላይ አትፈፅም እንደሚባለው አንዱ የሚፈልገውን ነጻነት ሌሎች እንዳያገኙት ማድረግ አይችልም።

የሁሉም ዜጎች መብት ሳይሸራረፍ ገቢራዊ የሚሆነው፣ አዲሱ አመራር በአገራችን ውስጥ ዴሞክራሲን ለማጎልበት ካለው ፍላጎት አኳያ ነው። በመሆኑም የማንኛውም ሰው ሃይማኖታዊ የአምልኮ ነጻነት ሊረጋገጥ የሚችለው የሌሎችን ነፃ አመለካከት የመያዝ ዴሞክራሲያዊ መብት አክብሮ ሲንቀሳቀስ ነው።

እነዚህ እውነታዎች በአገራችን ውስጥ ያሉ ናቸው። ህዝቡም ቢሆን ተቻችሎና በአንዱ በዓል ላይ ሌላው እየተገኘ በዓልን በማድመቅ የሚታወቅ ነው። ይህም ህዝቦች በሃይማኖት እንዲጋጩ የሚያደርጋቸው ነገሮች እንደሌሉ ያመላክታል። በኢትዮጵያ ሱማሌ የተከሰተው ግጭት ይህን ሃቅ በሚገባ የሚያውቀውን የሱማሌን ሀዝብ የሚመለከት አይደለም።

በአገራችን ማንኛውም ዜጋ የመሰለውን እምነት የመከተል መብት አለው። እንዲሁም ኢትዮጵያ የሃይማኖቶች እኩልነት የተረጋገጠባት አገር ናት። መብቶቹ ለአገራዊው ሠላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው መፋጠን ከፍተኛ ድርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ። ይህም አሁን አገራችን ባለችበት የለውጥ ተጨባጭ ሁኔታ ሃይማኖት የመቻቻልና የመከባበር እንጂ የግጭት መንስኤ ሊሆን እንደማይችል የሚያስገነዝበን ነው።

እርግጥም የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሃይማኖት የግጭት መንስዔ ሊሆን እንደማይችል ከማንም የሚሰወር አይደለም። የሃይማኖት እኩልነት በተረጋገጠባት ኢትዮጵያ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚካሄድ ማናቸውም እንቅስቃሴ ምንም ዓይነት ቦታ የለውም። ምክንያቱም ህዝቦች ለዘመናት ይዘውት የመጡትን ይማኖታዊ መቻቻል በአንድ ጊዜ ሊያፈርሱት ስለማይችሉ ነው። በኢትዮጵያ ሱማሌ የታየው “…ራሳችን እንገነባቸዋለን!” የህዝቦች ፍላጎት የዚህ እውነታ ማረጋገጫ ነው።

ሆኖም እንደ ኢትዮጵያ ሱማሌው ዓይነት የህዝቦችን ፍላጎት የማይወክለው የጥቂት ስልጣን ፈላጊዎች የግጭት ተግባር እንዳይደገም መስራት ያስፈልጋል። ስልጣንን የሚሹ ጥቂት ሃይሎች በዚህም በዚያም ብለው ሊፈጥሩት የሚችሉትን ችግር ህብረተሰቡ አስቀድሞ በመገንዘብ ተምሳሌታዊ እንደሆነው የኢትዮጵያ ሱማሌ ህዝብ ሁሉ የመቻቻል እሴቶቹን ማጠናከር ይኖርበታል።