Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እስኪ የያዝነውን እናበርታ!

0 692

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እስኪ የያዝነውን እናበርታ!

አባ መላኩ

አገራችን  በርካታ ልዩነቶች  በርካታ ማንነቶች የሚስተዋልባት  አገር ናት። እነዚህ በርካታ ማንነቶች  በፌዴራል ስርዓታችን ሙሉ ለሙሉ ምላሽ አገኝተዋል ባይባልም ከየትኛው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ  ልዩነቶችን ማስተናገድ የሚቻልበት ሁኔታ በአገራችን ተፈጥሯል። የእኛን አይነት የፌዴራል ስርዓት በተለይ ጎልተው  የሚወጡትን ሁለት ማንነቶች ማለትም የቡድንና ኢትዮጵያ ማንነቶች አጣጥሞ መያዝ የግድ ይለዋል። የፌዴራል ስርዓታችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ወይም ቡድኖች አካባቢያቸውን ራሳቸው እንዲያስተዳደሩ ዕድል ከመስጠቱም  ባሻገር በመዕከላዊ መንግስትም እያንዳንዱ ቡድን ተገቢው ውክልና እንዲያገኝ አድርጓል።

ከዚህ በፊት በነበሩት  ስርዓቶች በርካታ ብሄረሰቦች  እንኳን በአገር ደረጃ ተወካይ ሊኖራቸው ይቅርና አካባቢያቸውን እንኳን እንዲያስተዳድሩ  ሁኔታዎች አልተመቻቹላቸውም ነበር። ይሁንና አገራችን የፌዴራል ስርዓት መከተል ከጀመረች ወዲህ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ሁኔታዎች ከመመቻቸታቸውም በላይ በማዕከላዊ መንግስት ተገቢው ውክልና እንዲኖራቸው በመደረጉ  በአገሪቱ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማሳለፍ ችለዋል። የፌዴራል ስርዓታችን ገና ጅምርና በርካታ ክፍተቶች የሚስተዋልበት ቢሆንም ህዝቦች አካባቢያቸውን አላስተዳደርንም ወይም  በፌዴራል ደረጃ ተገቢው ውክልና አላገኘንም የሚል ቅሬታ እንዳይኖር ማድረግ ተችሏል።

የፌዴራል ስርዓትን ያለ ዴሞክራሲ  መተግበር ከባድ እንደሆነ በተጨባጭ በአገራችን ተመልክተናል። ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት  በአገራችን ተከስተው ለነበሩ ሁከትና ነውጦች አንዳንዶች የፌዴራል ስርዓቱ አወቃቀር እንደሆነ አበክረው ይሞግታሉ። እንደእኔ ይህ ነጥብ  አመክኖዊ አይመስለኝም። የአገራችን ሁከት ዋንኛ መንስዔ የፖለቲካ ምህዳሩ እያደር እየጠበበ መምጣትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማሽቆልቆል በአጭሩ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር  መዳከም እንደሆነ በርካታ ማስረጃዎችን ማንሳት ይቻላል። ጥቅመኛ ግለሰቦችና ፖለቲከኞች የህዝቦችን አብሮነት የሚሸረሽር የአገራችንን አንድነት የሚያናጋ ድርጊት ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ በተጨባጭ ተመልክተናል። እነዚህ ሃይሎች ራሳቸውን በየጊዜው እየቀያየሩ፣ ለአገርና ለህዝብ መብት የቆሙ በመምሰል በተለይ ወጣቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለማምራት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ያሰቡት አልተሳካም ብንልም በርካታ የማይገባ መስዋዕትነት  እንድንከፍል ምክንያት መሆናቸውን መካድ አይቻልም።

የጥፋት ሃይሎች  ለውጡን ለመቃወም ጠንክረው እየሰሩ ያሉት ይህ ለውጥ ጥቅማችንን  ያሳጣናል ወይም ትላንት ለፈጸምነው ቆሻሻ ድርጊት ተጠያቂነትን  ያነግስብናል ብለው በመስጋት የሚያደርጉት መንፈራገጥ ነው። ይሁንና አሁንም  ይህ መንፈራገጥ አይኖርም ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ እጅግ ሰፊ አገር  በመሆኗ ነገም በተለየ ዘዴና በተለያ ቦታ የጥፋት ድርጊታቸውን መፈጸምና ማስፈጸማቸውን ያቆማሉ  ማለት አይቻልም። በመሆኑም እነዚህን ሃይሎች የመታገል የእያንዳንዱ አገር ወዳድ ዜጋ ግዴታ መሆን መቻል አለበት።

ከላይ እንዳነሳሁት በኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ውስጥ ሁለት ጉልህ ማንነቶች ይስተዋላሉ። እነዚህም የብሄር/የብሄረሰብ ወይም የቡድን ማንነቶችና ኢትዮጵያዊ ማንነቶች ናቸው። እነዚህ ሁለት ማንነቶች  ሳይዛነፉ እኩል ሊዳብሩና ሊተገበሩ የሚችሉበት ሁኔታ እያለ ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት እነዚህ ሁለት ማንነቶች እኩል ባለመተግበራቸው አገራችን ለሁከትና ለነውጥ ተዳርጋለች። እንደእኔ እይታ እነዚህን ሁለት ማንነቶችን የኢፌዴሪ የፌዴራል ስርዓት ማስታረቅ የሚቻልበትን ሁኔታ ነበረው። አማራ ሆኖ ኢትዮጵያዊ፤ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ፤ ሶማሌ ሆኖ ኢትዮጵያዊ ወዘተ መሆን ይቻላል።  ይሁንና ባለፉት 27 ዓመታት የቡድን ማነነት ላይ የተሰራውን ያህል ኢትዮጵያዊ ማንነት አባት ያገኘ አልነበረም። በዚህም ሳቢያ በርካታ ኢትዮጵያዊን በአንድነት የሚያስተሳስረንን እሴት እንዳያውቁት ወይም ተገቢውን ክብር እንዳይሰጡት ምክንያት በመሆኑ ወጣቱ የተለየ ወይም የእኔ አይደለም ብሎ በሚያስበው ላይ ጥቃት መሰንዘርን እንደትግል መስመር ቆጥሮተ ነበር።

ጥቅመኛ ፖለቲከኞች ይህን  የተሳሳተ የትግል መስመር በወጣቱ ውስጥ  ዘርተውበታል። እነዚህ ሃይሎች በፈጠሩት ሁከት ዜጎች ተገድለዋል፣ ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለዋል፤ ንብረታቸው ተዘርፏል፣ የስነልቦና ጫና እንዲፈጠርባቸው ወዘተ በአጠቃላይ መልካም ያልሆኑ ነገሮች እንዲደርስባቸው ተደርጓል። እነዚህ መጥፎ ነገሮች ዳግም በአገራችን እንዳይከሰቱ ጥገኞችን መዋጋት የሁላችንም ግዴታ  መሆን መቻል አለበት። መንግስትም ለመልካም አስተዳደር መስፈንና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ የሚያግዙ ተቋማትን ማጎለበት ተቀዳሚው ተገባር መሆን መቻል አለበት።

የብሄር ማንነቶችንና ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለማጋጨት ጥረት የሚያደርጉ አካላትን ከድርጊታችሁ ታቀቡ ካላልናቸው ችግሮቻችን ሊያወሳሰቡብንና ከየፋ መስዋዕትነት ሊያስከፍሉን  ይችላሉ። እነዚህ ሁለት ማንነቶች አንዱ በአንዱ መስዋዕትነት የሚገኝ ሳይሆን ሁለቱንም ማታረቅ የሚቻልበት ሁኔታ በፌዴራል ስርዓታችን ተመቻችቷል። ከላይ እንዳነሳሁት መንግስት በዘርፉ  በቂ ልምድና እውቀት ካላቸው ምሁራን ጋር በቅርበት በመስራት ህዝቦች ስለፌዴራል ስርዓታችን በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ማደረግ ይኖርበታል። ከዚህ ባሻገር መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት በመስራት ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት ይኖርበታል።ከዚህ ጎን ለጎን ትናንሽ ለሚባሉ ችግሮች ሳይቀር የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ምላሽ በወቅቱ ሊሰጥ ይገባል። የክልል ወሰን ወይም የማንነት ጥያቄዎች ለአገራችን የሁከት መነሻ ከቶ መሆን የለባቸውም።  

እኛ ኢትዮጵያዊያን ሁላችንም ከተለያዩ  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብንሆንም ሁላችንንም በአንድነት የሚያስተሳስር  የጋራ ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት መኖሩን ማሰብ ተገቢ ነው። የፌዴራል ስርዓት ትላልቅ የህዝብ ግጭቶች እንዳይከሰቱ እንጂ  ትናንሽ ግጭቶች ነገም ሆነ ከነገ ወዲያም መከሰታቸው የሚቀር ጉዳይ አይደለም። ግጭት እንኳን በአገር ደረጃ ይቅርና በቤተሰብ ደረጃም የሚከሰት  ማህበራዊ መስተጋብር ነው። ይሁንና ዋናው ቁም ነገር ለችግሮች በሰለጠነ መንገድ መፍትሄ መፈለግ እንጂ የበቀልን ስሜት ማራገቡ ለማንም የሚበጅ አካሄድ   አይደለም። በአገራችን የተከሰቱ ግጭቶች ምክንያቶች ስንመረምር በህዝቦች መካከል ስር የሰደደና ለግጭት የሚዳርግ ቅሬታ የለም።

ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት የራስን ቋንቋና ባህልን መጠቀምና ማዳበር እንጂ  አናሳዎችን ማጥቃት መሆን የለበትም። የቡድንና ኢትዮጵያዊ ማንነቶች ማመጋገብ የማይቻል ከሆነ   አደገኛ ነገር ሊፈጠር እንድሚችል በአገራን ከተከሰተው ሁከት ተረድተናል። ኢትዮጵያዊ ማንነት ሌሎች ማንነቶችን ደፍጥጦ እንዲገኝ አለማድረግ በተመሳሳይ የቡድን ወይም የብሔር ማንነትን ከኢትዮጵያዊ ማንነት  በላይ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ የፌዴራሊዝም ስርዓት እንዲፈጠር ምክንያት ስለሚሆን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ሁሉንም በልክ በልክ የማናስኬደው ከሆነ ዋጋ ያስከፍለናል።

 

80%
Awesome
  • Design

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy