Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አሻጥሩን ለመግታት

0 380

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አሻጥሩን ለመግታት

                                                  ታዬ ከበደ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በአገሪቱ የኢኮኖሚ አሻጥር መስተዋሉን ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ላይ ጠቅሰዋል። ለችግሩ መፍትሄ የሚያፈላልግ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ እንደገባም አስረድተዋል። የኢኮኖሚ አሻጥሩ ዓላማ ህዝቡ የታየው ለውጥ በታሰበው መልኩ እየሄደ አይደለም የሚል አንድምታ እንዲይዝ ለማድረግ ያለመ ነው።

በዚህ አሻጥር ሳቢያም ወደ ኢኮኖሚው መፍሰስ የነበረበት በርካታ ገንዘብ በግለሰቦች እጅ ስር እንዲገኝ አድርጓል። ህዝቡ ይህን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት አሻጥሩን ለመግታት በሚደረገው ርብርብ አገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።

ሰሞኑን በህገ ወጥ ሁኔታ በጥቁር ገበያ በግለሰቦች እጅ የታያዘው ገንዘብ አንድ ማሳያ ነው። በህጋዊ ንግድ ፈቃድ ስም ህገ ወጥ ገንዘቦችን ይመነዝሩ የነበሩ የንግድ ቤቶች ታሽገዋል። የንግድ ቤቶቹ የታሸጉበት ምክንያትም በህጋዊ የንግድ ፍቃድ ህገ ወጥ ተግባር በመፈፀማቸው ነው። ተግባሩም በህገ ወጥ መንገድ የውጭ አገራትን ገንዘብ መግዛትና መሸጥ መሆኑ ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለከተማ ጋንዲ ሆስፒታል፣ ኢትዮጵያ ሆቴል እና ቴሌ ባር አካባቢ የሚገኙ የንግድ ቤቶች ተግባሩን ሲፈፅሙ ነበር። እንዲሁም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አሜሪካ ግቢ ተብሎ በሚጠራ አካባቢና በቦሌ ክፍለ ከተማ ሁለት አካባቢዎች ላይ የሚገኙ የሚገኙ የንግድ ቤቶችም ተግባሩን ሲፈፅሙ ነበር።

ድንገተኛ ፍተሻ ተካሂዶ በቁጥጥር ስር የዋሉት ገንዘቦች 5 ሚሊየን 466 ሺህ 632 የኢትዮጵያ ብር፣ 4 ሺህ 16 የእንግሊዝ ፓውንድ፣ 56 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ 2 ሺህ 70 ዩሮ እና 6 ሺህ 505 ድርሃም ናቸው።

በተጨማሪም በርካታ የደቡብ አፍሪካ ራንድ፣ የቱርክ ሊሬ፣ የጅቡቲና የሶማሊያ ሽልንግ እንዲሁም የማሊ ፍራንክ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ይህም ኢኮኖሚውን የሚፈታተን ተግባር መሆኑ ግልፅ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የኢኮኖሚ አሻጥር በተፈጠረ ቁጥር አገሪቱ ታገኘው የነበረውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ እንዲወጣ ዕድል ይፈጥራል።

የኢኮኖሚው አሻጥር በገበያው ላይም ይስተዋላል። መንግስት መሰረታዊ የመገልገያ ሸቀጦች እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊውን ተግባር በማከናወን ላይ ስለሚገኝ እጥረት የሌለበት ቢሆንም አሻጥር የሚፈፅሙ ሃይሎች የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት መግታት እንደማይችሉ አልተገነዘቡም። ተግባራቸው በአገርና በህዝብ ላይ የሚከናወን በመሆኑም ከመንግስትም ይሁን ከህብረተሰቡ እንደማይሰወሩ አልተገነዘቡትም።

በመዲናችንና በተለያዩ ክልሎች ከውጭ የመጡ ምርቶችን በመጋዘን አከማችተው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው። እርምጃ የመውሰድ ስራውም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ገበያውን ለማረጋጋት የጅምላ መሸጫ ሱቆች መሰረታዊ ሸቀጦችን በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ ጥረት እየተደረገ ነው።

ይህ ሁሉ የመንግስት ጥረት ህዝቡ በዋጋ ንረት እንዳይጎዳ ለማድረግ የታሰበ መሆኑ ግልጽ ነው። በሌለ የገበያ ክፍተትና እጥረት አገርንና ህብረተሰቡን ለመጉዳት የሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ግባቸው ህዝቡን መጉዳት ነው። የገበያው ተዋናይ ህብረተሰቡም ጭምር በመሆኑ የችግሩ የመጀመሪያ ተጠቂ ይሆናል። አገርንና ህዝብን በሚጎዳ የኢኮኖሚ አሻጥር ሰው ሰራሽ ችግር በገበያው ላይ እየፈጠረ የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ያዳክማል።

ያም ሆኖ ህብረሰቡ በአገርና በህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ይህን እኩይ ሴራ በማጋለጥ መብቱን ማስጠበቅና የድርጊቱን ፈጻሚዎች መታገል አለበት። ለዚህም ተገቢውን መረጃ ለሚመለከተው አካል በመስጠትም የአሻጥሩን ፈፃሚዎቹን ድርጊት መቆጣጠር አለበት።

በገበያው ላይ እጥረት ሳይኖር እጥረት እንዳለ የሚያስመስሉና መሰረታዊ ሸቀጦችን በማከማቸት አላስፈላጊ ትርፍ ለማጋበስ የሚሹ አካላትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ አገርንና ህዝብን መጠበቅ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት የሸቀጦች እጥረት በገበያው ላይ አንዳይፈጠሩ የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ተከታታይ የሆኑ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። በዚህም ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን ራሱ በማስገባትና በሸማቾች ማህበራት አማካኝነት እያከፋፈለ ይገኛለ።

የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለምርት መጠኑ ማደግ መንግስት ከፍተኛ ተግባራት ሲፈጽምም መጥቷል። በዘላቂ መፍትሔነትም አርሶ አደሩ ምርጥ ዘርን፣ ማዳበሪያንና ሌሎች አቅርቦቶችን በበቂ ሁኔታ አግኝቶ ወደ ምርት ተግባር እንዲገባ እያደረገ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ለአርሶ አደሩ ልዩ ልዩ የቴክኒክ ድጋፎችን የመስጠት ስራዎችን በመከወን ውጤታማ ተግባራትን በመፈፀሙ የዋጋ ንረቱ ይበልጥ እንዳይንር በመቆጣጠር ላይ ይገኛል። ውጤትም እያገኘ ነው።

ህብረተሰቡ መንግስት እየተከተለ ባለው የግብርና ልማት ስትራቴጂ ትርፍ አምራች ዜጋዎችን መፈጠራቸውን በማወቅ እጥረት እንደማይኖር ማወቅ አለበት። እነዚህ አባቢዎች ለአገራችን የሚሆኑ መሰረታዊ የምግብ አቅርቦቶችን አየሸፈኑ ነው። አቅርቦቶቹ እጥረት የሚስተዋልባቸው ናቸው።

እንዲሁም በአሁኑ ሰዓት ከውጭ የሚገባውን ነዳጅ በየጊዜው ድጎማ በማድረግ በየወሩ ባለበት እንዲቀጥል እያደረገ ነው። ይህም መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች የዋጋ ጭማሪ ሳያሳዩ ባሉበት እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ነው። እናም ህብረተሰቡ በሸቀጦች ላይ የሚደረጉ የኢኮኖሚ ሳቦታጆችን መከላከል ይኖርበታል።

መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ከራሱ ካዝና በመደጎምም ይሁን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ በማድረግ የገበያውን ሁኔታ እያረጋጋ ነው። በዚህም የዋጋ ንረቱ አብዛኛውን ህዝብ እንዳይጎዳ እየሰራ ነው።

ያም ሆኖ በንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ አሻጥርን በተለያዩ መሰኮች ለመፈፀም የሚሰሩ አካላት እየታዩ ነው። እነዚህ አካላት ገንዘብን በህገ ወጥ መንገድ የሚይዙ እንዲሁም ያለ ዋጋ አንረው የሚሸጡ ናቸው። ይህም ህብረተሰቡን ከለውጥ ሃሳቡ እንዲዘናጋ ለማድረግ የታለመ ነው።

እነዚህ ወገኖች አላስፈላጊ ገንዘብ የሚያከማቹና ገበያው እጥረት እንዲያጋጥመው የሚሰሩ ናቸው። ሽርክና በመፍጠርም ትርፍ ያጋብሳሉ። የዋጋ ንረትን እየፈጠሩ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ለመጉዳት ይንቀሳቀሳሉ።

ከዚህ ጎን ለጎንም የኮንትሮባንድ አሰራርን በማጧጧፍ ህጋዊው ግብር ከፋይ ነጋዴ ተወዳድሮ ሸቀጡን እንዳይሸጥ እያደረጉት ነው። በተለይ በመሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን ብቻ ሳይሆን ዋጋቸውም ንሮ ህብረተሰቡ ለምሬት አንዲጋለጥና የለውጥ ተነሳሽነቱን ለመስለብ ጥረት እየተደረገ ነው።

ህዝቡ ይህን ሁኔታ በሚገባ መገንዘብ አለበት። በአሻጥረኞች ላይ ተገቢውን ክትትል ማድረግ አለበት። የአሻጥረኞችን እኩይ ተግባር ሲመለከት ወዲያውኑ ለህግ አስከባሪ አካላት ማሳወቅ አለበት።

የአሻጥሩን ተዋናዩች ለመግታት የሚደረገው ርብርብ ለውጡን ከማስቀጠል አኳያ ትርጉም ያለው መሆኑን መረዳት ይኖርበታል። አሻጥረኞች በሁሉም መስኮች የህዝቡን የለውጥ ተነሳሸነት ለማስተጓጎል እየሰሩ ሰለሆነ እነዚህን አካላት ወደ ህግ ፊት በማቅረብ የለውጡን ባለቤትነት ራሱ ማረጋገጥ ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy