Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኃላፊነትን እንዲህም…

0 238

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኃላፊነትን እንዲህም…

                                                           ሶሪ ገመዳ

መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃና በክልል ገበያውን ለማረጋጋት ፈርጀ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው። መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች የዋጋ ንረትን በመፍጠር ችግር በሚያስከትሉት ላይ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። እርምጃዎቹ ለህብረተሰቡ ያላቸውን ጥቅም ግልጽ ነው። የዋጋ ንረትን ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት በቅድሚያ የሚጠቅመው በንረቱ የሚጎዳው ህብረተሰብ ነው።

ስለሆነም ህብረተሰቡም ከመንግስት እርምጃዎች ጎን በመቆም የዋጋ ንረት ለመፍጠር የሚፈልጉ አንዳንድ አካላትን ተከታትሎ ጥቆማ በመስጠትና በማጋለጥ አገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል። ዜጎች ኃላፊነትን እንዲህም በመወጣት ለውጡን ያለ ችግር ማስቀጠል ይችላሉ።

መንግስት በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱን ለመፍታት ብርቱ ጥረት እያደረገ ነው። ሆኖም መንግስት ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ የለም። በመሆኑም ችግሩን ለመከላከል የህብረተሰቡ ወሳኝ ሚናውን መጫወት አለበት።

ሸቀጦች በስውር እጅ በኮንትሮባንድ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ በውድ ዋጋ እየተሸጡና ህብረተሰቡን እያማረሩት ስለሆነ እንዲህ ዓይነት ችግርን አይቶ እንዳላየ ማለፍ አይገባም። ጥቆማ በመስጠት መንግስት ማገዝ ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት ከመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችና ሸቀጦች ስርጭት አኳያ ስንዴን፣ ዘይትንና ስኳርን ጨምሮ እና የዋጋ ንረት እና እጥረት እንዳይከሰት የዋጋ ቁጥጥር እያደረገ ነው።

ህብረተሰቡ በዋጋ ንረት እንዳይጎዳ የተለያዩ የአቅርቦት ቦታዎችን በመክፈት የህዝቡን ጥያቄዎች የመለሰና በመመለስ ላይ የሚገኝ መንግስት ነው። ለዋጋ ንረት ምክንያት የሆኑ ጉዳዩችን እየዘጋ ነው። ዋጋን ሊያንሩ የሚያስችሉ ጉዳዩችን በመለየት የችግሩን መንስኤ እየተቀጣጠረ ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው። አንዳንድ ከህግ ውጭ የሚሰሩ ነጋዴዎች ከውጭ የመጡ ምርቶችን በመጋዘን አከማችተው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ነው።

እርግጥ ይህ ሁኔታ በህብረተሰቡ ይታወቃል። እንዲያውም እነዚህ ነጋዴዎች አንድን ሸቀጥ ቀደም ሲል የገባ ነው እያሉ እጥፍ ድርብ ትርፍ ለማግኘት እየጣሩ ነው። ስለሆነም ህብረተሰቡ ራሱን ከእንዲህ ዓይነት ነጋዴዎች ለመከላከል ጥቆማ በመስጠት ከመንግስት ጎን መቆም አለበት።

ህብረተሰቡ በያዝነው ዓመት የተገኘው የመኸር ምርት የዋጋ ንረትን የሚቀንስ መሆኑንና ለንረቱ የሚሰጡ ምክንያቶች ተገቢ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። በአሁኑ ሰዓት መንግስት እየተከተለ ባለው የግብርና ልማት ስትራቴጂ ትርፍ አምራች ዜጋዎችን ምፍጠር ተችሏል። እነዚህ አባቢዎች በድርቅ የተጎዱት አካባቢዎችን እየሸፈኑ ነው። ይህም የድርቅ አደጋ ተጋላጭነት ቢኖርም ችግሩን በራስ አቅም ለመቋቋም አስችሏል።

ዛሬ ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሥራው ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል።

አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ አማካይነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል። በዚህም ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው። የግብርናው ዘርፍም በአስተማማኝ ሁኔታ ገበያው ሳያሳስበው ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ ብቻ አተኩሮ ለልማት ለውጥ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል።

አርሶ አደሩን በማህበር የማደራጀት ሥራ በተናጠል ሊፈቱ ያልቻሉ ችግሮች በጋራ እንዲፈታ አስችሎታል። መንግሥት ያቋቋመው የምርት ገበያም በተለይ ቡና፣ ሰሊጥ፣ በቆሎና ቦሎቄ በዘመናዊ ግብይት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት አረጋግጧል።

ከዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሩ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የማድረግ ጥረት ለምርታማነቱ የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች የፈጠሩት ምርታማነት ለዋጋ ንረት የሚዳርጉን አይደሉም። አገር ውስጥ የሚመረተው የሰብል ምርት የዜጎችን ፍጆታ የሚሸፍን ነው። ምርታማነቱ አርሶ አደሩንም ይሁን ተጠቃሚውን እየጠቀመ ነው።

ይህ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት በሁሉም ዘርፎች ንረቱን ለመቆጣጠር ብርቱ ስራ እያከናወነ ነው። በአሁኑ ወቅት እየወሰዳቸው ካሉ ርምጃዎች መካከል የብድር ሥርዓቱን መቆጣጠር መቻሉ ተጠቃሽ ሲሆን፤ ሌላው ከነጻ ገበያ ሥርዓቱ ጋር ተያይዞ በገበያው ውስጥ የተሰራጨውን ከፍተኛ መጠን ያለው የብር ተመን ንረት እንዳይፈጠር ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ ሌሎች ማሳያዎች ናቸው፡፡

ለዋጋ ንረቱ መባባስ ምክንያት ሆነው የቆዮት ከላይ የጠቀስናቸው ጉዳዮች ብቻ አይደሉም። ከንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ የራሳቸውን ፍላጎት ለማርካት ብቻ በዋጋ በመመሳጠር ክፍተት ሲፈጥሩ የቆዩበት የአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች የኮንትሮባንድ አሰራር ሁኔታም አንዱ ነው። በስኳር፣ በዘይትና በብረት ምርቶች ላይ የሚካሄዱ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ ነው።

እንቅስቃሴዎቹ መልሰው የሚጎዱት ህብረተሰቡን ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ ምንም ዓይነት ከመልካም አስተዳደርና ከሙስና ጋር የተያያዙ ጉዳዩችን ሲመለከት ያለ አንዳች ማመንታት እርምጃ እንዲወሰድ ማመልከት ይኖርበታል። ይህም በኑሮ ውድነት ሊከሰትበት የሚችለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ያስወግድለታል።

የኑሮ ውድነት ሰው ሰራሽ ሲሆን መፍታት ይቻላል። ሰው ሰራሽነቱ የሚፈጠረው በስግብግብ ነጋዴዎች ነው። ስግብግብ ነጋዴዎች ተገቢ ያልሆነ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ምንም ነገር ከማድረግ አይቆጠቡም። ትላንት ያልገባን ዕቃ የቆየ መሆኑን በመግለጽ ህብረተሰቡን ለመበዝበዝ ይጥራሉ።

እነዚህ ነጋዴዎች እርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው። እናም የገበያውን ዋጋ ተመካክረው በህገ ወጥነት ይወስናሉ። ውሳኔዎቹም ህብረተሰቡን ሆን ብሎ ለማማረር የሚደረጉ ናቸው። በምሬትም መንግስት ላይ ቅሬታ እንዲፈጥሩ ለማድረግ ይሞክራሉ።

ይህን ፍላጎታቸውን ህብረተሰቡ በመገንዘብ መጠቆም አለበት። የዜግነት ኃላፊነትን እንዲህም መወጣት ስለሚቻል ህብረተሰቡ የችግሩን ምንጭ እያጠራ ህገ ወጥነትን በመታገል ረገድ ቁልፍ ሚናውን ማበርከት አለበት።

 

 

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy