Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በስሜታዊነት የሚለወጥ ነገር የለም

0 302

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

በስሜታዊነት የሚለወጥ ነገር የለም

ስሜነህ

 

ኢሕአዴግ ለሶስት አስርት አመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሀገርን የመምራት ሃላፊነት ተረክቦ በሁሉም መስክ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት ሲሰራ መቆየቱና በዚህም ሀገራችን ለዘመናት ስትታወቅበት የነበረውን ረሃብ፣ ጦርነትና ኋላ ቀርነት ከመሰረቱ ለመለወጥ የሚያስችሉ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡

 

ይሁንና የመጡ ለውጦች ሁሉን አቀፍ አለመሆናቸውና የህዝቡን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ፍላጎት ማርካት ያለመቻላቸው፤ ብሎም ከራሱ ከድርጅቱ ውስጥ በመነጩ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ባህሪዎች የተነሳ ካለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ወዲህ በሀገራችን ከፍተኛ አለመረጋጋቶች ሲከሰቱና ያልተገባ ዋጋ ሲያስከፍሉን ቆይተዋል፡፡ኢህአዴግ የመሪነት ሚናው በከፍተኛ ሁኔታ እየተጓደለና መርህ ወደ መልቀቅ እየተጓዘ መሆኑን በጥልቅ ተሃድሶ በሚገባ ገምግሜያለሁ ብሎ በአዲስ የመደመር አስተሳሰብ መመራት ከጀመረ ደግሞ ግና መንፈቅ እንኳን ያልሞላው መሆኑም ይታወቃል፡፡ በግምገማው የተለዩ ችግሮችን ግዝፈትና አስከፊነት በመረዳትም ሰፊ የማስተካካያ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ በሀገራችን የተጀመረውን ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ለማሳለጥ ብሎም ረጅሙን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት የአመራር ለውጥ በማድረግ ወደ ተጨባጭ ስራ ገብቷል፡፡

 

አዲሱ አመራር የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚና የኢሕአዴግ ምክር ቤት ባስቀመጡት አቅጣጫ ብሎም ባደገና በጎለበተ አስተሳሰብ በመመራት ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም እጦትና ሲስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በጥቂት ጊዜያት በመቅረፍ በአንድነት፣ በፍቅርና በመደመር እሳቤ ሀገራችንን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እየለወጣት ይገኛል፡፡ ሀገራችን አንጻራዊ መረጋጋት ማግኘት የቻለች ከመሆኗም ባሻገር መላ ህዝቦቿ ለቀጣይ ለውጥ ተስፋ የሰነቁባት መሆን ችላለች፡፡

 

ኢሕአዴግ ለብልሽት የዳረጉትን አላስፈላጊና ከድርጅቱ ባህሪ ውጭ የሆኑ ባዕድ አስተሳሰቦችንና ድርጊቶችን ለይቶ በመሰረታዊነት ወደ ማስተካከል የተሸጋገረበት ሁኔታም ተስተውሏል፡፡ ለአብነት የህግ የበላይነትን በማስከበር ሽፋን ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባር ሲፈፀምባቸው የነበሩ ተቋማት በግምገማ ተለይተው ሪፎርም እንዲደረጉና በአመራርም በተቋምም ደረጃ እንዲስተካከሉ ተደርገዋል፡፡

የዜጎች ሰብዓዊ መብት ቅድሚያ ተሰጥቶት በማረሚያ ቤት ተፈርዶባቸው የሚገኙና ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ ግለሰቦች በይቅርታና በምህረት እንዲለቀቁ ተደርገዋል፡፡ ይህ ታራሚዎችን ነፃ የማውጣት ጉዳይ በተለያዩ ሀገራት ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ጭምር ያማከለ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትም የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ በውጪ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ግለሰቦች በሰላማዊ መንገድ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ተደርጓል፤ ጥሪውን ተቀብለው ብዙዎቹም ገብተዋል።

 

በተጨማሪ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነትና ወዳጅነት ለማጠናከር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በተለይም የባህልና የታሪክ ቁርኝት ካለው የኤርትራ ህዝብ ጋር ሰላምን ለመመለስ የኢሕአዴግን ስራ አስፈፃሚ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የድርጅቱ ሊቀመንበር ያቀረቡት የሰላም ጥሪ በኤርትራ መንግስት ተቀባይነት በማግኘቱ በሀገራቱ መካከል ታሪካዊ፣ ጊዜ የማይሽረውና ከአፍሪካ አልፎ ለመላው አለም አርዓያ የሆነ ግንኙነት ተጀምሯል፡፡  

 

በቅርቡም የለውጡ መሪ የሆኑት የድርጅቱ ሊቀመንበር ጓድ ዶ/ር አቢይ አህመድ በአሜሪካን ሀገር ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኖች ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ባደረጉት ውይይትም በእጅጉ ተራርቆና በተለያየ ፅንፍ ላይ ቆሞ ሲወቃቀስ በነበረው ዲያስፓራ መካከል ያለውን የጥላቻ ግንብ አፍርሰዋል፡፡ እነዚህ የአንድነትና የመደመር መድረኮች በመንግስትና በዲያስፖራው መካከል ለሀገር ልማት በጋራ ለመስራት መግባባት የፈጠሩ ናቸው፡፡ በውጪ የሚገኙ መላ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ አመለካከት ሳይገድባቸው ለሀገር ልማት የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ለመወጣትና የሀገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ ቁርጠኝነታቸውን ገልፀዋል፡፡ መድረኮቹ ለረጅም ጊዜ ተሞክሮ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ያልተቻለበትን ሀገራዊ መግባባት የመፍጠር አላማ ከማሳካት አንፃርም ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ሆነው በታሪክ የሚመዘገቡ ናቸው፡፡ያም ሆኖ ግን ለውጡ ያልገባቸው ሃይሎች ይህን ስኬት ለመቀልበስ ለሚሰሩ ሃይሎች መደላድል ሆነው ተስተውለዋልና በጉዳዩ ላይ መነጋገርና የጋራ የሆነ ሃገራዊ አቋም መያዝ ተገቢ ይሆናል።

 

ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች፣ በተለይም በኢትዮጵያ ሱማሊ፣ በኦሮሚያ፣ በድሬዳዋና በደቡብ ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች የታዩት ግጭቶች የዚሁ ማሳያዎች ናቸው። ቀውሱን ከሚያባብሱ ዋነኛ ምክንያቶች መካከልም ተደምረናል የሚለው ሃይል በማህበራዊ ሚዲያ  የሚያሰራጫቸው የተሳሳቱ መረጃዎች እንደሆኑም ብዙዎች ይስማማሉ። የመንግስት የሚባሉት የሚዲያ ተቋማትም ቢሆኑ ግጭቶችን ከመዘገብ ባለፈ ምንጫቸውንና ተጠያቂነትን የሚወስዱ አካላትን በማጋለጥ፣ እንዲሁም መፍትሄዎቹን በማመላከት ላይ ያተኮሩ አለመሆናቸው በብዙዎች እየተኮነነ ነው።

 

የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ የክልሉ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የፌደራል የፀጥታ ሃይል ወደ ክልሉ ገብቶ ሰላም የማስከበር ስራውን እየሰራ ነው። እዚህም ላይ ቢሆን ብዙዎች ህገ መንግስቱን ከለላ ያደረገ ውዥንብር ፈጥረዋል። የፌዴራል መንግስት የፀጥታ ኃይሎች ወደ ክልሉ የገቡት ክልሉ ለፌዴራሉ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት መሆኑን ያላገናዘበ እና ህገ መንግስቱ የተናደ የሚያስመስል ውዥንብር ሲነዛ ሰንብቷል። የክልሉ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ አብዲ ስልጣናቸውን የለቀቁት በራሳቸው ውሳኔ ሲሆን፤ ይህም በመሆኑ የክልሉ ምክር ቤት አዲስ ፕሬዝዳንት እስኪመርጥ ድረስ በጊዜያዊነት ክልሉን የሚመሩ ኃላፊ መመደባቸውን እና ምክር ቤቱ ግን ገና ያላፀደቀው መሆኑንም የሚጻረር መረጃ ሲዥጎደጎድ ከርሟል፡፡ያም ሆኖ የተከናወነው ሁሉ ህገ መንግስቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው።

 

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በመግለጫቸው በክልሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈፀሙ በነዋሪዎች ሲነሳ መቆየቱን አስታውሰው፤ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በታየው የፍቅርና የመደመር ሂደት ውስጥ እኛም እንካተት በሚል ጥያቄ ያነሱ የህዝብ ተወካዮች እና የሀገር ሽማግሌዎች ላይ ከፍተኛ ወከባ በክልሉ መንግስት ጥቂት አመራሮች ሲደርስ መቆየቱን ተናግረዋል።“ስልጣን ልቀቅ ተብያለሁ፤ ስልጣኔን ከምለቅ ብሞት ይሻለኛል” በሚል ሰፊ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደነበርም ነው ያነሱት። ያለ ክልሉ ነዋሪዎች ፈቃድና ይሁንታ “ክልሉን አስገነጥላለሁ” በማለት ከፍተኛ ውዥንብር በመፍጠር ኢ-ህገመንግስታዊ እና ሀላፊ ሚኒስትሩ አስነዋሪ ብለው የገለፁት ድርጊት ሲፈፀም ቆይቷል ብለዋል።

የሀገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ ለመጣል እንዲሁም አካባቢው እንዳይረጋጋ የተለያዩ ፕሮፖጋንዳዎችን የማሰራጨት ተግባር ሲፈፀም ነበርም ሲሉ የሚገልጹት ሃላፊ ሚንስትሩ፤ ስልጣኔን እነጠቃለሁ በሚል የክልሉ ልዩ ሀይልን ላልተቋቋመለት ዓላማ በማዋል መንገዶች ሲዘጉ ነበር በማለት ለአብነትም ከሀረር ጅግጅጋ እና ወደ ጅቡቲ የሚወስዱት መንገዶች ተዘግተው እንደነበር አንስተዋል።

 

በክልሉ በተለይም በጅግጅጋ ለተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች የሰው ህይወት፣ የሀይማኖትና የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን የተለያዩ መረጃዎች ገልፀዋል።ከዚህ መገንዘብ እና ማጤን የሚያስፈልገው ይህ ሁሉ ጥፋት እና ውዥንብር የደረሰው በለውጥ ቀልባሾች ብቻ ሳይሆን መደመር ባልገባቸው የቀልባሹ ሃይል ሰለባ ሃይሎችም ጭምር መሆኑን እና ከዚህም የከፋ እንዳይመጣ መፍትሄውም እዚሁ ላይ ማነጣጠር ያለበት መሆኑን ነው።

 

ለውጥ ከአንድ በአንፃራዊ መልኩ የተረጋጋ ሥርዓት ወደ ሌላ በአንፃራዊ ሁኔታ የተረጋጋ ሥርዓት መቀየር ማለት ነው ። ስለሆነም ለውጥ የአዲስ አስተሳሰብ መሠረት ነው የሚባለው ያለምክንያት አይደለም። በለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የሀይል አሰላለፍ ወሳኙ ጉዳይ ነው። ይህ ማለት ህዝቦች የሚፈልጉትን ለውጥ ስር ነቀል በሆነ ጥልቅ ግምገማ እያስተካከሉ በመምጣት የህዝቦችን ፍላጎት ማሟላት ከተቻለ ያለጥርጥር በለውጡ ሂደት ውስጥ ሰፊውን የለውጥ ሀይል በባለቤትነት ስሜት ማሰባሰብ ይቻላል፡፡

 

ይሁንና ግን ለውጡ በሚፈጥረው የእርማት እንቅስቃሴዎች የጥራትና የፍጥነት ሁኔታ ግራ ሊጋቡ የሚችሉ አካላት ሊኖሩ እንደሚችሉም መገመት ተገቢ ነው። ከዚህ አኳያ የለውጥ አራማጆች ዋነኛ ሥራ የለውጡን አስፈላጊነት የማሳመን፣ የመቀስቀስ፣ እና ለለውጡ ውጤታማነት በየደረጃው የሚገኘውን ሀይል የለውጡ አካል ሁኖ ለህዝቡ ጥቅም እንዲቆም የማደራጀት ስራ መስራት ነው።ይህን ደግሞ የለውጡ አመራር ያሳለፍናቸው አራት ወራት ዋነኛው ስራ አድርጎ መሰንበቱን ከላይ በተመለከተው መልኩ አስተውለናል።

