Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ባለውለታዎቹ

0 391

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ባለውለታዎቹ

                                                          ይሁን ታፈረ

አሁን የምንገኝበት ወቅት የግብር መክፈያ ነው። በመሆኑም በሁሉም አካባቢ የሚገኘው ግበር ከፋይ የህብረተሰብ ክፍል ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል። እስካሁን ድረስ ህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ ለመክፈል የሚያደርገውን ጥረት የሚበረታታ ነው። ይሁን እንጂ ሙሉ ለሙሉ እየተፈጸመ ነው ለማለት አያስደፍርም።

ግብር ዓላማው የዜጎችን ህይወት ለመቀየር በሚከናወን ልማት ላይ የሚውልና ዜጎች ከመንግስት የሚያገኟቸውን አገልግሎቶች ለማከናወን የሚያስችል የተሟላ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። በአሁኑ ሰዓት ግብራቸውን በወቅቱ እየከፈሉ ያሉ ዜጎች የዚህች አገር ባለውለታዎች ናቸው። በግብር ከፋይነታቸው ኩራት የሚሰማቸው ዜጎችም ናቸው። ሌሎች ወገኖችም የእነዚህን ባለውለታዎች አርአያነት በመከተል ግብራቸውን በወቅቱ መክፈል ይኖርባቸዋል።

መንግስት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በርካታ ውጥኖችን ይዟል። በተለይም የህዝቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚችሉ የመሰረተ ልማትና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ነው። እነዚህን ፕሮጀክቶች ለማስፈፀም በቂ በጀት ሊኖረው ይገባል።

ይህን በጀት ማግኘት የሚችለው ደግሞ ከህዝቡ ከሚሰበስበው ግብር ነው። ምንም እንኳን መንግስት መጠነኛ ብድርና እርዳታ የሚያገኝ ቢሆንም ዋነኛው የልማት ማሳለጫው በጀት ግን ከህዝቡ የሚሰበስበው ግብር ነው። እናም ግብር መክፈል እነዚህን መንግስታዊ ዕቅዶች ለማስፈፀም ያግዛል።

የህዝቡ ግብር በጥሩ ሁኔታ ለታለመለት ግብ ከዋለ የመንግሥት ጠቅላላ ገቢ በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 199 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በሁለተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጨረሻ ዓመት በሆነው በ2012 ዓ.ም ወደ 627 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ከፍ ይላል። በ2012 ዓ.ም ከሚጠበቀው ገቢ ውስጥ 605 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር የሀገር ውስጥ ገቢ የሚሰበሰብ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ይህም አገራችን በዕቅድ ዘመኑ አሳካዋለሁ ብላ ላቀደቻቸው የልማት ስራዎች የሚውል ይሆናል።

ከዚህ ውስጥ መንግስት ዕድገትን በማፋጠን ድህነትን ለማስወገድ የሚረዱ የድህነት ተኮር ዘርፎች አወጣዋለሁ ብሎ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ላይ ለያዛቸው የልማት ፕሮጀክቶች 469 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እንዲደርስ ያደርገዋል።

ይህም ከጠቅላላ የመንግስት ወጪ 64 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ እቅዱ ያመላክታል። እንግዲህ እነዚህ እውነታዎች የሚያሳዩን ነገር ቢኖር በመንግስት የሚከናወኑት ማናቸውም ስራዎች በዋነኛነት ህዝቡ በሚከፍለው ግብር ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ ለፓርላማ እንዳስረዱት የ2011 ዓ.ም በጀት ውስጥ 64 በመቶው ለድህነት ተኮር የልማት ስራዎች የተያዘ ነው። ይህ የበጀት ድልድል እንደ እኛ ላለ ድህነትን ለመቀነስ እየተረባረበ ላለ ሀገር ትርጉሙ ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው።

በጀቱ የኢትዮጵያን ዕድገትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ፤ ድህነትን ለመቅረፍ ለሚያስችሉ የልማት ስራዎች የሚውልና የዜጎችን የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲያድግ የሚያደርግ ነው።

ከአጠቃላይ በጀቱ ውስጥ 16 በመቶው ለክልሎች የሚፋፈልና የታዳጊ ክልሎችን ልዩ ፍላጎት መሙላት የሚያስችል ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይም የያዘ ነው። ይህም በህገ መንግስቱ ላይ ታዳጊ ክልሎችን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች ከኢኮኖሚ አኳያ ያላቸውን እኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው። የሁሉም ክልሎች ተጠቃሚነትና እኩልነት እንዲረጋገጥ ደግሞ ዜጎች ግብር መክፈል ይኖርባቸዋል። ድህነት ተኮር ስራዎቹ የሚከናወኑት ህዝቡ በሚከፍለው ግብር ነውና።

በአገራችን የተገነቡትና እየተገነቡ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ገንዘብን የሚጠይቁ ናቸው። በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተሰርተው ዜጎችን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ አሁንም ገንዘብ የግድ አስፈላጊ ነው። እንደሚታወቀው በሁለተኛው የዕድገት ዕቅድ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ድርሻ በአሁኑ ወቅት ከሚገኝበት በአራት እጥፍ እንዲያድግ በማድረግ ወደ መጀመሪያው የመካከለኛ ጉዞ መንገድ ለመድረስ ለታለመው ዕቅድ እስከ 18 በመቶ የማድረስ ግብን ይጥላል።

በአገራችን እንዲፈጠር የታሰበውን መዋቅራዊ ለውጥ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚናው ሁነኛ ማሳያ ነው። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ ሲታይ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ከአስር በመቶ አይበልጥም። ይህን አሃዝ ከፍ ለማድረግ ገንዘብ ያስፈልጋል።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንጂ ለብቻው ተፈፃሚ እንዲሆን ብቻ አይደለም። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ኢንቨስትመንትን ዕውን ከማድረግ አኳያ መቆራኘት ይኖርበታል።

ይህን ዕውን ለማድረግም በአሁኑ ወቅት ያሉትም ይሁኑ በቀጣይ ወደ ስራ የሚገቡት ኢንዱስትሪዎች፤ መንግስት የቴክኖሎጂ አቅማቸውን፣ ምርታማነታቸውን፣ የጥራት አመራር አቅማቸውን ብሎም ተወዳዳሪነታቸውን በቀጣይነት መገንባት ይችሉ ዘንድ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል።

እነዚህን ድጋፎች ለማድረግ አሁንም ገንዘብ በበቂ ሁኔታ መገኘት ይኖርበታል። ይህ ገንዘብ የሚገኘው ደግሞ ህዝቡ ከሚከፍለው ግብር ነው። ስለሆነም ግብር መክፈል እንዲህ ዓይነቶቹን ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ መንግስታዊ ስራዎችን የሚፈጥሩ ናቸው።

ለአገር የሚያስብ ወገን ግብሩን በሰዓቱ በመክፈል መንግስት የአገርንና የህዝብን ደህንነት እንደሚያስጠብቅ፣ ልማትን እንደሚያፋጥን፣ እድገትን እንደሚያመጣና ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ትግል የሚደግፍ ነው። ለውጡንም የሚያግዝ ነው።

ለአገርና ለወገን የሚያስብ ዜጋ ግብር መክፈልን እንደ እዳ ሳይሆን እንደ መብት የሚቆጥር ነው። ለአገር የሚሰራ ነገር ዕዳ ሳይሆን መብት ስለሆነ። እናም የግብር ወቅት ሲደርስ ግብር የሚከፍለው የዜግነት ግዴታውን ለመወጣትና መብቶቹንም ከመንግስት ለመጠየቅ መሆኑን ይገነዘባል።

ይህን አውቀው ግብራቸውን የሚከፍሉ ዜጎች የዚህ አገር ባለውለታዎች ናቸው። በአሁኑ ሰዓት እየታየ ባለው ሁኔታ የግብር አከፋፈሉ የሚያበረታታ ነው። ባለውለታዎቹ ግብራቸውን በጊዜው እየከፈሉ ነው። እስካሁን በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግብራቸውን ያልከፈሉ ዜጎች የባለውለታዎቹን አርአያነት በመከተል አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።  

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy