Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢኮኖሚው እንዲጠናከር

0 322

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢኮኖሚው እንዲጠናከር

                                                     ይሁን ታፈረ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዩችን አንስተዋል። በዚህም መንግስት ኢኮኖሚው ያለበትን ችግር ለመቅረፍ ያደረጋቸውን ውጤታማ ተግባሮች አብራርተዋል። ተግባሮቹ በለውጥ ሂደት ላይ ያለውን ህዝብ ህይወት መቀየር የሚችሉ ናቸው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢኮኖሚውን በተሻለ ሁኔታ ለማስቀጠል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ያሰፈልጋል። ለዚህም አገራችን የምትከተለው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ፣ ያቀደችውን የተለጠጠ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳካት የሚያስችል ስለሆነ ነው። ምርታማነትንም ሊያሳድግ ይችላል።

የልማቱ አማራጭ አብዛኛውን የአገሪቱን ጠቅላላ ምርት ነዳጅና ተመሳሳይ የሀይል ምንጮችን ከውጭ በማስገባት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አገሪቱን ለውጭ ምንዛሪ እጥረት ይዳርጋታል፡፡

ከታዳሽ ሃይል በተለይም ከውሃ ሀይልን በማመንጨት በተነጻጻሪ ከሌሎች ሀገራት ቀድማ አረንጓዴ ልማትን መተግበር የጀመረችው ኢትዮጵያ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላትን ተጋላጭነት ለመቀመስ እየሰራች ነው፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን፣ የደን ልማት፣ ታዳሽ ሀይል አማራጭ መከተል እንዲሁም የትራንስፖርት፣ የኢንዱስትሪ የቤት ልማትን በተስማሚ ቴክኖሎጂ መተግበር የአገሪቱ የአረንጓዴ ልማት መሰረቶች ናቸው፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ያስፈልጋል። ምክንያቱም ዘርፉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሪ ዘርፍ መሆኑና የአብዛኛው የሀገሪቱ ዜጎች መተዳደሪያ ስለሆነ ነው፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ከዚህ ቀደም በተለምዶ እንደሚደረገው የሚታረስ መሬትን ማስፋፋትና የቀንድ ከብቶችን ቁጥር ከማሳደግ ይልቅ የመሬትንና የቀንድ ከብቶችን ምርታማነት ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡

የተሻሻሉ የሰብልና የቀንድ ከብት ዝርያዎችን አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ማድረግ የግብርና ዘርፍ ማሳደጊያ አንዱ ስልት ሆኗል፡፡ የደን ጭፍጨፋን ለመቀነስ በተለይም በተራቆቱና በተጎዱ አከባቢዎች ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እንዲሁም ከፍተኛ የመስኖ ልማት ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ አገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና መፍጠር ይገባል። ለዚህ ስኬት በመንግስት በኩል የተወሰዱት እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ ለእርሻ የሚውል ሰፊ መሬት አላት። ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችውም መሬት ቢሆን የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው።

ይህን ሁኔታ በመገንዘብ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። ይህም አርሶ አደሩ ለምርትና ምርታማነት ማደግ የበኩሉ ሚና እንዲወጣ ያደርገዋል። ምርትንና ምርታማነትን ማሳደግ ከተቻለ ኢኮኖሚውን በዘላቂነት ለማጠናከር ትልቅ እርምጃ ይሆናል።

በአርብቶ አደሩም አካባቢ ተመሳሳይ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በመቅረፅና ቀደ ተግባር እንዲገባ በማድረግ ምርታማነትን ማጉላት ይቻላል። ይህም አርብቶ አደሩ ከልማዳዊ የአኗኗር ባህል ወጥቶ ወደ ዘመናዊ ህይወት እንዲቀየር፣ ከአርብቶ አደሩ ጋር በመነጋገር ምርታማነትን የሚያሳድጉ የመስኖ ልማት ስራዎችን በማስፋፋት ወደ ከፊል አርሶ አደርነት እንዲሸጋገር ብሎም ምርጥ ዝርያዎችን አግኝቶ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ ማድረግ ያስፈልጋል።

እንዲሁም የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃዎችን በአግባቡ የማሰባሰብ ስራዎችን እንዲያጠናክር በማድረግ በአርብቶ አደርነትም ይሁን በከፊል አርሶ አደርነት ምርቱን የሚያሳድግበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል።

በተለይም ምርታማነትን የሚቀሱ ጉዳዩችን እየተከታተሉ መፍትሄ መስጠት ይገባል። በተለይ ተባዮችን በባህላዊ መንገድ መከላከል ከአቅም በላይ በሚሆንበት ወቅትም ፀረ- ተባይ ኬሚካሎችን በመርጨትና መከላከል ያስፈልጋል።

እንዲሁም በድህረ- ምርት አያያዝና አጠባበቅ ጉድለት የተነሳ አርሶ አደሩ በዓመት አንድ ሶስተኛው የግብርና ምርታችን እንደሚባክን ተረጋግጧል። መባከን ብቻም ሳይሆን በአጨዳ፣ በመሰብሰብ፣ በመውቃት፣ በማበራየት፣ በመጓጓዝና በማከማቸት የማምረት ሂደት ወቅት የምርት ጥራት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል።

ይህ ሁኔታም አርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ ከለፋበት ምርት እንዳይጠቀም የሚያደረግ ነው። ምርት ለብክነት ከተጋለጠና ጥራቱም ካሽቆለቆለ ተገቢውን ዋጋ ሊያስገኝ አይችልም። አንድ የምርት ዓይነት ሲታጨድ፣ ሲወቃና ሲበራይ እንዲሁም ሲጓጓዝና ሲከማች የሚባክን ከሆነ ከብዛት ሊገኝ የሚችል ጥቅም አይኖርም። በተለይም የምርቱን ጥራት በመቀነስ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከትላል። ስለሆነም ይህን ጉዳይ በርብርብ ማስቀረት ይገባል።

በተጨማሪም የሰብል ምርቱን ለማሳደግ አዳዲስና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል። ስለሆነም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ መንግስት በአሁኑ ሰዓት እያደረገ ያለውን ጥረት ማገዝ ይገባል።

የዋና ዋና ሰብሎችን ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ዋናው ጉዳይ የአብዛኛውን አርሶ አደር የምርታማነት መጠን ምርጥ አርሶ አደሮች የደረሱበት ደረጃ ማድረስ ይገባል። በተለይ በምግብ ሰብሎች፣ በፋብሪካ ግብዓቶች እንዲሁም የኤክስፖርት ሰብሎች ውጤታማ እንዲሆኑ መረባረብ ይገባል።

በአጠቃላይ ኢኮኖሚው እንዲጠናከር ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን አጠናክሮ ማስፋት ያስፈልጋል። ምርትና ምርታማነት ሲሰፉና ሲጎለብቱ ኢኮኖሚያችን ተጠናክሮ ያድጋል። ኢኮኖሚው ሲጠናከር የነፍስ ወከፍ ገቢ ይጨምራል።

የነፍስ ወከፍ ገቢ በጨመረ ቁጥር የህዝቡ የኑሮ ሁኔታ ይስተካከላል። ከላይ ከጠቀስኳቸው ጉዳዩች በተጨማሪ ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳርፉ የሚችሉ እንደ የገንዘብ ዝውውርና አሻጥርን የመሳሰሉ አደናቃፊ ተግባሮችንም መከላከል ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ህዝቡ የተለመደ ሚናውን መወጣት አለበት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy