Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተስፋዎቻችን እንዳይጨናገፉ

0 433

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተስፋዎቻችን እንዳይጨናገፉ

ገናናው በቀለ

ሰሞኑን የተለያዩ አገራት ልዑካን ቡድኖች አገራችንን ጎብኝተዋል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ከእነዚሁ ሀገራት ጋር ተወያይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ባለሃብቶች ጋር በመሆን የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክን የጎበኙ ሲሆን፤ ጉብኝቱም ከአራት ወራት ወዲህ የተገኘው የዲፕሎማሲ ድል ማሳያ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ልዑካን ጋር በመሆን የጎበኙት የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት እና ወደ ውጭ በመላክ ኢኮኖሚያችንን ለማሳደግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ወደፊት ኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ በሚደረገው ስራ የራሱን በጎ ሚና ይጫወታል።

በተመሳሳይም የኤርትራ ልዑካን ቡድን በአገራችን ጉብኝት ማካሄዱን እና የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ላይ የፈጠረው ጫና የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከድንበር በላይ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን እየተገነዘብን ነው።

በአሁኑ ሰዓት የአሰብ-ምፅዋ መንገድ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በመተባበር በመጠረግ ላይ ከመሆኑም በላይ፣ የአሰብና የምጽዋ ወደቦች የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ንግድ ለማስተናገድ የሚችሉበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው። ይህም ለአገራችን አማራጭ የወደብ አገልግሎት የሚያስገኝ ነው። በመሆኑም እነዚህና ሌሎች የዲፕሎማሲያችን ታላላቅ ተስፋዎች በመጠነኛ ቀውሶች የተነሳ እንዳይጨናገፉ ህዝቡ ለውጡን ነቅቶ መጠበቅ ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በሀገራችን ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው ለውጥ የአገሪቱን ገፅታ ከመለወጡ ባሻገር፤ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረኮችም ተሰሚነቷንና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ እንዲል አድርጓል። በለውጡ ሳቢያ አገራችን እያካሄደች ያለው ዲፕሎማሲ ስኬት አንዱ ማሳያ የተለያዩ አገራት ልዑካን ወደ አገራችን መምጣታቸው ነው። ይህ ጉብኝት ልማትን በመደገፍ ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው። ኢትዮጵያ ከየትኛውም የዓለም አካባቢ የሚመጡ ባለሃብቶችን ማስተናገድ የሚችል ፖሊሲ ያላት አገር ናት።

እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና በቂ የሰው ሃብት ያላት በመሆኑም አገራት ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እያደረጓት ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አማካኝነት እየተካሄደ ያለው የዲፕሎማሲ ስራ አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ በተገቢው መንገድ መጠቀም እንድትችል እያደረገ ነው።

በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነው። አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየት ላይ ይገኛሉ። ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚባሉት አገራት ጭምር ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ፍላጎታቸውን ከማሳየት በላይ አብረውን በመስራት ላይ ይገኛሉ።

ዲፕሎማሲው ለዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነው። በዚህ ረገድ የውጭ ባለሃብቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በመሳብ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው። የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ልዑካን ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በመሆን የጎበኙት የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የዚህ መገለጫ ነው።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮችም ከግብርና ስራቸው ጎን ለጎን በፓርኩ ውስጥ ተጨማሪ ስራ ተፈጥሮላቸዋል።  ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በሚፈልገው ሙያ ተመርቀው ስራ ያላገኙና በፓርኩ በሙያቸው መስራት የሚችሉ 50 ወጣቶች ተለይተው ወደ ውጪ ለስልጠና ለመላክ ቅድመ ዘግጀትም ተጠናቅቋል።

ዓለም አቀፍ ግዙፍ አምራች ኩባንያዎች የማመረቻ መሳሪያዎችን መትከል ጀምረዋል። በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ላይ ለመሰማራት የማሽን ተከላ ከጀመሩት ኩባንያዎች ውስጥ በዋናነት የአሜሪካ፣ የቻይና እና የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች ይገኙበታል። ኩባንያዎቹ የማምረቻ መሳሪያ ተከላ ካጠናቀቁና ግብዓቶችን ካሟሉ በኋላ ወደ ምርት ይገባሉ። የገቡም አሉ። በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክም እንደ አረብ ኢምሬቶችና ሌሎች የውጭ ባለሃብቶች ከገበቡት የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ታላቅ እገዛ ያደርጋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሁለተኛው የመንግስት የማኑፋክቸሪንግ ልማት ዕቅድ አካል ናቸው። ዋነኛ የትኩረት ጉዳይም ሆነዋል። የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለአገራችን ህዳሴ ወሳኝ ትርጉም አለው። በመፈጠር ላይ ያለው ቀጣይና ተከታታይ ዕድገት ዘላቂ እንዲሆንና የህዳሴ ጉዟችንን ለማፋጠን በዕቅዱ ዓመታት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርበታል።

እርግጥ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንጂ ለብቻው ተፈፃሚ እንዲሆን ብቻ አይደለም። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ኢንቨስትመንትን ዕውን ከማድረግ አኳያ መቆራኘት ይኖርበታል።

በአሁኑ ሰዓት ያሉትም ይሁኑ በቀጣይ ወደ ስራ የሚገቡት ኢንዱስትሪዎች፤ የቴክኖሎጂ አቅማቸውን፣ ምርታማነታቸውን፣ የጥራት አመራር አቅማቸውን ብሎም ተወዳዳሪነታቸውን በቀጣይነት መገንባት ይችሉ ዘንድ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ከዚህ አኳያ የሚታይ ነው።

እርግጥ ማንኛውም የልማት የዲፕሎማሲ የአገርን ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ ጉልህ ሚና አለው። በዲፕሎማሲው መስክ እየተሰሩ ያሉት ስራዎች ተጠናክረው ከቀጠሉ አሁን ከሚከናወነው በላይ አስተማማኝ የፋይናንስ ግኝት ማግኘት እንችላለን።

የልማት ዲፕሎማሲው ጥረት ቀጥተኛ የውጭ ምንዛሬን ከማምጣት ባሻገር በአገር ውስጥ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችንም መደገፍ ይችላል። መንግስት ይህን ታሳቢ በማድረግ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረውን የሰላም ግንኙነት ለማጠናከር አገራችንም ይሁን ኤርትራ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የአሰብንና የምፅዋን ወደብ ለመጠቀም ስራዎች እየተካናወኑ ነው።

በተለይ ከኢትዮጵያ ወደ አሰብ የሚወስደውን መንገድ ለመጥረግና የነዳጅ ቱቦ ዝርጋታ ለማከናወን የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች መዋዕለ ነዋይ እንድታፈስ የተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከፍተኛ መሆኑ ግልፅ ነው።

ይህ ተግባር መጻዒ ተስፋችን እንዲያንሰራራ የሚያደርገው ነው። ስለሆነም በአሁን ሰዓት መንግስት እያካሄደ ያለው ልማትን የሚስብ የዲፕሎማሲ ስራ ባልባሌ ጥቂት ግጭቶች እንዳይደናቀፍ ለውጡን ከምንግዜውም በላይ መጠበቅ ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy