Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኦብሰሲቭ ኮምፓልሲቭ ዲስኦርደር

0 652

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኦብሰሲቭ ኮምፓልሲቭ ዲስኦርደር

(obessisive compulsive disorder)

በአብዩ የኔአለም

1 ኦሲዲ ምንድን ነው?

ከነባራዊ አለም ጋር የማይጣጣም በጎ ተጽእኖ የሌለው ፤አሉታዊ ስሜትን የሚፈጥር፤ የሚያሸማቅቅ፤ የሚያስፈራ፤ የሚያስጨንቅ አፍራሽ ሃሳብ በተከታታይና በተደጋጋሚ በእዝነ ህሊናው በማሰብና ለዚህም ምላሽ ለመስጠት በመጣጣሩ ምክንያት የሚፈጠር የጭንቀት አይነት ነው፡፡ “ኦብሰሲቭ ኮምፐልሲቭ ዲስኦርደር” ዘርን፣ ጾታን፣ ቀለምን፣ ሃይማኖትን፣ ባህልንና የኢኮኖሚ ደረጃን ሳይለይ ህብረተሰቡን በመላ የሚያጠቃ ነው፡፡

ይህን የመሰለ  የተዛባ ፍጹም አሉታዊና አፍራሽ ተጽዕኖ ያለውን ሃሳብ የሚያስበው ሰው በራሱ አይቀበለውም፡፡ በገዛ ሃሳቡ ከመፍራቱ፤ ከመጨነቁና ከመሸማቀቁ ባሻገር ሃሳቡን ራሱ አለመቀበሉ ተጠቂው ከራሱ ጋር ግጭት ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ይሆናል፡፡

የዚህ አይነቱ የአስተሳሰብና የስሜት ችግር በሰውየው ላይ ከታየ ኦብሰሲቭ ኮምፐልሲቭ ዲስኦርደር ለተባለ የአእምሮ ህመም እንደተጋለጠ መረዳት ይቻላል፡፡ የኦሲዲ ችግር ያለበት ሰው አእምሮው ሌላ ነገር ማሰብ እስኪሳነው ድረስ የማይፈለጉ አስፈሪና አሳፋሪ በሆኑ አፍራሽ ሃሳቦች ተሞልቶ ቀኑን በሙሉ በጭንቀት ይገፋል፡፡

ኦሲዲ በችግሩ ተጠቂ ዘንድ የማይፈለግና ለመቆጣጠር የሚያስቸግር ሃሳብ በእዝነ ህሊናው እየተመላለሰ እንዲያስጨንቀው የሚያደርግ ነው፡፡ ይህን ችግር ለማስወገድም የሚደረግን ተፈጥሮአዊ የአእምሮው እንቅስቃሴንም የሚያውክ የጤና ችግር ነው፡፡

2 የኦሲዲ መገለጫ ባህሪያት፤

ኦሲዲ በሁለት መሰረታዊ ነገሮች ይገለጻል፡፡ እነዚህም “ኦብሴሽን” ና “ኮምፐልሽን” በመባል ይታወቃሉ፡፡ የአሜሪካን “ሳይካትሪስት አሶሴሽን” ሁለቱን ነገሮች እንዲህ ሲል ያብራራቸዋል፤

 

     2.1 ኦብሰሺን

  • የችግሩ ተጠቂ የሆነው ሰው የማይፈልጋቸውና የማይወዳቸው ነገር ግን የማይቆጣጠራቸው እና የማያቆማቸው ሃሳቦችና ምስሎች በአእምሮው ውስጥ ተደጋግመው ያለማቋረጥ መከሰት
  • በአእምሮው የሚመላለሱበት እነዚህ ሃሳቦችና ምስሎች በነባራዊ ዓለም ያሉ ችግሮች ተባብሰውና ተጋነው የሚታዩበት ብቻ ሳይሆን የችግሩን ተጠቂ እውነተኛ አስተሳሰብን የማይወክሉ መሆናቸው
  • የችግሩ ተጠቂ የሆነው ሰው እነዚህን “ኦብሰሺን” ሃሳቦ ወደ አእምሮ ሲመጡ ለመከላከል የሚሞከር መሆኑ
  • አብዛኛው ህጻን ያልሆነ የኦሲዲ ችግር ተጠቂ በ “ኦብሰሺን” ሃሳብ ውስጥ ባልሆነበት ጊዜ እነዚህ ምስሎች ድንገት የተፈጠሩ እንጅ የራሱ ትክክለኛ ማንነት መገለጫ ሃሳብ አለመሆናቸውን የሚያውቅ መሆኑ

      2.2 ኮምፐልሺን

የ “ኮምፓልሺን” ባህርያት ደግሞ የሚከተለውን ይመስላሉ

  • “ኦብሴሺን” በአእምሮ በሚከሰትበት ጊዜ ያለማቋረጥ የተግባራዊና አእምሯዊ ምላሽ ለመስጠት የሚደረግ “ኦብሴሺን”  የመከላከል ተፈጥሯዊ ተግባር ነው፡፡
  • ይህ ምላሽ በጊዜው የተከሰቱ ኦብሴሺንን ለማቃለል ወይም የተፈራው ነገር እንዳይከሰት ለመከላከል  የሚወሰድ እርምጃ ሲሆን በጣም የተጋነነና በተደጋጋሚ የሚደረግ ነው፡፡

በአጠቃላይ የኦሲዲ ተጠቂ ሊያስበው፤ ሊፈጽመውና ሊደርስበትም የማይፈልገው ሃሳብ ወደ አእምሮው በመምጣትና ይህንን አስጨናቂ ሃሳብም ለመከላከል ከራሱ ጋር ከሚያደርገው የማያባራ ትግል ጋር በተያያዘ በሚፈጠር የጭንቀት ስሜት ውስጥ ተውጦ የሚሰቃይ ሰው ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በ “ኦሲዲ” ለሚፈጠረው “ኦብሴሺን” የሚታይም ሆነ የማይታይ አጸፋዊ ምላሽ (ኮምፓልሺን) ይኖራል፡፡ በሌላ በኩል በተጠቂው አእምሮ የሚመላለሰው ሃሳብ ወይም ምስል የ ኦሲዲ “ኦብሰሺን” ካልሆነ (እየተፈለገ የሚታሰብ ከሆነ) መጨነቁ ቢኖርም ግን ከላይ በተገለጸው መልኩ ይህን ሃሳብ ለመከላከል የሚደረገው “ኮምፓልሺን” አይኖርም፡፡

3 የኦሲዲ ኡደት

በኦሲዲ የጭንቀት ችግር ውስጥ “ኦብሰሺን” እና “ኮምፓልሺን” እርስ በእርስ ተደጋጋፊ መሆናቸውን በሚያሳይ መልኩ ከዚህ በታች በስዕል ተቀምጠዋል፡፡

 

ስዕሉ ከላይ እንደሚያመለክተው የኦሲዲ ተጠቂው በ “ኦብሴሺን” ምክንያት ከሚፈጠረው ጭንቀት ጊዚያዊ ምላሽ  በመስጠት እፎይታ የሚያገኝ ቢሆንም ይህ ሁኔታ ተጠቂውን ለሌላ ኦብሴሺንና ጭንቀት እንዲጋለጥ ያደርገዋል፡፡

ከችግሩም ለመውጣት ሃሳቡን ለመጫንና ጭንቀቱን ለመገላገል ምላሽ በመስጠት በተጠቂው በኩል የሚወሰደው እርምጃ የችግሩን መጠን አባብሶ ከዚያም አልፎ ችግሩ አቅም ፈጥሮ እየከረረ በመሄድ በተጠቂው ውስጥ የችግሩ ዑደት ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ያደርገዋል፡፡

