POLITICS

‹‹አምባገኑ ስርዓት ቢወድቅም ገና ወደ ዴሞክራሲው አልተሸጋገርንም››- አቶ ጃዋር መሃመድ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ሥራ አስኪያጅ

By Admin

August 21, 2018

አዲስ አበባ፡- ‹‹በአሁኑ ወቅት የአምባገነን ሥርዓት ቢወድቅም ገና ወደ ዴሞክራሲ አልተሸጋገርንም›› ሲሉ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦ.ኤም.ኤን) ሥራ አስኪያጅ አቶ ጃዋር መሃመድ ገለጹ፡፡ ሥራ አስኪያጁና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ጃዋር መሃመድ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ አሁን የአምባገነን ስርዓት ወድቋል፤ የጠብመንጃ ህግም የለም፡፡ ይሁንና አገሪቱ ገና ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት አልተሸ ጋገረችም፡፡ ‹‹ወደ ዴሞክራሲው የሚደረገው ሽግግር ገና ስለመሆኑ ማሳያዎቹ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታዩ ግጭቶች እንዲሁም ሥርዓት አልበኝነት ናቸው›› ያሉት አቶ ጃዋር፣ ለዚህ መፍትሄው በፍጥነት ወደ ዴሞክራሲ መሸጋገር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ህዝቡ ተወካዮቹን መርጦ የሚያም ንበትን ህግ ሲደነግጉለት ያንን ህግ እያከበረ የሚኖርበት ዕድል እስኪፈጠር ድረስ ግን ወጣቱም ሆነ ማህበረሰቡ በየቦታው ግጭቶችና ጦርነቶች እንዳ ይፈጠሩ የመከላከል ኃላፊነት እንዳለ ባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ ከአቶ ጃዋር መሃመድ ጋር ያደረግነውን ሙሉ ቃለ ምልልስ

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሰብአዊ መብት ጥናት /በሂዩማን ራይትስ ስታዲስ/ አግኝተዋል፡፡ባለፉት አመታት በኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በኦሮሞ ብሄር ላይ ትኩረት በማድረግ የሰብአዊ መብት ተሟጋችና የፖለቲካ ተንታኝ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በተለያዩ አጋጣሚዎች ላይ ፖለቲካዊ ትንታኔ በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ የተሰኘ የመገናኛ ብዙሃን ስራ አስኪያጅ አቶ ጃዋር መሀመድ፡፡ ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉት አቶ ጃዋር በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይታወቃል፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከእኚህ የፖለቲካ ተንታኝ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

አዲሰ ዘመን፡- በቅርቡ ለኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በስጦታነት ላፕቶፕ አበርክተዋል፡፡ ስጦታው የሚያስተላ ልፈው መልዕክት ምንድን ይሆን ? አቶ ጃዋር፡- (ትንሽ ፈገግ ብለው በረጅሙ አየር ከሳቡ በኋላ) ላፕቶፕዋን ለረጅም ጊዜ ተጠቅሜባታለሁ፡፡ይህ መንግስት ሊሰባብራትና ወደ ኮምፒውተሯ ሰርጎ በመግባት የውስጧን ለማወቅ እንዲሁም ሊያሰርቃትም በጣም ብዙ ገንዘብ አፍስሷል፡፡ ይሁንና እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ከቄሮ ጋር በመሆን በርካታ እድሎችን አስመዝግባለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ትግላችን ያንን አካሄድ መከተልን ምርጫው አለማድረጉን ለማሳወቅ የሚለው አንዱ ማሳያ ሲሆን፣ ትግላችንም ከመቃወም ፖለቲካ ወደ ገቨርናንስ ፖለቲካ መሻገርን ለማሳየት ነው፤ይህን ሽግግር በማስመልከት እማኝ ትሆን ዘንድ የተበረከተች ናት፡፡ ኮምፒውተሯ ታሪካዊ በመሆኗም ጭምር ነው በስጦታነት ለማበርከት የተነሳሳሁት፡፡ በአሁኑ ወቅት ከተቃዋሚነት ወደ ገንቢነት እንዲሁም አምባገነናዊ ስርዓትን ከማፍረስ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ወደመገንባት መሄዳችንንም ለማመላከት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ያለንን ክብር ለመግለጽ በማሰብ ነው፡፡አቶ ለማ መገርሳ በለውጡ ሂደት ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ የእርሳቸው ወደ ስልጣን መምጣት ለቄሮ ትግል ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ወደ ስልጣኑ ባይመጡና በመንግስት ውስጥ የሚያዳምጥና ለውጥ ለማምጣት የሚችል አካል ባይኖር ኖሮ ግዴታችን ኢህአዴግን መገልበጥ ይሆን ነበር፡፡ እሱ ደግሞ ምናልባት አሁን የምንመለከተውን ውጤት ላያመጣ ይችላል፡፡ በመሆኑም እርሳቸው ለፈጸሙት ተግባር ክብር ለመስጠት በማሰብም ጭምር ነው በስጦታነት የማበረከቴ ምስጢር፡፡ (በድጋሚ ፈገግ ብለውና ድምጻቸውን ከፍ አድርገው)….ከዛ ውጪ ደግሞ እኔም ከሽፍታነት ወደ ሰላማዊ ዜጋነት መለወጤን ለማሳየት ያህል ነው፡፡ አዲስ ዘመን፡- ጃዋር የአቋም መቀያየር ይታይበታል፤ አንዴ ብሄር ተኮር፣ አንዴ ደግሞ እስልምና ተኮር ሌላ ጊዜ ደግሞ ኢትያጵያዊነት ላይ አጥብቆ ሲሰራ ይታያል ይባላልና እርስዎ እዚህ ላይ ምን ይላሉ? አቶ ጃዋር፡- እኔ እኮ አክቲቨስት ነኝ እንጂ የፖለቲካ አይዶል አይደለሁም፡፡ የአካባቢ ደህንነት ጉዳይ ሲመጣ የዚህ ጉዳይ ጠበቃ እሆናለሁ፤ የሴቶች መብት ተነክቶ ሳይ በተመሳሳይ ለሴቶች ጥብቅና እቆማለሁ፡፡ የኦሮሞ ህዝብ መብት ሲገፋ ደግሞ የኦሮሞን ህዝብ አደራጅቼ ታግያለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ ለሁሉም ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ አለ፤ ይሄውም በማንኛውም ጊዜ የኦሮሞን ጉዳይ ብቻ ይዘን በምንሄድበት ወቅት የኢትዮጵያን ጉዳይ ወደጎን ትተን አሊያም ለመጉዳት አስበን አይደለም፡፡ ለኦሮሞ የሚሆነው ሁሉ ለኢትዮጵያ ይሆናል፤ ለኢትዮጵያ የሚሆነው ሁሉ ደግሞ ለኦሮሞ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ አንድነት ኦሮሞን አይጎዳም፡፡ ነገር ግን ደግሞ በአንድነት ስም ህብረተሰብ መጨቆን የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ሲሰፍን ኦሮሞን ይጠቅመዋል፡፡ በሰላም ስም ግን ኦሮሞ ላይ ጦርነት ሊታወጅ አይገባም፡፡ ስለዚህ የእኛ ትግል የነበረው ለኛም ሆነ ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት ላይ ነው፡፡ ከሙስሊም ጋር ተያይዞ የተነሳው ጉዳይ ምስጢር አይደለም፤ መንግስት በሙስሊሞች ላይ የማይፈልጉትን ኃይማኖት ለመጫን በሞከረበት ወቅት የሙስሊሙን ህዝብ ቁጣ ማስነሳቱ ይታወሳል፤ በዚያ ወቅት እኔ ጉዳዩን አስቀድሜ የማውቀው በመሆኑ ያንን አይነት ጣልቃ ገብነት የሙስሊሙን ወጣት ወደ አክራሪነት ሊገፋው ስለሚችል ባለኝ እውቀት ወጣቱ ወደእዛ እንዳይገፋፋ እና በሰላማዊ ትግል የመንግስትን አጀንዳ እንዲጥል ነው የፈለኩት፡፡ ስለዚህ ልክ በኦሮሞ ውስጥ እንዳደረኩት የሰላማዊ ትግል ስልትና ስትራቴጂ የሙስሊም ልጆችን አሰለጠን ኳቸው፤ ረዳኋቸው፤ በመገናኛ ብዙሃንም ደገፍኳቸው፤ በእርግጥም ካሰብነው በላይ ደግሞ ተሳክቶልናል፡፡ በወቅቱ መንግስት እንደፈለገው ቢገፋ ኖሮ እነዚያ ወጣቶች በንዴት ወዳልተፈለገ ነገር ውስጥ ይገቡ ነበር፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ግጭት ይከሰትና መንግስትና የሙስሊሙ ህብረተሰብ ወደማይሆን ጉዳይ ውስጥ ይገቡ ነበር፡፡ ያንን ጉዳይ በመቀልበስ ዛሬ ላይ በአገሪቱ የታየው አይነት ሰላም በመፈጠሩ የተረጋጋ ሁኔታ እንዲመጣ ረድተናል፡፡ ስለዚህ የእኔ አጀንዳ መቀያየር ለመልካም ነው፡፡ ምክንያቱም እኔ ግትር እንጨት አይደለሁም፡፡ የፖለቲካ ስትራቴጂስት እንጂ፡፡ አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ብዙዎች የኦሮሞ ጥያቄ ተመልሷል የሚል እምነት አላቸው፤ እዚህ ላይ የእርስዎስ አመለካከት ምንድን ነው? አቶ ጃዋር፡- የኦሮሞ ህዝብ እኮ የታገለው አብይና ለማን አሊያም ጃዋርን ወደ ስልጣን ለማምጣት አይደለም፡፡ ለእኛ ዋናው ጉዳይ አምባገነናዊ ስርዓትን መጣል በራሱ ዓላማችን አልነበረም፡፡ እንዲያም ሆኖ አምባገነናዊ ስርዓት ለምንፈልገው ዓላማ ጋሬጣ ነበር፤ እንቅፋት ሆኖብን ነበር፡፡ እንቅፋቱን ማስነሳት ለሚቀጥለው ጉዞ አስፈላጊ ነበር፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ሶስት ነው፤ አንዱ ነጻነትና ዴሞክራሲ ነው፡፡ በቀዬው ላይ በሰላም የመኖር፤ ያለመታሰርና ያለመደብደብ እንዲሁም ደግሞ በመረጠው መንግስትና በመረጠው ግለሰብ መተዳደር ነው፡፡ ከላይ በሚሾምለት አሊያም ደግሞ ከውስጡ በሚመረጥለት ሳይሆን እርሱ ይሆነኛል፤ ይበጀኛል ባለው ሰው እና ህግ መተዳደር ይኖርበታል፡፡ ይህ የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ፈጣሪ በሰጠው ሀብት በመጠቀም ጥሮ ግሮ ከድህነት ራሱን ማላቀቅ ነው፡፡ የራሱ መሬት ተዘርፎ በሚሰራ ፎቅ ላይ ዘበኛ ላለመሆን አሊያም ደግሞ እሱ እጁ እስኪላጥ አርሶ፣ አለስልሶ፣ ለፍሬ አብቅቶና ለቅሞ ሌላው ሀብታም የሚሆንበትና እሱ እዛው ድሃ ሆኖ የሚቀር ስርዓት እንዳይኖር እንፈልጋለን፡፡ ሌላው ደግሞ የሰላም ጥያቄ ነው፤ በመካከሉና በቀዬው እንዲሁም ከጎረቤቱ ጋር ሰላም እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ ከእነ ታደሰ ብሩ ጀምሮ እስከ እኔ ትውልድ ምንም ያልተሳሳትንበትና ትክክለኛ ዓላማ የነበረውም ይሄው ነው፡፡ ለምሳሌ የነታደሰ ብሩን ብትወስጂ እሱ እዚህ ጀነራል ሆኖ ወጣ ሲባል፣ የኦሮሞ ህዝብ እልም ያለ ማሃይም ሆኖ ነው የምትመለከችው፡፡ ምንም ሲማር አይታይም፤ ስለዚህም ነው ህዝቤ መማር አለበት ብሎ ወደ ትግል የገባው፡፡ በእነ አሊ ቢራ ጊዜ ሲደረግ የነበረውን የአፍራን ቃሎን ትግል ብትወስጂው ደግሞ በማንነታችን መሸማቀቅ የለብንም የሚል እሳቤ ይዘው ነው ትግል ውስጥ የገቡት፡፡ ስለዚህ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከእነዚህ ጋር የተያያዘ እንጂ ከእነዚህ የወጣ አይደለም፡፡ ግቡን መትቷል ወይ ላልሽው ለእነዚህ ለሶስቱ አበይት ጉዳዮች እንቅፋት የሆነውን ጉዳይ መለወጥ ተችሏል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት እንዳይኖረው ያደረገ የፖለቲካ ስርዓት ነበር፤ ይህ ደግሞ አምባገነናዊ ስርዓት ሲሆን፣ በተለያየ ስም በመቀመጥ ማለትም ትናንት በአንድነት ስም ቀጥሎ ደግሞ በፌዴራል ስም ህዝባችንን ሲጨቁን፣ ሲዘርፍና ሲገድል ነበር፡፡ ያንን ስርዓት እንዳይመለስ አድርገን ንደነዋል፡፡ ከዚህም በኋላ አምባገነናዊ ስርዓት በዚህች በምንኖርባት ምድር ላይ ተመልሶ አይመጣም፡፡ ይህንን አስረግጬ መናገር እችላለሁ፡፡ ያ ጋሬጣ ዛሬ ላይ ተነስቷል፡፡ እንዲህ ማለት ግን የኦሮሞ ህዝብ የፈለገውን አግኝቷል ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የፈለገውን አገኘ ማለት የምንችለው በመረጠው መንግስት መተዳደር ሲችል ነው፡፡ ዛሬ የኦሮሞ ህዝብ የሚወደው አመራር አለው፤ ግን አልመረጠውም፡፡ የመረጠው መንግስት ሲኖረው ሰላም ይኖረዋል፡፡ ዛሬ ሰላም የለውም፡፡ ከሳምንት በፊት ከ40 በላይ ንጹኃን ዜጎች ሀረርጌ ላይ ተገድለዋል፡፡ ሰው እየሞተ ነው፤ በየቦታው ፍራቻ አለ፤ ልማት የለም፤ እየተስተዋለ ያለው ከፍተኛ ስራ አጥነት ነው፡፡ በመረጠው መንግስት መተዳደር ሲጀምርና ያ መንግስት ለሰላምና ለልማት የሚበጅ ፖሊሲ ማምጣት ሲጀምር የኦሮሞ ህዝብና የሌላውም ህዝብ ትግል ግብ መታ ማለት እንችላለን፡፡ አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል እርስዎ እንዳሉትም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ችግሮች፤ እየተፈጠሩ ናቸው፡፡ በየቦታው የተለያዩ ትንኮሳዎችና ግጭቶች ለመፈጠራቸው መንስዔው ምንድን ነው ብለው ያስባሉ? አቶ ጃዋር፡- እንግዲህ ችግሮቹን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ናቸው ልበላቸው፡፡ ተፈጥሯዊ የምንለው ከአንድ አምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በምናደርገው ሽግግር ውስጥ በማንኛውም ጊዜ የሚመጡ ናቸው፡፡ እንዲህ ሲባል በአምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ ሰው ለመንግስት የሚገዛው ዱላ፣ ጠብመንጃንና በጥቅሉ የኃይል እርምጃን ስለሚፈራ ነው ፡፡ በዴሞክ ራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ሰው ህግን ስለሚያከብር ለመንግስት ይታዘዛል፡፡ አሁን አምባገነን ስርዓት ወድቋል፤ የጠብመንጃ ህግ የለም፡፡ ወደ ዴሞክራሲ ግን አልተሸጋገርንም፤ ገና በሽግግር ላይ ነን፤ምክንያቱም ግጭቶችን እንዲሁም ስርዓት አልበኝነትን እናያለን፡፡ ለዚህ መፍትሄው ምንድን ነው ሲባል በፍጥነት ወደ ዴሞክራሲ መሸጋገር ነው፡፡ ህዝቡ ተወካዮቹን መርጦ የሚያምንበትን ህግ ሲደነግጉለት ያንን ህግ እያከበረ የሚኖርበት እድል ይፈጠራል፡፡ ይህ እስኪሆን ድረስ ግን ወጣቱና ማህበረሰቡ በየቦታው ግጭቶች እንዳይ ፈጠሩ የመከላከል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጓቸው ቃለ ምልልሶች ቄሮ ማለት የለውጡ አካል ነው ብለዋል፤ አንዱ የህብረተሰብ ክፍል መሆኑንና በሲቪክ ማህበረሰብ ውስጥ የሚካተት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህም የፖሊስን ሚና ተክቶ መጫወት እንደሌለበት ተናግረዋልና ባለፈው ወደ ሻሸመኔ ባቀኑበት ወቅት የከፋ ጉዳይ ተከስቷል፤ ከዚህም የተነሳ እንዲህ አይነቱ ተግባር እንዳይከሰት በቀጣይ ተመሳሳይ መድረክ እንደማይኖር ማስታወቅዎ በተከሰ ተው ችግር ምክንያት ነው? አቶ ጃዋር፡- በመድረኮችማ እሳተፋለሁ፤ ይህ ግዴታ ነው፡፡ በሰዎች ዘንድ ራሮት አለ፤ ብዙ ሰው ሊያየኝ ይፈልጋል፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ ምቹ ሁኔታች በጣም አነስተኛ ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው አምቦም በተጓዝኩበት ጊዜ ቦታው ከመጠን ባለፈ ሞልቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ምቹ ሁኔታዎች በሌሉበት ሁኔታ ህዝቡ እንዳይጎዳ በማሰብ ነው፡፡ በእርግጥ ሻሸመኔም መሄድ አልፈለኩም ነበር፤ የሄድኩት በከፍተኛ ጫና ነው። አሁን እንደዚያ አይነት ሁኔታን ማረጋጋት ተገቢ ሰለሆነ ነው ይህንን ያልኩት፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በህዝቡ ውስጥ ከመጠን ያለፈ ስሜታዊነት አለ፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የግድያ ሙከራ ከተቃጣ በኋላ የህዝቡ ስጋት አይሏል፡፡ ምክንያቱም የኦሮሞ ህዝብ አመራሩን ሲነጠቅ ነው የቆየው፡፡ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ብቅ ያለውን ሲያጠፉት ዘመን ተቆጥሯል፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ውስጥ ሰቀቀን አለ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ሙከራ የተደረገ ጊዜ የነበረው ምላሽ በጣም የከፋ ነበር፡፡ አሁንም እንደዚያ አይነት ችግር ከተከሰተ አገርና ህዝባችንን የሚጎዳ ሁኔታ ይፈጠራልና የመደንገጥ ሁኔታ ይታያል፡፡ ሻሸመኔ ላይ ለደረሰው ጉዳት አንዱ ምክንያት ሰዎች መረጋገጣቸው ነው፡፡ ይህ የሆነው እኛ በስፍራው ሳንደርስ ነው፡፡ ከደረስንም በኋላ ሁኔታውን አይተን በፍጥነት መርሃ ግብሩ እንዲቋረጥ በማድረግ ወጥተናል፡፡ በተለይ በከፋ ሁኔታ የአንድ ግለሰብ ህይወቱ ያለፈው ከእነርሱው ጋር የመጣን አንድ ቄሮ ልክ ቦምብ የያዘ አስመስለው ሲጮሁበት በዛ አይነት ሁኔታ ነው ህይወቱ ያለፈው፡፡ ይህ አይነቱ ሁኔታ በሻሸመኔ ብቻ አይደለም የተፈጠረው፤ ባለፈው በአማራ ክልል በበለሳ፣ በትግራይ ክልል እንዲሁም በጅግጂጋም ሆኗል፤ በድሬዳዋም ምንም የማያቁ የጂቡቲ ዜጎች በአንድ ቤት ውስጥ ተቃጥለዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ መነሻ ግን በተለይ በሻሸመኔ የደረሰው ሲታይ ምክንያቱ ህዝቡ ከፍተኛ የሆነ መጠራጠር ከመግባቱ ጋር ይያያዛል፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ ሆነ ብለው ከውስጥ የሚረብሹ አካላት አሉ፡፡ እነዚህም ዱርዬዎች ሳይሆኑ በደንብ ተደራጅተው ለውጡን ለመቀልበስ እና ለማስተ ጓጎል የሚፈልጉ ኃይሎች ናቸው፡፡ እንዲህ ሰውን ሊጎዳ በማይችልበት ሁኔታ በአደባባይ ሳይሆን በአዳራሽ ውስጥ ውይይቶችን እናደርጋለን፡፡ በዚህ ጉዳይ ከኤምባሲዎች ጋርም በስፋት ተወያይተናል፡፡ በዚህም ወጣቱን መያዝ መቻል አለብን፡፡ ወጣቱ የድሉ ባለቤት ነኝ ብሎ ያስባል፤ የድሉ ውጤት ተቋዳሽ ነኝ ወይ ብሎም እየጠየቀ ነው። ውጤቱም ልማቱ እስኪመጣ የሽግግሩ አካል ነኝ ብሎ ማሰብ መቻል አለበት፡፡ አሁን እየተደረገ ባለው ሽግግር ውስጥ መሳተፍ መቻል አለበት፡፡ የገዥው ፓርቲም ሆነ የተቃዋሚ እንዲሁም የሲቪክ ማህበራት ወጣቱን ፖሊሲ በሚቀርጽ ባቸው ውይይቶች ውስጥ እንዲሳተፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በወጣቱና በፖሊስ መካከል ያለውን የሻከረ ግንኙነትም ማስታረቅ ያስፈልጋል፡፡ ለአብነት ማንሳት ካስፈለገ በቄሮና በፌዴራል ፖሊስ መካከል ያለው ግንኙነት በጣም መጥፎ ነው፡፡ ፌዴራል ፖሊስንና መከላከያን በጣም ይጠላሉ፡፡ ሁለቱ ወገኖች ለረጅም ጊዜ የነበሩበት ሁኔታ ይህ እንዲሆን አስገድዷል፡፡ በመሆኑም በመካከላቸው መተማመን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በተያያዘ አሁን ምንም ችግር የለም፤ ወጣቶቹም ያቀርቡታል፡፡ ስለዚህም ተወያይተው ሂስ እያቀረቡ አብረው በሚሄዱበት ሁኔታ ላይ መሰራት አለበት፡፡ እኔ በዚህ አይነቱ ላይ መስራት እፈልጋለሁ፡፡ አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ አሁን የጠቀስኩት አንድ ጎኑ እርቅ የሚመስል ነውና እንደ አገር ሲያስቡት ብሄራዊ እርቅ መደረግ አለበት የሚል እምነት ይኖሮት ይሆን ? አቶ ጃዋር፡- ብሄራዊ እርቅ እናደርጋለን፤ ይህ ግን ከምርጫ በኋላ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም አሁን አንዳንዶች የሽግግር መንግስት ሌሎች ደግሞ የዩኒቲ መንግስት የሚሉ አሉ፡፡ ይህን ጉዳይ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ እቀበለዋለሁ፡፡ ወደ ተግባር ሲመጣ ግን እኔ የፖለቲካል ሳይንቲስት እንደመሆኔ ችግር እንዳለው ይታየኛል፡፡ ዛሬ ማን ከማን ይታረቅ? የትኛውንስ ወገን ነው ወክሎ የሚታረቀው? ቢባል በራሱ ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ በኦሮሞ ውስጥ እታወቃለሁ፤ ውክልና ግን የለኝም፡፡ ስለዚህ ማድረግ አልችልም፡፡ መንግስት ውስጥ ያሉትም በተጭበረበረ ምርጫ የመጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ያንን እንከፍታለን ካልን እንዲያውም ሌላ ብጥብጥ ይከሰታል፡፡ ምክንያቱም ማነው አማራን የሚወክለው? ማነው የትግራይ ህዝብን የሚወክለው? ማነው ሴቶችን እንዲሁም የኃይማኖት ተቋማትን የሚወክለው? ይህ ሁሉ ግልጽ አይደለም፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ወደ ምርጫ መሄድና የህዝቡን ውክልና ማግኘት ያስፈልገናል፡፡ እርቁን ህዝቡ ውክልና ከሰጠን በኋላ ማከናወን ይቻላል፡፡ ያለውክልና ወደ መለወጡ ከሄድን የከዚህ ቀደሙን ስህተት እንደግማለን፡፡ ብሄራዊ እርቅ መደረግማ ይደረጋል፤ ብዙ ድርድሮች ማለትም በህገ መንግስቱ ላይ እንዲሁም በስልጣን አከፋፈሉና በሌሎች ጉዳዮች ላይ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ህዝብን ወክሎ የሚደራደረው ቡድን ውክልና ሊኖረው ይገባል፡፡ አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡ አቶ ጃዋር፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