 

ስለሆነም የቀረውና ከላይ ለተመለከቱት እና መሰል ቀውሶች ምክንያት የሚሆነው ይህንን በአዲስ መልክ የተከሰተ ለውጥ የሚሸከም ወቅቱን የተከተለ የህዝብ ተሳትፎ እና ድጋፍ ይሆናል ማለት ነው። የሕብረተሰብ እድገት በሀገራዊ ኢኮኖሚው በፖለቲካውም ሆነ በቴክኒዮሎጂው በትምህርቱም ሆነ በተለያዩ መስኮች ይከሰታል፡፡ እድገትና ለውጥ ራሱን ችሎ ይዞ የሚመጣቸው አዳዲስ ጥያቄዎች ይፈጠራሉ፡፡ የትምህርና የቴክኒዮሎጂው እውቀትና እድገት ሕብረተሰቡን የነቃና የበቃ ያደርገዋል፡፡ለውጡ በራሱ ለምን ባይ ሞጋችና ለመብቱ ተከራካሪ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የላቀ ሚና ይጫወታል፡፡በድሮ በሬ ያረሰ የለም እንዲሉ ትላንት የነበረው አስተሳሰብና እምነት አካሄድ በብዙ መልኩ የሚቀየርበት ሁኔታም ይፈጠራል፡፡ የግድ ግዜውን ዘመኑንና እድገቱን መከተል ይጠበቅበታል፡፡ይህ ካልሆነ ኃላፊነትን መሸከምና መምራት አዳጋች ይሆናል፡፡

 

በሌላ በኩል መንግስት  በስፋት እያካሄደው የሚገኘው የለውጥ ተሀድሶ በራሱ የአዲሱ ለውጥ ጅማሬ ነው፡፡ ስለሆነም ድሮ እንዲህ ነበርን በዛው እንቀጥል የማይባልበት ወቅትን ግዜን የሕብረተሰብን እድገት ተከትሎ ለወቅቱ የሚመጥን አዲስ አሰራርና አመራርን በየደረጃው መፍጠርንም ይጠይቃል። ይህ ብቻም አይደለም የነበሩ አሰራሮችን ፈትሾ መቀየር መለወጥ የሕብረተሰቡን ጥያቄ አቅም በፈቀደ መጠን በፍጥነት መመለስ የሕብረተሰቡ እድገት ያመጣውና የወለደው በመሆኑ ለዚህ ተዘጋጅቶ መስራትን ይጠይቃል፡፡

 

ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ መምራት የሚገባው ተመሪ ሁኖ የጋሪው ከፊት መቅደም የፈረሱ ከኃላ መሆን አይነት ዝብርቅርቅ ሁኔታዎችን ይፈጠራል፡፡እያየን ያለውም ይህንኑ ነው።ለምን ቢሉ ሁልግዜም በሕብረተሰቡ ውስጥ አዳዲስ ግዜውን ተከትለው የሚመጡ ለውጦች እድገቶች አሉ፡፡ይህ ደግሞ የሕብረተሰብ እድገት ሕግ የሚያመጣው ስለሆነ በነዚህ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ውስጥ እየበቁ ስሕተትን እያረሙ እየታደሱ ግዜውና ወቅቱ በሚመጥነው መልኩ መራመድ ግድ ይላል፡፡

 

ፍጹም የሚባል ነገር ፍጹማዊ የሚባል የመንግስት አስተዳደር አመራር አሰራር በምድር ላይ የለም፡፡ ስህተቶችን ሁልግዜም እንደ መንግስትም እንደ ፓርቲም እያረሙ መሄድ የሕብረተሰቡን ጥያቄ መመለስ ወቅትና ግዜዎችን ተከትሎ በፈጣን ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ውስጥ የሚከሰቱትን ችግሮች መፍታትን ከድክመት ተምሮ ጥንካሬን ማጎልበት ስህተትን ማረም የበለጠ ለመስራት መንቀሳቀስ የግድ ይላል፡፡ከዚያ ባሻገር ያለው ደግሞ የዜጎች ሁሉ ሃላፊነት ይሆናል።

 

በፖለቲካው መንደር ውስጥ የሚታየው ውዥንብርና ምስቅልቅል ወገንን ከወገኑ ለጊዜው ቢያጋጭም፣ ከዚህ ማጥ ውስጥ መውጣት እንደሚቻል ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ያስተምራል፡፡ አስተዋዩ ሕዝብ እርስ በርሱ እንዴት አብሮ እንደሚኖር በሚገባ ያውቃል፡፡ አንዱ ለሌላው መከታ ሆኖ መኖር ለሕዝባችን ብርቅ አይደለም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በየሥፍራው የሚጫር እሳት ቢኖርም፣ በሕዝቡ አርቆ አሳቢነት ፍሙ ወደ አመድነት እንደሚቀየር የታወቀ ነው፡፡ የሕዝቡ አገር በቀል ዕውቀትና የጋራ እሴቶች ምርኩዝ በማድረግ ዘመናዊውን የዳበረ አስተሳሰብ ማከል ከተቻለና በክፋት ላይ ቀናነት የበላይነት ከያዘ የማይታለፍ ችግር አይኖርም፡፡  

 

በገዛ ወገን ደም የቆሸሸ እጃቸውን እየተለቃለቁ ሌላ ዙር ግጭት በመቀስቀስና የተዛቡ መረጃዎችን በመልቀቅ አገር ማተራመስ ከሕዝብ ጋር ያጣላል፡፡ ከሕዝብ የሚደበቅ ምንም ነገር ስለሌለ ማታለል አይቻልም፡፡ በጨለማ የተፈጸመን ወንጀል እንደ ፀሐይ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ሕዝብ ማንም አያታልለውም፡፡ የታሪክ መልካም ነገሮችን ለአሁኑ ዘመን መልካም ሥራዎች ስንቅ ማድረግ፣ አሳዛኝ ክስተቶችን ዳግም እንዳያንሰራሩ ምዕራፋቸውን መዝጋት ይገባል፡፡ ያለፉት ዘመናትን ክፉ ሥራዎች እያራገቡ በዚህ ዘመን የባሰ ድርጊት ለመፈጸም ከመንሰፍሰፍ፣ ለዘመኑ የሚመጥን ታሪክ መሥራት ያስከብራል፡፡ በተለይ ወጣቶች በማኅበራዊም ሆነ በመደበኛ ሚዲያዎች አማካይነት ፈጣን መረጃዎችን በሚለዋወጡበት በዚህ ዘመን፣ ለዕድገታቸውና ለስኬታቸው የሚበጅ ዕገዛ ከማድረግ ይልቅ በሐሰተኛ ወሬዎች በማደናገር አገር ላይ እሳት ለማዝነብ መፍጨርጨር ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ በዚህ ዘመን በስሜታዊነት የሚነዱ ሰዎች አንድም ዕውቀት ካልሆነም ማስተዋል ይጎድላቸዋል፡፡ ከእነሱ በስተጀርባ የሚሠለፉት አውቆ አጥፊዎች ደግሞ ውስጣቸው በቂምና በጥላቻ የተመረዘ በመሆኑ የጥፋት እጃቸውን በየአቅጣጫው ያስረዝማሉ፡፡

 

ኢትዮጵያን በመሰለች ታላቅ አገር የይስሙላ ምርጫዎች እየተካሄዱ የደረሱትን አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊቶች፣ በእንዲህ ዓይነት ወሳኝና ዘመኑን የሚመጥን ተግባር መቀየር እንደሚገባ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ውስጥ ምን ያህል የማደግ፣ የመለወጥና የመዘመን ፍላጎት እንዳለ ማመላከቻ ነው፡፡ ፍትሐዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲኖር ግን በግራና በቀኝ የሚያወላክፉ መሰናክሎች መነሳት አለባቸው፡፡ ትልልቅ አገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ውኃ የማያነሱ ጥቃቅን ነገሮች ላይ ውሎ ማደር ለአገር ፋይዳ የለውም፡፡ አገር የምትለወጠው በምክንያታዊ አስተሳሰብ እንጂ በስሜታዊነት አይደለም፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy