Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ባንደመር ኖሮ…

0 454

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ባንደመር ኖሮ…

                                                         ዋሪ አባፊጣ

የመደመር ፅንሰ ሃሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ባህር ተሻጋሪ ሆኗል። በዓለም ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የሃሳቡ ባለቤቶች ሆነዋል። በተለይም የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በሚገኙባቸው በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራችን የተያያዘችውን የይቅርታ፣ የፍቅርና የአንድነት ጉዞ እየተደመሩ በመቀላቀል ድጋፋቸውን አየቸሩት ነው። መደመርን ከፍ…ከፍ እያደረጉት ይገኛሉ።

የመደመር ፅንሰ ሃሳብ ለተወለዱባት ሀገራቸው ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘባቸውም፤ እነርሱም ተደማሪነታቸውን እያረጋገጡ ነው። በእውነቱ ደስታን ያጭራል። ባንደመር ኖሮ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ወገናችን አሁን እያደረገ ያለውን ያለውን የመነቃቃት ስሜትና ሀገራዊ ድጋፍ ፈፅሞ አናይም ነበር። ስለ ሀገሩ እንደ ልቡ በመዘመር የበኩሉን እገዛ ለማድረግም እንዲነሳሳ የሚያስችለው ምህዳር አይኖርም ነበር። እናም በእኔ እምነት፤ ሀገራዊ ለውጡ ባህር ተሻጋሪ ሆኖ ለዚህ አብቅቶናል።

የመደመራችን ስኬቶች ምስራቅ አፍሪካ ሀገራትንም ያካተቱ ናቸው። ሀገራዊ ለውጡ ቀጣናውንም እያካለለ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ሀገራችን በቀጣናው ላይ የሚጠበቅባትን ሚና እንድትጫወት እያደረጋት ነው። አንድ ምሳሌ ላንሳ—ሰሞኑን የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በኢጋድ አስታራቂነት በካርቱም ስለደረሱበት ስምምነት። ነገሩ እንዲህ ነው።…

ወጣቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ራሷን የቻለች ሆና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዕውቅና ካገኘች ሰባት ዓመታት ቢሆናት ነው። እነዚህ ሰባት ዓመታት ለሀገሪቱ ህዝቦች በጎ ጊዜያቶች አልነበሩም። ርግጥ ከሱዳን ጋር የረጅም ዓመታት ጦርነትን ያካሄዱት የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች ነፃነታቸውን በተጎናፀፉ ማግስት ወደ እርስ በርስ ጦርነት መግባታቸው ብዙዎችን አሳዝኗል።

በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ምክትላቸው በነበሩት ዶክተር ሪክ ማቻር መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል፤ አካላቸው ጎድሏል፤ ንብረትም ወድሟል። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ዜጎች ቀያቸውን ትተው ወደ ኢትዮጵያና ወደ ሌሎች ጎረቤት ሀገራት እንዲሰደዱም ምክንያት ሆኗል። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ባደረጋቸው ጥረቶች የኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውታለች።

በተለይ ዶክተር አብይ አህመድ ወደ መንግስት ኃላፊነት ከመጡ በኋላ፤ ግጭቱ እንዲያበቃ ከኢጋድ ጋር በመሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ሁለቱን ተፋላሚ ኃይሎች በተናጠልና በጋራ በማነጋገር የዚያች ሀገር ህዝቦች ስቃይ እንዲያበቃ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል። እርቅና ሰላም እንጂ ጥላቻና ጦርነት ለየትኛውም ህዝብ እንደማያዋጣ አስረድተዋል። መነጣጠል ሳይሆን አንድነት ለአፍሪካ የሚበጅ መሆኑን አብራርተዋል። ስልጣን በያዙ ማግስትም በውጭ ጉዟቸው ወደ ኡጋንዳ በማቅናትም ከፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር በመነጋር የደቡብ ሱዳንን ግጭት በጋራ እልባት ለመስጠት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ታዲያ ይህ ጥረታቸው ከንቱ አልቀረም። በስልጣን ይገባኛል እሰጥ አገባ ሳቢያ ጦር መዘው ሲፋለሙ የነበሩት ሁለቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች፤ በሱዳን ካርቱም ላይ ስልጣን ለመከፋፈልና ዳግም ወደ ጦርነት ላለመመለስ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በስምምነቱ መሰረት ሁለቱ ተቀናቃኞች በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ የሽግግር መንግስት የማቋቋም ግብ ጥለዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ስምምነት፤ በአስር ሺህዎች ለሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጐች ሞት እንዲሁም ለሚሊዮኖች መፈናቀል ምክንያት የሆነውን ግጭት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያስቆማል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። ያም ሆኖ ተፋላሚዎቹ እዚህ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ፤ ኢትዮጵያ እንደ ወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበርነቷ፣ በደምና በባህል እንደ ተሳሰረ እህት ህዝብ እንዲሁም እንደ የሀገሪቱ ስደተኞች አስጠላይ ሀገር፤ ፋና ወጊ ሚናዋን ተወጥታለች።

በዚህ ጥረቷ ደቡብ ሱዳኖች ዘግይተውም ቢሆን የጦርነትን አስከፊነትና የሰላምን ጠቃሚነት የተገነዘቡ ይመስለኛል። ሁለቱ ወገኖች የግል ጉዳያቸውን ወደ ጎን ብለው ለህዝባቸው ለመስራት ይቅር መባባልንና ፍቅር መርጠዋል። ከሁለትነት ወደ አንድነት ተቀይረው ተደምረዋል ማለትም የሚቻል ይመስለኛል። ይህም አሁን በምንገኝበት የጋራ ተጠቃሚነት ዘመን ጦርነት፣ መቃቃር፣ በጎሪጥ መተያየትና ለግል ጥቅም ሲባል የገዛ ዜጋን ማባላት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የሚያሳይ ነው። በእኔ እምነት፤ መደመር ስኬቱ እስከዚህ ድረስ ነው—ጎረቤቶቻችንን የእኛን ፈለግ እንዲከተሉ የሚያደርግ። እናም በአዲስ አስተሳሰብ እየተመራች ያለችው ኢትዮጵያ ዛሬም የቀጣናው አውራና የሰላም ቀንዲል ሆና እየቀጠለች መሆኑ ሰሞነኛው የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች የደረሱት ስምምነት ሁነኛ አስረጅ ነው። ባንደመር ኖሮ የአብሮነት ብርሃናዊ ፋኖሳችን ለሌሎችም ባልተረፈ ነበር።  

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለ ሶስተኛ ወገን አሸማጋይነት በሁለቱ ሀገራት ፍላጎት ብቻ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ዓለምን ያስደነቀ ተግባር ነው። ለዚህም ነው—የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላም እንዲሰፍን በማስቻላቸው በፊታችን መስከረም ወር በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ስብሰባ ላይ የክብር ተናጋሪ ሆነው እንዲቀርቡና አርአያነታቸውን ለሌሎች  ሀገራት እንዲያቀርቡ በድርጅት የስዊዲን አምባሳደር ሊጠየቁ የቻሉት።

ከዚህ በተጨማሪ ሀገራችን ከጂቡቲና ከሱዳን እንዲሁም ከኬንያ ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በወደብ ማልማት ስራዎች የተፈራረመቻቸው ስምምነቶች፤ ምስራቅ አፍሪካን ከተናጠል አስተሳሰብ አራማጅነት ወደ ጋራ ተጠቃሚነት የደመሩ እሴቶች ሆነው እውቅና የተሰጣቸው ተግባራት ናቸው።

ምን ይህ ብቻ። የመደመር ፋኖሳችንን ከፍ አድርገን ከሳዑዲ አረቢያና ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ጋር ሀገራችን የፈጠረቻቸው ጠንካራ ትስስሮችን መፍጠር ችለናል። ቁርኝቱ የውጭ ምንዛሬ ጊዜያዊ ችግራችንን እስከመቅረፍ የደረሰ ነው። ይሀም ሀገራችን በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ተሰሚነቷ ምን ያህል እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ ይመስለኛል። እናም አንድ ሆነን መደመራችን ትናንት ያልነበረንን የትስስር ድር አጥብቆ ያጋመደን ሆኗል።   

ዶክተር አብይ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ አይኤም ኤፍና ወርልድ ባንክን የመሳሰሉ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማትም የእኛን የመደመር ፋኖስ የሚረጨውን ብርሃን እንዲመለከቱ አድጓቸዋል። ተቋማቱ በቅርቡ እንዳስታወቁት፤ ሀገራችን የተያያዘችውን ለውጥ እንደሚደግፉና አብረውን ለመስራት ፍላጎት አላቸው። ተቋማቱ ያሳዩት ፍላጎት ዝም ብሎ የተባለ አይደለም—ኢትዮጵያ ውስጥ እየተቀጣጠለ ያለው የለውጥ ሂደት ያሳደረባቸው ከፍተኛ እምነት እንጂ።

ያም ሆኖ፤ የተቋማቱ አብሮ እንስራ ባይነት እያደገ ላለው ኢኮኖሚዋ የገንዘብ አቅሟን ጠንካራ ማድረግ ላለባት ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ትርጉሙ ከፍተኛ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። ምክንያቱም ሀገራችን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ያቀደቻቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ስላሉ ነው። እነዚህን ፕሮጀክቶች ለመፈፀም ተቋማቱ ድጋፍ ካደረጉ፤ ሀገራችን ልማቷን በማፋጠን ወደ ህዳሴዋ ለማምራት የምታደርገውን ጥረት ሊያግዙ ይችላሉ። ይህም የህዝቡን ተጠቃሚነት በሚታይ መልኩ ለመለወጥ በሚደረገው ርብርብ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። እናም በለውጥ ሂደቱ መደመራችን ሀገራዊና ህዝባዊ ጠቀሜታው ይህን ያህል ከፍታ ያለው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ታላላቅ የገንዘብ ተቋማት ከፍተኛ አመኔታ የጣሉበት መደመራችን፤ እንደ አሜሪካና እንግሊዝ የመሳሰሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገራትንም ወደ ራሱ መሳብ የቻለ ነው። የዋሽንግተን አስተዳደር ኢትዮጵያዊያን የጀመሩትን ለውጥ እንደሚደግፍ በተደጋጋሚ ገልጿል። ለተግባራዊነቱም በቅርበት አብሮን ለመስራት ቃል ገብቷል። የእንግሊዝ መንግስትም በቅርቡ ለሀገራችን የልማት ስራዎች የሚውል የ115 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ ሰሞኑን አድርጓል። እነዚህ ሁሉን አቀፍ ድጋፎች ስለተደመርን ያገኘናቸው ናቸው።

ባንደመር ኖሮ፤ በውጭ የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የለውጠ አካል ሆነው አይንቀሳቀሱም ነበር። ባንደመር ኖሮ፤ የቀጣናችን የሰላም ፋኖስ ሆነን ጎረቤቶቻችን የፍቅርና የእርቅ ዋንጫን ከፍ አድርገው እንዲያነሱ ማድረግ አንችልም ነበር። ባንደመር ኖሮ፤ የልማት አጋሮቻችን ከጎናችን ባልሆኑ ነበር። በሀገራት ኢኮኖሚያዊ ግስጋሴ ላይ የበኩላቸውን ድርሻ የሚጫወቱት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትም ‘አይዞን’ ባላሉን ነበር። ተፅዕኖ ፈጣሪ ምዕራባዊያን የገንዘብና የሃሳብ ድጋፍ ባላደረጉልን ነበር።

ባንደመር ኖሮ፤ የለውጡ መሃንዲስ ዶክተር አብይ አህመድ በመጪው መስከረም ወር በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባዔ ላይ የክብር ተናጋሪ ሆነው በመቅረብ አርአያነታቸውን ለሌሎች ሀገራት እንዲያካፍሉ ባልተጠየቁ ነበር።…ሌላ ሌላም ህልቆ ማሳፍርት ጉዳዩችን እንድንከውን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጎ ዕይታ ውስጥ ባልገባን ነበር። እናም ለውጡ የፈጠረውን መደመራችንን እንደ ዓይናችን ብሌን ልንጠብቀውና ሂደቱም እየጎለበተ እንዲሄድ በማድረግ ኢትዮጵያዊያን ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል እላለሁ።        

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy