Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በ‹‹ዲሞ›› ጨዋታ አይቆጡም ‹‹ጌታ››

0 273

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በ‹‹ዲሞ›› ጨዋታ አይቆጡም ‹‹ጌታ››

ተፈሪ መኮንን

በ1945 ዓ.ም (እኤአ) ግድም፤ አሌክሲስ ዲ. ቶኮቪሌ (Alexis de Tocqueville) ‹‹How democracy affects the relation of masters and servants›› በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ ፅፎ ነበር፡፡ እኔም በዚህ መጣጥፍ፤ ይህንኑ የቶኮቪሌ ፅሁፍ መሠረት አድርጌ፤ የሐሳብ ‹‹ቶኒክ›› ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችን ለማንሳት እሞክራለሁ – እንዳሰብኩት ከተሳካልኝ፡፡ ቶኮቪሌ ‹‹masters and servants›› ሲል ያፈራቸውን ቃላት፤ እኔ ‹‹ጌታ›› እና ‹‹ሎሌ›› በሚል ልተረጉማቸው ብሞክርም፤ በፍቺ ቀጣሪ እና ተቀጣሪ ወይም አዛዥ እና ታዛዥ ወይም መሪ እና ተመሪ ወዘተ የሚሉ ሐሳቦችን እንዲይዝ እፈልጋለሁ፡፡

እስከ ዛሬ ድረስ፤ ሐብታም ወይም ድሀ የሚባሉ ሰዎች የሌሉበት፤ ‹‹ጌታ›› እና ‹‹ሎሌ›› የሚል ማህበራዊ ክፍፍል የማይታይበት ሐገር በታሪክ አልታየም፡፡ ስለዚህ የዴሞክራሲ መኖር እንደዚህ ዓይነት መደቦችን አያጠፋቸውም፡፡ ነገር ግን፤ በሁለቱ መደቦች መካከል ያለውን የእርስ በርስ ግንኙነት ባህርይ እንዲለወጥ ማድረጉ አይቀርም፡፡ እናም፤ በዲሞክራሲያዊ ስርዐት ውስጥ የ‹‹ጌታ›› እና ‹‹ሎሌ›› ግንኙት ምን እንደሚመስል ለማየት፤ የቶኮቪሌን መጣጥፍ መሠረት በማድረግ ትንሽ ፍተሻ አደርጋለሁ፡፡

ቶኮቪሌ እንዲህ ሲል ይጅምራል፡፡ ‹‹በአንድ ወቅት፤ አውሮፓን ለረጅም ጊዜ ሲጎብኝ የቆየ አንድ አሜሪካዊ እንዲህ ብሎኝ ነበር፤ ‹የእንግሊዛውያን የሠራተኛ አያያዝ የማያፈናፍን እና ፍፁም የበላይነት የሚንፀባረቅበት ነው፡፡ ለእኛ ለአሜሪካውያን እንዲህ ያለ ነገር እንግዳ እና አስገራሚ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ፈረንሳውያን ሠራተኞቻቸውን ቤተሰባዊ መንፈስን በተላበሰ ወይም ትህትናን በተሞላበት አኳኋን ሲይዟቸው እንመለከታለን፡፡ ይህም ለእኛ ለአሜሪካውያን ግራ አጋቢ ነገር ነው፡፡ የፈረንሳውያን ቀጣሪዎች የሠራተኞች አያያዝ፤ ለማዘዝ የፈራ ሰው ሁኔታ ይንፀባረቅበታል፡፡ በፈረንሳውያን ዘንድ የጌታ እና የሎሌ ድንበር በግልፅ የተሰመረ አይደለም›› ይላል፡፡

ቶኮቪሌ አያይዞ፤ ‹‹ይህ አስተያየት ትክክል ይመስለኛል›› ካለ በኋላ፤ ‹‹እኔም ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነት አስተያየት መስጠቴን አስታውሳለሁ፡፡ በኔ አመለካከት በእንግሊዝ የጌታ እና የሎሌ ግንኙነት ድንበር ጠበቅ ያለ ሲሆን፤ በተቃራኒው በፈረንሳይ ውስጥ ዘና ያለ ነገር ይታያል፡፡ እንደኔ ገጠመኞች፤ ‹ጌታ› እጅግ ከፍ ብሎ ወይም ዝቅ ብሎ የሚታይባቸው፤ እንደ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ያለ ሐገር አይቼ አላውቅም›› በማለት አትቷል፡፡

‹‹ታዲያ በኒህ በሁለት ፅንፎች መካከል የተቀመጠች አንዲት ሐገር አለች፡፡ እሷም አሜሪካ ነች፡፡ የሦስቱን ሐገራት ሁኔታ የተመለከተ ሰው ከፍ ብሎ ከተገለፀው ነገር የተለየ ግንዛቤ ሊይዝ አይችልም›› የሚለው ቶኮቪሌ፤ ‹‹ታዲያ የእነዚህ ነገሮች መንስዔ ምንድን ነው?›› የሚል ጥያቄ አንስቶ፤ መልስ ለማግኘት ነገሩን በዝርዝር ማየት አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ማብራሪያውን ይቀጥላል፡፡

