Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እውነተኛው መንስኤ ምንድነው?

0 577

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እውነተኛው መንስኤ ምንድነው?

                                                   እምአዕላፍ ህሩይ

ግጭቶች በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ እየተስተዋሉ ነው። ታዲያ ሁሌም ግጭቶች ሲከሰቱ ‘ግጭቶች ተከስተዋል’ ብሎ ማለፍ ብቻ በቂ አይደለም። ‘እውነተኛው መንስዔ ምንድነው?’ ብሎ መጠየቅ ይገባል። ከጀርባ ያሉትን ተዋንያንን እንቅስቃሴ መመልከት ያስፈልጋል። ምንም እንኳን ግጭቶች በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰቱ የሚችሉ  ቢሆንም፤ የግጭቶቹ እወነተኛ አነሳሾች የተዘረፈ የህዝብ ሃብት እንዳይመለስ የሚፈልጉና በሰሩት ጥፋት የህግ ተጠያቂነት እንዳይመጣባቸው የሚፈልጉ አካላት መሆናቸው ግልፅ ነው።

እነዚህ አካላት የህብረተሰቡን ሰላም ለመንሳት በተለያዩ ቦታዎች የጦር መሳሪያዎችን የሚያዘዋውሩ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ዶላር እና የሌሎች ሀገር ገንዘቦችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው በማሸሽ የኢኮኖሚ ሳቦታጅ የሚፈፅሙ ናቸው። ይህም ለውጡን ለማደናቀፍ እየተደረገ ያለው ሴራ መሆኑን በመገንዘብ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። በእነዚህ አካላት የሚፈፀመው ተግባር ህግና ስርዓትን ያልተከተለ ህገ ወጥ ድርጊት መሆኑን በተለይ ወጣቱ መረዳት ይኖርበታል።

ስለሆነም ወጣቱ የህግ የበላይነትን ምንነትና ፋይዳ በመገንዘብ ከእነዚህ አካላት ሴራ ራሱን ማቀብ ይኖርበታል። በአሁኑ ወቅት ከግጭቶች ጀርባ ያሉት እውነተኛ ተዋንያን ወጣቱን በገንዘብ በመደለል ጭምር ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ እያደረጉት ስለሆነ የችግሩ ፈጣሪዎች እነዚህ አካላት መሆናቸውን ተገንዝቦ ራሱን ለህግና ለህግ ብቻ ተገዥ በማድረግና የህግ የበላይነትን በማክበር ፊቱን ለውጡን ወደ ማጠናከር ማዞር አለበት። ወጣቱ ህግና ስርዓትን በማክበር የሴረኞቹ መጠቀሚያ እስካልሆነ ድረስ የግጭቱን እውነተኛ መንስኤ በመገንዘብ ለሰላምና ለመረጋጋት እንዲሰራ ያደርገዋል።

እነዚህ አካላት የጦር መሳሪያዎችንና የተለያዩ ሀገራትን ገንዘቦች በማዘዋወር በሰላማችንና ኢኮኖሚያችን ላይ አሻጥር ለመፈፀም ሲሞክሩ ይስተዋላል። ያለፉት ጊዜያትን ትተን ሰሞኑን የተፈፀመ አንድ ድርጊት ብንመከት እንኳን፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የጦር መሳሪያዎች በህገ ወጥ መንገድ በነዳጅ ማመላለሻ ቦቴ ላይ ተጭኖ ሲያዘዋውር መያዙን አስታውቋል።

ርግጥ የጦር መሳሪያዎችን በህገ ወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ ሃይሎች ፍላጎት ግልፅ ነው። ይኸውም በሀገሪቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት የሌለ በማስመሰል ግጭቶች በሚፈጠሩበት ወቅት በችግሩ ላይ ቤንዚን የማርከፍከፍ ተግባር ለመፈፀም መሆኑ ምንም ዓይነት ምርምር የሚጠይቅ አይደለም።

እነዚህ አካላት በቅድሚያ በተለያዩ መንገዶች በብሔሮች ውስጥ መቃቃርን በመፍጠር አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር እንዲጋጭ ያደርጋሉ። ግጭቱም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጦር መሳሪያን በግብዓትነት ያቀርባሉ። ከዚያም ራሳቸው መልሰው እገሌና እገሌ ተጋጨ የሚል ዜናን በፈበረኳቸው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የፌስ ቡክ አካውንቶች በመጠቀም ያስተጋባሉ።

በውሸት የተቀናበሩ ፎቶዎችን በማቅረብ ጭምር (ለዚያውም ህጋዊ የመንግስት ተቋማትን አርማ እየተጠቀሙ) ዜጎችን በማደናገር ወደ ሁከትና ብጥብጥ ውስጥ ለመክተት ይሞክራሉ። ያም ሆኖ ጨዋው የኢትዮጵያ ህዝብ በእነዚህ ሃይሎች እኩይ ምግባር መደናበር ይኖርበትም። እንዳልኩት በተለይ ወጣቱ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።

እነዚህ አካላት ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያዩ መንገዶች ከሀገራቸውና ከህዝባቸው የዘረፉት ሃብት እንዲመልሱ እንጠየቃለን ብለው የሚሰጉ ናቸው። የተጠያቂነት አሰራር ተፈፃሚ ይሆንብናል ብለው ይሰጋሉ። ይህ እንዳይሆን መንግስትና ህዝብ ሙሉ አቅማቸውን ግጭትን ወደ ማብረድ ተግባር እንዲያውሉት ለማድረግ ሁከትን መፍጠር ስራዬ ብለው ተያይዘውታል።

ለዚህም በአጋጣሚ በተፈጠረ አሊያም ራሳቸው በፈጠሩት ግጭትን ለማባባስ የጦር መሳሪያ በማዘዋወር በብጥብጥ ውስጥ ሆነን እንድንቀጥል ይሻሉ። በዚህም ህዝቡ በደሙ እውን ያደረገውን ለውጥ የማደናቀፍ ሴራቸውን ሲጠነስሱ ይውላሉ። ታዲያ ይህን እውነታ በተለይ ወጣቱ መንቃት አለበት። የእነዚህ ሴረኞች ሰለባ ላለመሆን ህግንና የህግ የበላይነትን አክብሮ መንቀሳቀስ ይኖርበታል።

ሴረኞቹ ግጭትን ለመፈጠር የሚጠቀሙበት መንገድ ገንዘብ ማፍሰስ ነው። በአንድ በኩል በህገ ወጥ መንገድ የአሜሪካ ዶላርን ጨምሮ ከህዝብ የዘረፏቸውን የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችን ወደ ውጭ ያሸሻሉ። በዚህም የሀገርን ኢኮኖሚ ለመጉዳት ጥረት ያደርጋሉ። ይህ ተግባራቸውም ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው በማድረግ ቅሬታን ሊፈጥርልን ይችላል ብለው ያስባሉ።

ዳሩ ግን በተለያዩ ወቅቶች በህገ ወጥነት የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችን ወደ ውጭ ለማሸሽ ሲሞክሩ በህዝብና በፀጥታ ሃይሎች ትብብር በቁጥጥር ስር ይውላሉ። በሌላ በኩልም በሚያዘዋውሩት ገንዘብ ወጣቶችን በማሳሳት የጥፋት ተልዕኳቸው አስፈፃሚዎች እንዲሆኑ ይገፋፋሉ። ወጣቶችን በመቅጠር አሊያም በማሳሳት የህገ ወጥ ተግባራቸው ማስፈፀሚያ ያደርጓቸዋል። ገንዘብ እየከፈሉ ወጣቱ በእሳት ሲጋይ እነርሱ እሳቱን ዳር ቆመው ይመለከታሉ። ይህን ሃቅ ወጣቱ በሚገባ በማወቅ የእነዚህ አካላት መጠቀሚያ ላለመሆን መጣር አለበት።

በሀገራችን ብቅ ጥልቅ እያለ የሚታየው ግጭት እውነተኛ መንስኤ እነዚህ አካላት ናቸው። እነዚህ ወገኖች ቀደም ሲል በፈጠሩት ስህተት በህግ እንዳይጠየቁ ያገኙትን አማራጮች ሁሉ ይጠቀማሉ። አማራጮቹ ሀገርን የሚበትኑ ቢሆኑም እንኳን ምንም አይገዳቸውም። የሚያስቡት ስለራሳቸው ብቻ በመሆኑም፣ ሀገር ይበተን አሊያም ወገን ይጎዳ ለእነርሱ ምናቸውም አይደለም። እናም በህግ እንዳይጠየቁ የህግ የበላይነትን በመፃረር እኩይ ሴራዎችን ይጠቀማሉ። ለዚህም ገንዘብ በመርጨት ወጣቶችን ያሳስታሉ። ወጣቶቹም ባለማወቅ ተገፋፍተው ህግንና ስርዓትን ያለማከለ ስራዎችን ሲከውኑ ይስተዋላል። አንዳንዴም በእነዚህ አካላት ገፋፊነት በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ህግና ስርዓትን ያላማከለ የመንጋ ፍርድ ሲሰጥ እየተመለከትን ነው።

የእንዲህ ዓይነቱ ችግር እውነተኛ መንስኤ እነዚህ አካላት ናቸው። እነርሱ በሚያራምዱት ህገ ወጥ ስራዎች ውስጥ ሌሎች እንዲዘፈቁ በማድረግ በሀገራችን ውስጥ የህግ የበላይነትን ይጥሳሉ፤ እንዲጣስም ይሰራሉ። ሆኖም በህግና በስርዓት በሚመራ ሀገር ውስጥ የህግ የበላይነትን መጣስ አይቻልም። የህግ የበላይነት ከተጣሰ የትኛውመ አካል በሀግና በስርዓት ሊተዳደር አይችልም። ይህም ሀገር የጉልበተኞች ብቻ እንድትሆን በር ይከፍታል።

የሀገራችን ህዝቦች ለሶስትና አራት ዓመታት ታግለው እውን ያደረጉት ለውጥ የህግ ነፃነትን ለመቀዳጀትና የበላይነትን ለማስፈን መሆኑ ግልፅ ነው። ነፃትንና የህግ የበላይነትን ለማምጣት ህይወቱን፣ አካሉንና ንብረቱን መስዕዋት ያደረገ ህዝብ (በተለይ ወጣቱ) የሌሎችን ነፃነት እያከበረ ለህግ የበላይነት ልዕልና ይቆማል እንጂ የታገለላቸውን እውነታዎች ተፃርሮ አይቆምም። ስለሆነም በሀገራችን ውስጥ ብቅ ጥልቅ እያሉ እዚህም እዚያም የሚስተዋሉ ግጭቶች እውነተኛ መንስኤዎች ከላይ የጠቀስኳቸው አካላት መሆናቸውን በመገንዘብ፤ ህዝቡ በአጠቃላይ፣ ወጣቱ በተለይ ለህግ የበላይነት ተግቶ መስራት የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑን መረዳት ይገባዋል።     

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy