Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኑ የሰላም ዋጋን እንተምን!

0 2,927

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኑ የሰላም ዋጋን እንተምን!

ወንድይራድ ሃብተየስ

የሰላም ዋጋ የሚታወቀው ሰላም ሲደፈርስ ወጥቶ መግባት ሲከብድ  ነው። አንድ ወዳጄ በአንክሮ እየተመለከተኝ እንዲህ አለኝ። “የሰላም ዋጋው ስንት ይሆን” ሲል ያላሰብኩትንና ያልጠበቅሁትን ጥያቄ አቀረበልኝ። ዝምታዬን ተመልክቶ  ፍንጭ ሊሰጠኝ ፈልጎ “የሰላም ዋጋ ከቶ ሊተመን ይችላልን? ሲል አትኩሮ እየተመለከተኝ ወጉን ቀጠለ “ሰላም በመገለጫው ካልሆነ በስተቀር የሚተመንበት ሆነ የሚሰፈርበት ልኬት ከቶ የለውም”  አለኝ። እውነት ነው ሰላም ልማት ነው፤ ሰላም ዕድገት ነው፤ ሰላም አብሮነትና አንድነት ነው፤ ሰላም ወልዶ ለመሳም፤ ወጥቶ ለመግባት፤ ሠርቶ ለመለወጥ፤ ነግዶ ለማትረፍ፤ ሰርቶ ለማደግ ሰላም ለሁሉም ካስማ ነው፤  በአጭሩ ሰላም የመልካም ነገሮች ሁሉ መሠረት ነች።

ኢትዮጵያዊያኖች ለሰላም የሚሰጡት ዋጋም ሆነ  ክብር እጅግ ከፍ ያለ በመሆኑ “ጠዋት ሲወጡ ሰላም አውለኝ እንዲሁም ማታ ሲገቡ ሰላም አሳድረኝ”  በማለት ፈጣሪያቸውን በመማጸን ለሰላም ያላቸውን ፍላጎት ይገልጻሉ። ኢትዮጵያዊያኖች ሰላም ምን እንዳስገኘላቸው፤ በአንጻሩም የሰላም እጦት  ምን እንዳመጣባቸው ከሌላ ሳይሆን ከራሳቸው የህይወት ልምዳቸው ጠንቅቀው ያውቁታል። የሰላም እጦት ሞትን፣ አካል መጉደልን፣ የንብረት መውደምን፣ ስደትን፣ ረሃብን፣ መታረዝን፣ ችግርን፣ ስቃይን፣ ወዘተ በአጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን አስከትሎባቸዋል።

አንዳንዶች አብዮት ሌሎች ደግሞ ሪፎርም  ቢሉትም አገራችን በፈጣን የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ናት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራች አንዳንድ አካባቢዎች እየተቀሰቀሱ ያሉ ሁከቶች አገሪቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመምራት ጥረት በመደረግ ላይ ነው።  ለሁከቶቹ መፈጠር ምክንያት የሆኑት ጥቅማችን ተነካ ወይም ሰላም ከሰፈነ ተጠያቂነት ይመጣብናል የሚል ስጋት የተፈጠረባቸው አካላት ናቸው። እነዚህ ግለኞች በሚፈጽሙት የሻጥር ፖለቲካ አብሮ የኖረውን ህዝብ በማጋጨት የለውጡን አቅጣጫ ለማስቀየር ወይም ለውጡን ለማጨናገፍ ጥረት በመደረግ ላይ ነው። እነዚህ ግጭቶች እንደው በዘፈቀደ  የሚፈነዱ ሳይሆን በርካታ ገነዘብ ፈሶባቸው ታስበውና ታቅደው የሚካሄዱ ናቸው።

የአገሪቱን ትንሳኤ ያበስራሉ የተባሉ በርካታ ፕሮጀክቶች ለአብነት የስኳርና የማዳበሪያ ፕሮጀክቶች ቢሊዮን ዶላሮችን ቆርጥመው በልተው መክነዋል።  እድገታችንን ያፋጥኑልናል፣ ይደግፉናል ያልናቸው ፕሮጀክቶች የተገላቢጦሽ ሆኖ ከደሃው ህዝብ የሚሰበሰበው ገንዘብ ብድር ከነወለዱ እንድንከፍል ምክንያት ሆነዋል።  ለአገራችን ለውጥ አንዱ ምክንያት ግለኝነትና ሌብነት በአገራችን እየገነገነ መምጣቱ እና ተጠያቂነትና ግልጸኝነት ያለመኖር ነው። ዛሬም ያን ሁኔታ ለመመለስ አንዳንድ ሃይሎች   ቀን ከሌት በመታተር ላይ ናቸው። እነዚህ ሃይሎች አልተረዱትም እንጂ ስህተትን በሌላ ስህተት ለማረም መሞከር ወደከፋ ውድቀት ያመራል እንጂ ከችግር ሊያወጣ አይችልም።

መንግስት  በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል  የነበረውን ሁኔታ በትዕግስትና አርቆ አሳቢነት  ያዘው እንጂ የተሸረበው ሴራ ክልሉን ለማንደድ አገር ለማፈራረስ  ታስቦ የተሰራ ነበር። መንግስት ነገሮችን በከፍተኛ ትዕግስት ይዞት እንኳን  በክልሉ የደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ከፍተኛ ነው። ይሁንና ለማድረስ የታቀደው  ጉዳት ከዚህም እጅግ የከፋ እንደነበር ሁኔታዎች ያመላክታሉ። የፌዴራል መንግስቱ ከሶማሌ ክልል ሰላም ወዳድ ህብረተሰብ ጋር በመሆን ባደረገው ጥረት ሁኔታዎችን ማብረድ ችሏል።  አሁን ላይ በክልሉ ሁኔታዎች ሙሉ ለሙሉ ተቀይረዋል ባይባልም ለመከላከያ ሃይላችን ምስጋና ይግባውና አንጻራዊ ሰላም በመስፈን ላይ ነው። ይህን ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው ህብረተሰቡ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በጋራ መስራት ይኖርበታል።  

ከሰላም የመጀመሪያ ተጠቃሚ ህዝብ እንደሆነ ሁሉ የሰላም ባለቤቷና ጠባቂዋም ህዝብ  መሆን መቻል አለበት፤ ከምንም በላይ የአንድ አገር ሰላም የሚረጋገጠው በህዝብ እንጂ  በጸጥታ ሃይል ብዛትና ጥንካሬ አይደለም። ይህ ሲባል የጸጥታ ሃይሉ በአገሪቱ የሰላም ማስከበር ጉዳይ ላይ አስተዋጽዖ የለውም  ለማለት ፈልጌ ሳይሆን ያለህዝብ ተሳትፎ ዘላቂ ሰላም አይረጋገጥም ለማለት ነው፡፡ ለዘላቂና ዋስትና ያለው ሰላም መረጋገጥ ሁሉም  ባለድርሻ አካል የራሱን አስተዋጽዖ ማበርከት ይኖርበበታል። ኦሮሚያ ሰላም ካልሆነ ኢትዮጵያ ሰላም አትሆንም፤ አማራ ሰላም ካልሆነ ኢትዮጵያ ሰላም አትሆንም፤ ሶማሌ ሰላም ካልሆነ ኢትዮጵያ ሰላም አትሆንም፤ ደቡብ ሰላም ካልሆነ ኢትዮጵያ ሰላም አትሆንም፤ ወዘተ። ለዚህ ነው የአገራችን  ሰላምና መረጋጋት የእያንዳንዱ አካባቢ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ድምር ውጤት ነው የሚባለው። መንግሥት የትኛውንም ያህል የጸጥታ ሃይል ቢኖረውና በእያንዳንዱ አካባቢ ሊያሰማራ ቢችል እንኳን ዘላቂ ሰላም ሊረጋገጥ አይችልም።

ከላይ እንደተመለከትነው  ሰላም ለልማት፣ ሰላም ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት፣ ሰላም ለመድብለ ፓርቲ መጠናከር፣ ሰላም ለህዝቦች አብሮነት፣ ሰላም ለዕድገት፣  በአጭሩ ሰላም ለሁሉም ነገር ቁልፍ ነት። ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር የለም። በመሆኑም ሁሉም ለሰላም መረጋገጥ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። አንዳንዶች  እንደሚሉት መንግስት መንግስት የሚባለው የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ሲችል ብቻ እንደሆነ አበክረው ይናገራሉ። እውነት ነው ዜጎች ደህንነታቸውን በተመለከተ በመንግስት ላይ ሃሳባቸውን ጥለው በነጻነት የሚንቀሳቀሱት። ይሁንና ለሰላም ዘብ መቆም፤ ለሰላም መዘመር ያለበት መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰላም ወዳድ የህብረተሰብ ክፍል መሆን መቻል ይኖርባቸዋል።  