4 በኢሲዲ ተጠቂ ላይ የሚታዩ ባህሪያት፤

የኦሲዲ ተጠቂ የሆነ ሰው የሚከተሉትን ብህሪያት ያሳያል፡

  • ተጠቂው በራሱ ወይም በሌሎችላይ አሳፋሪና አደጋ ፈጣሪ ነገሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ በመገመት ይፈራል በዚህም በይበልጥ ራሱን ይጠራጠራል
  • ተጠቂው ችግሩን በሚስጥር ይዞ ይቆያል
  • ከፍተኛ የሃላፊነት ስሜትና በኦሲዲው ሃሳብ ምክንያት የጥፋተኝነት ስሜት የኖረዋል
  • ተጠቂው ወደ አእምሮ ህመም እያመራ መሆኑን ይገምታል፤ በዚህም አብዝቶ ይጨነቃል

5 የኦሲዲ ችግር በግልጽ የሚታይበት እድሜ

ኦሲዲ በግልጽ ችግር ሆኖ የሚታይበት አማካኝ እድሜ ከ25-35 ሲሆን እድሜ በገፋ መጠን ኦሲዲ እንደ አዲስ የመታየቱ እድል አነስተኛ ነው፡፡

6 የኦሲዲ መነሻ መንስኤ

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ኦሲዲ የሚከሰተው በአእምሮ ውስጥ በሚገኝ ሴሮቶይን (serotin) የሚባለው ኬሚካል አለመመጣጠን ችግር መሆኑን ነው፡፡ ለዚህም ተፈጥሯዊ (biological) እና እና ስነ-ልቦናዊ (psychological) ኩነቶች አስተዋጽኦ ያላቸው መሆኑን ያብራራሉ፡፡ ኦሲዲ በዘር የመተላለፍ እድልም አለው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለችግሩ መከሰት አስተዳደግ አካባቢያዊ ወይም ስነልቦናዊ ምክንያቶችም አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመን ሲሆን በአደጋ ምክንያት ሊፈጠር የሚችልበት ሁኔታም አለ፡፡

 

7 የችግሩ ስፋት

በዓለማችን ከ1-3% የሚሆነው ህዝብ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ኦሲዲ ችግር ተጠቂ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በሃገራችን ኢትዮጵያም የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከጠቅላላ ዜጋው መካከል 2% የሚሆነው የዚህ ችግር ሰለባ ነው፡፡

8 የኦሲዲ አይነቶች

የተለያዩ መልክ ያላቸው የኦሲዲ አይነቶች በተለያዩ የችግሩ ተጠቂ ሰዎች ላይ እንደሚኖሩ የሚታወቅ ሲሆን ይዘቶቻቸውንና ምልክቶቻቸውን መሰረት በማድረግ በአጠቃላይ ስድስት የኦሲዲ አይነቶች እንዳሉ ይገለጻል፡፡ እነሱም፡-

  • የንጽህና መበከል ኦሲዲ
  • አደጋን የመፍጠር ኦሲዲ
  • ደህንነትን የማረጋገጥ ኦሲዲ
  • የጾታ ግንኙነት ኦሲዲ
  • ባህላዊና ሃይማኖታዊ ኦሲዲ
  • የመሰብሰብ ኦሲዲ

9 የኦሲዲ ህክምና

አሁን በአለንበት ዘመን ኦሲዲ በሚገባ የሚታከም የአእምሮ ችግር ነው፡፡ በኦሲዲ ህክምና ተጠቃሽ የሆኑ ሁለት የህክምና አይነቶች አሉ፡፡  እነሱም

1 የስነ-አእምሮ ምክርና ተግባራዊ ልምድ

2 የመድሃኒት ህክምና

ለኦሲዲ ህክምና ሁለቱንም ዘዴዎች በጣምራ መጠቀም የላቀ ውጤት እንደሚያስገኝ የአእምሮ ሃኪሞች ይመክራሉ፡፡ እንደ አጠቃላይ ሲታይ ግን የስነ-አእምሮ ምክርና ተግባራዊ ልምድ ህክምና ቅድሚ የሚሰጠው ቢሆንም የኦሲዲ ችግር ጠንከር በሚልበት ጊዜ የመድሃኒት ህክምና በጊዚያዊነትም ሆነ ለዘለቄታው ጊዜ ሊሰጥ ይችላል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy