Artcles

“ትሻልን ትቼ ትብስን” እንዳይሆንብን

By Admin

August 14, 2018

“ትሻልን ትቼ ትብስን” እንዳይሆንብን

ይቤ ከደጃች ውቤ

ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የታጩትና የተመረጡት በኢህአዴግ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባላት በተደረገ ሰፊ ምክክርና ውይይት ነው።  በኢህአዴግ መስመር ሆነው ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመረጡ ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የታዩትን ቀውሶች እንዲያስወግዱ፣ አድማዎችና ጎሣ ተኮር ብጥብጦችን እንዲያስተካክሉ፣ የሀገሪቱን አንድነት የሚያስጠብቁ ብሔራዊ መግባባትን የሚያጠነክሩ የገፅታ ግንባታን የሚፈጥሩ ሥራዎችን እንዲከውኑ መሆኑ ግልፅ ነው። ከዚህ ቀደም በተፈጠሩት ችግሮች በሞቱና በቆሰሉ ዜጎች በወደሙ ንብረቶችም ምክንያት ኢህአዴግ ቀደም ሲል አካሂዶት በነበረ ስብሰባ “በስብሰናል ችግር አለብን” ብሎ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል። ዶክተር ዐቢይ አህመድም በፓርላማ በኢህአዴግ ስም ይቅርታ መጠየቃቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

በሀገሪቱ አንፃራዊ ሠላም ሰፍኖ በየጊዜው ሲደመጡ የነበሩ ሁከትና እልፈት (ሞት) ቢቀንሱም አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች አልፎ…አልፎ የምንሰማው ሁከትና ግጭት የዕለት ተዕለት ክስተት እየሆነ ነው። በአንዳንድ የሶማሌ አካባቢዎች ከሰሞኑ ችግር ቢከሰትም የዋሁና ገራገሩ የኢትዮ ሶማሌ ሕዝብ በእንዲህ ዓይነት ርካሽ ተግባር ተሳታፊ እንደማይሆን ሀገር ሁሉ የሚያውቀው ዕውነታ ነው። የግጭቱ ዓላማ ኃይማኖትን በኃይማኖት ላይ ለማነሳሳት ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም አርቆ ሃሳቢው የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ በእንዲህ ዓይነት ሁከት ለመሳተፍ እንደማይፈልግ በተግባር አሳይቶናል። እንዲህ ዓይነቱ አኩሪ ተግባር ሊቀጥል ይገባል። ሁከት ጠንሳሾችንም መምከርና መገሰፅ አልታረም ካሉም ለፀጥታ አካላት አሳልፎ መስጠት ከሠላም ፈላጊ ዜጎች ይጠበቃል።

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ተጥሶ፣ ሥርዐተ አልበኝነት ነግሦ በጥቃቅንና አነስተኛ በተደራጁ ሁከት ፈጣሪዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ችግር እየተከሰተ መሆኑ አልፎ…አልፎ የምንሰማው ሂደት ሆኗል። ‘ይኼ የኛ ድንበር ነው ይኼ የኛ ብሔር  አይደለም’ እያሉ፤ ዜጎችን እያፈናቀሉ፣ ሰው እየገደሉና እያቆሰሉ የእምነት ተቋማትም እየተቃጠሉ ንብረቶች እየወደሙ በፀጥታ አካላት አስቸኳይ ጥበቃና ከለላ የማይደረግላቸው ከሆነ ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበሩት ቀውሶች የሚደገሙበት ዑደት ነው የሚሆነው።

ኢህአዴግ አዲስ አመራር ቀይሮ ላለፉት ሦስት ዓመታት የታዩት ቀውሶችና ሁከቶች እየረገቡ የማይሄዱ ከሆነ የሥልጣን ሽግሽጉ “ትሻልን ትቼ ትብስን” እንዳይሆንብን እንሰጋለን። በተለያዩ ክልሎች በተፈጠሩ ቀውሶች ምክንያት ንብረት አፍርተው፣ ጥረው፣ግረው የሚኖሩ የተለያዩ ብሔሮች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ዕርዳታ ጠባቂ ሆነዋል። ይኼ ደግሞ ዞሮ…ዞሮ በኢህአዴግ ላይ የሚዘዋወር ችግር ነው የሚሆነው። አሁንም አመራር በመቀየር ለመፍታት ጥረት ቢደረግ ሂደቱ ዕቃ…ዕቃ ጨዋታ ነው የሚሆነው። የብሔራዊ ምርጫ ጊዜ እየተቃረበ ከመሆኑ አንፃር የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ትጥቃቸውን ፈተው እየተሰለፉ ስለሆነ ኢህአዴግ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን ጠብ ጫሪዎችን ሁከት ፈጣሪዎችን በፀጥታ ኃይሎቹ እልባት ሰጥቶ ለፓርቲውም ሆነ ለሀገሪቱም ተቀባይነት የሚያስገኝ የሠላምና የፅሞና ጊዜ በመፍጠር ለልማት መጣደፍ አለበት።

እስካሁን በተፈጠሩት ችግሮች  የተወሰኑ ቡድኖች ላይ ፊት ማጥቆርም ሆነ ጣት መቀሰር አሊያም ጠጠር መወርወር እንኳን አይገባም። የፀጥታ አካላትም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ነቅተውና ተግተው መወጣት መቻል አለባቸው። የመንግሥት አካላትም የተረከቡት ኃላፊነት ‘በተፈጠረው ሁከት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልፃለን’ ብለው የሀዘን መግለጫ ማሰማታቸው ብቻውን እኛም  ጥልቅ ሀዘን እንዲሰማን ከማድረግ ውጪ ፋይዳ ያለው አይደለም። ትልቅ ፋይዳ የሚኖረው ሕዝቡን በማፅናናትና በማረጋጋት እንደ ኤሊ ያዘገመ ሳይሆን እንደ ብርሃን የፈጠነ የሠላምና ማረጋጋት ርምጃ ሲወስዱ እንዲሁም ህክምናና የምግብ ዕርዳታ ለማድረስ ሲጥሩ ማየት ነው። የብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ዓላማው አደጋ ለሚያጋጥማቸው ዜጎች አስቸኳይ የሆነ የምግብና የአልባሣት ድጋፍ መስጠት ይመስለኛል። ዜጎች ችግር ደርሶባቸው እየተዘጋጀሁ ነው፤ እየሰራሁ ነው ብሎ ማዝገሙ በተጎጂዎች ሕይወት ላይ መቀለድ ነው። አዲሱ ለውጥ ያማረና የሰመረ እንዲሆን መንግሥትና ሕዝብ  እጅና ጓንት ሆነው ለሠላምና ፀጥታ ዘብ መቆም አለባቸው።

በሰሞኑን ጉዳት ደርሶባቸው ምግብና መጠጥ አጥተው በጅግጅጋ በረሃብ የተቸገሩ ዜጎች እንደነበሩ ከመገናኛ ብዙሃን የሰማነው እውነታ ነው። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው አህያ ዓይነት አመለካከት ያላቸው አመራሮችና አኩራፊዎች ከሁከቱና እልቂቱ ጀርባ ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል። ጉዳቱ ደርሶም በአስቸኳይ የህክምና ዕርዳታና የምግብ ድጋፍ በሚመለከታቸው አካላት የማይደርስላቸው ከሆነ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ተጨማሪ ጉዳት ነው። ይህም ለሌላ ጊዜ ትምህርት ሊሆነን ይገባል።

የሠላምና ፀጥታ አስከባሪ አካላት ችግሩን በጊዜ እልባት በመስጠት ረገድ ዘገምተኝነት ታይቶባቸዋል። ቀደም ሲል በኢትዮ ሶማሌና በኦሮሚያ ድንበር አካባቢዎች በተከሰቱት ችግሮች ለተፈናቀሉ ዜጎች  በጊዜ እልባት ቢሰጥ ኖሮ ከሰሞኑ የሰማነውን ሁከት፣ ሞትና እልቂት አናየውም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ ፋና ወጊ ርምጃ አሳይተውናል። ነገር ግን በአንዳንድ አካባቢዎች ልብ ወጊ ሁከቶች እየታዩ ነው።  በርግጥም እንደ ደርግ ወታደራዊ ርምጃ እና ግድያ አንጠብቅም። በዚህ በኩል መንግሥት የተኮነነበት ነገር አልታየም። ለውጥ አልጋ በአልጋ ሊሆን ባይችልም መሰናክሎችን ለመፍታት ግን ጥረት መደረግ አለበት።

በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዜጎች በፈለጉበት አካባቢ የመዘዋወር፣ ሀብት የማፍራትና የመኖር መብት አላቸው። ዜጎች በክልላቸው ሲኖሩ እነ እከሌ የኔ ብሔር ጎሣ አይደሉም ይውጡ በማለት ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት ማጥፋትና ንብረት መዝረፍ ሕገ መንግሥቱን መፃረር ነው። የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሁከት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ሲገባ ሕገ መንግሥቱ እየተጣሰ ነው ብሎ ማላዘን ግን ለሰው ሕይወት የማይቆሮቆሩ ሰዎች ቅሬታ ነው። እነዚህ ሰዎች በክልሎች የሰዎች ሕይወት እየጠፋ ዝም ያሉት ምናልባት መረጃው ስላልደረሳቸው ወይም ሕገ መንግሥቱ አልተጣሰም ብለው ስላሰቡ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ከሁከቱ አትራፊዎች ሊሆኑ ይችላሉና መጠርጠር ደግ ነው።