Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አስታዋሽ ያጣው ቤተ መንግሥት

0 1,429

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እንጦጦ የሚገኘው የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ከታነፀ 135 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ከቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በስተጀርባ ቤተ መንግሥቱ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሦስት ቤቶችን ያካተተ ነው፡፡ እነሱም የግብር አዳራሽ፣ የአፄ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ባለ አንድ ፎቅ ሰገነት መኝታና እንግዳ ማረፊ ቤቶች አሉት፡፡ ቤቶቹ ከተገነቡበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይዘታቸውን ሳይለቁ እንዳሉ ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል ሥራ ስላልተሠራባቸው፣ ከአገልግሎት ውጪ ለመሆን ተቃርበዋል፡፡

የግብር አዳራሹና መኝታ ቤቱ ግድግዳዎቻቸው አልፎ አልፎ የተደረመሱ ሲሆን፣ የጣሪያዎቹ ክዳን የሆነውን ቆርቆሮ የሸፈነው ሳር በመበታተኑ ቆርቆሮው ለፀሐይና ለዝናብ ተጋልጧል፡፡ በተለይ መኝታ ክፍሉ ውስጥ ያለው የጣውላ ወለል የመፈራረስ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ሰው በተረማመደበት ቁጥር ይዋልላል፡፡ እግር ከበዛበት የተፈራው አደጋ መከሰቱ አይቀሬ ነው፡፡ በአጠቃላይ በአንድ ወቅት የንጉሥ ቤት የነበረ አይመስልም፡፡ አደጋውን ፍራቻ ይመስላል መኝታ ክፍሉ ከሰው ንኪኪ ነፃ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

የቤተ መንግሥቱ አጠቃላይ ቅጥር ግቢ በእንክብካቤ ስላልተያዘ የከብት መዋያ ይመስላል፡፡ በግቻ ሳርና በቁጥቋጦ የተወረረ ሲሆን፣ የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ክምርም አልፎ አልፎ ይታያል፡፡

አፄ ኃይለ ሥላሴ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለማስቀደስም ሲመላለሱ ቤተ መንግሥቱን በርቀት ዓይቶ ከማለፍ የዘለለ ምንም የፈየዱት እንደሌለ ይነገራል፡፡ በደርግ ሥርዓት ግን የአዲስ አበባን 100ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ ከቁስቋም ማርያም እስከ ቤተ መንግሥቱ ድረስ የሚዘልቅ ከሁለት ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት መንገድ ተሠርቷል፣ ሙዚየምም ተቋቁማል፡፡

በአሁኑ ሥርዓት ግን ቤቶቹ ይዘታቸውን ሳይለቁ ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል ሥራ እንዲሠራላቸው ጉዳዩ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካላት በጽሑፍ ተጠይቀው መልሱ የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ግን ቤተ መንግሥቱን ለመንከባከብ አቅሟ የሚፈቅድላትን ጥረቶች ሁሉ ማድረጓን የአፄ ምኒልክ ሙዚየም ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

የአፄ ሚኒልክ 174ኛ ዓመት የልደት ቀን ነሐሴ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በተዘከረበት ሥነ ሥርዓት ላይ ኃላፊው ሊቀ ሥዩማን ጥበቡ ዳኜ እንዳመለከቱት፣ ቤተ ክርስቲያኗ ካከናወነችው ጥረቶች መካከል አንደኛው በግቢው ውስጥ የመኖሪያ ቤት ቀልሰው ይኖሩ የነበሩ ስምንት አባወራዎች ከቅጥር ግቢ ለቀው እንዲወጡ ማድረግ ይገኝበታል፡፡

ከዚህም ሌላ ቤተ ክርስቲያኗ የቤተ መንግሥቱን ቅጥር ግቢ ዙሪያውን በግንብ ያጠረች ሲሆን፣ ሁለት ትልልቅ የመግቢያ በሮችን አሠርታለች፡፡

ከዚህም ሌላ ቅጥር ግቢውን በአረንጓዴ ሳር ለማስዋብ፣ ቱሪስቶች አረፍ ብለው ሻይና ቡና የሚሉበት ካፍቴሪያ፣ የአገር ባህል ምግቦችና መጠጦች የሚቀርቡበት ሬስቶራንትና ለሠርግ ዝግጅት የሚውል ሁለገብ አዳራሽ ለማቋቋም አቅዳ ለተግባራዊነቱ ኮሚቴ አዋቅራለች፡፡

ነገር ግን ከከተማ ወጣ ብላ በመገኘቷ የተነሳ ምዕመናንን እንደ ልብ አግኝታ የማስተባበር ሥራ ለማከናወን እንደተሳናት፣ ኮሚቴ ከማዋቀር በዘለለ ለተግባራዊነቱ የአቅም ማነስ ችግር እጅና እግሯን ጠፍሮ እንደያዛት ከኃላፊው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በቅርቡ ወደ አገራቸው የተመለሱት አምባሳደር ካሳ ከበደ (ዶ/ር) የተጠቀሱትን ቤቶች ቅርፅና ይዘታቸውን እንዲጠብቁ፣ ለትውልድ ለማቆየት የሚስችል ሥራ ለመሥራት የሚረዳ ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት እንዳቀዱ ተናግረዋል፡፡ ለዕቅዱም ስኬታማነት በፌዴራልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙና ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከታቸው የመንግሥታዊ አካላትና የሌሎችም በጎ ፈቃደኞቸ ዕገዛና ትብብር እጅግ ወሳኝ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የሥነ ጥበብ ታሪክ መምህር አቶ አበባው አያሌው እንደገለጹት፣ አፄ ምኒልክ ከመቅደላ በወጡ በአምስት ዓመታቸው ከተማ መቆርቆ ጀመሩ፡፡ በ1864 ዓ.ም. ወረኢሉን፣ ከዚያም አንጎላ እነዋሪ አካባቢን፣ እንዲሁም ከደብረ ብርሃን ወጣ ብሎ የሚገኘውን ሉቼ ከተሞችን የመሠረቱ ሲሆን፣ የአያታቸው ቦታ የነበረውን የአንኮበር ከተማንም አስፋፍተዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባም እንደተመለሱ ፉሪን፣ መናገሻን፣ ወዘተ ለመቆርቆር በቅተዋል፡፡

‹‹በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩ ነገሥታት መካከል አፄ ምኒልክን የሚያክል ንጉሠ ነገሥት በዚች አገር ነግሦ አያውቅም፡፡ ያደረጉትም ሥራ ትልቅ ነው፡፡ ነገር ግን ታሪካቸው ሆን ተብሎ እንዳይታወቅና አወዛጋቢ እንዲሆን ለማድረግ ተሞክሯል፤›› ብለዋል፡፡

ምኒልክ የሚታወቁት እንዲያው በደፈናው በዚህ ዘመን የነበሩ ንጉሥ ናቸው በሚል ሳይሆን፣ የመጀመርያዋን ዘመናዊቷን ኢትዮጵያ ጉዞ ያስጀመሩ በመሆናቸው ነው ብለዋል አቶ አበባው፡፡ ከዚህ አኳያ አሻራቸውን በደንብ አድርገው የሚያመለክቱት ቤተ መንግሥቶች፣ ሐውልቶችና ሙዚየሞች በአግባቡ እንዲጠበቁ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑም ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባን ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ በመወከል የአስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ነብዩ ባዬ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ከ100 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለውን ይህን ቅርስ እኛ እንዳገኘነው ሁሉ የእኛ ልጆችና የልጅ ልጆች ባለው ለዛ፣ መንፈስና፣ አቋም እንዲያገኙት ጠብቆ ማቆየት አለብን፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የከተማው አስተዳደር የማንንም ድጋፍ ሳይጠይቅ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰርፀ ፍሬ ስብሐት፣ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባውን የጎንደር አብያተ መንግሥታት የማኅበር (ይዘቱን ሳይለቅ ጠብቆ የማቆየት) ሥራ በጥሩ ሁኔታ እንዳከናወነ ገልጸው፣ የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ልዩ ልዩ የመገልገያ ቤቶችን በተመሳሳይ መንገድ ለመሥራት የሚሳነው ነገር እንደሌላ አስረድተዋል፡፡

ለዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ እንዲሁም ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ተገቢውን ዕገዛና ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትም ቤተ መንግሥቱ ሰዎች እየሄዱ እንዲጎበኙት ለማድረግ የሚያስችል የማስተዋወቅና የመስህብ ልማት ሥራዎች ለማከናወን ዝግጁ መሆኑን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

በአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ቅጥር ግቢ በተከናወነውና ሰውኛ ፕሮዳክሽን ኢንተርቴይመንት፣ ጉዞ ዓደዋና ኤጋ መልቲ ሚዲያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በዚሁ የዝክር ዝግጅት ላይ የአፄ ምኒልክን ታሪክ የሚያወድሱ መጻጽፎችና ግጥሞች ቀርበዋል፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ቅፅር ግቢ በሚገኘው ሐውልታቸው የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓትም ተካሂዷል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy