Artcles

ማን ምን አደረገ?

By Admin

August 13, 2018

ማን ምን አደረገ?

ገናናው በቀለ

በየትኛውም አካባቢ የሚካሄዱ ግጭቶች የትኛውንም እምነትና ማንነት የሚወክሉ አይደሉም። ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች፣ በተለይም በኢትዮጵያ ሱማሊ፣ በኦሮሚያ፣ በድሬዳዋና በደቡብ ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች የታዩት ግጭቶች ከሃይማኖትና ከየትኛውም ብሔር ጋር የተያያዙ አይደሉም። ሊሆኑም አይችሉም። ምክንያቱም በታሪካችን የምናውቀው ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ቤተ ክርስቲያኖችን ሲያሰሩ፣ ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖችም መስጊድ ለማሰራት ድጋፍ ሲያደርጉ ስለነበር ነው። እንዲሁም ክርስቲያኑ በዓል ሲኖረው ለሙስሊም ጎረቤቱ በተለየ ድስት ወጥ አዘጋጅቶ ሲጠራ፤ ሙስሊሙም በሮመዳንና በመውሊድ እንዲሁም በሌሎች በዓላቱ ለክርስቲያኑ የተለየ ምግብ በማዘጋጀት ሲጎራረስ የነበረ ነው። ይህ ተቻችሎና አንዱ የሌላውን ሃይማኖት አክብሮ በአንድነት የሚኖር ህዝብ በእምነት ሳቢያ የሚጋጭበት ምንም ምክንያት የለም።

በተጨማሪም የትኛውም ገጭት በህዝብ አማካኝነት ሊነሳ አይችልም። በማንኛውም አገር ውስጥ የሚገኝ ህዝብ ለሰላም እንጂ ለጠብ ቦታ ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም ህዝብ የሚፈልገው በሰላም መኖርን እንጂ በሁከትና በግጭት ውስጥ መኖርን አይደለም። ከሰላም የሚገኘውን ፍቅር፣ አንድነትና ይቅርታ ስለሚያውቅ እንዲሁም የሚገነባቸውን እሴቶች ስለሚገነዘብ ግጭትን ይፀየፋል።

ለዘመናት አብሮ የኖረ፣ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኦኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውጣ ውረዶችን አብሮ ያሳለፈ ህዝብ ለጊዜያዊ ሁኔታ ብሎ የሚጋጭበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። እናም ህዝቦች በወሰን መካለል ጉዳይ ሊጋጩ የሚችሉበት ነባራዊ ሁኔታ እዚህ ሀገር ውስጥ ሊፈጠር አይችልም። በመቻቻል፣ በመከባበርና አንደኛው ህዝብ የሌላኛውን በሚያከብርበት አገር ውስጥ ህዝቦች በጊዜያዊ ሁነት ሊጋጩ አይችሉም።

ሆኖም በተነሱት ግጭቶች ሳቢያ አንዳንዶች ግድያን፣ ንብረት ማውደምን ህገ ወጥ አካሄዶችን የሚከተሉ ናቸው። ይህን ለማመቻቸት ሲሉም ደጋፊዎችን በማብዛት የጥቃት ዱላቸውን ሊሰነዝሩ ስለሚችሉ ህዝቡ ጥንቃቄ ከማድረግ በላይ እነዚህን አካላት ወደ ህግ ማቅረብ ይኖርበታል። ምክንያቱም ለሚፈጠሩ ችግሮች መቼም ቢሆን ግጭት መፍትሔ ሊሆን ስለማይችል ነው።   

በመሆኑም ከላይ በጠቀስኳቸው ግጭቶች የተከሰቱባቸው አካባቢዎች ተጨማሪ ጉዳቶች እንዳይደርሱ ህዝቡ በንቃት መከላከል አለበት። ለዚህም የግጭቶቹ ፈጣሪዎች እነማን እንደሆኑና ተጠያቂነትን እንዲወስዱ ለማድረግ ከፀጥታ አካላት ጋር ተባብሮ መስራት እንዲሁም መፍትሄዎቹን ማመላከት ይኖርበታል። ህዝቡ ማን ምን አደረገ? የሚል ጭብጥ በመያዝ፤ አጥፊዎችን በማጋለጥና ትምህርት ሰጪ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ምንጫቸውን በማድረቁ ሂደት ግንባር ቀደም መሆን አለበት።

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ግጭቱ በምን ምክንያትና እንዴት እንደተከሰተ፣ እነማን እንዲከሰት እንዳደረጉት፣ በግጭቱ ሳቢያ የተፈጠሩ ጉዳቶች ምን ዓይነት እንደሆኑ፣ አስቀድሞ ሁኔታዎችን መቆጣጠር ቢቻል ኖሮ ግጭቱን በምን ያህል መጠን መቀነስ እንደሚቻል ወዘተ መረጃዎችን በትክክለኛው ሳይንሳዊ መንገድ በመተንተን በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ግንዛቤን መያዝ መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል። ይህም ግጭቱ ዳግም እንዳይከሰት የሚያስችል መረጃን የሚሰጠን መሆን አለበት።

ስለሆነም ለወደፊቱ በየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ግጭት እንዳይከሰት ሁሉንም የይሆናል መንስኤዎችን ከነቀዳዳቸው መድፈን ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ከተቻለ በአገራችን ውስጥ እዚህም ሆነ እዚህ በየጊዜው ብቅ ጥልም እያሉ የሚከሰቱ ጊዜያዊ ግጭቶችን ማስወገድ የሚቻል ይመስለኛል።

ስለሆነም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ግጭቱ በምን ምክንያትና እንዴት እንደተከሰተ፣ እነማን እንዲከሰት እንዳደረጉት፣ በግጭቱ ሳቢያ የተፈጠሩ ጉዳቶች ምን ዓይነት እንደሆኑ፣ አስቀድሞ ሁኔታዎችን መቆጣጠር ቢቻል ኖሮ ግጭቱን በምን ያህል መጠን መቀነስ እንደሚቻል መረጃዎችን በትክክለኛው ሳይንሳዊ መንገድ በመተንተን በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ግንዛቤን መያዝ መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል።

ይህም ግጭቱ ዳግም እንዳይከሰት የሚያስችል መረጃን የሚሰጠን መሆን አለበት። እናም ለወደፊቱ በየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ግጭት እንዳይከሰት ሁሉንም የይሆናል መንስኤዎችን ከነቀዳዳቸው መድፈን ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ከተቻለ በሀገራችን ውስጥ እዚህም ሆነ እዚህ በየጊዜው ብቅ ጥልም እያሉ የሚከሰቱ ጊዜያዊ ግጭቶችን ማስወገድ የሚቻል ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜው የሚታዩ ጊዜያዊ ግጭቶች እየተከሰቱ መሆናቸውን ማንም የሚክደው እውነታ አይደለም። የቅርቡን በምሳሌነት ብናነሳ እንኳን በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የነበረው ግጭት፣ በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች፣ በጌዴኦና በጉጂ ህዝቦች መካከል ህይወት ያጠፋ፣ ንብረት ያወደመና ዜጎችን ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ እንዲፈናቀሉ ያደረገ ግጭት ተከስቷል።

ግጭቱ በክልሎች ጠያቂነት ፌዴራል መንግስት ጣልቃ በመግባቱ ሳቢያ ቀደም ሲል ከነበረው ሁኔታ በእጅጉ ሊቀንስ ቢችልም፤ አሁንም ሙሉ በሙሉ አለመቆሙን መንግስት በቅርቡ ገልጿል። ምንም እንኳን ግጭቱ ለዘመናት አብረው የኖሩ፣ ተጋብተው የተዋለዱና የጋራ የሰላምና የመቻቻል እሴቶች ያሏቸው ህዝቦች ፍላጎት እንዳልሆነ ቢታወቅም፤ አሁንም ግን ህገ ወጦች ከሁለቱም በኩል ሁከትን የመቀስቀስ አዝማሚያ አይኖርም የብሎ አይታሰብ። እናም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

ይህም በፍቅር፣ በመከባበርና በመቻቻል ሲጓዙ የመጡ ህዝቦች ሰላማዊ ፍላጎትን የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ፤ እንደ አገር በማይረባው ጉዳይ በግጭት እየታመስን ኢትዮጵያዊ የማደግ ራዕያችንን እንዳናሳካ እንቅፋት ይሆናል። እናም በየአካባቢው የፀጥታ ሃይሎች የችግሩን ፈጣሪዎችና ተዋንያን ወደ ህግ ፊት እንዲቀርቡ እያደረጉት ያለው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አሁንም ቢሆን ሰላምን የሚያጠናክሩ አጀንዳዎችንና መድረኮችን በመዘርጋት ለሰላም አበክሮ መስራት ያስፈጋል።

ህዝቡ እነማን የግጭት አነሳሽ በመሆናቸውን በሚገባ ያውቃል። ከእርስ የተሰወረ ነገር የለም። ሊኖርም አይችልም። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ማንም ህሊና ያለው ሰው ግጭትን ሊናፍቅ አይችልም። በየትኛውም ቦታ የሚከሰቱ ችግሮች ባይከሰቱ እሰየው ነበር። ሆኖም ከተከሰቱ በኋላ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም።

በመሆኑም ህዝቡ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስና ግጭቱ እንዳያገረሽ ህዝቡ ወሳኝ ሚናውን መሆን ይኖርበታል። እነማን ምን ሰርተው ወደ ግጭት እንዳመሩ፣ ችግሮችን በማራገብ የዜጎችን ህይወት ለመቅጠፍ እንዴት እንደሚሰሩ እንዲሁም በምን ዓይነት መንገድ እንደሚንቀሳቀሱ ስለሚያውቅ ሳያመነታ ማጋለጥ ይኖርበታል። የችግሩ ዋነኛ ሰለባ የሚሆነው እርሱ ስለሆነም ለውጥን ለመቀልበስ የሚፈልጉ ሃይሎችን ያለ ርህራሄ መፋለም ይኖርበታል።

ታዲያ ይህ ተግባር ሲፈፀም ከበቀልና ከቂም በቀል በነፃ ሁኔታ መሆን አለበት። ምክንያቱም የበቀል ስሜት ለበቃዩም ሆነ ለተበቃዩ አስፈላጊ አይደለም ነው። ብቀላ ተጨማሪ ደም መፋሰስን ከመፍጠር ውጭ ሰላምን ሊያመጣ የሚችል አቅም የለውም። በበቀል የሚገኝ ትርፍም የለም። እንዲያውም መቃቃርንና የከረረ ጥላቻን ከመፍጠር በስተቀር ምንም ዓይነት ርባና የለውም። በመሆኑም በግጭት ውስጥ ያለ የትኛውም ወገን ከብቀላ አዕምሮ ነፃ በመሆን ሰላምን ሊያመጡ ስለሚችሉ ተደማሪ ሃሳቦችና መፍትሔዎች መጣር ይኖርበታል።

በብቀላ መንገድ የሚጓዝ ህዝብ አንዱ የሌላኛውን ህይወት ያጠፋል፣ አካል ያጎድላል፣ ንብረቱንም ያወድማል። ሌላኛውም የተፈፀመበትን ለመመለስ ሲል ተመሳሳይ ጥፋት ይፈፅማል። በዚህ መንገድ ውስጥ የሚመላለሱ ሁለት ወገኖች እርስ በርሳቸው ከመተላለቅ ውጭ የሚያገኙት ጥቅም አይኖርም።

ይሁን እንጂ የይቅርታና የፍቅር መንገድ ግን ለሰላም ያለው ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ለሰላም ሲባል ከብቀላ በነፃ መንገድ ማን ምን አደገረ? የሚል ጭብጥን በመያዝ አጥፊዎችን በማጋለጥና ለጸጥታ ሃይሎች አሳልፎ በመስጠት ዜጎች ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው። ከየአካባቢያቸው መስተዳድርና ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን የግጭቱን መፍትሔ በማመላከት የሰላም ሃዋርያ መሆንም ይጠበቅባቸዋል።