NEWS

በጋምቤላ ክልል በተካሄደ የኦዲት ምርመራ ከ349 ሚሊዮን ብር በላይ ጉድልት መታየቱ ተገለፀ

By Admin

August 06, 2018

በጋምቤላ ክልል በመንግስት መስሪያ ቤቶች በተካሄደ የኦዲት ምርመራ ግኝት ከ349 ሚሊዮን ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድልት፣ የሰነድ ክምችትና ያልተገቡ ክፍያዎች ተፈጽመው መገኘታቸውን የክልሉ ኦዲተር ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ጀኔራል ዋና ኦዲተር አቶ ጋርዊች ኩን የቢሮውን የዕቅድ አፈጻፀም ለክልሉ ምክር ቤት ጉባዔ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት በ2010 በጀት ዓመት በተለያዩ መስሪያ ቤቶች የኦዲት ምርመራ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በኦዲት ምርመራው መሰረት በክልሉ 18 የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከ5 ሚሊዮን 300ሺህ ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት እንደተገኘባቸው ተግልጿል፡፡

በክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ 15 ሚሊዮን 700ሺህ ብር ያልተገባ የውሎ አበል፣ ከኮንትራት ውል ውጪ ክፍያና በበጀት ዓመቱ ያልተሰራ መንገድ እንደተሰራ ተደረጎ መከፈሉን በኦዲት ምርመራ ተደርሶበታል፡፡

ስድስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች በውክልና ከሰበሰቡት ገቢ ከመንግስት ፋይናንስ መመሪያ ውጪ ለስራ ማስኬጃ አውለው መገኘታቸውንም አቶ ጋርዊች ገልጸዋል፡፡

ከክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የቀረበውን የሂሳብ ሪፖርት መሰረት በማድረግ በተከናወነው የኦዲት ግኝት መሰረት በጥቅሉ ከ187 ሚሊዮን ብር በላይ በክልሉ በሚገኙ 42 መስሪያ ቤቶች፣ በዞንና በወረዳ በሚገኙ ጽህፈት ቤቶች ያልተወራረደ የሰነድ ክምችት እንደተገኘም ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም እስከ ወረዳ በሚገኙ መስሪያ ቤቶች ከ137 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፋይ የሰነድ ክምችት መኖሩንም አመልክተዋል።

ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ በኦዲት ግኝቶች መሰረት የገንዘብ ማስመለስና ከአቅም በላይ የሆኑትንም ጉዳያቸውን በህግ እንዲታይ የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይም የመንግስትና የህዝብ ሐብት የፋይናንስ መመሪያን ባልተከተለ መልኩ ለብክንት እንዳይደርግ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመው ለስኬቱ የምክር ቤቱ ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባ አቶ ጋርዊች ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በበጀት ዓመቱ አበረታች ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል።