Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተመራቂ  ተማሪዎች ስለቫይረሱ  ያላቸው ግንዛቤ

0 438

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ተመራቂ  ተማሪዎች ስለቫይረሱ  ያላቸው ግንዛቤ

ሰናይት አበራ

 

ይህ ወቅት ብዙ ወጣቶች ዬኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቀው የሚመረቁበት ወቅት ነው፡፡ እነዚህ ወጣች ወሳኝ ወደ ሆነው የሕይወት ምዕራፋቸው የሚሸጋገሩበትም ጊዜ ነው፡፡ ብዙ ዘመን በሌሎች ድጋፍ ይኖሩ ከነበረው ሕይወት ተላቅቀው ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለሀገራቸው ቁም ነገር ለመሥራት የሚዘጋጁበትም ነው፡፡ ሕልማቸው እውን እንዲሆን፣ ሐሳባቸው እንዲሳካ ግን ጤናማ ሆኖ መገኘትን ይጠይቃል፡፡ ሰው ከራሱ አልፎ ለሌሎች ብሎም ለሀገር አንዳች ነገር ማድረግ የሚችለው ጤናማ ሲሆን ነው፡፡ በመሆኑም ወጣቱ  ለራሱ ወይም ለሀገሩ መሥራት ያለበትን ነገር መሥራት እንዲችል ራሱን ከቫይረሱ መጠበቅ ቀዳሚ ተግባሩ መሆን ይኖርበታል፡፡ ቀጥሎም ሌሎችን ለመጠበቅ የሚያውቀውን ማስገንዘብንና ማስረዳትን የዕለት ዕለት ተግባሩ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በተጨማሪም ወጣቶቹ ተመራቂዎች በአንድ በኩል በተማሩበት ሙያ ህብረተሰቡን በማገልገል በሀገሪቷ ዕድገትና ልማት ውስጥ የራሳቸውን አስተዋዕኦ ማበርከት ሲኖርባቸው በሌላ በኩል ደግሞ በወጣቶቹም ሆነ በማህበረሰቡ ዘንድ የተዘነጋውን የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት ባገኙበት አጋጣሚ ተጠቅመው ማስተማርና ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል።

 

ይህንን አስመልክተን አንድ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን ያነጋገርን ሲሆን ከነዚህም መካከል ወጣት አስቻለው ጥላሁን አንዱ ነው፡፡ በማስተርስ ዲግሪ በቋንቋ፣ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል የተመረቀ ወጣት ነው።

 

ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ ምን አይነት ግንዛቤ እንዳለውና የሚያስከትለው ጉዳት ጠይቀን ነበር። እንደ ወጣቱ ገለፃም ቫይረሱ የሚያደርሰው ጉዳት ከባድ ነው፡፡ ይህ ቫይረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በእያንዳንዱ ግለሰብ ሕይወት ላይ ጉዳት ያደርሳል፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ የቫይረሱን ስርጭት ትኩረት ሰጥቶ ማሰቡ የራሱ አንድምታ ይኖረዋል፡፡ ለውጥ ከግለሰብ ይጀምራል። ግለሰቦች በየራሳቸው የሚያስቡት፣ የሚኖሩት የሚያቅዱት ተደምሮ የሀገር ውጤት ይሆናል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዳችን  ለቫይረሱ ሥርጭት አንዳች ትኩረት ሰጥቶ ማሰብ እንደሚጠበቅብን አስገንዝቧል፡

ለምሳሌ ያህልም እሳት በባሕሪው እርጥቡን ከደረቅ፣ ምርቱን ከግርድ ፍሬውን ከገለባ ሳይለይ ያቃጥላል፡፡ ለእሳት የተጋለጠ የትኛውንም ነገር ዳግም ለጥቅም ማዋል ያስቸግራል፡፡ የእሳት ጎጂነት የበለጠ የሚከፋው ደግሞ ፍግ ውስጥ ሲሆን ነው፡፡ ፍግ ውስጥ ያለ እሳት ልኩ አይታወቅም፤ መጠኑም አይገለጥም፡፡ የፍግ ውስጥ እሳት ጎጂነት የሚታወቅው ሁሉን ካወደመ በኋላ ነው፡፡  እንደ ፍግ ውስጥ እሳት አውዳሚ የሆነው ኤች አይ ቪ በአሁን ሰዓት በገሀድ ሳይታይ ውስጥ ለውስጥ እያረሰ ያለው ጉዳት ከባድ ነው ፡፡ የፍግ ውስጥ እሳትን ቁብ ሚሰጠው እንደሌለ ሁሉ ይህንን በሽታም በአሁን ሰዓት ከቁብ የቆጠረው ሰው ያለ አይመስልም። ነገር ግን ኤች አይ ቪ ውስጥ ውስጡን እየጎዳ ነው፡፡ ጉዳቱ ከግለሰብ ይጀምራል፡፡

 

አንድ ሰው ጤናማ ካልሆነ ሰርቶ ማግኘት፤ በልቶ ማደር አይችልም፡፡ ስለዚህ አልፎ የሌሎች ሸክም ይሆናል ይላል ወጣቱ ተመራቂ፡፡ በዚህ ምክንያት ከግለሰቡ ጀምሮ እስከ ሀገር ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት ማድረሱ አይቀርም፡፡ ማኅበራዊ ግንኙነትም እንዲናጋ በማድረግ የሚያደርሰው ጉዳት ቀላል አይሆንም፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተደምረው የሀገርን ኢኮኖሚ ማኅበራዊ እሴቶች እና ሌሎችንም ጉዳዮች ይጎዳሉ በማለት ያለውን አስተያየት ይገልጻል፡፡

 

እንደ ወጣት አስቻለው  ኤች አይ ቪ ኤድስን መከላከል የሚጀመረው ከራስ ነው። አንድ ሰው እራሱን መጠበቅ ካልቻለ ሌሎቹን መጠበቅ አይችልም፡፡ በዚህ ምክንያት የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል ማድረግ የሚችለው ቀዳሚው ተግባር እራስን መጠበቅ ነው፡፡ ከዛ በኋላም ሁሉም ግለሰብ ከቫይረሱ እራሱን መጠበቅ ከቻለ ሥርጭቱን መግታት ይችላል፡፡ ከዚያ ባሻገር በዚህ ጉዳይ ላይ ከግለሰቦች ጋር ውይይት ሲደረግ ጉዳቱን በማስረዳት ሰዎች እንዲገነዘቡ ለማድረግ ጥረት ለማድረግ ፍላጎት አለው፡፡

 

ሌላው ተመራቂ  አቶ ስንታየሁ ኤርሚያስ ይባላሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተርስ ዲግሪ በቋንቋ፣ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል ተመርቀዋል።  ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ያላቸውን አስተያየት እንዲህ በማለት ይገልፃሉ። ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት ኤች አይ ቪ ኤድስ የብዙ ሰዎች የመነጋገሪያ ርእስ ነበር:: በዚያን ወቅት ሁሉም ዜጋ ስለ በሽታው አስከፊነት ይናገር ነበር:: የሚድያ ተቋማቱም ቀን ከሌሊት ሲዘግቡ የነበረው ስለዚህ አስከፊ በሽታ ብቻ ነበር:: ኮንዶም በሽታውን ለመከላለከል አይነተኛ መፍትሄ ተደርጎ በየቢል ቦርዱና በየኤሌክትሮኒክስ ሚድያው ለሕዝቡ ይቀርብለት እንደነበር አስታውሰው በዚህ መሰረት የቫይረሱ ስርጭት ጥሩ ነው በሚባል ደረጃ ቀንሶ ነበር።

 

ሆኖም ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዚህ አስከፊ በሽታ ዜና ከመንግሥት አካላትም ሆነ ከግብረ ሠናይ ድርጅቶች በኩል ትኩረት ተነፍጎታል:: ስለ በሽታው ተዘውትሮ ባለመነገሩ ምክንያት የጤና ጥበቃሚኒስቴር በቁጥጥር ሥር እንዳዋለው ያህል ግንዛቤ: ተወስዷል: ይህ ደግሞ መዘናጋትን በመፍጠሩ የቫይረሱ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመስፋፋት ብዙ ወገኖችን በመጉዳት ላይ ይገኛል። በተጨማሪም የቫይረሱ ስርጭት ከፍ ብሏል:: በበሽታው ምክንያት የአልጋ ቁራኛ የሆኑትም ቤቱ ይቁጠራቸው:: በዚሁ በሽታ ምክንያት የሚሞቱ ወገኖችም ብዙ ናቸው:: ጸረ ኤች አይ ቪ ኤድስ መድሀኒት የሚወስዱት ወገኖችም በርካታ ናቸው:: ስለዚህ ከድሮው የተቀየረ አንዳችም ነገር የለም ባይ ናቸው::

እንደ አቶ ስንታየሁ አገለላለጽ በዚህ ረገድ የሚመለከተው አካል የሚጠበቅበትን ሥራ ከመሥራት ታቅቧል:: ምናልባት በነዚህ ጊዜያት ውስጥ የተቀየረው የእኛ አመለካከትና አስተሳሰብ ብቻ ነው:: ይኸውም ስለ በሽታው የምንሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን ነው:: እኛ እንደ ሕዝብ ተዘናግተናል:: እንዲያውም ዝም ብዬ ስመለከተው ኤች አይ ቪ ጉዳይ ከመንግሥት እና ከማኅበረሰቡ እይታ ራዳር ውጪ እየሆነ ነው:: እንደኔ እንደኔ በእኛ ዘንድ ዘና ማለት በዝቷል:: በተለይም ይህ መዘናጋት በእኛ በአዳጊ ሀገራት ዘንድ ሲሆን ውጤቱ በእጅጉ የከፋ ይሆናል ብለዋል፡፡

 

ስለዚሀ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች ለዚህ አስከፊ በሽታ ትኩረት ሰጥተው እራሳቸውንና ሌላውን የማኅበረሰቡን ክፍል ጤናውን እንዲጠብቁ ግንዛቤ ማሰጨበጥ ይጠበቅባቸዋል:: ምክንያቱም የተማረው ማኅበረሰብ ከዚህ ችግር ካልወጣ በሀገር ደረጃ የሚከሰተው ጉዳት ከፍተኛ ስለሚሆን ነው:: እሳቸውም እንደ አንድ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ማኅበረሰብ ለበሽታው ትኩረት በመስጠት ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከዚህ አስከፊ በሽታ መጠበቅ ይፈልጋሉ:: ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው ጤና መጠበቅ የበኩላቸውን አስተዋፆኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ለሌሎች አቻ ተመራቂዎችም በሚሄዱበት ማህበረሰብ ውስጥ ስለ ቫይረሱ ጎጂነት ግንዛቤ በመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለባቸው ይመክራሉ።

 

በአጠቃላይ በሀገራችን ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት በተደረገ ጥናት እድሜያቸው ከ15-24 የሚሆኑ ወጣቶች ስለኤች አይቪ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ እንደሆነና በተለይም ደግሞ በዚህ የእድሜ ክልል ከሚገኙ ሴቶች 76 በመቶ የሚሆኑት የኤች አይቪ መተላለፊያ እና መከላከያ መንገዶችን እንደማያውቁ ታውቋል። እናም በኢትዮጵያ ከአፍላ ወጣቶች ግንዛቤ ማነስ ጋር በተያያዘ የኤች አይቪ ስርጭትም በዚሁ የእድሜ ክልል ከፍተኛ መጣኔ እንደሚታይበት የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ስለዚህ ተመራቂ ተማሪዎችም ከተማሩበት ትምህርት ክፍል ጎን ለጎን ለቫይረሱ ስርጭት ትኩረት በመስጠት ለራሳቸውም ሆነ ህብረተሰቡን መታደግ ይኖርባቸዋል ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy