NEWS

በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በተጠናከረ የአመራር ብቃት ለመደገፍ እንሰራለን – የብዓዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ

By Admin

August 18, 2018

በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በተጠናከረ የአመራር ብቃት ለመደገፍ እንደሚሰሩ የብዓዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ በመጪው መስከረም ወር በሚካሂደው 12ኛው ጉባዔ ለውጡን ማስቀጠልና የህዝብ ፍላጎት ማሟላት የሚችሉ ጠንካራ አመራሮችን እንደሚሾም ገልጿል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ድርጅቱ በቀሪ የክረምት ጊዜያት በሚያከናውናቸው ተግባራትና የቀጣይ ጉባዔ አጀንዳዎች ዙሪያ ውይይት እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ብዓዴን ድርጅት ብቻ ሳይሆን የክልሉ ህዝብ መሪ በመሆንም በሀገራችን የተጀመረውን ለውጥ ደግፎ ከግብ ለማድረስ ጠንክሮ ይሰራል ብለዋል፡፡

የህዝቡ ጥያቄዎች በአፋጣኝ እንዲመለሱና የህግ የበላይነት እንዲከበር ድርጅቱ ከምንጊዜውም በተሻለ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የተገለጸ ሲሆን የድርጅቱን አቅም የሚጠናክርና ለውጡን ለማስቀጠል የሚያስችሉ አመራሮች ተመርጠው በቀጣይ ጉባዔ እንደሚሾሙ ታወቋል፡፡

በጉባዔው ላይ መሻሻል የሚገባቸው የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንቦችና የአሰራር መመሪያዎች ማሻሻያ እንደሚደረግባቸውም ተገልጿል፡፡

በድርጅቱ ውስጥ የሚታየውን ጉራማይሌ የሆነ የአመራር ብቃት ለማስተካከልም በትኩረት እንደሚሰሩ አቶ ምግባሩ ተናግረዋል፡፡

በመስከረም ወር የሚካሄደው ጉባዔም በአጀንዳዎቹ ዙሪያ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

fbc

 

በሙሉጌታ ደሴ