Artcles

በሰላም ውስጥ ሁሉም አለ …!

By Admin

August 15, 2018

በሰላም ውስጥ ሁሉም አለ …!

 

ነጻነት አምሃ

የሰው ልጅ ካለፈ ታሪክ እየተማረ ጠቃሚ ጠቃሚ ነገሮችን እያሰፋና ችግሮችን እየቀረፈ መሄዱን  መረጃዎችን ብናገላብጥ የምናገኘው እውነታ ነው፡ ፡ በትርፍ የሚገኘው ከግጭት ሳይሆን ከሰላም እንደሆነ በአሁኑ ወቅት  በኢኮኖሚ በጽገው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች አገራት ህዝቦች እየተረፉ ያሉ አገራት ን ታሪክ ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡

የዜጎቻቸውን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ያልቻሉ ታዳጊ አገራት ውስጥ የሚከሰት ግጭት ደግሞ አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡ መልካሙን ነገር ካደጉ አገራት መማር የምንችለውን ያህል የሚያስከትለው ችግር ደግሞ  የግጭት አውድማ ከሆኑት እንደ ሊቢያ ሶርያና የመን የመሳሰሉ አገራት ቀደም ሲል በሰላሙ ጊዜ የነበራቸውን ሁኔታና አሁን ያሉበትን ደረጃ ማየት በቂ ነው፡፡

እሩቅ ሳንሄድም ጎረቤት አገራት ሶማሊያንና ደቡብ ሱዳንን መመልከትም የራሳችንን ሁኔታ ለማረቅ ከፍተኛ ትምህርት የሚናገኝበት ይሆናል፡፡   ሶማሊያ ለረጅም ዓመታት የአሸባሪዎች መፈልፈያና መፈንጫ በመሆኗ ምክንያት ሰላሟ ተዘርጎ ዜጎቿ ለብስቁልና ተዳርገውና አገሪቱ ተከፋፍላ ትገኛለች፡፡ ደቡብ ሱዳንም በተመሳሳይ መልኩ ሰላሟ በመደፍረሱ የተነሳ ህዝቧ ለስቃይ እየተዳረገ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ የሰላምን ዋጋ ተገንዝቦ ቀድሞ አንድነትን ፈጥሮ ባለመስራትና እልህ በመጋባት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በመግባታቸው የመጣ መዘዝ ነው፡፡

በአጭር ዓመታት ውስጥ በሁለቱ አመራሮች አለመግባባት ወደ እርስ በርስ ትርምስና ሁከት የገባችው ደቡብ ሱዳን በአሁኑ ወቅር ያለችበት ሁኔ አስከፊ እንደሆነ ለመረዳት ከኛ የቀረበ የለም፡፡  አመራሮች ከመተባበር ይልቅ መነጣጠልን ሲመርጡ ህዝቦችም ሰላምን ከማስፈን ይልቅ በስሜት መነዳት ሲጀምሩ ጉዞው በእሾህ ላይ ይሆናል፡፡ የከፋና አሰቃቂ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ሞት ርሃብና እርዛት ይንሰራፋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ራስ ወዳድነት ነው፡፡  ራስ ወዳድነት አንድነትን ይበትናል፡፡ በዜጎች መካከል መቃቃርንና የእርስ በርስ ፍጅትን ያስከትላል፡፡  ይቅርታ ፍቅርና ትህትና ግን አንድነትን ያጠናክራል፡፡ ለዚህም ነው የአገራችን ህዝቦች በትህትናና በፍቅር ይቅር ተባብለው ይኖሩ ዘንድ የሚያስፈልገው፡፡

ትእቢትና መናናቅ እርስ በርስ አለመከባበርና አለመተሳሰብ የሚያስከትሉት ነገር ውድቀት ብቻ ነው፡፡ በህዘቦች መካከል በሚደረጉ ግጭቶች ከቶ አሸናፊና ተሸናፊ ሊኖር አይችልም፡፡ ሠላማዊ የነበረ አገር ወይም ክልል ከመበጥበጥና ዜጎች ለሞትና ለእንግሊት ከመዳረግ ኢኮኖሚን ከማውደም የዘለለ ይህ ነው የሚባል የሚያመጣው ነገር  የለም፡፡ በህዝቦች መካከል የማይሽር ጠባሳ ከማሳረፍ ሌላ አሸናፊ ሊኖር አይችልም፡፡ የሃገራችን አመራሮችና ህዝቦች ከዚህ መማርና ለህዝብ የሚበጀውን ነገር ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

ሰላም ከራቀ  ዕድገትም አይኖርም ተስፋም ይጨልማል፡፡ ሰውም ስለዛሬ መኖሩን እንጂ ስለነገ እድገትና ልማት ሊያስብ አይችልም፡፡  ከሠላምና መረጋጋት ውጭ ልማት ብዙም ትኩረት አያገኝም፡፡ ሠርቼ እለወጣለሁ የሚል ዜጋ አይኖርም፡፡ ጦረኛና ቀማኛ ዜጋን እንጂ በጦርነትና በግጭት አምራች ዜጋን ማፍራት አይቻልም፡፡

ፈርጀ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በተለያየ መልክ እየፈታች እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰችው አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከሁሉም በላይ ሰላምና አንድነት ከሚያስፈልጋት ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡   ባዕድ ጠላትን ከመከላከልና እምቢይ ያሉ ለትም ከመፋለም ጀምሮ በአገር ውስጥ በሚፈጠሩ የእርስ በርስ ግጭቶች ቀላል የማይባል ዋጋ መክፈሏ የሚታወቅ ነው፡፡

ለበርካታ ዓመታትም ያላትን ጸጋ መጠቀም ያልቻለችበት ሁኔታ በመፈጠሩ  መድረስ ከሚገባት ከፍታ መድረስ ሳትችል ቆይታለች፡፡ ከቀደመው ታሪኳ ተነስተን ሲናይ ከበርካታ ተግዳራቶች ጋር ባለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት መልካም የሚባል የለውጥ ሂደት ላይ እንደነበረች የሚካድ አይደለም፡፡ ይሁንና ያንን ለመቀጠል በማይቻልበት ሁከትና ብጥብጥ እንደገና በመግበቷ የተነሳ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደና ህዝቡን እያረጋጋ ይገኛል፡፡

ልማትን በማፋጠን የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በተከሰቱ የመልካም አስተዳደርና የስራ አጥነት ችግሮች ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ወደ ግጭት የመሩ ተግባራት ተስተውለዋል፡፡   በበርካታ ችግረሮች ብትታጠርም መንግስት ለተግዳሮቶቹ እጅ ሳይሰጥ አሁን ላለንበት የመደመርና አንድ ሆኖ ለአገር ሰላምና ልማት የመጣር ምዕራፍ ደርሰናል፡፡

ሰላማችን በጃችን ነው፡፡ የሰላም ባለቤትም ህዝቡ ነው፡፡ ህዝቡ ሰላሙን ማስጠበቅ ይቻለዋል፡፡ ራስ ወዳድ ወገኖችንም ወግ ማስያዝ ይችላል፡፡ ይህ ግን በአስተውሎና በእወነተኛነት ሊከናወን ይገባል፡፡ ይህ አማራ ነው ይህ ትግራይ ነው ይህ ኦሮሞ ነው እያሉ እርስ በርስ መናቆር ለከፋ ውድቀት ከሚዳርገን ውጪ የሚያስገኝልን ተስፋ የለም፡፡  

 

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አጋጥሞን ያለው ችግርም እልባት ሊያገኝና ህዝቦች የሰላም አየር የሚተነፍሱበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል፡፡ ቀደም ሲል የተከሰተውና የበርካቶችን ህይወት የቀዘፈውና ቀላል የማይባል ንብረት ያወደመው ዓይነት ግጭት እንዳይከሰት ብርቱ ትግልና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡ ፡ ለዚህ ደግሞ ህዝቡ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡

 

ሁሉም ዜጋ ለሰው ህይወት መጥፋት ለንብረት ውድመትና ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት ከሚሆነኑ የተለያዩ ድርጊቶች ሊቆጠብ የግድ ይላል፡፡    ዜጎችን በብሔርና በሃይማኖት ለማጋጨት የሚደረጉ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎችም አደብ ሊገዙ ይገባል፡፡

 

ህዝብን ለማቀራረብ እንጂ ለማራራቅ የሚጻፉ ጽሁፎች ሃላፊነት የጎደላቸው በመሆናቸው ሃይ ሊባሉ ይገባል፡፡ ለሁሉም ነገር ወሳኙ ህዝብ በመሆኑ እነዚህ ዓይነት ማደናገሪያ ጽሁፎችንም ወደጎን በመተው አንድነቱን ሊያጠናክር ይገባል፡፡

 

መሞከር ውጤቱ ዜጎችን ማቅ ማልበስ፤ አገርን የጥፋት አውድማ ማድረግ ነው፡ ፡ በግጭት እሳት ህዝብን እየማገዱ በዜጋ ስቃይና ሞት መቀለድ ታሪክ አይሽሬ በደል ነው፡ ፡ ስለሆነም የግጭት ምዕራፍን ለመዝጋት ሁሉም በደንብ ሊረባረብ ይገባል፡ ፡

 

በተለያዩ ዘመናት የተገለጹ የግጭት ምዕራፎች ትተውልን ከሄዱት ጥቁር አሻራዎች ብዙ ልንማርና ልንጠነቀቅ ይገባል፡ ፡ እነዚህ በመጥፎ መልካቸው የምናውቃቸው ጥቁር ጠባሳዎች አንድነታችንን ከማጠናከር የመበታተንን ገፅ እንድናነብ ያደረጉ ናቸውና ዳግም ላይገለጹ መዘጋት አለባቸው፡ ፡

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው ድርጊትም መቋጫ ሊያገኝ የግድ ይላል፡፡ ዜጎች  በአገራቸው በፈለጉት ሥፍራ የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት እንዳላቸው ቢታወቅም እያጋጠማቸው ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው፡ ፡  

 

በሕዝብ ላይ በደል የሚፈጽሙትን የሚቆጣጠራቸውና ለሕግ አቅርቦ ተገቢውን ፍርድ የማስወሰድ ተግባርም ሊጠናከር ይገባል፡፡   አሁን መስተዋል ያለበት ጉዳይ የህግ በላይነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ ህግ ሊከበር ይገባል፡፡ በክፋትና በወንጀል የሚሰማሩ ዜጎችም በህግ ተጠያቂ ሊሆኑ የግድ ይላል፡፡

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ በቅርቡ በአሜሪካ ከኢትዮጵያውያንና ከትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመፋለም በረሃ ከገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያደረጉዋቸው ውይይቶች በኢትዮጵያውያን መካከል መልካም ግንኙነትን ለማጠናከር መልካም መንገድ ከፍተዋል ማለት ይቻላል፡፡

 

ይህ በውጭ ሆነው ግጭትን ለሚቀሰቅሱ ወገኖች መክሰምና ወደ አንድ መጥቶ መደመር እድል የሰጠ በመሆኑ ግጭቶችን በማርገብ የሚኖረው ድርሻ የጎላ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡

 

በሰላም ውስጥ ሁሉም አለ፡፡ ከቶ የሌለ ነገር የለም፡፡ ሰላማችን ጠፋ ማለት ሁለንተናችን ጠፋ ማለት ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ምንም ዓይነት ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ሰላማችን ልክ እንደ አይን ብሌናችን ነው፡፡ ልንጠብቀው ይገባል፡፡ የሃገራችን ህዝቦች እነደሁለየው በተባበረ ክንዳቸው ሠላምን ለማረጋገጥ ከመቸውን በተለየ መልኩ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከሰላም እጦት ተጠቃሚ ሊሆን የሚችል ሰው ባለመኖሩ ሁሉም ዜጋ ሰላምን እንደ አይን ብሌን ልንጠብቀውና ልንከባከበው እንደሚገባ አጠያያቂ ሊሆን አይችልም፡፡