የመልካም አስተዳደር  ችግሮችን በሃይልና በነውጥ  ለማስተካከል ጥረት ማድረግ አገራችንን ወደ ከፋ  ነገር ሊያመራት እንደሚችል መታወቅ ይኖርበታል። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ወይም ሌሎች ጥያቄዎችን ለመንግስት ለማቅረብ ሲባል ወይም መንግስትን ለመቃወም ወይም ለመደገፍ ሲባል የዜጎችን ህይወት ማጥፋት  እንዲሁም የግለሰቦችን፣ የማህበራዊ መገልገያዎችን፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን፣ የኢንቨስተሮችን ንብረት ወዘተ ላይ ጥቃት መሰንዘር በየትኛውም መስፈርት ህገወጥነት ነው። በቄሮና ፋኖ ስም የሚንቀሳቀስ አጥፊ ሃይል ሃይ ሊባል ይገባል። ቄሮና ፋኖ  የለውጥ አንቀሳቃሽ የዴሞክራሲ ስርዓት ፈንጣቂ እንጂ የጥፋት ምንጭ አይደሉም፤ ሊሆኑም አይችሉም። ይሁንና በእነዚህ ሃይሎች ስም የሚንቀሳቀስ ሌላ የጥፋት ሃይል ተደራጅቶ የጥፋት መርዙን እየረጨ ነው። ሰሞኑን በሻሸመኔና በባህር ዳር እየተፈጸሙ ካሉ ነገሮች  በቄሮና በፋኖ ስም የተደራጀ ሃይል መኖሩን መገመት የሚከብድ አይደለም።

እንደኢትዮጵያ ያለ ጅምር የዴሞክራሲ ስርዓት ተከታይ አገር ይቅርና የሁለትና የሶስት መቶ ዓመታት የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ተሞክሮ አላቸው የሚባሉት ምዕራባዊያን ሳየቀሩ የዴሞክራሲ ስርዓታቸው ያለቀለትና የበቃ ነው ማለት አይቻልም። የዴሞክራሲ ስርዓታችን ገና ጅምር በመሆኑ በርካታ ያልተፈቱ ነገር ግን ሊፈቱ የሚገባቸው ጠያቄዎች እንዳሉ አሌ የማይባል ሃቅ ነው። እነዚህን ነቅሰን አውጥተን በሰለጠነ መልኩ ለመንግስት በማቅረብ መፍትሄ ማፈላለግ የተሻለ አማራጭ ይሆናል እንጂ ነውጥና ሁከት መፍትሄ አይሆንም። አሁንም ሆነ በቀጣይ በአገራችን ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፤ ለእነዚህን ችግሮች መፍትሄ  በሃይል ለመፈለግ መሞከር አለመሰልጠንና ካለፈ ውድቀታችን አለመማር ይሆናል።

ኢትዮጵያ  ህገመንግስታዊ አገር ናት።  ዛሬ በአገራችን ማንም ሃሳቡን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ ይችላል። ከዚህም ባሻገር አዲሱ የአገራችን አመራር ከፍተኛ የህዝብ ይሁንታ ያገኙ  በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአገራችን ሰላም በአንጻራዊነት ተሻሽሏል። ህብረተሰቡ መገንዘብ ያለበት ጉዳይ አዲሱ አመራር ሁሉንም ችግሮች በአንዴ እልባት ይሰጣል ማለት የለበትም ። እንኳን በታዳጊ አገር ይቅርና  በምዕራባዊያኖችም ዘንድ ቢሆን ችግሮች በአንድ ጀንበረ መፍትሄ አያገኙም። መንግስት የህዝብ ጥያቄዎችን በቅደም ተከተል እልባት ለመስጠት ተጠናክሮ በመስራት ላይ ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉት ምንም እንኳን ዛሬ ለነገ መሰረት የመሆኗ ነገር ባያጠያይቅም፤ ዛሬ ሰላም መሆን ማለት ግን ነገም ሰላም ትሆናለች የሚል ዋስትናን አይሰጠንም፤  በመሆኑም ነገ ሰላም የምትሆነው ሁላችንም ለሰላም መሰረት የሆነውን ፍቅርን፣ አንድነትንና መደመርን ስንተገብር ፍቅር ብቻ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy