በለውጡ ጉዞ ውስጥ
ወንድይራድ ኃብተየስ
ሰፊ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብትና የማህበራዊ እንቅስቃሴ ማዕከል በሆነችው ኢትዮጵያ በየእለቱ አዳዲስ ክስተቶች የሚታዩባት አገር ናት። መሽቶ በነጋ ቁጥር ያልታሰቡና ያልተገመቱ እውነታዎች ሆነው ሲገኙ እየተመለከትን ነው። ጨርሶ አይሆኑም የተባሉ ክስተቶች መሬት ላይ ወርደው እውን ሲሆኑ ታይተዋል።
ይህንን መነሻ ይዘን ስለመልካም አስተዳደር ጉዳይ አንዳንድ ነጥቦችን እንዳስሳለን። በቅድሚያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታን በግብነት አስቀምጦ መረባረብ ወሣኝ ጉዳይ ይሆናል። ታዲያ ይህን እውነታ በውል በመገንዘብ ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳቡን ወደ ድርጊት ለመለወጥ በጥረት የታገዙ ጠንካራ እንቅስቃሴዎች ከተጀመሩ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።
እስቲ በቅድሚያ ስለ መልካም አስተዳደር የሂደት ግንባታ ጥቂት እንበል። በዓለም ባንክ ብያኔ መሠረት መልካም አስተዳደር ማለት ሊተነበይ የሚችልና በነጠረ ፖሊሲ አወጣጥ የተካነ ነው። እንዲሁም በሙያው ሥነ ምግባር የሚታገዝና በሚወስዳቸው ርምጃዎች ተጠያቂ ሊሆን የሚችል መንግሥትና በመንግሥታዊ ጉዳዮችም በንቃት የሚሳተፍ ኅብረተሰብ ያለበትም ነው። በዚህም ሁሉም አካላት በህግ የበላይነት አምነው የሚንቀሳቀሱበት ሥርዓት ነው።
እርግጥ በዚህ ትርጓሜ ውስጥ ያሉት አባባሎች ለመልካም አስተዳደር ጠቃሚ መሆናቸው አያጠያይቅም። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታቸውን ከዛሬ ሁለት መቶ ዓመታት በፊት መሥርተው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል በሚባሉት ምዕራባውያን አገሮች ዛሬ ላይ ሙሉ ለሙሉ ገቢራዊ ሆኗል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ከኢትዮጵያ የ25 ዓመታት ታዳጊ ዴሞክራሲ አንጻር ተግባሩ ሲፈተሽ ይህንን ያህል የሚያኩራራ አይደለም።
ከመልካም አስተዳደር አኳያ በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ተግባሩ በሂደት እንጂ በአንድ ጀምበር የሚሟላ አይደለም። ምዕራባውያንም ቢሆኑ ዛሬ ለደረሱበት የመልካም አስተዳደር ተግባር ለዚያውም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ባላደረጉበት ሁኔታ ረጅም ጊዜ ወስዶባቸዋል። እንደ ኢትዮጵያ ባለ ጀማሪ የዴሞራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ አራማጅ አገር ተግባሩን በጥቂት ጊዜያት ውስጥ አለማምጣቷ ብዙዎችን ያግባባል።
መልካም አስተዳደርን ማስፈን የኪራይ ሰብሳቢነትን ቁልፍ መንገድ ይዘጋል። የአገር ልማትን ያፋጥናል። በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ለመልካም አስተዳደር መስፈን የተለያዩ ርምጃዎችን ቢወስድም ተግባሩ ግን ያን ያህል የሚያኩራራ አይደለም። በእርግጥ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባር የአንድ ጀምበር ሥራ አለመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው። ጊዜን ይጠይቃል፤ በሂደቶች የሚከወን እንደሆነም ይታወቃል።
አንዳንድ ወገኖች በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር የለም እያሉ በተደጋጋሚ ሲያስተጋቡ ይደመጣሉ። እንዲያውም መንግሥት መልካም አስተዳደርን ማስፈን ተስኖታል ሲሉ በስፋት ይተቻሉ።
መንግሥትና ገዥው ፖርቲ ኢሕአዴግ በየበኩላቸው መልካም አስተዳደር ጊዜ ይወስዳል። ተግባሩን ላለማከናወን እጃችንን አጣጥፈን አልተቀመጥንም ይላሉ። ይልቁንም ላለፉት 27 ዓመታት መልካም አስተዳደር በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ ውስጥ ሥር እንዲሰድ ዘርፈ ብዙ ጥረት መደረጉን ይገልጻሉ።
በዚህ አገር ባለፉት ዓመታት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ አጥጋቢ ውጤቶችም ተገኝተዋል ባይ ናቸው። ሁሉንም ወገኖች የሚያግባባው ቁምነገር የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሥር መስደድ ይችል ዘንድ በሁሉም ደረጃዎች የዴሞክራሲ ተቋማት መቋቋምና መጠናከር ይኖርባቸዋል። የዳበረ የፍትህ ሥርዓት እንዲገነባ፣ የህዝቡ ዴሞክራሲያዊ ባህል መጎልበት የግድ ይሆናል። በየደረጃው ባሉ የመንግሥት አካላት ውስጥ የግልፅነት፣ የተጠያቂነትና የህዝብ አገልጋይነት መርህ መስፈን ይኖርበታል። የተግባር መመሪያ እንዲሆን ብሎም በሁሉም መስኮች የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ብርቱ ጥረት ሊደረግ ግድ ነውና።
መንግሥት በአገሪቱ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባር ልማታዊ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከሚኖረው ሚናና የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ አንጻር መንግሥት አሁን ላይ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ መያዝ ግዴታው ይሆናል። መልካም አስተዳደር የህልውና ጉዳይ ነውና። መልካም አስተዳደርን ማስፈን ካልተቻለ በአገሪቱ ገንግኖ የሚታየውን ኪራይ ሰብሳቢነትን ደፍቆ ልማታዊነትን ማረጋገጥ በእጅጉ አዳጋች ነው። የመልካም አስተዳደር ትግበራ የዜጎች እለታዊ ህይወት በቀጥታ የሚነካ በመሆኑ፤ በአተገባበሩ ዙሪያ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ መጠነ ሰፊ ተግባራዊ ክንዋኔዎች ሊደረጉ ይገባል።
የሆነ ሆኖ በለውጡ ጉዞ ውስጥ የዜጎችን ቅሬታዎች ለመፍታትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ልዩ ትኩረት በመስጠት በቁርጠኝነት መሥራት የግድ ይሆናል።
ከአገልግሎት ተደራሽነትም ሆነ ከአፈጻፀም ጉድለት ጋር የሚነሱ በርካታ ቅሬታዎች አሉ። ይህንንም ኅብረተሰቡ በተለያዩ መድረኮች ላይ በግልጽ ተናግሯል።
የህዝብን ቅሬታዎች የመፍታትና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባራት ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ መንቀሳቀስ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። በየመድረኩ ዜጎች ባካሄዷቸው ውይይቶች ከአገልግሎት ተደራሽነትም ሆነ ከአፈጻፀም ጉድለት ጋር የሚነሱ ቅሬታዎች እንዳሉ በግልጽ አሳይተዋል።
እነዚህ ቅሬታዎች በዝርዝር የተለዩ በመሆናቸው ጊዜ ሳይሰጡ ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመፍታትና ለወደፊቱም እያደጉ የሚሄዱ ፍላጎቶችን ለማርካት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መሥራት ተገቢ ይሆናል። በተለይም ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን አምርሮ በመታገል ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር በማጎልበት የታዩ ጉድለቶችና የህዝብ ቅሬታዎች በሚገባ ተፈትሸው መፍትሄ ለመስጠት መረባረብ የግድ ይሆናል።