Artcles

  ከመፋዘዝ እንውጣ

By Admin

August 15, 2018

  ከመፋዘዝ እንውጣ

 

ዮናስ

 

የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዋነኛ ዓላማ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2017 ሀገራችንን ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ (Lower Middle Income) ካላቸው ሀገሮች ተርታ ማሰለፍ ነው።ስለሆነም በተለይ ለማኑፋክቸሪንግ ፈጣን ዕድገት ብሎም የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ዕውን ለማድረግ የተደራጀና የተቀናጀ እንቅስቃሴ የሚደረግ ስለመሆኑ በእቅዱ ተመልክቷል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ መሠረተ ሰፊ እና በዋናነት ግብርና የዕድገቱ ዋና ምንጭ ሆኖ ኢንዱስትሪ በላቀ ፍጥነት የሚያድግበትና፣ የአገልግሎት ዘርፍ የበኩሉን ሚና የሚጫወትበት የሚሆን መሆኑም በተመሳሳይ፡፡

 

በዚህ መሠረት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ኢኮኖሚው በአማካይ በየአመቱ በ11 በመቶ እንደሚያድግ ትንበያው ያመለክታል፡፡ ይህ ስትራተጂክ ግብ ሊደረስበት እንደሚችል ያለፉት ዓመታት አፈፃፀሞች መነሻ የተደረጉ መሆኑም በእቅዱ የተመለከተ ቢሆንም የብሄራዊ ፕላኒንግ ኮምሽን የሶስት አመታት ግምገማ ግን በዚህ ልክ አለመፈጸሙን ያሳያል፡፡

 

ላሳለፍናቸው ሶስት አመታት የሕዝባችንን ብሶት ካጋጋሉ ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ሙስና አንዱ ነው። ሙስናን ጸረ-ሙስና ተቋም በመመስረት ብቻ መከላከል እንደማይቻል ተረድተን፤ ሁላችንም፣ ኢትዮጵያችን፣ አንዱ ሰርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ በእቅዱ የተመለከተ ቢሆንም ጠብም ያለ ነገር የለም።

 

ትናንት የተፈጠረን ሃብት ከሌላው በመቀማት ሂሳብ ለማወራረድ የሚተጋ አገርና ሕዝብ ወደፊት ለመራመድ አይችልም። ገበታው ሰፊ በሆነበት፣ ሁሉም ሰርቶ መበልጸግ በሚችልበት ኢትዮጵያችን አንዱ የሌላውን ለመንጠቅ የሚያስገድድ ይቅቅርና የሚያሳስብ ምንም ምክንያት ይለም። ይልቁንም ወቅቱ የፈጠረልንን ልዩ አጋጣሚና ሀገራዊ አቅማችንን አቀናጅተን የእጥረትና እጦት አስተሳሰብን በማስቀረት ለጋራ ብልጽግና መትጋት የሚጠበቅብን ቢሆንም በዚህም ጠብ ያለ ነገር አልታየም።  

በእርግጥ ሀገራችን ባለፉት ዓመታት ባስመዘገባችው ፈጣን እድገት የተነሳ በድህነት ቅነሳ፣ በመሰረተ-ልማት ግንባታ፣ በሰው ሀይል ልማት እና በመሳሰሉት ያገኘናቸው ስኬቶች ለሁሉም የሚሰታዩ ናቸው። ከዚህ አኳያ መንግሥት የዋጋ ንረት እና የውጪ ምንዛሬ ዋጋን ለማረጋጋ፣ የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ለመጠበቅ፣ ለኢኮኖሚ የሚቀርበውን የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት እና አካታችነትን ለማስፋት፣ የውጪ ምንዛሪ ግኝትን እንዲሁም ቁጠባን እና ኢንቨስትመንት ለማበረታታት፣ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ የሕዝቡን የነፍስ ወከፍ ገቢ ለማሳደግ እንዲሁም አስከፊ ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የፖሊሲ እና የትግበራ አርምጃዎችን ወስዷል።

በአንፃሩ፣ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት የኢኮኖሚ እድገቱን እና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋቱን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ተከስተዋል። ከእነዚህም ችግሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ የውጪ ንግድ በሚገው መጠን አለማደጉ፣ ይሄን ተከትሎ የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፣ የውጪ እዳ ጫና እና የሀገር ውስጥ ቁጠባና ኢንቨስትመንት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ናቸው።

 

በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረየታች ቢሆኑም ዘርፉን በተገቢው ሁኔታ በቴክኖሎጂ መደገፍ ባለመቻሉ እንደ ሀገር ማግኘት የሚገባንን የኢኮኖሚ ትሩፋት ሳናገኝ ደቆየተናል።እንደ ደትልቅ ሀገር እና ሕዝብ ከምናስበው የስኬት ጫፍ ላይ መድረስ የምንችለውና ችግሮቻችንን የምንፈታበትን ዋና ቁልፍ የምናገኘው በትምህርት እና በትምህርት ብቻ እንደሆነ በማመን መንግሥት ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ቢሆንም በተለይ የትምህርትን ጥራት ከማስጠበቅ አንጻር እጅግ ብዙ የቤት ሥራዎች ከፊታችን ተጋርጠዋል።

 

ኢትዮጵያ ከ2003 እስከ 2007 የተገበረችውን የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎ ርሜሽን እቅድ በድል በፈተናም አጠናቃለች። ከላይ በተመለከተው አግባብ የዚህ እቅድ ዋና ግብ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2017 አገሪቱን ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ማሰለፍና ለዚህ የሚመጥን አጠቃላይ አገራዊ አቅም መገንባት ነው፡፡የማክሮ ኢኮኖሚ ዋና የፖሊሲ ግቦችም ይህንኑ ራዕይ ከማሳካት አንፃር የተቃኙ ናቸው፡፡ በተለይም በአገሮች ተሞክሮ ለስኬታማ የኢኮኖሚ ትራንስፎ ርሜሽን ቁልፍ አመልካች እንደሆኑ የሚታመ ንባቸው ሦስት መሠረታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ክስተቶች ማለትም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥና፣ ከፍተኛ የካፒታል ክምችት ምጣኔ የማክሮ ኢኮኖሚ ዋና ግቦች ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተሳካ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ መኖር ወሳኝ በመሆኑ ይህንንም ማረጋገጥ የዕቅዱ አንዱ ግብ ነው፡፡  

 

በሁለተኛው የእድገትና ትርንስፎርሜሽን እቅድ የኢኮኖሚውን የዕድገት አቅጣጫ በአምራች ዘርፎች በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪው እንዲመራ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ እነዚህንና ሌሎች ተጓዳኝ ግቦችን ለማሳካት የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ የማረጋገጥና ዋና ዋና ግቦቹን የመደገፍ ዓላማ ያላቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ግቦችም ተቀምጠዋል፡፡ በአጠቃላይ በዕቅድ ዘመኑ በመሠረታዊ የዕድገት አማራጭ የ11 በመቶ እና በከፍተኛው የዕድገት አማራጭ የ12 ነጥብ 3 በመቶ አማካይ አገራዊ የምርት ዕድገት፣ የ29 ነጥብ 6 በመቶ አገራዊ የቁጠባ ምጣኔ፣ የ41 ነጥብ 3 በመቶ የኢንቨስትመንት ምጣኔ፣ መዋቅራዊ ለውጥና የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታን ማስፈን ዋና ዋናዎቹ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎ ርሜሽን ዕቅድ የማክሮ ኢኮኖሚ ግቦች ናቸው፡፡

 

ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በመነጨበት ክፍለ ኢኮኖሚ የ11 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ግብ ተቀምጦ የነበር ቢሆንም፤ በኤልኒኖ ክስተት በተፈጠረው ድርቅ ሳቢያ እና በግጭቶች  መፈተኑ ለበጀት ዓመቱ ከተቀመጠው የ11 ነጥብ 2 በመቶ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት ግብ የ3 ነጥብ 2 መቶኛ ነጥብ ቅናሽ በማሳየት ኢኮኖሚው በ8 በመቶ ብቻ አድጓል፡፡ በተለይም በበጀት ዓመቱ ለኢኮኖሚው የ36 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ ያለው የግብርናው ክፍለ- ኢኮኖሚ የ8 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ምጣኔ ያመጣል ተብሎ በእቅድ ቢያዝም፤ በ2.3 በመቶ ብቻ ሊያድግ ችሏል። በዚህም ምክንያት ለአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ከዕቅድ በታች መሆን ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን የብሄራዊ ፕላኒንግ ኮምሽን ይገልጻል፡፡

 

በሁለተኛው የእ.ት.ዕ አፈፃፀም ላይ በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ አሁንም መፋዘዙ እንዳለ ነው። ገበያውን ለማረጋጋት በየክልሉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እዚህ ግባ የሚባሉ ሆነው አልተገኙም።  የዋጋ ንረትን በመፍጠር ችግር በሚያስከትሉት ላይ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችም እየታዩ አይደለም። ህዝቡም በዚህ በኩል ተገቢውን ጥቆማ በመስጠት ኃላፊነቱን አልተወጣም። በመልካም አስተዳደርና በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚታዩትን ልዩ ልዩ ችግሮች በተመለከተ ለህብረተሰቡ ትክክለኛና አሳማኝ ምክንያቶች እየተሰጡ አይደለም።  

 

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አገራዊ ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን በማሳደግ የፈጣን ዕድገቱ ምንጭ እንዲሆኑ የማስቻል ግብ ተቀምጧል። በዚህም መሠረት በኢኮኖሚው ውስጥ የተደረገው የኢንቨስትመንት መጠን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 38 ነጥብ 5 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም ከተተነበየው የ37 ነጥብ 7 በመቶ ምጣኔ ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡ ፡ በተመሳሳይ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ቁጠባ ምጣኔ በ2007 በጀት ዓመት ከነበረበት የ21 ነጥብ 9 በመቶ ወደ 22 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡

በእቅድ ዘመኑ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ከማምጣት አንጻር ከታቀደውና ከተጠበቀው አንፃር የተመዘገበው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ዝቅተኛ ቢሆንም ከግብርና ዘርፍ ወደ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች (ኢንዱስትሪና አገልግሎት) የመዋቅራዊ ሽግግር ታይቷል፡ ፡ ከኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ አንፃር ትልቅ ትኩረትና ትርጉም ተሰጥቶት የነበረው የማኑፋ ክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በ18 ነጥብ 4 በመቶ በማደግ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለውን ድርሻ ለመጀመሪያ ጊዜ 5 ነጥበ 4 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በአንጻሩ የሀገሪቷ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራትም ሆነ በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ከሚገኙ የዓለም ሀገራት አማካይ አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር ግማሽ ያህል ነው፡፡

 

በተመሳሳይ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለውን ድርሻ በማሳደግ እና የኢኮኖሚ ዘርፎችን የሥራ ስምሪት ስብጥር ዝቅተኛ ምርታማነት ካላቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ከፍተኛ ምርታማነት ወዳላቸው ዘርፎች በማሸጋገር የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን ለማፋጠን የታቀደውን ግብ ከማሳካት አኳያ ዝቅተኛ አፈጻጸም እንደሆነ መረጃው ያሳያል፡፡ ይህም ከግብርና ዘርፍ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚደረገውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማፋጠን የተቀመጠውን ሀገራዊ ራዕይና ግብ ለማሳካት በቀጣይ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ያመለክታል፡፡

 

የወጪ ንግዱ እንደመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ሁሉ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም በአዲሱ የለውጥ አመራር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።  በለውጡ አመራር አቅጣጫ መሰረት የተቋማት ብቃትና ለውጥ ለትራንስፎርሜሽኑ ስኬት ወሳኝ ነው።የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በተሞክሮ እየዳበሩ በረጅም ጊዜ ሂደት በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ስለመሆናቸው ብዙም የሚያከራክር ጉዳይ የለም። ነገር ግን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ወደ አዳዲስ አሠራሮች ስለሚያመራ ይህን አዲስ አሠራርና የኢኮኖሚ መጠን ማሳለጥ የሚችል ተቋማዊ ብቃት የሚጠይቅ እንደሆነም በለውጡ አመራር ተመልክቷል። በመሆኑም ቀጣይ ግምገማዎች የተቋማት አፈጻጸም ላይ ጭምር ያተኮሩ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡   

 

በአጠቃላይ በሁሉም የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጮች የሥራ ሥምሪትን በማሳደግ፣ ምርታማነትን በማሻሻል፣ ጥራትንና ተወዳዳሪነትን በማረጋገጥ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚጠበቀውን የመዋቅር ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራ ሲሆን ይህንኑ ለማረጋገጥ በዘርፎች መካከል ጠንካራ ትስስር እና ተመጋጋቢነት እንዲፈጠር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የሚጠበቀው ፈጣንና ቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር የሚያስችል መሆን እንዳለበት በለውጡ አመራር ተመልክቷል፡፡ ከዚህ አኳያ የማኑፋክቸሪንግን መሠረት የሚያሰፉ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርኘራይዞች በከፍተኛ ፍጥነት እንዲበራከቱና ትላልቅ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችም ጉልበትን በስፋት የሚጠቀሙ ሆነው ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ለማድረግ በሚያስችል ቅኝት ሩጫው ሊከናወን ይገባል፡፡

 

የኢኮኖሚው የማምረት አቅም ላይ ለመድረስ ቅልጥፍና መጨመርና አምራች ዘርፎችን በማጐልበት በጥራት፣ በምርታማነትና በተወዳዳሪነት የላቀ ዕድገት ማምጣት፣ የሀገራችን ኢኮኖሚ አሁን ባለበት ደረጃ የማምረት አቅሙ ላይ ለመድረስ ገና ከፍተኛ ቅልጥፍና መጨመር እንዳለብን የሚያመላክት አፈጻጸም ነው የተመለከትነው፡፡ ስለሆነም አመራሩ ባለሃብቱ እና ህዝቡ በዚህ ቅኝት ከለውጡ አመራር ጋር ሊደመር ይገባል።