ግን የቶኮቪሌን ማብራሪያ ከማየታችን በፊት፤ ከሦስት እና ከአራት አስርታት በፊት፤ የእኛን ሐገር ‹‹የጌታ›› እና ‹‹ሎሌ›› ግንኙነት ምን እንደሚመስል ለማሳየት ‹‹አደፍርስ›› በተሰኘው የዳኛቸው ወርቁ ልቦለድ የሚገኙ ሁለት ገፀ ባህርያት የሚያደርጉትን ውይይት አንስቻለሁ፡፡ ተረኩ፤ በዲሞክራሲያዊ ስርዐት ውስጥ የ‹‹masters›› እና የ‹‹servants›› ግንኙነት ምን እንደሚመስል ለማሳየት ያግዛል፡፡ ወይዘሮ አሰጋሽ፤ ቸግሮት እህል ሊበደር የመጣ አንድ ጭሰኛ ጋር ይነጋገራሉ፡፡ ‹‹በመንገድ ስንገናኝ ሸረር ብሎ መንገድ አለቀቀልኝም፤ አግዘኝ ብለው እምቢ አለ›› በሚል ቂም ይዘውበታል፡፡ እናም ነገር እያሳቀሉ እንዲህ ይሉታል፤

‹‹[እግዚአብሔር] የበደሉትን ሰዎች እግሮች ተንበርክኮ ያጥባል – እንደፈለጋችሁ – እንደምላዳችሁ – እንደ ስሜታችሁ ኑሩ የሚል ይመስላል ለብልሃቱ፡፡ አንድ ቀን የሱን ትልቅነት የሱን ወሰን የለሽነት፤ የሱን አይመረመሬነት ዘንጋ ያልን ጊዜ ድራሻችንን ሊያጠፋ፡፡ ሊያመጣው ውርጅብኙን፡፡ ሥልጣናችሁን በደንብ አልተጠቀማችሁበትም – ለክብሬ የሚገባኝን አላቀረባችሁልኝም- ….ስለዚህ እኔም የምሰራውን አውቃለሁ ሊለን… ተጓባቢውን ጎረምሳ፣ ጥጋብ የነፋውን፣ በዱላ የሚመላጎደውን ዱለኛ፤ ለባለርስቱ፣ ለባላባቱ የማይታዘዘውን ገበሬ፤ አንገቱን ሰብረው ጭራውን እንደ ውሻ እንዲሸጉብ እስኪያደርጉት ድረስ – ሊለን! ሊያመጣው የጭቃ ጅራፉን……›› እያሉ፤  ያስፈራሩታል፣ ያንጣጡታል፣ ይወርፉታል፡፡

‹‹ገባኝኮ አሁን ገባኝ›› ይላል እህል ሊበደር የመጣው ጭሰኛ፡፡ እሳቸው ግን መለስ አይሉም፡፡ የነገር አኮርባጃችውን ይሰነዝራሉ፤ የጭቃ ጅራፋቸውን ያለ ፋታ ይሰነዝራሉ፡፡ ወ/ሮ አሰጋሽ፤ ያን ‹‹ይገባኝል….ይገባኛል›› እያለ የሚለማመጣቸውን ጭሰኛ፤ ኑሮውን እና እግዚአብሔርን እየታከኩ፤ ደግሞም ‹‹ቆይ ቆይ ልጨርስ!…›› እያሉ በወቀሳና በትችት ዱላ ያርበደብዱታል፡፡

‹‹ቆይ ቆይ ልጨርስ! እግዚአብሔር ሁልጊዜ ማስታወሻ ነገር ይልካል፣ ለሚረሱት ሁሉ፡፡ ማጉረምረም የለብንም – ለኛ ሲል ነው የሚያደርገው – እንዲገባን ያሻል፡፡ አስቀድመን አስታውሰነው በነበር፤ እሱም በበትረ መንግስቱ ባልረሳን፤ የፈለግነውን በሰጠን ነበር -ጤፍ – ስንዴ – ገብስ – ማሽላ – ባቄላ – ጨረቂት ያውልህ የፈለገህን ያህል ባለን ነበር፡፡ አሁን ግን ይኸውልህ – የእጅህን ፈለግ፣ የእግርህን ንቃቃት፣ የለበስከውን ቡትቶ…›› ይሉታል፤ እሬሳ ላይ የሚተኩሱት ወ/ሮ አሰጋሽ፡፡ ጭሰኛው እየደጋገመ፤ ‹‹ምንኮ አላጣሁትም….›› እያለ ቢለምናቸውም፤ ወ/ሮ አሰጋሽ መለስ አይሉለትም፡፡፡

‹‹ዐውቃለሁ እመየቴ!

‹‹ምናልባት ታውቀው ይሆናል፤ ግን አዙረህ ብትመለከት፣ ሥራ ላይ እንዳልዋለ ልትረዳ ትችላለህ፡፡ አሁን ለምሳሌ ትንሽ ማሽላ ልትበደር መጣህ፡፡ እርግጥ ነው፤ የዛሬን አያድርገውና አክባሪዬና መልካም ሰው ነበርህ፡፡ ነገር ግን አምና ትዝ ይልህ እንደሁ፤ ትዝ ይልሃል፤ ርግጠኛ ነኝ፤ ላጨዳና ለውቂያ እንድታግዘኝ ብጠይቅህ ምን ብለህ ነበር የመለስክልኝ? ‹ደህና ዋል ስልቻ፣ ፍሬውን ከትቻለሁ› …. ራሴንም አላጨድሁ – የራሴንም አልወቃሁ፤ እኔም የሚረዳኝ እፈልጋለሁ! አላልክም? ለመንግስት እኮ ግብር ከፋይ ነኝ፤ ግዳጅ የለብኝም እስከዚህ አላልክም? አምቧትረህብን ነበር እኮ በል፤ ታዥረህብን ነበር! ‹ዝናብ ባይመጣ ሁሉ ቤት፤ እንግዳ ባይመጣ ሁሉ ሴት!› አዎ፤ ርግጥ ነው፤ ግዳጅ የለብህም …. ግን እየው…. እየው…. ጊዜው ባይሆንልህ፤ እንዲህ ሱልል ብለህ፤ ጭራህን እንደ ቡችላ ስታወናውን -! ‹የወደዱትን ቢያጡ፤ የጠሉትን ይቀላውጡ!› በኔ ላይ ተንዣርረህብኝ ነበር…   

‹‹‹ጠጉራም ውሻ አለ ሲሉት በራብ ይሞት› የለም…?

‹‹በጣም ኩሩ ነህ፡፡ ስለዚህ ነው ችግር የጎለሰሰህ … ግን ምን ታደርግ፤ ‹አወራ ዶሮ በየፍጉ ክምር ላይ ቆሞ ይጮሃል› … እኔን ተመልከተኝ ለምሳሌ – አዎ እግዜር ሞገሱን፣ ንጉሠ ነገሥቴ ክብርን አልነሡኝም፡፡ ሆኖም አልኮራም፤ እንዴት ልኮራ እችላለሁ? ማነኝና! ትል ለራሴ! ትንሽ ፍጥረት – ምናምን! ግን እንደምታየው ራሴን ዝቅ ዝቅ በማድረጌ እግዜርና ንጉሤ ከፍ ከፍ አደረጉኝ በፊታቸው … በሰማያዊ ኃይል የጎለበተ እንዲህ ነው ይኸውልህ … እግዜር ሞገሱን ሰጥቶ፤ በንጉሤ ፊትም ሞገስ እንዳገኝ አደረገኝ…

‹‹የዱሮው ጊዜ ይሻል ነበረ እመየቴ፤ እንዲህ እንደ ዛሬው ሳይሆን ባላባትና ገበሬ የሚተሳሰቡበት …

‹‹እንዴታ ምን ጥርጥር አለው እንዲህ እንደዛሬ የጌታና አሽከር መንገራበብ ያልነበረበት- በየጊዜው የሚያፈጠፍጥ ክፉ ዐመል … ጥሩው ጊዜ አለፈ፤ ዓለማችሁን ያያቸሁበት – አደንጓሬው፣ በቆሎው፣ ደንጎሎው፣ ጨረቂቱ፣ ዘንጋዳው … ምን ያረጋል ብቻ ያለፈውን ቢያስታውሱት? አሁን ማስታወሱ አይበጅም፡፡ ዱሮ ዱሮ ነው – ስለዱሮው የረሳሁትን. ..! ‹ፍላጻ ባየር ውስጥ አለፎ ፍለግ አይተውም!› እና አሁን ታዲያ የመጣኸው ትንሽ ዘንጋዳ ለመበደር ነው አልክ …?››

‹‹ነበራ እመየቴ ማስቸገሬ ባይሆን…

‹‹ለመግዛት ነው የምትፈልገው…?

‹‹ከየቴ እመየቴ፤ ብሩ ከየት ተገኝቶ? በዚያው ባይነቱ ለመክፈል ነው እንጂ በትሣሥ…

እንግዲህ ወደ አሌክሲስ ቶኮቪሌ እንመለስ፡፡

የቶኮቪሌ እይታ

ከፍ ሲል በጠቀስነው ተረክ የሚታየው ሁኔታ በቅድመ አብዮት ኢትዮጵያ የነበረውን ህይወት የሚያሳይ ነው፡፡ በቅድመ አብዮት ኢትዮጵያ የዘር ግንድ እየቆጠሩ በፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ብዙሃኑን የነበሩ ንጉሣውያን ቤተሰብ፣ መሳፍንት፣ መኳንንት ወዘተ…  ነበሩ፡፡ የኅሩያን ምስፍና መንግስታዊ አስተዳደር (Aristocracy) ሊባል የሚችል አገዛዝ ነው፡፡ ቶኮቪሌ ንጽጽር ሲያደርግ፤ በዲሞክራሲ እና በኅሩያን ምስፍና አስተዳደሮች የሚገኙ ‹‹ጌታ›› እና ‹‹ሎሌ››ዎችን ወስዶ ነው፡፡ የኅሩያን ምስፍና በህብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ባላቸውና ‹‹ምርጥ›› ነን በሚሉ ጥቂት ሰዎች የመንግስት ሥልጣን የተያዘበት የአገዛዝ ስርዐት ነው፡፡ ይህ በአብዛኛው እውን የሆነው በባሪያ አሳዳሪውና በፊውዳሉ ሥርዐተ ማህበሮች ውስጥ ነው፡፡ የኅሩያን ምስፍና መንግስታዊ አስደዳደርን የሚደግፉ የፖለቲካ ፈላስፎች (አፍላጦን፣ ስፒኖዛ፣ ሆብስ ወዘተ) እንደሚሉት ‹‹የሀገር አስተዳደር እና የመንግስት አመራር ውስብስብ በመሆኑ ከፍተኛ ችሎታና ልዩ ሰዎችን የሚጠይቅ ነው፤ ስለዚህም ከማንኛውም ዜጋ የተውጣጣ ኃይል ሊያካሂደው አይችልም፡፡ የዚህ ዐይነቱ ኃላፊነት በትውልድ ለተመረጡ፤ በተለየ ስጦታቸውና የችሎታ ብቃታቸው ለላቁ ለተወሰኑ ምርጥ ሰዎች መሰጠት አለበት፡፡

እኩልነት በሌለበት ወይም የበላይ እና የበታችነት የኑሮ ዘይቤ በሰፈነበት ማህበራዊ ስርዐት፤ በአገልጋዮቹ እና በጌቶቻቸው መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገዛ፤ የጨዋ እና የባለጌነት ሚዛን እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ በመሳፍንታዊ ሐገራት የሚገኝ አንድ ደሀ፤ ገና ከህፃንነቱ ጀምሮ ከመታዘዝ መንፈስ ጋር ይዛመዳል፡፡ ዓይኑን ወደ የትኛውም አቅጣጫ ቢወረውር፤ የማህበረሰቡ የበላይ እና የበታችነት መዋቅር ይታየዋል፡፡ በየቦታው የታዛዥነት ህይወት ይጋፈጠዋል፡፡

ከፍ ሲል ያየነው፤ የወ/ሮ አሰጋሽ እና የጭሰኛው ዓይነት ግንኙነት በብዙ መሳፍንታዊ ሐገሮች የሚታይ ነው፡፡ በነዚህ ሐገሮች ውስጥ የሚኖር ጌታ፤ ከአገልጋዮቹ ማቅማማት የሌለበት ፈጣን እና ፍፁም ታዛዥነትን በቀላሉ ያገኛል፡፡ አገልጋዮቹ ለጌቶቻቸው የሚያሳዩት አክብሮት፤ ለአንድ ጌታ ሳይሆን ለጠቅላላ መሳፍንታዊ መደቡ የሚሰጥ ክብር ነው፡፡ ጌታው፤ የአገልጋዩን ፈቃድ (will) የሚጫነው፤ በመሳፍንቱ መደብ አባላት ሰዎች ጥቅል ክብደት ልክ እንጂ በአንድ ግለሰብ መጠን አይደለም፡፡

ጌታው የተገዢዎቹን ድርጊት ፍፁም ይወስናል፡፡ በተወሰነ ደረጃም ሐሳባቸውን ይገዛል፡፡ በመሳፍንታዊ ስርዓት ውስጥ ጌታው (አንዳንዴም ሳያውቀው) በተገዢዎቹ አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል፡፡ አኳኋናቸውን እና ባህርያቸውንም ይቀርፃል፡፡ በጥቅሉ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ካለው ስልጣን እጅግ በጣም የሚበልጥ ነው፡፡

በመሳፍንታዊ ስርዐት ውስጥ ከዘር ወደ ዘር የሚሸጋገር የ‹‹ሎሌነት›› እና ‹‹ጌትነት›› ይኖራል፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ የአንድ አሽከር ቤተሰቦች ለአንድ ጌታ ቤተሰቦች ለተከታታይ ትውልዶች ተገዢ የሚሆኑበት ሁኔታም ይኖራል፡፡ እንደ ሁለት ትይዩ መስመሮች መቼም የማይገናኙ ግን የማይለያዩ ሆነው ይዘልቃሉ፡፡ የሁለቱ መደቦች አባላት ሰዎች ግንኙነት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያለው ጉዳይም ይህ ነው፡፡ ስለዚህ በመሳፍንታዊ ህብረተሰብ ውስጥ ጌታና ሎሌ ምንም ዓይነት የባህርይ ዝምድና ባይኖራቸውም፤ በማህበራዊ መሰላሉ አንዱ ከአንዱ እጅግ የተራራቁ ቢሆኑም፤ እንዲሁም በትምህርት በአስተሳሰብ ፍፁም ቢለያዩም፤ በቀላሉ የማይበጠስ ትስስር ይዘው ይዘልቃሉ፡፡

በመሳፍንታዊ ሥርዐት ውስጥ አገልጋይ ያለው ሥፍራ የተዋራጅነት ነው፡፡ ከዚህ የተዋራጅነት ቦታ የሚያወጣው የለም፡፡ ሁሌም፤ ከሱ በላይ ሌላ ሰው አለ፡፡ ከሱ ደረጃ ከፍ ያለ ደረጃ የተቀመጠ ጌታ አለ፡፡ ሎሌውም ሆነ ጌታው ቦታቸው የፀና ነው፡፡ በአንድ በኩል፤ ‹‹አባ ከና›› የሚለው የማጣት፣ የድህነት እና የተገዢነት የዕድሜ ልክ ዕጣ ፈንታ ሆኖ ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል ዝና፣ ሀብት እና አዛዥ- ናዛዥነት ዘላለማዊ መስሎ ቆሟል፡፡ እነኝህ ሁለት መደባዊ ማንነቶች፤ እንደ ትይዩ መስመሮች የተለያዩ እና ሁልጊዜም ጎን ለጎን የሚኖሩ ናቸው፡፡ እነኝህን ሁለት መደቦች የሚያገናኛቸው ገመድም ዘላቂና ዘላለማዊ ነው፡፡

ቶኮቪሌ ይህን መጣጥፍ በፃፈ ጊዜ፤ ፈረንሳይ ውስጥ የጥንቱ መሳፍንታዊ ስርዓት ርዝራዥ የሆኑ ሎሌዎች አልፎ አልፎ ይታዩ እንደ ነበር ገልጧል፡፡ ‹‹ሆኖም በቅርብ ጊዜ ‹ዘራቸው› ጨርሶ ይጠፋል›› ብሎ ነበር፡፡ አሁን ሄደን ድፍን ፈረንሳይን ብንዞር አናገኛቸውም ይሆናል፡፡ እኛ ዘንድ ግን የሁለቱም ‹‹ጎሳ›› አባላት አሁንም በህወይወት እንዳሉ በእርግጠኝት መናገር ይቻላል፡፡

እንደ ፈረንሳይ ሎሌዎች ያሉ ሰዎች በአሜሪካ ጉብኝቱ እንዳልገጠሙት የጠቀሰው ቶኮቪሌ፤ አሜሪካውያን እንዲህ ያሉ ሰዎችን አይተው አያውቁም ብቻ ሳይሆን፤ ስለነዚህ ሰዎች ብትነግሯቸውም ለመረዳት እጅግ ይቸገራሉ ይላል፡፡ ሆኖም፤ በፈረንሳይ እንዲህ ያሉ ሰዎች እንዲፈጠሩ ካደረገው ስርዓት መወገድ ጋር ቀስበቀስ የሎሌ መንፈስ ተሸክመው የሚገኙ ሰዎች እየጠፉ መሆኑን ይናገራል፡፡

ዲሞክራሲ

በተቃራኒው፤ የዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ አባላት አንዱ ከአንደኛው ጋር ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ሆኖም፤ አንዱ ለሌላኛው ሁልጊዜም እንግዳ ነው፡፡ ከእኩልነት ስርዓት መፈጠር ጋር፤ የድሮዎቹ ‹‹ሎሌ›› እና ‹‹ጌታ››ዎች አዲስ ሰውነት ይይዛሉ፡፡ አዲሱ ስርዐት የሁለቱን መደቦች ተነፃፃሪ ማኅበራዊ ቦታ እንዲቀየር አድርጎታል፡፡ ማህበራዊ ምህዳሩ ከሞላ ጎደል የእኩልነት ባህርይ ሲይዝ፤ ሰዎች በኑሮ አውድ ውስጥ የሚይዙት ቦታ ያለማቋረጥ የሚለወጥበት ሁኔታ አለ፡፡ በዲሞክራሲያዊ ስርዐት ውስጥ ‹‹የጌቶች›› እና ‹‹የአሽከሮች›› መደብ መኖሩ አልቀረም፡፡  ሆኖም፤ የእነዚህ መደቦች አባላት የሆኑት ሰዎች ሁልጊዜም አንድ ዓይነት ሰዎች ወይም አንድ ዓይነት ቤተሰቦች አይሆኑም፡፡ ይቀያየራሉ፡፡ የአዛዥነት ዕድል ያገኙት እና የታዛዥነት ዕጣ የደረሳቸው ሰዎች እንዲያ እንደሆኑ ሊቆዩ አይችሉም፡፡ ታዛዡ ሰው፤ ‹‹ታዛዥ እንደሆንኩ ዕድሜዬን እገፋለሁ›› የሚል ስጋት ሊኖረው እንደማይችል ሁሉ፤ አዛዡም፤ ‹‹ያለ አንዳች ስጋት ሁልዜም እንዳዘዝኩ እኖራለሁ›› የሚል መተማመን የለውም፡፡ አገልጋዮቹ የተለየ መደብ አይፈጥሩም፡፡ ስለዚህ የተለየ ባህርይ፣ ዝንባሌ ወይም የእነሱ ብቻ መገለጫ የሚሆን አድራጎት አይኖቸውም፡፡ የእነሱ ልዩ መገለጫ ሆኖ የሚጠቀስ የአስተሳሰብ እና የስሜት ዝንባሌ የላቸውም፡፡ ከማህበራዊ አቋማቸው የመነጨ ጥሩ ወይም መጥፎ ምግባር ተብሎ የሚነሳ ነገር የላቸውም፡፡ ይልቅስ፤ የዘመነኞቻቸውን የትምህርት፣ የአስተያየት፣ የስሜት፣ የጥሩ ወይም መጥፎ ምግባር ባህርያትን ይጋራሉ፡፡ ያው ጌታ እንደሚባሉት ሰዎች ሐቀኛ እና ሸፋጮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የአሽከሮቹ የኑሮ ሁኔታ ያን ያህል ከጌቶቹ የተለየ አይደለም፡፡ ምክንያቱም፤ በመሳፍንታዊው ስርዐት እንደምንመለከተው፤  በሁለቱ ቡድኖች መካከል የማይለወጥ የደረጃ፣ የማዕረግ ወይም የታዛዥነት መገለጫ የለም፡፡ የትንሽነት ወይም የታላቅነት መገለጫ ባህርይ የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ ‹‹በአውሮፓ አሁንም ርዝራዡ ያልጠፋውን የአሽከሮች መደብ ባህርይ እና ድርጊት እንዳስታውስ የሚያደርግ ሰው አሜሪካ ውስጥ አልገጠመኝም›› የሚለው ቶኮቪሌ፤ ‹‹በፈረንሳይ እንዳለው lackey የሚል ቃል በአሜሪካ አልሰማሁም፡፡ የሁለቱ መደቦች መገለጫ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ድራሻቸው ጠፍቷል›› ይላል፡፡

በዲሞክራሲ ውስጥ አገልጋዮቹ እርስ በእርስ የሚበላለጡ አይደሉም፡፡ ፍፁም እኩል ናቸው፡፡ እኩልነታቸው እርስ በእርስ ብቻ ሳይሆን፤ በሆነ መንገድ ካየነው ከጌቶቻቸውም እኩል ናቸው፡፡ ይህን ሐሳብ በደንብ ለመረዳት ነገሩን ትንሽ አፍታቶ ማየት ይጠይቃል፡፡

አንድ ሎሌ በማናቸውም ጊዜ ጌታ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእርሱ በላይ ወዳሉት ሰዎች መድረስን ይመኛል፡፡ ስለዚህ አገልጋዩ ከጌታው የተለየ ሰው አይደለም፡፡ ታዲያ ጌታው የማዘዝ መብቱን ያገኘው፤ ሎሌው የታዥነት ግዴታ የተጫነት በምን ምክንያት ነው?  በዲሞክራሲ ስርዐት በነፃ ፈቃድ ከተመሠረተው ጊዜአዊ ስምምነት ሌላ፤ ታዛዡን እና አዛዡን የውል ግዴታ ውስጥ የሚያስገባ ምን ነገር አለ?

በተፈጥሮ አንዱ ከሌላው ያነሰ አይደለም፡፡ አንዱ የሌላው ታዛዥ የሆነው በጊዚያዊ ስምምነት ነው፡፡ ከዚህ የውል ስምምነት በመነጨ ሁኔታ አንዱ አዛዥ ሌላው ታዛዥ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጭ ሁለቱም ሰዎች የአንድ ፖለቲካዊ ህብረት ዜጋ የሆኑ ሁለት ሰዎች ናቸው፡፡ ይህም ነገር በታዛዡም ሆነ በአዛዡ ህሊና ተቀባይነት አግኝቶ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡ ታዛዦቹ የሚገኙበትን የኑሮ ሁኔታ የሚመለከቱት ከአዛዡ ሰው በተለየ አይደለም፡፡ የስልጣን እና የታዛዥነቱ ድንበር በግልፅ የተሰመረ እና በሁለቱም ህሊና ውስጥ መልስ አግኝቶ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡

የሚበዛው የፖለቲካ ማህበረሰቡ አባላት የኑሮ ሁኔታ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ሆኖ ውሎ ካደረ እና እኩልነት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ብዙ በቆየበት ሁኔታ፤ የህዝቡን አስተሳሰብ የሚያዛባ ልዩ ግምት የሚያገኝ ሰው በሌለበት ሁኔታ፤ የሰውን ልጅ ዋጋ የሚወስን አንድ አጠቃላይ ገመታ ይፀናል፡፡ ለአንድ ሰው ከተሰጠው ‹‹ሲቪክ ዋጋ›› በላይ ወይም በታች የሆነ ዋጋ የሚሰጠው ሰው አይኖርም፡፡

በዲሞክራሲ ስርዐት፤  ሐብት እና ድህነት፤ አዛዥነት (ስልጣን) እና ታዛዥነት (ተመሪ) መሆን፤ በመካከላቸው ትልቅ ልዩነት ወይም ርቀት መጋረጡ አይቀርም፡፡ ሆኖም፤ የዘወትራዊ ህይወት ስርዐት ላይ ተደላድሎ የተቀመጠው ህዝባዊ አስተያየት ወይም ህሊና (public opinion)፤ ይህን ልዩነት ጎትቶ ወስዶ በአንድ ሰልፍ ያቆመዋል፡፡ በዚህም በሁለቱ ሰዎች መካከል ያለው ተጨባጭ የኑሮ ሁኔታ ልዩነት እንዳለ ሆኖ፤ ሌላ ሐሳባዊ የእኩልነት መንደር በመፍጠር እኩል አድርጎ ያስተካክላቸዋል፡፡ ይህ ፍፁም ኃያል የሆነ የህዝብ አስተያየት፤ ሌላው ቀርቶ ይህን አመለካከት እንዳይቀበሉና ግድግዳ ሰርተው እንዲከላከሉ የሚያደርግ ጥቅም ካላቸው ሰዎች ልብ ዘልቆ በመግባት፤ መሻታቸውን በማንበርከክ በህሊና ዳኝነታቸው ላይ ተፅዕኖ ያሳርፍበታል፡፡ ስለዚህ፤ ጌታ እና የሎሌዎች፤ ከጥልቅ የልባቸው በኣት ገብቶ ያደረና ሥር ሰድዶ የተቀመጠ ልዩነት በመካከላቸው መኖሩ አይሰማቸውም፡፡

በተለመደ የነገሮች ስርዓት ላይ ተመስርቶ የሚፈጠረው የህዝብ አስተያየት፤ ሁለቱንም ወገኖች ጎትቶ ወስዶ በአንድ ደረጃ ላይ እንዲቆሙ ያደርጋቸዋል፡፡ ተጨባጭ የኑሮ አቋማቸው ውስጥ የሚታየው ተጨባጭ ልዩነት (የበታች እና የበላይ እንዲሆኑ ያደረገው ነገር) እንዳለ ሆኖ፤ በሁለቱ ወገኖች ህሊና ምናባዊ እኩልነት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡

ይህ ኃያል ጉልበት ያለው አመለካከት፤ ተጨባጩ ጥቅማቸው እኩልነቱን እንዳይቀበሉ ከሚገፋፋቸው ሰዎች ልብ ውስጥ እንኳን ዘልቆ በመግባት፤ የውስጥ ምኞት እና ፍላጎታቸውን አንበርክኮ፤ ለነገሮች በሚሰጡት ዳኝነት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በእኩልነት እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል፡፡

በጌታ እና በሎሌው ህሊና ጥልቅ የእኩልነት እምነት ተፈጥሯል፡፡ ሁለቱም በመካከላቸው ጥልቅ መሠረት ያለው ልዩነት መኖሩን የሚያምኑ አይደሉም፡፡ በማናቸውም ሰዓት፤ አንዱ አንደኛውን ለመገናኘት በፍርሃት ወይም በተስፋ አይጠብቅም፡፡ ስለዚህ፤ አንዱ በሌላው ላይ የቁጣ ወይም የንቀት ስሜት የለውም፡፡ አንዱ ሌላውን በመለማመጥ ወይም በኩራት ስሜት አይቀርበውም፡፡ ‹‹በጌታው›› ዘንድ ያለ ትልቅ ብቸኛው የስልጣን ምንጭ የስራ ስምምነቱ ነው፡፡ በተመሳሳይ፤ ‹‹ሎሌው›› ለቀጣሪው እንዲታዘዝ ምክንያት የሚሆነው ብቸኛ ነገር ይኸው የሥራ ስምምነት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ጌታው የማዘዝ መብት እንዲያገኝ፤ ሎሌው የመታዘዝ ግዴታ እንዲቀበል የሚያደርግ ነገር የላቸውም፡፡ ሁለቱም ሚናቸውን ያውቁታል፡፡ ከሚናቸው ጋር በተያያዘ ፀብ ውስጥ አይገቡም፡፡ ሁለቱም ወገኖች በየበኩላቸው የሚጠበቅባቸውን ነገር ያውቁታል፡፡ አውቀውም ያከብሩታል፡፡

አሌክሲስ ዲ. ቶኮቪሌ (Alexis de Tocqueville)፤ በምሣሌ የሚያነሳው አንድ ነገር አለ፡፡ በፈረንሳይ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በተራ ወታደርነት የሚቀጠሩት እና በመኮንንነት የሚያገለግሉት ሰዎች ብዙ ጊዜ ከተወሰነ መደብ የሚወጡ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እናም ከሁለቱም መደቦች የተውጣጡት የሠራዊቱ አባለት፤ በሰራዊቱ የሚሰጣቸው ኃላፊት ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፡፡ ሆኖም፤ ከወታደራዊ ማዕረጉ ውጭ የበታቹ ከበላዮቹ ጋር ፍፁም እኩል እንደሆነ ያስባል፡፡ በተጨባጭም እኩል ናቸው፡፡ ሆኖም፤ ወታደራዊ ተግባሩን በሚያከናውንበት ጊዜ፤ የበላዮቹን ትዕዛዝ ለመቀበል ፈፅሞ አያመነታም፡፡ ታዛዥነቱ፤ በጎ ፈቃደኝነትን የተጎራበተ፣ ተፈጥሯዊ የመሰለ እና ወትሮ ዝግጁነት ያልተየው ነው፡፡ ይህ ምሳሌ፤ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ በጌታ እና በሎሌ መካከል ያለው ግንኙነት ምን እንደሚመስል ፍንጭ ሊሰጠን የሚችል ነው፡፡

እነዚህ ሰዎች ያለ አንዳች ማቅማማት የሚታዘዙትን ይሰራሉ፡፡ ሆኖም፤ ከቀጣሪያቸው ወይም ከሚያዛቸው ሰው በተፈጥሮ እንደሚያንሱ የሚያስቡ አይደሉም፡፡ እነዚህ ሰዎች የዲሞክራሲ ስርዐት የወለዳቸውን ባህርያት ተላብሰው፤ በነፃ ፈቃዳቸው የገቡበትን የሥራ ውል አክብረው፤ ሳይሸፍጡ በጀግንነት የሚኖሩ ናቸው፡፡ አዛዦቻቸውን ለማታለል ሳይሞክሩ፤ የሰጧቸውን የሥራ ኃላፊነት በአግባቡ የመወጣት የባህርይ ብቃት ያላቸው ራሳቸውን የሚያከብሩ ጀግኖች ናቸው፡፡ አዛዦቹም ከሠራተኞቻቸው የሚፈልጉት፤ የሥራ ውላቸውን አክብረው፤ በታማኝነት እና በትጋት እንዲሰሩላቸው እንጂ፤  እንዲያሸረግዱላቸው ወይም እንዲወዷቸው ወይም ‹‹እኔ ከርሱ ሌላ…›› የሚል ፍቅር እና መስዋዕትነትን አይደለም፡፡ እንደ ሠራተኛ፤ ጥንቅቅ ያለ ሥራ እንዲሰሩ እና በሐቀኝነት እንዲያገልሏቸው ብቻ ይፈልጋሉ፡፡

ሆኖም በኛ ሐገር ቀጣሪዎች ከዚህ የተለየ ባህርይ ያሳያሉ፡፡ ሠራተኞቹ እንደ ቤት ሠራተኛ ቢሆኑለትም ይፈልጋል፡፡ ሠራተኞቹ ዕድሜ ልክ፤ ‹‹ራሳቸውን የማይችሉ›› የእርሱ አገልጋዮች መሆናቸውን ተቀብለው፤ በዚህም ኮርተው እንዲኖሩ ይሻል፡፡ ሆኖም አንድ ቀን ተቀጣሪ አገልጋይነታቸውን ትተው ቀጣሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዲሞክራሲ ስርዐት መቀጠር እንደ መሳፍንታዊ ስርዓት አዋራጅ ባህርይ የለውም፡፡ ምክንያቱም፤ ግንኙነቱ በነፃ ፈቃድ የሚወሰን እና አገልጋይነቱም ጊዜአዊ ነው፡፡

በህዝብ ህሊና ውስጥ ተቀባይነት ያለው አስተሳሰብ፤ በቀጣሪ እና በተቀጣሪ መካከል ያለው መበላለጥ ጊዚያዊ እና ሊለወጥ የሚችል መሆኑን የሚቀበል አስተሳሰብ ነው፡፡ ሠራተኛው ታዛዥነትን የሚጠይቅ ግንኙነት ውስጥ እንደ ገባ ያውቃል፡፡ ግን ይህ ግንኙነት ጠቃሚ ሆኖ ስለታየው በነፃ ፈቃዱ የገባበበት እና በርትቶ በመስራት ሊቀየር የሚችል ግኙነት መሆኑን ያምናል፡፡ አንዳንዴ፤ እኩልነቱ ከንቱ ህልም ሆኖ እየታየው ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ ስለዚህ አንዳንዴ በልቡ ያምፃል፡፡ ‹‹በእርግጥ እኩልነት የሚገኘው በዲሞክራሲ ክበብ ውስጥ ነው ወይስ ከዚያ ውጪ?›› የሚል ሐሳብ ሊፈጠርብት ይችላል፡፡ ጥቅም ስለሚያገኝበት ማገልገልን ይፈልጋል፤ ግን መታዘዝ ስላለ ቅር ሊሰኝ ይችላል፡፡ በዲሞክራሲ ስርዓት ውስጥ ያሉ ተቀጣሪዎች፤ ከአገልግሎት የሚገኘውን ጥቅም እንጂ አዛዣቸውን አይወዱትም፡፡ ‹‹በዲሞ ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› ማለት ይቻላል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy