Artcles

ቀጣናውን የታደገ ተግባር

ቀጣናውን የታደገ ተግባር

By Admin

August 27, 2018

ቀጣናውን የታደገ ተግባር

                                                         እምአዕላፍ ህሩይ

“በፊልም የሚታይ ልብ ወለድ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ አይመስልም።…” በማለት ነበር የገለፁት— የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሲፈፀም የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስመልክተው ለጋዜጠኞች ሲያብራሩ። የመብት ጥሰቱ፤ ሰዎች የሚጠበቅባቸውን ብቻ ሳይሆን ከሚጠበቅባቸው በላይ እንዲናዘዙ ከአንበሳ፣ ከጅብና ከነብር ጋር አብረው ይታሰሩ እንደነበር ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።

ርግጥም እንዲህ ዓይነቱ ክቡሩን የሰውን ልጅ ከእንስሳ ጋር አብሮ እያሰሩ የማሰቃየት የከፋ የመብት ጥሰት ለሰሚው ግራ የሚገባ ብቻ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደገለፁት ልቦለዳዊ የፊልም ትርክት እንጂ በገሃዱ ዓለም ላይ ይከሰታል ተብሎ የሚጠበቅ እውነታ አይደለም። በህግ የተያዙ ሰዎችን አስመልክቶ ዋስትና ሰጪ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ያላት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን “የልቦለድ ድርሰት” የሚመስል ተግባርን መስማት እጅግ አሳፋሪ ነው። ሲያስቡትም ያስጨንቃል።

በክልሉ ሲፈፀም የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሆን ተብሎ በድሬዳዋ የሚገኙ የጂቡቲ ዜጎችን እየለዩ በማጥቃት ቀጣናዊ ጥሰትን ለመፍጠር ያለመም ጭምር ነበር። መንግስት ጉዳዩን በብልሃትና በሰከነ ሁኔታ ባይዘው ኖሮ፣ ሁኔታውን ወደ ቀጣናዊ ግጭት በማዞር የከፋ ግጭት ለመፍጠር ታስቦም ነበር። ይህ ርጋታ የተሞላበት የመንግስት ተግባር ባይፈፀምና ችግሩን እንደተፈጠረ ወዲያውኑ ባልተጠና እና ያለ ጥንቃቄ ወደ ክልሉ ቢገባ ኖሮ፣ ሁኔታውን እንደ አሁኑ በቁጥጥር ስር ማዋል አይቻልም ነበር።   

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈጠረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ችግር ከአሳፋሪነቱም በላይ፣ ሀገራችን በቀጣናው ውስጥ ለምታካሂደው የትብብር ስራዎች እንቅፋት እንዲፈጥር ታስቦ እንደነበር ግልፅ ይመስለኛል። ርግጥ ይህ ጉዳይ በምርመራ ላይ ያለ በመሆኑ፤ በአሁኑ ሰዓት ከዚህ በላይ ማለት ባይቻልም፤ ወደፊት ጉዳዩን የያዘው አካል አጣርቶ ለህዝብ ይፋ ሲያደርገው በስፋት ማውሳት ይቻላል። በአሁኑ ወቅት ግን፤ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፈጥኖ አለመግባቱ ቀጣናውን ከግጭት ተግባር የታደገ ተግባር መሆኑን በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት በቀጣናው ሀገራት ያደረጓቸው ጉብኝቶች በሀገራችንና በቀጣናው ሀገሮች መካከል ጠንካራ የትብብር ማዕቀፍና አብሮ የመስራት ስምምነቶችን ፈጥረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የጋራ ተጠቃሚነት መርህን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ችለዋል—በተለይም ባለፉት አራት ወራት። ዶክተር አብይ ያካሄዷቸው ጉብኝቶች ለኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስህቦችን ማምጣት የቻሉ እንዲሁም መልካም ጉርብትናንና ከባቢያዊ ትስስሮችን በማጠናከር መናበብ የፈጠሩ ናቸው። በዚህም ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉልህ ሚና ማበርከታቸው የሚካድ አይደለም።

በተለይ ከጂቡቲ ጋር ጠንካራ መተማመንን መፍጠር በመቻላቸው በድሬዳዋ የጁቡቲ ዜጎችን ሆን ብሎ በማጥቃት ለመፍጠር የታሰበው የለውጥ አክሻፊዎቹ ሴራ አልተሳካም። ተግባሩ የቀሽሞች ስሌትም ይመስለኛል። ምክንያቱም ብልሁ አመራር አስቀድመው ሊፈጠሩ የሚችሉትን ቀዳዳዎች በመድፈን ፍላጎታቸውን ማምከን ስለቻሉ ነው። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግስታቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።

ርግጥ የኢትዮጵያንና የጂቡቲን ጠንካራ ግንኙነት ሴረኞች ሊሰብሩት አይችሉም። ምክንያቱ ደግሚ ግልፅ ነው። ይኸውም ሁለቱ ሀገራት በደም፣ በሃይማኖትና በባህል እንዲሁም የአንዱ ሀገር ህዝብ በሌላው ውስጥ የሚኖር ነው። ሀገራቱ ህልውናቸውና መፃዒ የጋራ ዕድላቸው የተሳሰረ በመሆኑ መቼም የሚነጣጠሉና በሴረኞች ጊዜያዊ እኩይ ምግባር የሚለያዩ አይደሉም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ጅቡቲ ባቀኑበት ወቅት ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌህ ጋር የደረሱት ስምምነቶች፤ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ጥቅም የተጋመዱና የአንዱ ማደግ ለሌላው መሰረት በመሆናቸው ይህ እንዲሆን የሚፈቅዱ አይደሉም።

ቀደም ሲል እንዳልኩት ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ጋር ያላት ጠንካራ ትስስር በቀላሉ የሚላላ አይደለም። የቁርኝቱ ገመድ ላይበጠስ የተሰናሰለ ነው። እንደሚታወቀው ጂቡቲ የኢትዮጵያ ገቢና ወጨ ንግድ ዋነኛው የኮሪደር መስመር ናት። ሀገራችን የራሷ ወደብ የሌላት በመሆኑ፣ የጂቡቲን ወደብ በጋራ ለማልማት ተፈራርማለች፤ ከጠቅላይ ሚስትር ዶከተር አብይ ጋር። ይህ ትልቅ እመርታ ነው። ኢትዮጵያና ጅቡቲ በመሪዎቻቸው በኩል የደረሱት የመሰረተ ልማት የባለቤትነት ድርሻ ልውውጥ ስምምነት፤ ሀገራችንን በጅቡቲ የወደብ ድርሻ ባለቤት እንዲሁም ጅቡቲን በኢትዮጵያ በተመረጡ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ ባለ ድርሻ የሚያደርጋት ነው። ይህም ሁለቱ ካላቸው ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ባሻገር ወደፊት እውን ለማድረግ ላቀዱት የኢኮኖሚ ውህደት በር ከፋች ተግባር ነው።

ምን ይህ ብቻ። ኢትዮጵያና ጂቡቲ በወደብ ልማት፣ በእርሻ ልማት፣ በመንገድ ልማትና ሀገራቱን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የግንኙነቱ ጥንካሬ አንድ ማሳያ ነው። ይህ ስምምነት ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ የትስስሩን ድር ይበልጥ ያጠብቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተስማሙት የመሰረት ልማት የባለቤትነት ድርሻ ልውውጥ ስምምነት ኢትዮጵያን በጅቡቲ የወደብ ባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራት ያደርጋታል። ይህም ኢትዮጵያ በወደብ ክፍያ ውሳኔ ላይ ድምፅ እንዲኖራት ያስችላል። ተደማሪ አቅምም ይፈጥራል። ጅቡቲም በኢትዮጵያ በተመረጡ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ በተመሳሳይ መልኩ ባለ ድርሻ እንድትሆን በማድረግ ሁለቱም ሀገራት አንዱ የሌለውን ከሌላው እንዲወስድ በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነትን ያሰፍናል።

ታዲያ ይህን የሁለቱን ሀገራት ፍላጎት የሚያስፈፅም የሚኒስትሮች ኮሚቴ ተቋቁሟሞ ስራውን ጀምሯል። በኢትዮጵያ በኩልም ጅቡቲ የምትሳተፍባቸው የተመረጡ መሰረተ ልማቶች በጥናት የሚወሰኑ ጉዳዩች ይኖራሉ። ርግጥ በሂደቱ ውስጥ የፖሊሲ ለውጥ የሚያስፈልገው ጉዳይ ካለም፤ በተቋቋመው ኮሚቴ አማካኝነት ወደፊት በሚደረግ ጥናት ተለይቶ ውሳኔ የሚሰጠው መሆኑ ግልፅ ነው።

እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ ጂቡቲ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ከኢትዮጵያ በመግዛት እየተጠቀመች ነው። ይህ ተጠቃሚነቷም ወደፊት እየታየ የሚጨምር ይሆናል። እንዲሁም ወንድም የሆነው የዚያች ሀገር ህዝብ ሀገራችን ካላት የከርሰ ምድር ውሃ የሚጠቀምበት ሁኔታዎች ተመቻችተውለታል።

ታዲያ እነዚህ ሁሉ ቱሩፋቶች በሁለቱ ሀገራት መካከል እያሉ፤ በድሬዳዋ በሚኖሩ ጂቡቲያዊያን ወንድሞቻችንን ላይ የተሰነዘረው ሆን ብሎ የማጥቃት ተግባርና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጥቂት አመራሮች የግል ጥቅምን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ ግጭት እየፈጠሩ ቀጣናዊ ቀውስ ለመፍጠር የተደረገው ስሌት ሊሰራ የሚችል አይደሉም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና መንግስታቸው የወሰዷቸው በሳል፣ ህግና ስርዓትን የጠበቁ ርምጃዎች እንዲህ ዓይነቱ የተሳሳተ ስሌት እንዳይሰራ ማድረግ ችለዋል።

በአሁኑ ወቅት የቀጣናው ሀገራት በጋራ ተጠቃሚ የሚሆነኑበትን መንገድ ከመቀየዳቸው ባሻገር የኢኮኖሚ ውህደትን በሂደት ለመፍጠር እየሰሩ ስለሆኑ ለግጭት የሚሆን ቦታ ሊኖራቸው አይችልም። ዛሬ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ባለፉት ጊዜያት በመወጣጠር ያሳለፏቸውን ጊዜያት ለመካስ እየሰሩ ነው።

አንዱ ጋ ያለውን የተደፈጥሮ ፀጋ ሌላው እንዲጠቀም የሚያስችል አሰራር በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ፋና ወጊነት አቅጣጫው ተተልሟል። የሚቀረው ነገር ቢኖር የተያዘውን መንገድ ወደ ተግባር በመቀየር ተጠቃሚነትን አጠናክሮ መቀጠል ብቻ ነው። ትላንት ከነበረው ቁርቋሶና ግጭት ለቀጣናው ሀገራት ከረሃብ፣ ከስደትና ከሰቆቃ በስተቀር አንዳችም የፈየደው ነገር የለም።

ርግጥ በሀገራቱ ውስጥና ውጭ በሚገኙ አካላት አማካኝነት ከተለያዩ ፍላጎቶች የሚነሱና ቀጣናውን ሊያውኩ የሚችሉ ሃይሎች መኖራቸው ነባራዊ ነው። ዳሩ ግን ሀገራቱ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ችግሮችን በሰከነና ብስለት በታከለበት ሁኔታ እግር በእግር እየፈቱ የተስማሙባቸውንና ወደ ብልፅግና ጎዳና የሚመሯቸውን የእኩል ተጠቃሚነት መርሃቸውን አጥብቀው በመያዝ ብቻ ወደፊት መትመም ይኖርባቸዋል— መፍትሔው ያለው ከልማትና ከዕድገት እንጂ ከግጭትና ከሁከት አይደለምና። ሰላም ለሀገራችን! ሰላም ለቀጣናችን!