Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከቅስቀሳው ጀርባ

0 674

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከቅስቀሳው ጀርባ

ዳዊት ምትኩ

በአሁኑ ጊዜ በለውጡ የተነሳ ጥቅማችን ተነክቷል ብለው የሚያስቡ ጥቂት ወገኖች በርካታዎችን በገንዘብ በመደለል፣ በማሰልጠንና በማሰማራት እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ሃሰተኛ የፌስቡክ አካውንቶችን በመክፈት የሃሰት ዜናዎችን በመፈብረክ ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች ያጋጠሙ ችግሮችን አጋንኖ በማቅረብና ሌላ ትርጉም በመስጠት እንዲሁም ከሌሎች አገራት ያገኟቸውን ምስሎች በፎቶሾፕ የኮምፒዩተር ጥበብ በማቀናበር ህዝብን በህዝብ ላይ ለማነሳሳት ሆን ብለው በስፋት እየሰሩ ናቸው።

ለምሳሌ በባሌ ጎባ የነበረውን ግጭት ለማባባስ ሲሉ ሴራሊዮን ውስጥ ከዓመታት በፊት የነበረን አስከፊ ጭፍጨፋ የሚያሳይ ፎቶግራፍ በፎቶሾፕ የኮምፒዩተር ጥበብ በማቀናበርና ኢትዮጵያዊ እንዲመስል በማድረግ ህዝብን ለጦርነት ሲቀሰቅሱ ተመልክተናል። የእነዚህን አካላት ድብቅ ፍላጎትና ዓላማን በማጋለጥ ከጥላቻ ቅስቀሳቸው ጀርባ ያለውን እውነታ መመልከት ይገባል።

ስለሆነም እነዚህን በብዙ ሺህዎች ምናልባትም እስከ 100 ሺህ ሊደርሱ የሚችሉ ሐሰተኛ የፌስ ቡክ አካውንቶች የሚነዙትን የውሸት መረጃና የሚያካሂዱትን የጥላቻ ቅስቀሳ በመገንዘብ ህዝቡ ከተግባራቸው መጠንቀቅ ይኖርበታል። ምክንያቱም ዓላማቸው ህዝብን በህዝብ ላይ ማነሳሳት ስለሆነ ነው። ያም ሆኖ አሁንም ግጭትን ማስወገድ ያስፈልጋል።

የህገ መንግስቱን መግቢያ በከፊል ስንመለከተው፤ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነጻ ፍላጐታችን፣ በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፤…ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን፤ መጪው የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል፤ ጥቅማችንን፣ መብታችንና ነጻነታችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን፤…” የሚል የህዝቦችን ፍላጎትን ይዞ እናገኛዋለን።

ይህም የአገራችን ህዝቦች የሚሹት ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ፣ ማህበረ-ኢኮኖሚ እድገታቸውን እንዲፋጠን አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንዲገነባ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የሚያመላክት ነው። ለግጭት ምንም ዓይነት ቦታ እንደሌለም ጭምር ያሳያል።

ከዚህ በተጨማሪ ሁሉም የአገራችን ህዝቦች የጋራ ጥቅምና አመለካከት ያላቸው፣ ይህን ጥቅማቸውን እየተደጋገፉ በጋራ በማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ፍላጎት እንዳላቸው እንጂ በተለያዩ ምክንያት እየተጋጩ የህይወት መስዕዋትነት መክፈል እንደሚኖርባቸው አያመላክትም።

ይህ እውነታ አንዳንድ አካላት ጥቅማችን ተነክቷል በሚል እሳቤ ህዝቡን እርስ በርሱ ለማባላት የሚያደርጉት ጥረት መኖሩን ያመላክታል። ሆኖም እንደ ኢትዮጵያ ያለ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መርስቶ አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ለመገንት በህገ መንግስቱ ላይ ሳይቀር ያሰፈረ ህዝብ ውስጥ ቦታ የለውም።

ስለሆነም አንድ በምጣኔ ሃብት የዳበረ ማህበረሰብ ለመገንባት ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሰው ሃብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ሊጠቀሙባቸው ይገባል።

የአንድነት ወግ፣ ባህልና ትውፊት ያለው፣ በዘመናት አብሮነት ገመድ የተሳሰረ፣ በተለይም አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ገንብቶ የማየት ራዕይ ያለው ህዝብ በጥቂቶች የውሸት ቅስቀሳ አራማጆች ፍላጎት እንዲህ በቀላሉ መሸወድ አይኖርበትም። መንቃት አለበት። ከቅስቀሳው ባሻገር ያለው እውነታ ህገ መንግስቱን ጭምር እየጣሱ ህዝብን ከህዝብ ጋር ማባላት መሆኑ ሁሌም ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት።

ይህን ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚደረግ እኩይ ጥረትን በተለይ የአገራችን ወጣት መገንዘብ አለበት። እንደሚታወቀው ሁሉ የአገራችን ወጣት ባለ ራዕይና ተስፋ ያለው ነው። የአገራችን ወጣት ዛሬ “ሰርተህ ተለወጥ፤ እኔ የምትሰራበትን ምህዳር አመቻችልሃለው” የሚል መንግስት ባለቤት ነው።

ችግሩን በህዝባዊ መንፈስ የሚጋራው መንግስት አለው። መፍትሔም በአፋጣኝ የሚሰጥ መንግስት አለው። በየዕቅዶቹ ሁሉ ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ትልሞችን የሚይዝ መንግስት ባለቤትም ነው። በውሸት ቅስቀሳ መሸወድ የለበትም።

እርግጥ በየትኛውም አገር ውስጥ ችግሮች ይኖራሉ። እንኳንስ ለልማቱም ይሁን ለዴሞክራሲው ጀማሪ የሆነችው ሀገራችን ቀርቶ ባደጉት ሀገሮችም ውስጥ ቢሆን ችግር መኖሩ አይቀርም።

የአልጋ በአልጋ መንገድ በየትኛውም ሀገር ውስጥ የለም። በመንግስት የስራ አስፈፃሚዎች ውስጥ ችግር ሊኖር ይችላል። ወጣቱ እነዚህን ችግሮች በመነጋገርና በመወያየት እየፈታ በፌስ ቡክ አካውንቶች የሚተላለፉ የሐሰት ወሬዎችን ለይቶም ማወቅ አለበት።

የሚፈጠሩ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እንጂ የራሳቸው አጀንዳ ያላቸውን የፌስ ቡክ አካውንቶች በመከተል አይደለም። ወጣቱ ማናቸውም መፍትሔ ያለው ለተጠቃሚነቱ እየሰራና ወደፊትም ከሚሰራው ህዝባዊ መንግስት እንጂ የውሸት አካውንቶችን እየከፈቱ ህዝብን ከህዝብ ለማባላት ቅስቀሳ ከሚያደርጉ ወገኖች አለመሆኑን መገንዘብ አለበት።  

ወጣቶች ይህን ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማባለት የሚደረግ ቅስቀሳን መታገል አለባቸው። የእነዚህ አካላት ፍላጎት የመጣውን ለውጥ መቀልበስ መሆኑን ማወቅ አለበት። ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት ከድህነት ጋር ፍልሚያ ገጥሞ ተጠቃሚ እየሆነ ያለው ወጣት፤ በምንም ዓይነት ምክንያት ሁለንተናዊ የጥቅም ተጋሪነቱ የኋሊት ተጎትቶ እንዲሸረሸርበት የሚፈልግ አይመስለኝም። ነገ ትልቅ የዕድገት ባለቤት ለመሆን ያለመው ወጣት ዜጋ፤ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት ለውጡን ጠብቆ እሱነቱን በስራ ለመቀየር ደፋ ቀና በማለት ነው።

ስለሆነም የእነዚህን አካላት የውሸት ቅስቀሳን ሊያዳምጥ አይገባም። እናም የውሸት ቅስቀሳዎችን ማምከን ይኖርበታል። በፌስ ቡክ ላይ የሰፈረ ነገር ሁሉ ትክክል ነው ብሎ መውሰድ አይገባም። እንዲህ ዓይነት የውሸት ቅስቀሳን በማካሄድ ህዝቦችን ለማባላት የሰለፉ አካላት መኖራቸውን በሰከነ ሁኔታ ማጤን ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy