Artcles

መሸርሸር የጀመረው…

By Admin

August 14, 2018

መሸርሸር የጀመረው…

አባ መላኩ

ለፌዴራል ስርዓት ስኬታማነት ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓት ትልቅ ሚና አለው። ፌዴራሊዝምን ያለዴሞክራሲ ለመተግበር መነሳት እጅግ ፈታኝ እንደሚሆን የዘርፉ ተመራማሪዎች ይመክራሉ፤ እናም ይላሉ ፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ወዲህ በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓቱ እንቅፋት እየበዛበት በመምጣቱ የፌዴራል ስርዓቱ ፈተና ላይ እንደወደቀ  ተመለክተነል። አገራችን ተራማጅ የሚባል ህገመንግስት ያላት አገር ብትሆንም በአፈጻጸም ረገድ በሚስተዋሉ ህጸጾች ሳቢያ አገራችን ለሁከትና ነውጥ ተዳርጋለች። ከሁለትና ሶስት ዓመታት ወዲህ በአገራችን የሚስተዋለው ሁከትና ነውጥ የ27 ዓመታት ድምር ውጤት እንጂ በእነዚህ ጥቂት ዓመታት በተከሰተ ድክመት የተፈጠረ አይደለም። ዛሬ ላይ ቀውስ በአገራችን እየገነገነ የመጣው አገራችን  በየጊዜው የሚገጥሟትን ትናንሽ ችግሮች በአግባቡ መፍታት ባለመቻሏ የገጠማት ፈተና ነው። ሰዎች ሃሳባቸውን በሃይል ለማራመድ በሞከሩ ጊዜ ሁሉ መልካም ነገር እንደማየመጣ መገመቱ የሚከብድ አይደለም።

 

ለአገራችንም ሆነ ለህዝባችን የሚበጀው  ሁሉንም ችግሮች በየፈርጁ ብንመለከታቸውና   በጋራ መፍትሄ ብንፈልግላቸው እንጂ ማዶ ለማዶ ሆነን ጣት መቀሳሰሩ ለማንም አይበጅም፤ የትም አያደርሰንም። አገራችን በለውጥ ያውም እጅግ ፈጣን የለውጥ ምህዋር ውስጥ ናት። የተጀመረው  ለውጥ ያለምነውንና የናፈቅነውን ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ሊያረጋግጥልን የሚችለው ሁሉም የድርሻውን መወጣት ሲችል እንጂ ሁሉንም ነገር መንግስት መፍትሄ ይፈልግላቸው በማለት አይደለም።  ይህን አይነት አካሄድ ለጋራ አገራችን ለጋራ ቤታችን መጽዳት አይበጅም። ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈጸመው ድርጊት ለፌዴራል ስርዓታችን አስፈሪም አሳፋሪም ተግባር ነው።

 

ከባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ወዲህ በበርካታ አካባቢዎች የአብሮነትና  አንድነት እሴታችንን የሚሸረሽሩ ድርጊቶች በስፋት ይከሰቱ እንጂ እንደነዚህ  ያሉ ድርጊቶች ባለፉት 27 ዓመታት በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ብልጭ ድርግም ሲሉ  የቆዩ ድርጊቶች ነበሩ። ከዚህ ቀደም ብሄር ተኮር ጥቃቶች ሲፈጸሙ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር መፍትሄ መስጠት ባለመቻሉ ለዛሬው የከፋ ቀውስ ተዳርገናል።  ዛሬ ላይ እየከፈልን ያለነው እዳ ትላንት ማከናወን የሚገባንን ተግባር በአግባብ ባለማከናወናችን የተከሰተ ይመስለኛል። በአንድ ወቅት አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ከጉራ ፈርዳ በርካታ ሰዎች ተገድለው፣ ተገርፈው፣ ቤት ንብረታቸው ተቃጥሎ ቀሪውም ሃብታቸው  ተዘርፎ ባዶ እጃቸውን የተባረሩበትን ምክንያት ለምክር ቤት ሲያስረዱ “ዛፍ በመቁረጣቸው” እንደሆነ ሲያብራሩ አድምጠናል። እንግዲህ ተመልከቱ የፌዴራል ስርዓታችን መሸርሸር የጀመረው ያን ጊዜ ነው። ያን ጊዜ የተከልነው መርዝ ዛሬ ላይ ዜጎች በድንጋይ ተቀጥቅጠው በእንጨት ላይ እንዲሰቀሉ  ምክንያት ሆኗል።

 

አሁን ላይ ደግሞ  አንዳንድ ቡድኖችና ሃይሎች የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ህዝቦችን ዕርስ በርስ በማጋጨት  የፌዴራል ስርዓቱን ለማፍረስ በመሯሯጥ ላይ ናቸው። ይህን አይነት አካሄድ ለየትኛውም ህዝብ የሚበጅ አይደለም፤  በዚህ ዘመን በመደጋገፍ፣ በመተሳሰብና በአንድነት እንጂ በመነቋቆርና በመለያየት የሚገኝ አንዳችም ትርፍ አይኖርም።  ባለፉት ዓመታት ተቻችለንና ተከባብረን በመኖራችን በርካታ ነገሮችን አትርፈናል፤ ለአብነት ሰፊና አማላይ ገበያ መፍጠር ችለናል፣ ጠንካራና አዳጊ ኢኮኖሚ ገንብተናል፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ መንግሥት አቋቁመናል፣ በሥነ ምግባር የታነፀ ህዝባዊ  የፀጥታ ኃይል ገንብተናል ወዘተ። ዛሬ ላይ አገራችን በለውጥ ጎዳነ ላይ ነች፤ ይህን ለውጥ ለማደናቀፍ ሲባል በፌዴራል ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከለላ በማድረግ ህዝባዊ ለውጡን ለማጨናገፍ ጠንክረው በመስራት ላይ ናቸው።

 

ባለፉት 27 ዓመታት የፌዴራል ሥርዓታችን ልዩነቶቻችንን ማስተናገድ በማስቻሉ አብረን እንድንኖር አድርጎናል። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁኔታዎች በመቀየር ላይ ናቸው።  አንዳንድ ሃይሎች ሆን ብለው ትናንሽ ግጭቶችን በማጎን  እከሌ የተባለው ብሄር ሊያጠቃህ ነው፤ ተነስ፣ ለወገኖችህ  ድረስላቸው ወዘተ በማለት  በግጭቶች  ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉ ተመልክተናል፤ የሚሰጧቸውን መግለጫዎችም አድምጠናል።  ይህን አይነት ቅጥ ያጣ አካሄድ ሊወገዝ ይገባዋል። መንግስትም  የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ዳተኝነት ተስተውሎበታል። በቅርቡ በኢትዮጵያ  ሶማሌ ክልል በተከሰተው ግጭት የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግስቱ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አልቻለም። ሰዎች እየተገደሉ፣ እየተገረፉ፣ ቤተ ዕምነት እየተቃጠለ፣ ንብረት እየተቃጠለና እየተዘረፈ  የፌዴራል  መንግስቱ ያለክልሉ ምክር ቤት  ጥያቄ  ጣልቃ  አልገባም በማለቱ   ምክንያት  በዜጎች ላይ እጅግ አሰቃቂ  ጭፍጨፋ እንዲደርስባቸው  ሆኗል።   

 

በተለያየ ምክንያቶች ህገመንግስት  በጠራራ ጸሃይ ሲጣስባት የኖረች አገር እየኖርን  እንደዚያ ያለ ህዝባዊ ቀውስ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሲፈጸም  የፌዴራል መንግስቱ እየተመለከተ የክልሉ ምክር ቤት ጥሪ አላደረገልኝም በሚል ተልካሻ ምክንያት   ጣልቃ መግባት ባለመቻሉ ሳቢያ በርከታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረስ ችሏል። እንደእኔ እንደኔ ይህ አይነት አካሄድ ህገመንግስት  ማክበር ሳይሆን ህገመንግስት መጣስ እንደሆነ ይሰማኛል። በአናሳዎች ላይ እንዲህ ያለ በቀል መፈጸም ከእንሰሳነት የሚለይ አካሄድ አይደለም። በበቀል  አሸናፊም ተሸናፊም የለም። ለየትኛውም አካል ቢሆን የበቀልና የእልህ መንገድ መዳረሻው እልቂትና ወድቀት ነው። በቀል ቁስልን አያደርቅም፤ በቀል ውድቀትን እንጂ ስኬትን አያመጣም።  በቀል መለያየትን፣ መቀነስንና ሽንፈትን እንጂ አንድነትን፣ መደመርንና ስኬትን አያመጣም።

 

አንዳንድ ቡድኖችና ግለሰቦች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይህን የፌዴራል ሥርዓት ችግር እንዲገጥመው  የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ናቸው። አንዳንዶች ትላንት ለፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ዋስ ጠበቃ እንደሆኑ አድርገው ሲናገሩ  የነበሩ ሃይሎች ዛሬ ላይ መርሻቸውን ቀይረው ለእኛ ካልተመቸን እንበትናታለን የሚል ሃሳብ አራማጅ ሆነዋል። ሌሎቹ ደግሞ የራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈጸም  የፌዴራል ስርዓቱን እንደከለላ አድርገው በመውሰድ ህዝቦችን በማጋጨት ላይ ናቸው። የግል ወይም የቡድን ጥቅምን በሌሎች ጉዳት ላይ እንዲመሰረት ማድረግ እጅግ ኋላቀርና ያልሰለጠነ ማህበረሰብ መገለጫ ነው።  

 

አገራችን  ብዙሃኑን ታሳቢ ያደረገ፤ በብዙሃኑ  የተደገፈ የለውጥ ጎዳና ውስጥ ናት። ይሁንና አንዳንድ  ሃይሎች ይህን የለውጥ ጎዳና በመልካም አልተመለከቱትም።  ለውጥን መደገፍም ይሁን አለመደገፍ ህገመንግስታዊ መብት ነው። ይሁንና ይህ መብት ህገመንግስታዊ የሚሆነው ሃሳብን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ ሲቻል ብቻ ነው። አሁን ላይ እየተመለከትን ያለነው  አካሄድ ከዚህ ወጣ ያለ ነገር እየሆነ ነው። ለውጥ ደጋፊዎችም ይሁኑ ለውጥ ተቃዋሚዎች እየመረጡት ያለው መንገድ አግባብነት የጎደለው ነው። ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እና በሻሸመኔ የተከሰተው ሁከቶች  ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። ስህተትን በስህተት ለማረም መነሳት መፍትሄ ሳይሆን የበለጠ ወደ አዘቅት የሚያመራ መጥፎ አባዜ ነው።

 

በአገራችን ባለፉት ዓመታት የተተበተቡት  የጥቅም ድሮች በቀላሉ የሚበጣጠሱ አይደሉም። ከላይ እስከ ታች ድረስ ደጋፊ በማብዛት የተዋቀረን  የጥቅም ትስስርን (Patronage Network) በአንድ ጀምበር ለመበጣጠስ መሞከር በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተከሰተው አይነት ችግርን የሚያስከትል ነው።  መንግስትም ብቻውን እንዲህ ያለውን የገነገነ የጥቅም ትስስር በቀላሉ ሊያስወግደው እንደማይችል አውቆ ህዝብን ማስተባበር መቻል ይኖርበታል። መንግስት የጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማጠናከር የጀመረውን የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት ሊገፋበት ይገባል። ለውጡን ስኬታማ ለማድረግ መንግስት  የጀመረውን ዴሞክራሲን የማስፋት ተግባራት ማጎልበት ይገባዋል። የተለያዩ ሃሳቦች እንደልብ እንዲንሸራሸሩ መንግስት የተለያዩ መድረኮችን ማመቻቸት ይኖርበታል። ማንም ጥቅሜ ተነካ፣ ተገለልኩ ወዘተ የሚል አካል ሁሉ ሃሳቡን በተመቻቸው መንገድ ማሰማት ይኖርበታል እንጂ በየቦታው ሁከትና ግጭት እንዲበራከት  የሴራ ፖለቲካ ውስጥ መዘፈቅ ለማንም አይበጅም። የጋራ አገራችንን ያፈርሳታል፤ ህዝብንም ያጫርሳል። በመሆኑም ማንም የተለየ ሃሳብ አለኝ የሚል አካል ወደ ሃሳብ መሸጫው መድረክ በመቅረብ በሃሰብ ሊሞግትና የሃሳብ ልዕልናን ሊያሳይ ይገባል።