Artcles

ችግሮችን በሰከነ መንፈስ…

By Admin

August 03, 2018

ችግሮችን በሰከነ መንፈስ…

                                                         ሶሪ ገመዳ

በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ ግጭቶችና ችግሮች መንስዔዎችን መለየት ይገባል። ተዋንያኑ እነማን ናቸው? ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል። ይህን በማድረግ የግጭቶቹና የችግሮቹ መንስኤዎች ከየትኛውም ህዝብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው መገንዘብ ይቻላል።

የግጭቶቹ ተዋንያኖቹም ጥቅሞቻችን ተነክቷል የሚሉ ጥቂት አካላት መሆናቸውንም ለመረዳት አይከብድም። ከዚህ በተጨማሪ የተከሰቱትን ችግሮቹን ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ጥረትን በመገንዘብ የጥረቱ ተደማሪ አካል ለመሆን ያግዛል። ይህም በአንድ ግጭት ወቅት ህብረተሰቡ የሚኖረውን ሚና በመገንዘብ የመፍትሔው አካል እንዲሆን የሚያግዘው ይመስለኛል።

እርግጥ ህብረተሰቡ እነዚህ ጥቂት አካላት ቆስቋሽነት ችግሮች ሲፈጠሩ በተረጋጋ መንፈስና በምክንያታዊ አስተሳሰብ በመመራት ችግሮቹን በውይይት መፍታት ይኖርበታል። እንዲህ ዓይነቱ ችግሮችን በሰከነ መንፈስ የመመልከት ባህልን ማዳበር የህዝብን ህይወትና ንብረት ከጥፋትና ከውድመት የሚታደግ ሁነኛ ተግባር ነው። ሰላምን ለማምጣት በሚደረገው መንግስታዊ ጥረት ውስጥ ተደማሪ መሆን ይገባል።

የሰላምን ጥቅም ሁሉም የአገራችን ዜጋ በሚገባ ይገነዘባል። በተለይም የጎሳ መሪዎች ለህብረተሰቡ ቅርብ በመሆናቸውና በህይወታቸው ብዙ ነገር የሚያውቁ በመሆናቸው የየአካባቢያቸውን ሰላም ወጣቱን በማስተባበር የሰላም አለመኖር ለማንኛውም ዜጋ ግልፅ ነው።

ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ስለ ዴሞክራሲ ማበበብና ስለ ኢኮኖሚያዊ እድገት መናገር ትርጉም የለውም። በመሆኑም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ መስጠት ይኖርበታል።

የሰላምና መረጋጋት እጦት ዕድገትን ያቀጭጫል። በመሆኑም ህብረተሰቡ ለሰላምና መረጋጋት በቂ ትኩረት መስጠት ብቻ ሳይሆን ሰላምና መረጋጋትን ሊያሳጡን ከሚችሉና ጥቅማችን ተነክቶብናል ከሚሉ ፀረ ለውጥ ተዋናይ ሃይሎች ራሱን ማቀብ አለበት። እነዚህን ሃይሎች በማጋለጥ ለውጡ እንዲቀጥል ማድረግ ይኖርበታል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች የለውጥ ቀልባሾችን፣ አሸባሪዎችንና ሴረኞችን ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግሮች በሰከነና ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ ፍትሐዊነትንና የህግ የበላይነትን እያረጋገጡ እንዲሁም ለሚፈፀምባቸው ማናቸውም የትንኮሳ ተግባራት ተገቢውን ምላሽ እየሰጡ ይጓዛሉ። የትኛውም መፍጨርጨር ይህን ሁኔታ ሊቋቋመው አይችልም።

ዛሬ አገራችን ውስጥ ምክንያታዊነት እየጎለበተ ነው። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ለህግ የበላይነት የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። ወጣቱ አካባቢውን ሁከት እያነፈነፉ ህግን ለመጣስ ከሚሹ አካላት እንዲጠብቅ ያደርገዋል። የሰላሙ ጠባቂ ራሱ ሆኖም የለውጥ አደናቃፊዎችን አደብ ሊያስገዛቸው ይችላል።

ወጣቱ በአሁን ሰዓት ችግሮች ቢኖሩም በምክንያታዊ አስተሳሰብ እንደሚፈቱ ያውቃል። ይህ አቋሙ ለውጥ አደናቃፊዎችን ከህግ ፊት ሲያቀርባቸው ታይቷል። ችግሮቹን በግልፅ ውይይት በማሳየትና የሚፈቱበትን አግባብ በማመለላከት ጭር የመፍትሄ አካል እየሆነ ነው።

ባለፉት ዓመታት ውስጥ ኢኮኖሚው ቢያድግም መጠነ ሰፊው ድህነት ከፍተኛ ስለነበር ሁሉንም ማዳረስ አልቻለም። ሆኖም በዶክተር አብይ መሪነት ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ወጣቱ ያውቃል። ይህ የለውጥና የነጻነት አውድ በሂደት እንደሚጠቅመውም ይገነዘባል።

በምክንያታዊነት የሚያምነው ወጣት ባለፉት ዓመታት የሚገባውን ጥቅም ባያገኝም፣ በአሁኑ ወቅት በራሱ ትግል የፈጠረው ለውጥ እንደሚጠቅመው ይገነዘባል። መንግስትና ህዝቡ በድህነት ላይ በከፈቱት ዘመቻ በዋነኛነት ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህንኑ ወጣት ነው።

መንግስት ለ2011 ዓመት የያዘው በጀት ድህነት ተኮር የሆነው በዋነኛነት ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል እንዲጠቀም ከማሰብ ነው። ሆኖም ይህን ጥቅሙን የሚጋፉ ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት ችግር ሊፈጥሩና ለየለውጡን አቅጣጫ ለማሳት ጥረት ሊያደርጉ ስለሚችሉ በየአካባቢው ዘብ ሆኖ መቆም አለበት።

ለውጡን እየመራው ያለው መንግስት የሚፈጠሩ ማናቸውንም ችግሮች የመፍታት አቅምም ይሁን ብቃቱ አለው። ወጣቶች ያሉባቸውን ጊዜያዊ ችግሮችንም ይፈታል። ወጣቱ በሚዛናዊ አስተሳሰቡ መንግስት ያለበትን ችግር እንደሚፈታ በመገንዘብ መጪው ጊዜ የእርሱ መሆኑን ማወቅ አለበት።

ወጣቱ አሁን በያዘው ህግና ስርዓትን በማስከበር ሃላፊነቱ መቀጠል አለበት። በማንኛውም ወገን መደናገር አይኖርበትም። ለውጡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ብቻ ሳይሆን ነጻነትንም አብሮ ያጎናጸፈ ነው።

በወጣቱ ትግል የተገኘውን ነፃነት ተጠቅመው ሌላ አጀንዳ የሚዘረጉ አደናቃፊዎችን በተጠናከረ ሁኔታ ሊቃወማቸው ይገባል። ያም ሆኖ ወጣቱ ስርዓቱ የእርሱ እንደ መሆኑ መጠን ሊጠብቀው ይገባል።

በተለያዩ ጊዜያት ብቅ ጥልም እያሉ በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶች መነሻቸውና መድረሻቸው ስርዓቱን በውል ካለመገንዘብ አሊያም የግል ጥቅማቸውን ለማሳደድ የሚሹ አካላት ናቸው።

እነዚህን አካላት ዓላማቸው በደም የተገኘውን ለውጥና ነጻነት ማደናቀፍ ነው። ታዲያ እነዚህን አካላት እንደ አመጣጣቸው በመመለስ አደብ ለማስገዛት መንግስት ማናቸውንም ተግባሮች እየከወነ ነው። ወጣቱም የያዘውን ምክንያታዊ አስተሳሰብ በማጠናከር ለውጡን የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት።

የለውጡን አቅጣጫ ለማሳከር የመፍጨረጨሩ አካላት የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማራመድ ሲሉ በተለያዩ አካባቢዎች ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ናቸው። እነዚህን ፀረ ለውጥ ሃይሎችን ከመገንዘብ ባሻገር ችግሮችን በሰከነ መንፈስ የመፍታት ባህልን ይበልጥ ማዳበር ያስፈልጋል።