NEWS

ኢሶሕዴፓ ስምንት አመራሮችን በግምገማ አነሳ

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትርና የኢሕሶዴፓ ሊቀመንበር አቶ አህመድ ሺዴ

By Admin

August 23, 2018

የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሕሶዴፓ) ባደረገው ግምገማ፣ ሦስት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና አምስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን አነሳ፡፡

ፓርቲው በአዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባደረገው የሦስት ቀናት  ስብሰባ ሦስት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ማለትም የክልሉ አፈ ጉባዔ አቶ መሐመድ ረሽድ፣ የክልሉ የፍትሕና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲ ጀማልና የፓርቲውን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከድር አብዲን አንስቷል፡፡

በግምገማው አቶ ከድርና አቶ መሐመድ ከፓርቲ አባልነታቸው መሰናበታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ መሐመድ ምንም አንኳን ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው ቢነሱም፣ አፈ ጉባዔ ሆነው እንደሚቀጥሉ ታውቋል፡፡

ፓርቲው ባደረገው ተመሳሳይ ስብሰባ የክልሉ የትምህርት ቢሮና የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊዎች፣ እንዲሁም የአፍዴር ዞን አስተዳዳሪ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊና የኢሶሕዴፓ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ኃላፊ የነበሩ አምስት አመራሮች ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው ተነስተዋል፡፡ ‹‹አመራሮቹ በራሳቸው ፍላጎትና በአመራሩ ትግል ሊነሱ ችለዋል፤›› ሲሉ በቅርቡ የፓርቲው ሊቀመንበር የሆኑት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው አቶ አህመድ ሺዴን ሊቀመንበር አድርጎ ከሳምንታት በፊት መሾሙን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ በክልሉ የሚተዳደረው አካራ የተባለ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ሹመቱን እንደማይቀበለው ገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ የአሁኑን ግምገማ ተከትሎ ግን ጽሑፉን ከድረ ገጹ አጥፍቷል፡፡

በሶማሌ ክልል በቅርቡ ለሳምንታት በዘለቀው የፖለቲካዊና የሰብዓዊ ቀውስ በርካታ ዜጎች መገደላቸው፣ መፈናቃቸውና የተለያዩ ተቋማት መውደማቸው አይዘነጋም፡፡ ይኼንን ቀውስ ተከትሎ በአዲስ አበባ የከተመው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ስብሰባውን የመሩት አቶ አህመድ የክልሉን የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) አምባገነንና ፈላጭ ቆራጭ የሆነ አገዛዝ አስፍነው ነበር ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

የፓርቲው አመራር የተለያዩ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ሲያሰራጭ ነበር ሲሉ፣ አቶ አህመድ በስብሰባው ላይ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ስብሰባ በመቀጠል ፓርቲው በወረዳና በዞን ደረጃ በአዲስ አበባ ግምገማ እያደረገ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